የዘር ማጽዳት (Ethnic Cleansing) ዘመቻ፡ በወልቃይትና በጠገዴ ማህበረሰብ ላይ

የዘር ማጽዳት (Ethnic Cleansing) ዘመቻ፡ በወልቃይትና በጠገዴ ማህበረሰብ ላይ

 የተባበሩት መንግሥታት ም/ቤት በ1948ና በ1992 ዓ.ም የዘር ማጥፋትንና የዘር ማጽዳትን ወንጀሎች አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ ለዚህ ጦማር እንደ መግቢያ ያገለግሉ ዘንድ የተመረጡ ናቸውና በቅድሚያ የሚከተሉትን ሊንኮች ይመለከቱ ዘንድ በአክብሮት ተጋብዘዋል፡፡ www.preventgenocide.org/genocide/officialtext.htm   www.un.org/documents/ga/res/47/a47r080.htm

የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ይህን ኢትዮጵያዊ ዘር ማፅዳት ለምን አስፈለገው? 

ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮችና መጣጥፎች እንደተገለጠው ሁሉ ወያኔ በጎንደር ህዝብ ላይ በተለይም በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ላይ የፈፀመው ወረራ በሁለት መሰረታዊና እኩይ ጭብጦች ላይ ይነሳል፡፡

1ኛ. ለታለመው የ“ታላቋ ትግራይ” ና ለ“ትግሪያዊው ወርቅ” ህዝብ የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ ለም መሬት በመፈለግ ሲሆን፤

2ኛ. ለወደፊት በ“ሃገርነት” ለታጨችው ለ“ታላቋ ትግራይ” ከቀሪው አለም ጋር የየብስ የመውጫና የመግቢያ  በር ለማግኘት በመቋመጥ የተተለመ ነበር፡፡

ይህም ታሪካዊ እውነታ በ1968 ዓ.ም. የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ወያኔ) ባወጣው ማኒፌስቶ መሰረት የጠለምት፣ የወልቃይትንና የጠገዴ መሬቶች በ“ታላቋ ትግራይ” ካርታ ውስጥ እንደሚጠቃለል በግልፅና በዝርዝር ያሳያል። ለግንዛቤ ይረዳዎ ዘንድ እባክዎ ኪዚህ በመቀጠል የተያያዘውን ሊንክ በመጠቀም የወያኔ ማኒፈስቶን ይመልከቱ፡፡

http://www.abbaymedia.com/TPLF_1976_Manifesto.htm

ታዲያ ከዚህ ስግብግባዊ ቅዠት በመነሳትና  ይህን እኩይ የወረራ አላማ እውን ለማድረግ ሁለት አበይት እቅዶችን ለመከተል ወደው ነበር፡፡ ወደ እቅዶቹ ዝርዝር ታሪክና አፈፃፀም ከመግባታችን በፊት ግን ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ በቅድሚያ እጅግ በአጭሩ ወረራ ስለተደገሰለት ወገናችን በተለይም ስለወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብና አካባቢ ትንሽ በአይነ ህሊናዎ እናስቃኝዎ፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ህብረተሰብን በጨረፍታ፡

ወልቃይት ጠገዴ በቀድሞው የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ወይም በአሁኑ የሰሜን ጎንደር ክፍለሃገር ሰሜናዊ ምዕራብ፣ በወገራ አውራጃ  የሚገኙ ወረዳዎች፣ ታሪካዊና ለም የጎንደር መሬቶች ሲሆኑ አዋሳኞቻችንም

በሰሜን -ኤርትራና የተከዜ ወንዝ

በደቡብ -ቆላ ወገራ

በምስራቅ – ትግራይና የተከዜ ወንዝ

በምዕራብ -አርማጭሆና ሱዳን ናቸው፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አማርኛና የራሱ የሆነ ዘይቤና ምልአት ያለው የትግርኛ (የድንበርተኛ) ቋንቋዎች ይናገራል። ዘፈኑ፣ የሀዘን እንጉርጉሮው፣ ቀረርቶውና ሽለላው እንዲሁም ምሳሌያዊ አነጋገሮቹ ሳይቀር በአማርኛ የሚከወኑ ሲሆን የራሱ የሆነው ትግርኛም ከኤርትራና ከትግራይ ድንበሮች እየራቀ በሄደ ቁጥር እየሞተ/ attenuate/ ይሄዳል።

የወልቃይትና የጠገዴ አብዛኛው ህዝብ በግብርና ሙያ የሚተዳደር ሲሆን  የወባ በሽታን፣ ጊንጥና እባብን ወዘተ… ተቋቁሞ  መዘጋ ወልቃይትንና ሁመራን የመሰሉ ገናና የእርሻ ቦታዎችን አልምቷል። እንዲሁም፡

 1. ያለማውን መሬትንም “መውፈር ቀደም” ስርአት በመጠቀም ለሁሉም ክፍት በማድረግ ከመላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በተለይም ደግሞ ከኤርትራና ከትግራይ ወገኑ ጋር ርስቱን ተካፍሎ ሲያርስ ኖራል። ቁጥራቸው የበዛ የትግራይ ሰዎችንም ለሀብትና ለማእረግ አድርሷል።  ለምሳሌ እንደነ አቶ ኪሮስ አለማየሁ (የወያኔው የቻይና አምባሳደር የሆነው የስዮም መስፍን አጎት)፣ ተስፋይ አድዋ፣ በጅሮንድ ቀፀላ፣ ሀጅ ያሲን፣ አባ መሰለ፣ ወዘተ…  በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ የትግራይ ሰዎችንም በወቅታዊ ደረጃ የስራ እድል ፈጥሯል።
 2. ትግራይ ውስጥ ርሀብ በተከሰተባቸው ዘመናትም በስደት ለሚመጡት በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ የትግራይ ወገኖች ጊዚያዊ መጠለያና ምግብ በማቅረብ እንዲያገግሙ ካደረገ በኋላም ራሳቸውን መልሰው እንዲያቋቁሙ የስራ እድል በመስጠት ሲረዳ የቆዬ የወገን አለኝታ ነበር።
 3. ለዘመናት በሰሜን ምእራብ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ተከላካይና ጠባቂ በመሆን ከሱዳንና በሱዳን በኩል ለመጡ ተስፋፊዎች እያሳፈረ ሲመልሳቸው የቆየ ወገን ነው።
 4. የወልቃይት፣ የጠገዴና የጠለምት ወረዳዎች ባህልና ትስስሩ ታሪኩና ግዛትነቱ የጎንደር እንጂ በታሪክ የትግራይም ሆን የኤርትራ ግዛት ሁነው አያውቁም ፤ ታላቁ የተከዜ ወንዝ የተፈጥሮ ድንበር ሁኖ ቆይቷል።

ስለ ወገናችን ይህን ያህል ያህል ካወጋን በኃላ ወደ ተነሳንበት የወያኔ የወረራ እቅድና አፈፃፀም እንመለስ፡፡

እቅድ አንድ፡ ያልነበረ ታሪክን በመፍጠር ወልቃይትን መቆጣጠር፤

እንደተለመደው ሁሉ ታሪክን በማንሻፈፍና በማወናበድ ዘዴ በመታገዝ የግፍ አላማውን ለመተግበር ይረዳው ዘንድ በታህሳስ ወር 1972 ዓ.ም. ታላቁን የተከዜ ወንዝ ድንበር በመጣስ ወደ ጎንደር ግዛት በመግባት የወልቃይት ጠገዴ አካባቢን የወረረው የወያኔ ሽፍታ ቡድን የጡት አባት የሆነው አቶ ስብሀት ነጋ ለዚህ የጥፋት አላማው ማስፈፀሚያነት አጋሩ ለነበሩት አቶ መኮነን ዘለለው ለተባሉ የወያኔ ታጋይና የዚሁ አካባቢ የክፍለ ህዝቢ መሪ (ዮሰፍ በመባል ይታወቁ ለነበሩት) ቀጭን ወያኔያዊ ትእዛዝ ይሰጣቸዋል፡፡ ይኃውም የወልቃይት ህዝብ “ትግሬ” መሆኑን የሚያሳይ የድጋፍ ሰነድ በ“ጥናት” መልክ እንዲያዘጋጅ የሚል ነበር። አቶ መኮነንም በተሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት የአካባቢው ታሪክ አዋቂዎችን አነጋግረው 15 ገጽ ያለው ረፖርት አቀረቡ። የሪፖርቱ ግኝት የወልቃይትም ፣ የጠገዴ መሬቶችም ሆኑ ህዝቡ የትግራይ አካል ሁነው እንደማያውቁ፣ የተከዜ ወንዝ ታሪካዊ የተፈጥሮ ድንበራቸው እንደሆነ ወዘተ… የሚል ነበር። ይህንም ረፖርት  ለአቶ ስብሀት ነጋ አቀረቡ፤ አቶ ስብሀት ሆዬ ወዲያው አንበበና በብስጭት ረፖርቱን ጨባብጦ  ከአቶ መኮነን ፊት ወረወረው።በዚህ ስአት ይመስላል ሁለተኛውና ጭራቁ የወያኔ አማራጭ ከአመራሩ መሳቢያ ወጥቶ ለአብዮታዊ ትግበራ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠው፡፡

እቅድ ሁለት፡  ማፅዳትና መተካት

የመጀመሪያ ምዕራፍ፡

በተቀነባበረ ዘዴና ሀይል በተሞላበት መንገድ ኢትዮጵያዊነቱንና ጎንደሬነቱን በኩራትና በክብር የሙጥኝ ያለውን የወልቃይትንና የጠገዴ እንዲሁም የጠለምትን ማህበረሰብ ተወልዶ ካደገበት ርስቱ በማፅዳት (systematic ethnic cleansing) በትግራይ ህዝብ በመተካት በተረጋገጠና ጠያቂ በሌለው ሁኔታ የ“ትግራይ” አካል ማድረግ ሲሆን።

ዛሬ ወገን በፀፀትና በቁጭት እንደሚዘክረው ይህ ወያኔያዊ ዘርን የማፅዳት ወንጀል በህዝባችን ላይ መተግበር የጀመረው ከዚያች ቀን ጀምሮ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹም ሰለባዎች በአቶ መኮነን ረፖርት ቃለ መጠይቅ ውስጥ የተካተቱንና ሌሎች ብዙ የሀገር ሽማግሌዎችና ታሪክ አዋቂዎች በነቂስ እየተፈለጉ በባዶ ስድስት የወያኔ ሴኩሪቲ እየታፈኑ ወደ ወያኔ ሰራሽ የጨለማ ጉድጓድ እስር ቤቶች በመጣል እዚያው ሟሽሸው እንዲሞቱ የተደረገው። ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የጥቂቶቹን ስም ዝርዝር የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ይመልከቱ  http://wolqait-tegede.tripod.com/Docs/Wolqayit_Victimst.pdf

የሚገርመው ነገር የወያኔ ወራሪ ሽፍታ ቡድን ምንም እንኳ በ1972 ዓ.ም. ጀምሮ ተከዜን አቋርጦ ቢገባም ክረምት በደረሰ ጊዜ ግን ወደ ትግራይ ተመልሶ ነበር የሚከርመው። ታዲያ በ1972 ዓ.ም. ስዩም መስፍንና  ግደይ ዘራጽዮን (የወያኔ ከፍተኛ አመራር አባላት ) በነሃሴ ወር ለድርጅታቸው ጉዳይ በአስቸኳይ ወደ ሱዳን መሄድ ስለነበረባቸው እንዚህን የወያኔ ባለስልጣናት ከትግራይ ወደ ሱዳን ድንበር የማድረሱ ሃላፊነት ለባጣሎኒ መሪ ለሳሞራ (ያሁኑ ጀኔራል) እስከነ ባጣሎኑ ተሰጠ። በዚህም ጊዜ የተከዜን ወንዝ ከስንት ውጣ ውረድና እንግልት በኋላ በመሻገር ወደ ወልቃይት (ጎንደር ግዛት) ደረሱ። በወቅቱም የአገሬው ሰው በክረምት ውሃ ሙላት የታጠረውን ወንዝ በመተማመን ተዝናንቶ በነበረበት ወቅት ነበር ሳሞራና ጀሌዎቹ አዲጎሹ መንደር በመድረስ 18 ሰላማዊ ሰዎችን አስረው የወሰዱት። በዚህም ጊዜ ነበር ገዳዮቹ ጌቶቻቸውን ሱዳን አድርሰው እግረ መንገዳቸውን ወንድሞቻችንን ይዘው ወደ ትግራይ የተመለሱት። እነዚህም ሰላማዊ ሰዎች በዚያው የውሃ ሽታ ሁነው ቀሩ፡፡ በጊዜውም እነዚህን ውድ ወገኖቻችንን ሳሞራ የኑስ እንደፎከረው  መጨፍጨፋቸውን አቶ መኮነን ዘለለው በቅርቡ ለኢሳት ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ እማኝነቱን አረጋግጠዋል፡፡ ከእነርሱም በከፊል፡-

 1. አቶ ማሞ ዘውዴ
 2. አቶ እንደሻው ታፈረ
 3. አቶ አያለው ሰሙ
 4.  “  በርሄ ጎይትኦም
 5.  “  ሃጎስ ኃይሉ ………..

በተጨማሪም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አዛውንቶችንም አፍነው በመወሰድ በወያኔ ሰራሽ የጉድጓድ እስር ቤቶች ውስጥ ተጥለው እንዲያልቁ ተደርገዋል። ጥቂቶቹም፡-

 1. አቶ ልጃለም ታዬ              የ80 አመት አዛውንት
 2. ግራ/ወልዴ የኔሁን              የ78 አመት   “
 3. ቄስ በለጠው ተስፋይ            60 አመት
 4. ቄስ ትእዛዙ ቀለመወርቅ
 5. ቄስ አለነ ቀለመወርቅ……..

አፈናው ሽማግሌዎችና ታሪክ አዋቂዎች ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም፡፡ ይልቁንስ በነፍጥ ይፋለሙናል ብለው የሰጉባቸውን ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶችም የአባቶቻቸው እጣ ደርሶባቸዋል ። ከነዚህ ውድ ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹን በዚህ ጦማር ላይ ለማዘከር ያህል፡-

 1. ወጣት ግፋቸው ዳኘው
 2. ወጣት አዲሰይ ልጃለም ታዬ (ከእስር አምልጦ እጅግ ከፍተኛ ውጊያ በማካሄድ በመጨረሻ ተሰውቷል)
 3. ወጣት ደረጀ አንጋው
 4. ወጣት ዋኘው መንበሩ
 5. ወጣት ህይወት አብርሃ……………..

ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ግፍ የወልቃይትና ጠገዴ ህዝብ በዝምታ አልተቀበለውም ነበር፡፡ ይልቅስ ራሱን ከወያኔ ወረራ ለመከላከልና ዘሩን ከጥፋት ለማዳን በ“ከፋኝ” የአርበኞች ቡድን ስር በመደራጀት እስከ አፍንጫው የታጠቀውንና በሻእቢያ የሚደጎመውን የጠላት ሃይል አቅሙ ከሚፈቅድለት በላይ ውድ ህይወቱን በመክፈል ወያኔን በጦርነት ተፋልሟል፡፡

ወያኔ የመጀመሪያውን ጦርነት ከወልቃይት ህዝብ ጋር በቆስቋሽነት የጀመረችው በየካቲት 21, 1972 ዓ.ም. አርብ እለት ከምሽቱ 8 ስዓት ላይ ነበር ። ቦታው በቃብቲያ ም/ወረዳ አድህርዲ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። ወያኔዎች አድፍጠው ጨለማን ተገን በማድረግ በአካባቢው ደብሮች ተወጣጥተው ከተማዋን በሚጠብቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፈቱ። ሽማግሌዉም ወጣቱም ጠባቂዎችን ለመርዳት ወጣ፤ ጦርነቱ አደረ። ህዝቡ  ዉድ ህይወቱን ከፍሎ ወያኔን አሳፍሮ መለሰ። በዚች ጦርነት ከወገን 12 ሲሞቱ 18 ቆስለዋል። በዚህ ቀን ውድ ህይወታቸውን በመስዋእትነት ከከፈሉት ጥቂቶቹን ዳግም ለማዘከር ያህል

 1. አቶ የልፋለም ተኰላ , እድሜ   65
 2. አቶ አለነ ክንድሽህ     >>       60
 3. አቶ አታላይ አበራ     >>       64
 4.  “ በየነ ያእብዮ      >>         70
 5. አዛውንት አባ ኃይሌ …

በወያኔም በኩል 73 እንደተገደሉ ይታወቃል።  እንግዲህ ከዚች ጦርነት በኋላ ነበር አቅም ያለውና ወጣቱ ራሱን “ከፋኝ”  በሚል ስም በማደራጀት ያላቋረጡ ጦርነቶች በየአቅጣጫው ያደረገው፡፡ ለአብነት ያህል፡-

በ1981 ዓ.ም በግንቦት ወር የከፋኝ ጦር በካልአይና በወዲ አፍሮ የሚመራ አንድ የወያኔንን ሀይል (80 ሰው የያዘ) በወልቃይት ወረዳ በአወራና አቀወርቅ ም/ወረዳ ልዩ ስሟ ድሽቃ በምትባል ቦታ ከቦ በማጥቃት ከ80 የወያኔ ታጋዮች መካከል 5 ብቻ ሲያመልጡ 70 ተገድለው 5 በህይዎታቸው በመማረክ ወያኔን ድባቅ መትቷል። በዚህ ጦርነት ከወገን በኩል ሁለት ወጣቶች ተስውተዋል፡፡ እነሱም፡-

1. ወጣት ታደለ አዛናውና         2. ወጣት ማሞ አጀበ ነበሩ

በዚህም ታሪካዊ መስዋዕትነት የወያኔን እንቅስቃሴ ለተወሰነ ጊዜ በመግታት የቅዥት አላማቸውን በቀላሉ እውን እንደማይሆን አረጋግጧል። (ወደ ኋላ ግን ወያኔ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥታዊ አቅሟን በመጠቀም በዚህ ጀግናና ድንበር ጠባቂ ኢትዮጵያዊ ላይ ቂሟን ለመወጣት ሞክራለች፡፡ እየተወጣችም ነው፡፡ እነሆ ዛሬም አካባቢውን በሃይል ትግራያዊ በማድረግ ላይ ናቸው። ይህን ጉዳይ በሌላ ጊዜ በስፋት እንመለስበታለን።)

ሁለተኛ ምዕራፍ

የወያኔ ወራሪ ቡድን በ1983 ዓ.ም የሃገሪቱን በትረ መንግስት እንደያዘ ኃይሉ በመጠቀም በወልቃይትና በጠገዴ ህዝብ ላይ የነበራቸውን ቂም ለመበቀል፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር፣ እንደታቀደው የ“ታላቋ ትግራይ” አካል ለማድረግና ፣ ከ15 ዓመታት በፊት የተጀመረውን ነባሩን ዘር አጥፍቶ በትግሪያዊነት የመተካት ዘመቻ አጠናክረው ቀጠሉ። ይኸውም፡-

 1. በአዋጅ የህዝብ ፍላጎት ሳይጠየቅ የወልቃይት፣ የጠገዴና የጠለምት ወረዳዎች (የጎንደር ታሪካዊና ለም መሬቶች) በትግርኛ ተናጋሪነት ሽፋን የትግራይ ክልል ማድረግ፤
 2. በገፍና በስፋት የትግራይ ሰፋሪዎች በእነዚህ ወረዳዎች በማስፈር  የአካባቢውን የዘር ስብጥር /Demography/ ወይም የህዝብ ሚዛኑን በትግሪያዊነት መቀየር፤
 3. የአካባቢው ተወላጆችን ከቦታቸው ማፈናቀል (በማሰር፣ በመግደል፣ ለም የርሻ መሬቶቻቸውን በመቀማት ወዘተ.)፤
 4. የአካባቢው ወጣት ሴቶችን በማስደፈር ወይም የትግራይ ሰው እንድያገቡ በማድረግ ማስወለድ ፤
 5. የህዝብ ንብረት በየምክንያቱ በመዝረፍ የድህነት ውስጥ ማስገባት የኢኮኖሚ ሃይሉ ማዳከም፤
 6. የአማርኛ ቋንቅን በትምህርት ቤትም ሆነ በማንኛውም የመንግስት ተቋም እንዳይጠቀም በማገድ፤
 7. ቀሪውን ህዝብ ለእርሻ በማያመቸው የደጋማው ክፍል ብቻ ተወስኖ መብቱና ነጻነቱ ታፍኖ በተወለደብት ቀዬው የሁለተኛ ደረጃ ዜጋና የበይ ተመልካች ሁኖ በድህነት እንዲማቅቅ ማድረግ
 8. የኢኮኖሚ አውታሮችን በሙሉ ከትግራይ የፈለሱ ሰፋሪዎች በበላይነት እንዲቆጣጠሩት በማድረግ የአካባቢው ተወላጆች በተለይም ሴቶችና አረጋውያኑ የመጤዎቹ የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ በማድረግ … ወዘተ በእነዚህና በሌሎችም የተቀነባበሩ መሰሪ ዘዴዎች በመታገዝ ወደ ቀደመ ግባቸው በመገስገስ ላይ ይገኛሉ፡፡

እስኪ ለዛሬ ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል ሁለቱን ብቻ በመውሰድ በመረጃ አስደግፈን ለመቃኘት እንሞክር፡፡ በመጀመሪያ ቁጥር 2 ከዛም ቁጥር  5 እናያለን፡፡

ተራ ቁ. 2)፡- በገፍና በስፋት የትግራይ ሰፋሪዎች በእነዚህ ወረዳዎች በማስፈር የአካባቢውን የዘር ስብጥር /Demography/ ወይንም የህዝብ ሚዛኑን በትግሪያዊነት መቀየር፤ ይህም በሁለት መንገድ የተደረገ ነበር፡፡

አንደኛው ወያኔ ስልጣን በያዘ የመጀመሪያዎቹ አመታት ቀደም ሲል በታቀደው መሰረት የተደረገ ሲሆን፤ ይኃውም በ9 ምርጥ ቦታዎች ወይም የሰፈራ ጣቢያዎች ላይ የትግራይን ህዝብ በገፍ ማስፈር ነው፡፡ እነሱም

 1. የመጀመሪያው እርምጃ በ 1984 ዓ.ም ወይናት በምትባለው ቦታ ከ23,000 (ከሀያ ሶስት ሺህ) በላይ የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ነባር ታጋዮች እስከ ሙሉ ትጥቃቸው እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። ይህ ቦታ ቀደም ሲል የማህበረሰቡ ነባር የእርሻ መሬት ነበር ፡፡ በዚህ የሰፈራ ጣብያ ክልል አንድም ወልቃይቴና ጠገድቸ እንዳይንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን ማንም ቢሆን ወደዚህ ክልል ከገባ ባይሞትም በከፍ ሁኔታ ተቀጥቅጦ ይወጣል፡፡ በዚህ  ክልል ውስጥ የገቡ ከብቶች በፍፁም አይመለሱም፡፡ የሰፋሪ ውርስ ይሆናሉ እንጂ፡፡

 

 1. ርዋሳ የተባለው መንደር ከደጋው ወልቃይትና ጠገዴ በመውረድ ከ500 በላይ ቤተሰቦች ቤት ሰርተው በግብርና የሚተዳደሩበት ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነባር ነዋሪዎችና ተወላጆች ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ከዚህ ቦታ እንዲለቁ ትእዛዝ ከ ይሰጣቸውል፡፡ ይህንን መፈናቀል የተቃወሙ የአካባቢው ነዋሪዎች በአቶ ብርሃኔ ዳኘህኝ  መሪነት የህዝቡን ፊርማዎች በማሰባሰብ ወደ ወረዳው ጽ/ቤት ሄዱ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዳይቀጥሉ ከቀጠሉ ለህይዎታቸው ዋስትና እንደማያገኙ ተነግሯቸው ተመለሱ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ወያኔ  በሚያዝያ ወር 1986 ዓ.ም ካድሬዎቹን አስልኮ ነዋሪዎቹ ንብረታቸውን ሳያወጡ 500 ቤቶችን በእሳት እንዲያጋዩት አድርጓል። ልክ በሁለት አመቱ በ1988 ዓ.ም ወራሪው የወያኔ ቡድን ከትግራይ አዲስ ሰፋሪዎችን አምጥቶና አስታጥቆ ሊያሰፍርበት ችሏል፡፡ ለግንዛቤ ያህል በወያኔ ከቀያቸው ተባረው ቤታቸው ከተቃጠለባቸው  ወገኖች ጥቂቶቹ፤
 2. አቶ ጫቅሉ አብርሃ 2. አቶ አብርሀ ሳህሉ 3. ወ/ሮ ስገዱ ተስፋይ (5 ዓመት ታስራ ከብቶቿና ግንዘቧ ተውስዶ ተለቃለች)  4. አቶ ዋኘው ይቀጥላል።

ከላይ በዝርዝር ከተገለፁት 2 ቦታዎች በተጨማሪ አዳዲስ ሰፈራዎች የተካሄደባቸው ቦታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ማይ ደሌ
 2. አንድ አይቀዳሽ
 3. እምባ ጋላይ ከ3000 በላይ ጥማዶችን ያርሱ የነበሩ ገበሬዎች ከቦታው በማፈናቀል 1988-1989
 4. ትርካን
 5. አደባይ
 6. ረውያን
 7. ግይጽ

ሁለተኛው ደግሞ ወያኔ ከተደላደለ በኃላ በመንግስት እርዳታና አጋዥነት እንዲሁም ቀስቃሽነት ጭምር ሰፍሮ የሚኖር ነው፡፡

 1. ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ከዋልድባ ገዳም ድንበር ጀምሮ የተከዜ ወንዝ እያካለለው ወደ ምእራብ እስከ ሱዳን ድንበር የተንጣለለው እጅግ ለም በሆነው መሬት በመዘጋ ወልቃይት( ማይ ህርገጽ፣ ቤት ሞሎ፣ ማይ ጋባ፣ ቃሌማ፣ እጣኖ፣ መጉእ፣ …..) ነዋሪ የነበሩትን የወልቃይትና ጠገዴ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን ይህን ለም መሬት ለቀው ወደ ደጋው እንዲሄዱ ቀጭን ትእዛዝ ይሰጣቸዋል። ይህን ትእዛዝ የተቃወሙትን ሁሉ ለእምቢተኝነታቸው አንዳንድ ሳምንታት እያሰሩ በመፍታት ቦታውን በግድ እንዲለቁ አስደረጉ። ከዛም በዚህ ለም የእርሻና የመኖሪያ መሬት ላይ በገፍ የትግራይ ህዝብ መጥቶ እንዲኖር በቂ ድጋፍ ተደርጎ በአሁኑ ሰአት ይህ አካባቢ 100% በትግራይ ህዝብ ባለቤትነት ይገኛል። አሁን በዚህ መዘጋ ወልቃይት ከሰሊጥ ፣ ጥጥና ማሽላ ገቢ ሌላ ማይ ጋባ በምትባል ከተማ ወያኔና አጋሮቿ እጅግ ትልቅ የከብት ገበያ በመክፈት ኪሳቸውን እያደለቡ ይገኛሉ፡፡
 2.  በወልቃይቴነታቸው ታዋቂዎቹና ዝነኞቹ በየባህላዊ ዘፈኑ ሳይቀር ዛሬም ድረስ የሚዘከሩቱ የሁመራ፣ አዲጎሹና፣ ማይጋባ አካባቢዎች  99.9% ነዋሪው ከትግራይ ፈልሰው በመጡ ሰዎች የተያዘ ነው።
 3. ባጠቃላይ በወልቃይትና በጠገዴ ለም መሬቶች የሰፈረው የትግራይ ህዝብ ብዛት ከ500,000 በላይ ነው። ብዙ የትግራይ ሰዎች ወልቃይት ድረስ በመምጣት የእርሻ መሬት ከተረከቡ በኋላ ነዋሪነታቸው ትግራይ ውስጥ በማድረግ የገዛ ለም መሬቱን ለተነፈገው ወልቃይቴና ጠገድቸ በእጅ አዙር መልሰው በማከራየት የሚጠቀሙ ሰፋሪዎች ቁጥር እየበዛ እንደሄደም መረጃዎቻቾ ያሳያሉ። ባጠቃላይ የአካባቢዉን ነባር ማንነት (Demography) በተለይም ማለት ይቻላል የወልቃይት ተወላጅ ነዋሪ ቁጥር በሰፋሪ የትግራይ ሰዎች ብቻ ተዉጧል።

ይህንን እውነታ ለመረዳት ይረዳዎት ዘንድ የኢትዮጵያ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1984፣ በ1994 እና በ2007 በአካባቢው ያደረገውን የህዝብ ቆጠራ ውጤት በወቅቱ ካወጣው የቆጠራ ረፖርት ላይ የተወሰደውን መረጃ ይመለከቱ ዘንድ ተጋብዘዋል፡፡

የወረዳዎች ስም                   በ1994G.C                                  2007G.C

                 ድምር            ወንድ            ሴት               ድምር          ወንድ          ሴት
 ሁመራ        48,690        25,456         23,234            92,167          47,909      44,258
ወልቃይት     90,186        45,657          44,529           138,926        70,504      68,422
ጠገዴ         59,846       30,282         29,564            103,852        52,763      51,089
በ1984 G.C               ድምር                   ወንድ                ሴት
ሰቴት(ሁመራ)             83,044               40,689              42,355
ጠገዴ                      69,000               35,611                33,389
ወልቃይት                 66,415                34,279               32,136
Notice: During 1984 Ethiopian Population and Housing Census Tegede and Welkayit were not covered. The population size is simply estimated. In addition to this in that time Humera was not considered as wereda.

Source: 1. The 1984, 94, & 2007 Ethiopian Population and Housing Census

ለግንዛቤ ይረዳን ዘንድ እስኪ ከላይ በቀረበው የወያኔ ድርጅት ቆጠራ ሪፖርት መሰረት ቢሆን የሁመራን ውጤት በመውሰድ እንመልከት።

በፈረንጁ አቆጣጠር 1984 ( በደርግ ዘመን መሆኑ ነው) የህዝቡ ቁጥር 83,044 እንደነበር ያሳያል፤ በ1994 ማለትም ወያኔ የመንግስቱን ስልጣን ከያዘ ከ3 ዓመታት በኃላ ግን የህዝቡ ቁጥር ከ83,044 ወደ 48,690 እንደቀነሰ ያሳያል፤ ይህም 34,354 ህዝብ ቦታውን ለቋል ማለት ነው።  በአንፃሩ ደግሞ ከ13 ዓመታት በኃላ (በ 2007 መሆኑ ነው) የሁመራ ህዝብ በእጥፍ እንደጨመረ ይታያል (ማለትም ከ48,690 ወደ 92,167)፡፡   ይህ ሁሉ ህዝብ ከየት መጣ ብላቹህ እንደምትጠይቁ  ግልጽ ነው።በእነዚህ አመታት ግን (ቀደም ሲል በስፋት ለመግለፅ እንደተሞከረው ) የአካባባቢው ተወላጅ በግፍ ሲታሰር፣ ሲገደል፣ እንዲሰደድ ሲደረግ  የነበረ በመሆኑ የሁመራን ህዝብ ቁጥር መጨመር ምንጩ ከትግራይ ብቻ እንደሆነ ለማሳወቅ እንወዳለን።  በአሁኑ ስአት ሁመራ ከተማ ውስጥ ከ 11 አባወራዎች የማይበልጡ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች ብቻ እንዳሉ ስናረጋግጥ በአንፃሩ ደግሞ 99.9% በትግራይ ፈላስያን የተወረረ መሆኑን እማኛችን የወያኔው የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ጭምር ነው።

ወልቃይት ከ1984 -2007 በቆጠራው መሰረት(1984 በፍረንጁ አቆጣጠር) ከ66,415 ወደ 138,926 አድጓል፡፡ ይህም ከእጥፍ በላይ ጨምሯል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በስደት እየተገፋ የወጣውን፣ በእስር ቤቱ ታጉሮ የሞት ጽዋ የተጎነጨውን ቁጥር ቀንሳችሁ ብታስቡት ደግሞ በተጠቀሱት አካባቢዎች ከትግራይ መጥቶ የሰፈረው ህዝብ ቁጥር ከዋናው ነዋሪ በብዙ እጥፎች በልጧል! ስለዚህም ዴሞግራፊው ወይም የህዝብ ሚዛኑ ያለጥርጥር ለትግራይ ሰዎች አጋድሏል!!

 

 

 

ተራ ቁ. 5) የህዝብ ንብረት በየምክንያቱ በመዝረፍ የድህነት ውስጥ ማስገባት የኢኮኖሚ ሃይሉ ማዳከም፤ እስኪ ይህንን እኩይ የወራሪ በደል በተጨባጭ መረጃ ለማብራራት እንሞክር፡፡

በመጀመሪያ ወያኔዎች  በሰላማዊው ህዝብ ላይ በተለይም ልጆቻቸው መሳሪያ አንስተው በሚዋጉት ላይ ልጁን ያላስገባ እስከ ሰባት ትውልድ ንብረቱን እንደሚወርሱና እንደሚያስሩ ያውጃሉ። በዚህም ወቅት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወላጆችና ቤተስቦችን አስረው መዳረሻቸውን አጥፉተዋቸዋል። ሀልዋ ሳውራ በሚባለው ዘራፊ ቡድናቸውም የህዝቡን ንብረት የእህሉንም፣ የከብቱንም የገንዘቡንም ዘረፋ በገፍ ፈፅመዋል። እንዲሁም አቅም አጥቶ ከቤት የዋለውን ወገን በሰበብ አስባቡ በቅጣት መልክ አራቁተዋል። ለምሳሌ ያህል፡-

 1. አቶ ዘነበ ሃጎሰይ                ከ450 በላይ የቀንድ ከብቶች
 2. አቶ ባየው ቢያድግልኝ         ከ600 በላይ የቀንድ ከብቶችና ፍየሎች በመጨረሻም እርሱን አስረው ገደለውታል
 3. አቶ ገ/ሕይወት ኃይሌ           ከ80 በላይ የቀንድ ከብቶችና ፍየሎች
 4. አቶ አለባ ህደጎ                 ከ500 በላይ የቀንድ ከብቶችና ቁጥራቸው በውን ያልታወቁ እጅግ ብዙ ፍየሎች                                                           ከሃያ በላይ የሰፋፊ ጎተራ እህልና ልኩ ያልታወቀ ገንዘብ (በ1981)
 5. ቀኛ/ ገብሩ ገብረመስቀል     12 ጥማድ (24) በሬዎች ከእርሻ አስፈትተው አርደው በመብላት 900 ማድጋ እህልና                                        አንድ የእርሻ መኪና ዘርፈው ወደ ትግራይ አሸሽተዋል።

በአጠቃላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችና ፍየሎች ንብረቶች እንዲሁም መጠኑ በውል ያልታወቀ ጥሬ ገንዘብ በተለያየ ምክንያት በመዝረፍ ህዝቡን አራቁተዉታል፡፡

የንብረት ዘረፋውና ወረራው በመራር በደልም የተጨማለቀ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ሁለት አሳዛኝና አስቀያሚ ትዝታዎችንን እንመልከት፡፡

አንደኛው በአንዲት አረጋዊት እናት እማሆይ ጀንበር አበራና አንድያ ልጃቸው ላይ የተፈፀመው መራር በደል ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡

የወያኔ ወራሪ ቡድን በ1973 ዓ.ም ደጋ ወልቃይት ቃብቲያ አጽም ሃርማዝ በምትባል መንደር ነዋሪ የሆነው  አቶ ነጋ ተበጀ የተባለ ገበሬ ይዘው ያስራሉ፡፡ በወያኔ ታስሮ ድምጹ የጠፋባቸው እናት እማሆይ ጀንበር አበራ ብቸኛና አንድ ብቻ ልጃቸውን ለማስፈታት የወያኔ ባለስልጣናትን መማፀን ይጀምራሉ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ ድርድር በኋላ ልጃቸው እንዲፈታ የ17,000.00 ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ተነገራቸው። አርከበ እቁባይ የተባለው የወያኔ አመራር ገንዘቡን እንዲሰበስብ በውቅቱ ለነበረው የወያኔ ገንዘብ ያዥ ለበያን ወድፍትዊ ትእዛዝ ሰጠ። እኒህ ምስኪን ሴት ከዘመድ አዝማድና ከቤተክርስቲያን ሳይቀር ተበዳድረው፣ የሚሸጥ ንብረት ሻሽጠው አንዱና ብቸኛ ልጃቸውን ለማዳን 17,000.00 ብር አዘጋጁ፡፡ ወዲፍትዊም ከእኒህ ምስኪን ሴትዮ ብሩን በጥሬው ተቀበለ።  እናት ልጃቸውን ለማዳን ያደረጉት ጥረት ግን በከንቱ ነበር። ምክንያቱም አንዱ ልጃቸው በወያኔ እጅ ከተገደለ አመት አልፎት ነበር፡፡ እኒህ አረጋዊት እናት ልጃቸውም ሆነ ገንዘባቸውም በወያኔ ተበሉ!!!

ሁለተኛው አሳዘኝ ታሪክ ደግሞ የሚከተለው ነበር፡፡

በ1974 ዓ.ም ስብሃት ነጋ  ለወልቃይት የወያኔ የበላይ የበጦሎኒ መሪ ወደ ጎሽሜ (ወድዝራብእ) ከወልቃይት ህዝብ በቅጣት መልክ 45,000.00 ብር አሰባስቦ በአስቸኳይ እንዲልክ ትእዛዝ ሰጠው። ለዚህም ዘረፋ እቅድ ወጣ፡፡ እቅዱም በአንድ ወቅት የደርግ ጦር ወልቃይት ውስጥ በነበረበት ጊዜ እኛን ለመውጋት ከደርግ ጦር ጋር አብራቹህ ዘምታቹህብናልና ለዚህም ካሳና እንዲሁም በጥማድ በሬ ሂሳብ 300.00 ብር  እንዲከፍል ህዝቡን ማስገደድ ነበር። በዚህም ዘረፋ ከታቀደው በላይ ለመዝረፍ ችለዋል። ለዛሬ እኒህን የመሳሰሉ በደሎችን በዚህ እንግታና ወደ ማጠቃለያ ሃሳባችን እንለፍ፡፡

 

ውድ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን እንግዲህ እንደዚህ አይነቱ ሆን ተብሎ አንድን ወገን አጥፍቶ በሌላ የመተካት ከባድ ወንጀልና የአካባቢውን ዴሞግራፊ መቀየር (የህዝብ አስፈፋፈር ሚዛን) በአለም ህብረተሰብ ዘንድ የተወገዘው የዘር ማፅዳት /Ethnic Cleansing/ ወንጀል አካል መሆኑን በመግቢያነት የተጠቀምንበት በ1949 (እ.ኤ.አ) የአለም መንግሥታት ባጸደቁት የዥኔቫ ስምምነቶችና በ1992 (እ.አ.አ) የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት፤

 1. በማንኛውም ሰላማዊ ህዝብ ላይ የዘር ግንድን መሰረት በማድረግ በተቀነባበረ መንገድ የሚፈጸም፣ ህዝብን ከመኖሪያ ቦታ የማፈናቀል፣ የኢኮኖሚ አቅሙን ማዳከም፣ የማሳደድ፣ ግድያና ግብረ ስጋዊ አመጽ መፈጸም፣ የመሳሰሉ ተግባሮች ወንጀልነታቸው Crime Against Humanity” በመባል ይታወቃል።
 2.  እንዲሁም አንድን ህዝብ ሆን ብሎ ከቀዬው ማፈናቀልና የሌላ ጎሳ ተወላጆችን በምትኩ ማስፈር በዘር ማጥፋት (Genocide) ደረጃ የሚፈረጅ የዘር ማፅዳት (Ethnic Cleansing) ወንጀል መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በ1992 (እ.አ.አ) ባስተላለፈው ውሳኔ በግልጽ አስቀምጦታል።

ስለዚህ ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሆይ

የዚህን አሰቃቂና አሳዛኝ የወገናችሁን እልቂትና መከራ ከስረ-መሰረቱ በመረዳት፤ ለዚህም የተቀነባበረ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዋነኛ ተዋናኝና ተጠያቂ ወያኔና አጋሮቹን (ተባባሪዎቹ) መሆናቸውን በመገንዘብ፤

1ኛ. ይህንንም እውነታ ላላወቀ ወገናችንና ለመላው አለም እንድታስታውቁልን፤

2ኛ.  በተለይም ደግሞ ቀሪው የወልቃይት፣ የጠገዴና የጠለምት ወገናችን ለነገይቱ ኢትዮጵያ እንዲተርፍ የሚቻላችሁን ሁሉ እንድታደርጉልን፤

3ኛ. ተጠያቂዎችም ይዋል ይደር እንጅ ከፍትህ ፊት የሚቀርቡበትን መንገድና በወገናችን ላይ ለፈፀሙት ግፍና በደል ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ የምናደርገውን ጥረት በሁሉም መስክ እንድታግዙን፤

4ኛ. መንግሥታትንና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን በማሳወቅና በመሳሰሰሉት ሁሉ ወገናዊ አለኝታችሁን እንድትወጡ፤ የአክብሮት ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም

ይህን የወያኔ ግፍና ጭካኔ ለወገንና ለዓለም ህብረተሰብ ለማዳረስ በምናደርገው ትግል የተባበራችሁንና መልእክታችንን ለሚመለከተው ሁሉ ያደረሳችሁልን የድረገጾች፣ የጋዜጣዎች፣ የሬዲዮኖችና የቴሌቪዥኖች ባጠቃላይ የህዝብ መገናኛ አውታሮች አዘጋጆች፣ ጋዜጠኞችና፣ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች ሁሉ ከፍ ያለው ምስጋናችንና አክብሮታችን ይድረስልን፡፡

በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት የወገናችንን ሰቆቃና በደል ተሰምቷቸው ጩኸቱን በባለቤትነት አንግበው በቻሉት መንገድ ሁሉ በመንቀሳቀስ የወያኔን ወንጀል በማጋለጥ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለሚመለከተው ሁሉ ላደረሱልን የክፉ ቀን ባለውለታዎቻችን ሁሉ በዚሁ አጋጣሚ በራሳችንና በተገፋው ወገናችን ስም ላቅ ያለ ምስጋና እናቀርባለን፡፡

እንዲሁም በዚህ ጦማር ላይ ትክክለኛ ማስረጃ በማቅረብ፣ ምክርም ሆነ ሀሳብ በመለገስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ያዘጋጁት በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በአውስትራሊያ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ አያሌ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ፡ ቀጥተኛ ጥያቄም ሆነ አስተያየት ካለዎት ግን ስማቸው ከዚህ በታች የተጠቀሱን ሰዎች በ aamg50@yahoo.com  መገናኘት ይችላሉ።

አቶ ቻላቸው ዓባይ ፣ አቶ ጎሹ ገብሩ፣ አቶ ዓባይ መንግስቱና፣ አቶ አብዩ በለው ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለ ትኑር! የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብም እንዲሁ!

የካቲት 7 ቀን  2004 ዓ.ም.■ To receive breaking news and important updates from Mereja.com, please subscribe to our email newsletter. ⇒ CLICK HERE እዚህ ላይ ይጫኑ ⇐

► Post your comment below
የአንባቢያን አስተያየቶች

 1. GONDERE says:

  weyane (NAZY) reched at its stage because of Amhara people but Today this patriotic people higly suffer from thise GANGSTER Group.Not Only Amhara’s of welqait tsegeda and particular areas but other ethiopian ethinic people Gambela,Ogaden,Afar And DEBUB N and Na.Such kind of Genocied Led to ICC or ICJ i hope in the Future ?ASALIEFENAL KFUDEGUN LE AND AGER!! LE AND DIENBER ENESUGIEN ENESUGIEN …This Type of Crime Against Humanity is Like British Colonial Time BOMB.This kind exploting in the FUTURE!!!GIEZE LE KULU!!!NEVER FORGAT IT.God bless Ethiopians.
  FROM ADDIS ABEBA.

 2. Dagmawi says:

  Woyane is not only doing this land grab. It is also introducing the devils religion of pente by prosletyzing the poor farmers in completely Orthodox following areas. Anyone who dares to speak against this large scale indoctrination of foreign belief will be branded as neftegna. Ara Egziabher bekachuh belen. Ethiopia hageren kemenafek ejj awtat.

 3. Kendeya Abreha says:

  WOLQAYIT TSEGEDE TSELEMT will never be part of Tigrai ….its all about time …mark my words …we made a grave mistake by trusting them in the past…they know what we can do …our bretheren will also be with us …we not few we are not diminishing …we will prevail …its wise for weyenti leave to shire and medebai zana before it is too late

  Wed qabtiya of WALQAYIT -GONDER

  Kindeya

 4. Derege Alemayehu says:

  TPLF has done similar crime on Gonder people as Nazi Germany did to the Jewish people. The difference between the two crimes is the Jewish people were able to bring the Nazi criminals to justice where as the Amara people has yet to bring the case into attention.

 5. koster says:

  Ethiopia which survived the scramble for Africa as an independent nation is now under what is called “internal colony”. It is very unfortunate that the terrorist Organization TPLF is looting Ethiopia in the name of the people of TIGRAI and to fulfill their dream of building “greater Tigrai”. Do they really think they will have lasting peace by forcefully taking areas fróm Gondar, Wollo and Afar and causing genocide and forced marriage among the “natives”. Meles has British advisors who have already experience in ethnic cleansing in the Falkland islands which once belonged to Argentinia and occupied by British until now. I hope the people of Ethiopia will say no to the genocide committed by the terrorist organization TPLF in Wolqait, Gambella, Ogaden and elsewhere in Ethiopia.

Leave a Reply

Please answer this math question before submitting your comment: