ከግብጻውያንና ከሌሎች ምን እንማራለን?

በታረቀኝ ሙጬ

‹ያማ ሲያማ፤ያም ሲያማ ለኔ ብለህ ስማ› የሚለውን የተወዳጁን ድምጻዊ የጥላሁን ገሠሠን ጥዑመ ዜማ ለአፍታ ያህል እናስታውስ፡፡ ቀጥየ ከማስቀምጠውም ነጥብ ጋር በማዛመድ ከዐረብ ሕዝባዊ የ‹እምቢ አሻፈረኝ ለአምባገነኖች› የአብዮት እንቅስቃሴዎች አንዳች ነገር ለመማር እንሞክር፡፡

‹ኢንሳይድ ስቶሬ› የትናንት ማታ የአልጀዚራ ዝግጅት ስለትናንትናው የዐርብ ዕለት ውሎ የግብጽ ዳግማዊ አብዮተኞች እንቅስቃሴ ሲዘገብ የራሴ ጉዳይ ያህል በጥሞና ነበር የተከታተልኩት፡፡ በራሳቸው በግብጻውያኑ ባለሙያዎችና የፓርቲ አባላት ስለአብዮታቸው በፈለጉት አቅጣጫ አለመጓዝ ብዙ የሚያሳስቡ ጉዳዮች ተገልጠዋል፡፡ ከአንድ ዩኒቨርስቲ የተጋበዘ ባለሙያና የአንድ እንቅስቃሴ አባል የሆነ አንድ ድንቡሼ ወጣት የለውጥ አርበኛ በውይይቱ ተሣትፈዋል፡፡ ከዚያ ያሰባሰብኩት ግንዛቤ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡

የግብጻውያን አብዮት ለውጥ ፈላጊው ሕዝብ በፈለገበት ጎዳና እየሄደ አይደለም፡፡ ከ800 በላይ ንጹሓን ዜጎች በቅልቦቹ የሙባረክ ጦረኞች በጭካኔ የተገደሉበት፣ ብዙ ሀብትና ንብረት የወደመበት፣ በሕዝበዊው አመፅ ዳፋ የሀገሪቱ የቱሪዝም ገቢ ለተወሰነ ጊዜ የተዳከመበት፣ የሥራ ሂደት ቆሞ ወይም ተቀዛቅዞ ብዙ ኪሣራ ያስከተለበት፣ በሙባረክ ጨቋኝ ሥርዓት ተመችቷቸውና ከብረው ሊኖሩ ይችሉ የነበሩ ወጣት ምሁራንና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ዓላማቸውን ከሕዝቡ ጋር አስተካክለው የአምባገነኑን የሙባረክን የበሰበሰ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማስወገድና በምትኩ በሕዝብ ድምጽ ሥልጣን የሚያዝበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ዕውቀታቸውን ያዋሉበትና ሕይወታቸውን የገበሩበት… ይህ አብዮት በተፈለገው መስመር እየሄደ አለመሆኑ ብዙዎቹን ግብጻውያን እያናደደና እልህ ውስጥ እያስገባ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአብዮታቸውን መጠለፍ ለመቀልበስ (To Reclaim the Revolution – ነው የተባለው) በጣህሪር ስኩየር (ነጻነት አደባባይ) እንደሌላው ጊዜ ሁሉ ሰላማዊ ሠልፋቸውን በማደስ አሁንም እየተፋለሙ ናቸው፡፡ ጠንካራ ሕዝባዊ መደላድል ያለው ብርቱ ሕዝብ የፈለገበት ዒላማ ላይ ይደርሳልና በአሁኑ ወቅት ትግላቸውን በማፋፋም ላይ ይገኛሉ፡፡

የማይናቁ ችግሮች ግን አሉ፡፡ የዩኒቨርስቲ ምሁሩ ሲናገር – ቃል በቃል ላልናገረው እችላለሁ -እንዲህ አለ፤‹ በአብዮቱ አፍላ ወቅት የለውጥ ማዕበሉ እንቅስቃሴ መሪ አልነበረውም፡፡ ይህ ገጽታው(መሪ አለመኖሩ) የጥንካሬው ምንጭ ነበር፡፡ በኋላም ይህ እንቅስቃሴ መሪ ሊኖረው አልቻለም፤ ይህ ሁኔታ ግን የድክመት ምንጭ ሊሆን ችሏል፡፡ …› የሚመስጥ አነጋገር ነው፡፡ ትክክለኛ ዕይታ፡፡ አንድ እንቅስቃሴ ካለመሪ አንድ ቦታ ሊደርስ ይችላል፡፡ በሂደት ግን የዚያ እንቅስቃሴ እሸትና ፍሬ ወደሌላ ያልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ በግድ መሪ ያስፈልገዋል፡፡ እናም የግብጽ አብዮት ይህን ዕድል በማጣቱ የለውጡ መሪ በህቡዕ ሙባረክ ራሱ ሆነና ዐረፈው፡፡ እንዴት?

የግብጽ የአሁኖቹ መሪዎች በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ከቀድሞ የሆስኒ ሙባረክ መንግሥት ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ዋናው መሪ ጄኔራል ታንታዊ ራሳቸው የሙባረክ ቀኝ ዕጅ እንደነበሩ ይነገራል፤አብረው የበሉ፤ ክፉና ደግን አብረው ያሳለፉ፤ የተሹዋሹዋሙ… ናቸው፡፡ ሌሎች ባለሥልጣናትም ለሙባረክ የሚራራ አንጀት ያላቸው እንጂ ለሕዝቡ ወግነው የሕዝቡን ፈቃድ በተፈለገው ፍጥነት ሊያሟሉ የተዘጋጁ አይመስሉም፡፡ ለዚህ ማስረጃ ብዙ ነገር መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዐውጀው በዚያ ነው ሀገሪቱን እያስተዳደሩ ያሉት፡፡ ሕዝብ ዴሞክራሲን ፈለገ እንጂ ጊዜያዊ የአስቸኳይ ዐዋጅ አልነበረም፡፡ ‹ያን አንሱና ቅጥ ያለው የጊዜ ገደብ ስጡን› ሲባሉ ከኦክቶበር 2012 ወዲህ ንቅንቅ አናደርግም እያሏቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል በሙባረክ ላይ እየተካሄደ ያለው የፍርድ ሂደት የቀልድና የፌዝ እንጂ የምር አይመስልም፡፡ በሀገሪቱ ወደ 47 የሚጠጉ ፓርቲዎች ቢርመሰመሱም አንዳቸውም የፖለቲካውን ዛብ ሊነኩ አልቻሉም፤ይህም በራሱ የድክመት ምልክት ነው፡፡ የመንግሥት መቆጣጠሪያ ቁልፎች ሁሉ የሚገኙት በዕጅ አዙር ግብጽን እየገዙ እንደሚገኙ በሚወራላቸው ሆስኒ ሙባረክ ሼሪኮች በወታደራዊው ጁንታ ዕጅ ነው፡፡ እንዲህ እየሆነ ያለውም በውጭ ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ተገምቷል፡፡

እዚህ አካባቢ አንድ ራሱን የቻለ አንቀጽ ማግኘት ያለበት ጠቃሚ ነጥብ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይሄውም አንድ መንግሥት በኃይልም ይሁን በሌላ ማናቸውም መንገድ ወድቆ በአዲስ ሲተካ አዲሱ ሥርዓት ከጨረቃ ወይም ከጠፈር አዲስ የሰው ኃይል ሊያመጣ አለመቻሉና በነበሩ ዜጎች የሚሞላ መሆኑ ነው፡፡ የኛን በምሳሌነት እንመልከት፡፡ የአፄው መንግሥት ወድቆ በደርግ ሲተካ፣የደርግ ወድቆ በወያኔው ሲተካና የወያኔውም ለማለፍ አብቅቶት በሌላ ሲተካ የተተካው የቀደመውን ጥምብ እርኩስ እያወጣና እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ አድርጎ ማዋረዱን መቀጠሉ የማይቀር ዕጣችን ከሆነ ለዕድገትና ለብሔራዊ መግባባት አይጠቅምም ብቻ ሳይሆን ክፉኛ ጎጂ ባህል ነው፡፡ በመሠረቱ በአንድ ቀን ሌሊት ሰው ተፀንሶ፣ ተወልዶ፣ በአካልና በትምህርት አድጎና በመንግሥታዊ የሥልጣን አያያዝ ክህሎት በልጽጎ በአንድ ቀን አዳር በመወለድ በማግሥቱ የመንግሥትን አመራር ሊረከብ እንደማይችል ይታወቃል፡፡ የአዲስ መንግሥት የሥልጣን ተዋረዶች ሁሉ የሚያዙት ከወደቀው መንግሥት ከነበሩ ዜጎች መካከል ነው፡፡ በዚህ ሂደት ከዜሮ መጀመሩ ሞኝነትና የማያዛልቅም ነው፡፡ ይልቁንስ በፊተኛው ሥርዓት ብዙ ያጠፉ እንደጥፋታቸው መጠን በቅጣትም ይሁን በምሕረት የሚገባቸውን ፍትህ እንዲያገኙ እየተደረገ ብዙ ጥፋት ያልፈጸሙ ወይም ምንም ያላጠፉ ደግሞ አሁንም በምሕረትና በፖለቲካዊ የንስሃ እጥበት ዳግም ላለማጥፋት ቃል እየገቡ አዲሱን ሥርዓት ማገልገላቸው ነው የሚበጀው፡፡ መጀመሪያ ደረጃ አገራቸውን ማገልገል መብታቸው ብቻ ሣይሆን ግዴታቸውም መሆኑን መረዳት ይገባል- በሠሩት ክፉ ሥራ ይቀጣሉ፤ ካላጠፉና ደግ ነገር ሠርተውም ከሆነ ይሸለማሉ እንጂ በጅምላ ሊወቀሱ ወይ ሊኮነኑ አይገባም፡፡ እንዲያ ከተደረገ በፈረንጅኛው ብሂል ሕጻን የታጠበበትን የቆሸሸ ውኃ ከነሕጻኑና ከነገንዳው አሽቀንጥሮ እንደመጣል ይቆጠራል፡፡ ኢትዮጰያችንን ጨምሮ ይህ ዓይነቱ ችግር በብዙ ሀገሮች ይታያል፤ የማስተዋል ጥበብን የመነጠቅ መጥፎ ዕድል ይመስለኛል ፡፡ እርግጥ ነው ጤናማውን ከበሽተኛው በመለየቱ ረገድ ችግሮች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል እንደግብጾች ሁሉ ቱኒዝያውያንና ሊቢያውያንም በዚህ መሰሉ ችግር ሲታመሱ የምንታዘባቸው፡፡ የአንድ ባለሥልጣንም ይሁን ተራ ዜጋ ችግር ከጋዳፊ ወይም ከቤን አሊ ጋር መሥራቱ ሳይሆን ከነዚህ አምባገነኖች ጋር ሆኖ ምን ሠራ? የሚለው ጉዳይ ነው ሊያስከስስም ሊያስወቅስም የሚገባው፡፡ ከሁሉም ግን ቀናነትና መቻቻል እንዲሁም በተለይ የእያንዳንዱን ባለሥልጣን የሕይወት ታሪክ በትክክል መዝግቦ ማስቀመጥ ከውዥንብርና ሰውን አለሥራው ከመወንጀል ያድናል፡፡ በዚህ ነጥብ ዙሪያ እኛም መጠንቀቅ ሳይኖርብን የሚቀር አይመስለኝም ከአሁኑ ልናስብበት ይገባናል፡፡

ግብጽ ያላት ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ የጂኦፖለቲካ ሚና ቀላል አይደለም፤ ይህንን ዕድልም በመጠቀም ተሰሚነቷን በቢሊዮን ዶላሮች ለዩ ኤስ አሜሪካ ስትሸጥ እንደኖረች ይታወቃል፡፡ አሁንም ለሕዝብ ጥቅም በመንበርከኳ ሰበብ የበጀት ደጋፊዎቿን በማስቀየም ያን ገንዘብ ማጣት አትፈልግ ይሆናል ፡፡ በዚያም ምክንያት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በተለይ በእስራኤልና በዩ ኤስ አሜሪካ ፖለቲካዊ የሙቀት መለኪያ (ቴርሞሜትር) እየተለካ ነው እንደቀድሞዎቹ ሁሉ አዲሶቹም መሪዎቿ እንዲራመዱ በሥውር የሚፈቀድላቸው እየተባለ ነው – በጣፋጭ መሪራዊ የ‹ካሮት ኤንድ ስቲክ› ነባር መርህ መሠረት፡፡ እናም እነዚህ ወታደራዊ መሪዎች የሕዝቡን ፍላጎት በተፈለገው ፍጥነት ለማሟላት አንድም ከራሳቸው ድብቅ የሥልጣን ፍላጎት፣ አንድም የቀድሞ ጌታቸውን በብዙው ላለማስቀየም ካላቸው ዝንባሌ፣ አንድም ከሕዝቡ ጊዜ የማይሰጥ የለውጥ ስሜትና ከውጪው ተፅዕኖ አንጻር ተደራራቢ ችግሮች እንደተጋረጡባቸው መረዳት አያዳግትም፡፡ ለዚህም ይመስላል በጊዜ ሂደትና ቀስ በቀስ በሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የመቸለስ አዝማሚያ እያሳዩ የሚገኙት፡፡ ሕዝቡ ግን ትግስቱ እየተሟጠጠ በመምጣቱ ትግሉን እንደገና እያደሰ ነው፡፡

እዚህ ላይ በግብጽ ላይ እስትራቴጂያዊ ጥቅም አለን እሚሉ ወገኖች እየተሳሳቱ ያለበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አመራሩ ወደ አክራሪዎች ዕጅ እንዳይገባ ከሚል ፍራቻ ይመስላል የውጪው ተፅዕኖ በሀገሪቱ አገም ጠቀም የሆነ ለውጥ እንደሚሻ በፖለቲካ ተንታኞች ይነገራል፡፡ ብልህነትና አስተዋይነት የተሞላበት አካሄድ ግን አይመስልም፡፡ የለውጡ አዝጋሚነትና የቀድሞው ሥርዓት ጥላ በዝቶ መታየት ሕዝቡን እያስቆጣ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በጣልቃ ገብነት የተፈረጁ ሀገሮችን ባንዲራዎች ከማቃጠልና በተቃውሞ ሠልፎች እነዚህኑ ሀገሮች በስም እየጠሩ ከማውገዝ አልፎ የኤምባሲዎችን ቅጽሮች መናድና መዛግብትን ማውደም ተስተውሏል፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ ለግብጽ አስፈሪ ነው፤ ለሀገራቱም አስደንጋጭ ነው፡፡ መድረሻውም በውል ተለይቶ አይታወቅም፡፡ ጥበብ የተላበሰ ጣልቃ ገብነት ያስፈልግ ነበር፡፡ አለበለዚያ አካባቢያዊ ትርምስንም ሊጋብዝ ይችላል፡፡ ሕዝባዊ አመኔታንም ያሳጣል፡፡ ለተጨማሪ አክራሪነትም በር ይከፍታል፡፡ የበደል ጥርቅም ተበቃይን ይፈጥራል ግጭትንም እያባባሰ የጠብንና የዕልቂትን አድማስ ያሰፋል እንጂ ገምቢ ገጽታ የለውም፡፡

በአንድ በኩል የሕዝቡን የለውጥ ስሜት የሚያፍን ውስጣዊና ውጫዊ እንቅስቃሴ በሚታይበት፣ በሌላ በኩል በነዚህ ሕዝባዊ አመፆች ጀርባ የተሠለፉና አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ያኮበኮቡ የአክራሪ ሙስሊሞች ድቁስ ቃሪያ ጠረን በሚከነክንበት ሁኔታ ግብጻውያን ከገቡበት አረንቋ በቀላሉ ይወጣሉ ብሎ መገመት ያዳግታል፡፡ ችግራቸው የተወሳሰበ መሆኑን ማጤን ከባድ አይደለም፡፡ ፓርቲዎች ኀብረት ፈጥረው ሕዝባቸውን በአንድነት በማሰለፍ መብታቸውን ከማስከበር ይልቅ ተበጣጥሰው የመገኘታቸው አጋጣሚ ለሸፍጠኞችና አብዮቱን መቀልበስ ለሚፈልጉ ውስጣዊም ሆኑ ውጫዊ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ በወፌ ቆመች ደረጃ ላይ የሚገኘው አብዮታቸው ቢስ እንዳያየው ገና ብዙ ትግል ከፊታቸው ተደቅኖ ይጠብቃቸዋል፡፡

በመሠረቱ ከፍ ሲል በግብጻዊው ምሁር እንደተገለጸውና የቅርብ ጊዜጣት ተሞክሮዎችም እንደሚያረጋግጡት አንድ አብዮት ካለመሪ ሲከሰት በቀላሉ ግቡን ይመታል ብሎ ማመን ይቻላል፡፤ የቱኒዚያው መሪ አልነበረውም፤ የሊቢያው መሪ አልነበረውም፤ የየመኑ፣ የባሕሬይኑና የሦሪያውም በሕዝብ አባልነታቸው ብቻ ከዳር ወይም ከመሃል ሆነው የሚያምቧትሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ይኖሩ ይሆናል እንጂ በአብዮት መሪነት የሚታወቁ ፓርቲዎች በጉልህ አልተስተዋሉም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን አንድ ዋና ነገር ነው፡፡ ይህም በሕዝብ የሚመራ የለውጥ እንቅስቃሴ አንደኛ ባለቤቱ ሕዝብ ነው – የሞተውም፣ የተጎሳቆለውም፣ ቤት ንብረቱ የወደመውም ራሱ የለውጡ ባለቤት የሆነው አጠቃላዩ ወይም አብዛኛው ሕዝብ ነው፤ ሁለተኛ ‹ደምቼ ቆስየበታለሁና ይህን የሥልጣን ቦታ ከፈለጋችሁ እንደኔው ጫካ ገብታችሁ ተዋጉና ውሰዱት› የሚል ኢሕአዴግን የመሰለ ደንቆሮ የትግል ወይም የአመፅ ቡድን የመኖሩ ዕድል በጣም የጠበበ ነው፡፡ ሦስተኛ የሃይማትም ሆነ የጎሣና የመሳሰሉት የመሠሪዎች ሕዝብን መከፋፈያ ሥልቶች በሕዝባዊ አመፆች ወቅት ብዙም ሥፍራ የላቸውም፡፡ አራተኛ ሥልጣን በሕዝብ ወደሕዝብ ከገባ በኋላ ማንም ዘመናይ ሥልጣንን እንደፈለገው ሊጠቀምና በሀገርና በሕዝብ ላይ ሊቀልድና ሊፈተፍት አይችልም – የሕዝቡን ኃያልነት በተግባር ወይም ከታሪኩ ይረዳልና፡፡

ስለዚህ ከዚህ ሁኔታ እኛስ ምን እንማራለን? ‹የአበራሽን ገጣባ ያየ በእሳት አይጫወትም›፡፡ ይባላል፡፡ ከደቡቡ የሀገራችን ክፍል ምሳሌያዊ ብሂሎች ሌላም ማከል ይቻላል፡- ‹የመጀመሪያው ቂጣ ቢያር ሁለተኛው አያርም›/ሃዲያ/፡፡ እኛ ደግሞ እንደመጥፎ ዕድል ሆኖ ብዙ ጊዜ ብዙ ቂጣዎች አርረውብናል፡፡ የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት በወታደሩ የተጠለፈው ለምንድነው? የ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ በአግራሞት በታዘብነውና አሁንም ድረስ እየታዘብነው ባለነው ሁኔታ ወዳልተፈለገ መቀመቃዊ አቅጣጫ ተጉዞ ሀገሪቱን ከነሕዝቧ እንጦርጦስ ያወረዳት ለምንድነው? ከነዚህ ዋና ዋና የታሪክ ስብራቶችም ሆነ እነግብጽን ከመሳሰሉ ጠንካራ ሕዝቦች ያሏቸው ሀገሮች ምን ምን አወንታዊ ነገሮችን ተምረን የወደፊቱን ትልም በተስተካከለ መደላድል ላይ ማስቀመጥ እንችላለን? ከስህተቱ የማይማር አንድም ሞኝ ነው አለበለዚያም የሞተ ነው፡፡ አንዴውን የሞተ ሰው አይሳሳትም – ሞቷልና፡፡ በቁም ያለ ግን ይሳሳታል – ሰው ነውና፡፡ ነገር ግን ስህተትን እንደመለያ ዓርማ አንግቦ ዝንተዓለሙን በስህተቱ ሊኮፈስ የሚገባው ሰው ሊኖር እንደማይገባ ሁሉ እኛም ከእስካሁኖቹ ስህተቶቻችን በቂ ትምህርት ቀስመን የወደፊቷን የጋራ ኢትዮጵያ በጋራ ትግልና ሁለንተናዊ ጥረት ለመመሥረት እስካሁን ሲያቆራቁሱን የነበሩ እንቶ ፈንቶ ሰበብ አስባቦችን አሽቀንጥረን በመጣል አዲስ መንፈስ መነሳት ይኖርብናል፡፡ ይህን የምናደርገውም ለራሳችንና ለራሳችን ብቻ ነው፤ ለሌላ ለማንም አይደለም፡፡ ከበቂ በላይ ተቀልዶብናል፤ ከበቂ በላይ በኅልውናችን ላይ ዳንኪራና ጮቤ ተረግጦብናል፤ ከበቂ በላይ የከፋፍለህ ግዛው አዚምና ደንቃራ ተጥሎብን በጨለማ ግርዶሽ ታውረን በከንቱ እየተነቃቀፍንና እዬተጎሻመጥን ቆይተናል፡፡ ከዚህም የተነሣ በሌሎቸ ሀገሮች ሕዝቦች ብዙ ተቀድመናል፡፡ ይሁንና ግዴለም ብዙም አልመሸብንም ብለን በማመን አሁን ከተኛንበት ጭልጥ ያለ ግን ቅዠት ከበዛበት እንቅልፋችን አሁኑኑ እንንቃ፡፡ ዋናው አሁንና ዘግይተንም ቢሆን መንቃታችን ነው፡፡ የፈሰሰ አይታፈስምና እስካሁን ለደረሰብን ችግርና በደል ቁዘማውን አቁመን ቢያንስ ቀጣይ ትውልዶቻችን ሲቻል የሚኮሩባት ባይቻል እንኳ እንደምንም ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገር ለመፍጠር አሁኑኑ እንነሳ፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እስካሁን የፈለግነውን እንደሆንነው ሁሉ አሁንና ከአሁን ጀምሮ ይህን ያልተባረከ የዘመናችንን አስቀያሚ የታሪክ ገጽታ መቀየር እንችላለንና ፈጥነን የሥራ ቱታችንን እናጥልቅ፡፡ ስደትና እንግልት እንዲያበቃ ሁላችንም በጋራ እንንቀሳቀስ፡፡ የሀገር ጉዳይ ለማንም የሚተው ባለመሆኑ ከኃላፊነት አንሽሽ፡፡ ሁሉም እኩል መብትና ግዴታ ያለው መሆኑን ተረድተን በአንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ባህላዊ መርህ እየተሳሰብንና እየተዛዘንን ሰላማዊና የከፋ ጉዳት ሊያስከትል በማይችል የትግል ሥልት ትግላችንን እናቀጣጥል፡፡ አንድ ሰው የሚያበረክተው ትንሽ ግን ጠቃሚ ነገር ሌላ ሰው ከሚያበረክተው ትንሽ ግን ጠቃሚ ነገር ጋር ሲተባበር ትልቅ ጠቃሚ ነገር ይገኛልና በምናበረክተው ነገር መጠን ትንሽነት ሳናፍር በትልቅነቱም ሳንኮራና ሳንታበይ ለአንድ የወል ሀገር ምሥረታ የጋራ ዓላማ ቆርጠን እንነሳ፡፡ ከዚህ በላይ ምን ሊባል ይችላል? ‹ምክር የድሃ ነበርሽ፤ ማን ቢሰማሽ› ይባላል፡፡ ሁሉን የሚችል ፈጣሪ ልቦና ሰጥቶን ወደየኅሊናችን ይመልሰንና ይህ የግርግርና የዕብደት ዘመን በሰላምና በጥጋብ ዘመን ተለውጦ ‹እንዲህ ነበርን› ለማለት እንዲያበቃን በተለይ ታላላቆች በጸሎት መትጋት ይኖርብናል፡፡ ወጣቶቻችንም በኋላ ቀር የመቧደኛ ወያኔያዊ ሥልቶች ሳይከፋፈሉና ሳይለያዩ በሚችሉት መንገድ ለነጻነታቸው ይታገሉ፡፡ ነጻነት የሌለው ትውልድ የአምባገነኖች ባሪያ እንደሆነ ይኖራልና እንደስካሁኑ ላለመኖር ለነገው ማሰብን ከአሁኑ ይማሩ፡፡ ከልብ ከጣሩ ትናንት ዛሬ እንዳልሆነ ሁሉ፣ ነገም ዛሬ የማይሆንበት ሰፊ ዕድል አለ፡፡■ To receive breaking news and important updates from Mereja.com, please subscribe to our email newsletter. ⇒ CLICK HERE እዚህ ላይ ይጫኑ ⇐

⇩ Post your comment below
Leave a Reply

Please answer this math question before submitting your comment: