የምንፈልገውን ለውጥ ለማምጣት

ከባሕር ከማል

“ለውጥ “ የሚባለውን ቃል ስንሰማ ወዲያውኑ በአዕምሮአችን ውስጥ የሚቀረፀው ጥሩነቱ ብቻ ነው። መጥፎ ውጤት የሚያስከትል ለውጥ መኖሩን ባንዘነጋም እምብዛም ትኩረታችንን አይስብም። የለውጥ ውጤት መቶ በመቶ ጥሩ ይሆናል ብሎ መገመት ባይቻልም በምኞት ደረጃ ግን ሁሉም የሚመኘው ጥሩውን ነው። አንዳንዴ ግን ምናባቱ ከዚህ የባሰ አይመጣም ይባላል።ይህ ከጭንቀትና ነባሩን ሁኔታ ለመቋቋም በማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደረስ ከብሶት የሚመነጭ እንጂ ምን ጊዜም የባሰ ሊመጣ እንደሚችል ቀደም ብሎ መገመቱ አይከፋም። ለጥሩ ውጤት ይበልጥ እንድንዘጋጅ ያደርገናልና።

ከላይ የተጠቀሰው ለውጥ ማህበራዊ ለውጥን በተመለከተ ሲሆን ይህ ለውጥ በሥነ-ማኅበረሰብ (sociology) ጥናት መሥረት በአንድ ሀገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን የሚያካትት በመሆኑ በተደራጀ ሃይል በሚመራ ህዝባዊ ተሳትፎ የሚመጣ ነው።
የሚፈልገውን ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የመሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው። ተሰጥዖ የሚይዘው ሥፍራ ከፍተኛ ቢሆንም በዕውቀትና በልምድ ያልተደገፈ አመራር ወደ ውድቀት ያመራል።

መሪዎች የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ከሚመሯቸው ህዝቦች ይበልጥ መስራት እንደሚኖርባቸው ግልጽ ነው።ህዝባቸውን ወደ ተፈለገበት አቅጣጫ መርቶ ለድል ለማብቃት በሚደረገው ጉዞ መሪዎች የሚከፍሉት መስዋዕትነት ቀላል አይደለም። መስዋዕትነቱ ከግላቸው ጀምሮ የቤተሰቦቻቸውን፤ የቅርብ ዘመዶቻቸውንና የጓደኞቻቸውን ህይወት የሚነካ ይሆናል።ከኛ የሚጠበቀውን ሳናደርግ ከነሱ ብዙ መጠበቅ መስዋዕትነቱን የበለጠ ከማክበዱም ሌላ ከታለመው ግብ ለመድረስ የሚደረገውን ጉዞ ያራዝማል።

በነገራችን ላይ እነ አቶ መለስ ከማህበራዊ ለውጥ ይልቅ መተካካትን ስለሚመርጡ ለዚህም ዝግጅት እላይ ታች ማለት የመጀመራቸው ወሬ ከተሰማ ሰንብቷል። ምክንያቱም እነሱ የማህበራዊ ለውጥ ውጤትን በሚገባ ያውቁታልና። ማንኛውም ማህበራዊ ለውጥ ጥሩም ሆነ መጥፎ የሚያስወግዳቸው መሆኑን ስለሚገነዘቡ ማህበራዊ ለውጥ እንዳይመጣ ቀንና ለሊት እየሰሩ ነው። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ኦባንግ ሚቶ እንዳሉት ለትንሸ ዳቦ ጫካ ገብተው (ትግራይን፡ነፃ ለማውጣት) ከዚያ ሲመለሱ ትልቁን ዳቦ ያለ ባለቤት አገኙ (ኢትዮጵያን)።ታዲያ ለውጥ ከመጣ እንኳንስ ትልቁን ትንሿን ዳቦ አያገኙም እድለኛ ከሆኑ ወይም ቀደም ብለው ካሰቡበት አብዮታዊድሞክራሲ፡ሻንጣቸውን ይዘው ወደ አዘጋጁት ሀገር መሸሽ ነው። እርግጥ ዛሬ በየመን ህዝብ የተተፋን አምባገነን መሪ አሊ አብደላህ ሳለህን ለማስተናገድ መዘጋጀቱ የኢትዮጲያን ህዝብ ከመናቅ የመነጨ ቢሆንም ነግ ተመሳሳይ እድል እንደሚያጋጥማቸው የተገነዘቡ አይመስሉም።በአሁኑ ወቅት የአምባገነኖች ቁጥር እየቀነሰ ስለመጣ ከህብ የመሸሻ ቦታ በቀላሉ እንደማይገኝ ከአሊ አብደላህ ሳለኢህ ልምድ በመቅሰም የተቀበሉን ማመልከቻቸውን ካሁኑ ቢያስገቡ ይሻላቸዋል፤ ያለበለዚያማ ለሠሩት ግፍ በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ለፍርድ መቅረባቸው አይቀሬ ነው።

አንድ መሪ አንድን ሃገር ወይም ፓርቲ በብቃት ሊመራ የሚችለው፤ ከማዘዝ ይልቅ ቀስቃሽ ስሜት የሚያሳድር (inspire)፤በራሱ የሚተማመን፤ስህተትን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ፤አስፈአጊ በሁነበት ሌሎች እንዲመሩ የሚያደርግ፤ከሌሎች የሚማር፤ ከራሱ በፊት የህዝቡን ጥቅም የሚያስቀድም፤ የሌሎችን በጎ አስተዋጽዖ የሚያደንቅ፤ከሥራው በስተቀር ሙግስና የማይፈልግ ሆኖ ሲገኝ ነው።የነዝህ ሁሉ መሰረት የሆነው ደግሞ እውቀት ነው። ለምንሠራቸው ሥራዎች በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ከሌለን በራስ ያለመተማመንን አለመግባባትንና ተረባን(Bullying) ከዚያም አልፎ ግብዝነትን ያስከትላል። ይህ በበኩሉ ደግሞ የአምባገነንነት መቆጥቆጫ ይሆናል። እነ አቶ መለስም አሁን ያላቸውን በህሪይ ያካበቱት እዚያው ከትግል ሜዳ ጀምረው ነው። ስለዝህ ይህንን ያላሟላ መሪ ህዝቡን ወዳልሆነ አቅጣጫ ስለሚመራ ለምንፈልገው ማህበራዊ ለውጥ አያበቃንም፤ ከጉልቻ መለዋወጥ አያልፍምና።

ከአንድ ወዳጄ ጋር ብዙውን ጊዜ በዚህ ጉዳይ እንከራከራለን። ካሁኑ እየተራረምን ካልተጓዝን “ይህ ጉደይ ወይም ስህተት አንገብጋቢነቱ ወቅታዊ አይደለምና አንድነታችንን ያናጋል ወይም ለተቀራኒው ወገን ቀዳዳ መክፈት ይሆናል” የሚባለው ደካማ አስተሳሰብ ነው። ስህተትን ወይም ድክመትን በእንጭጩ እንጂ ዛሬ ትንሹን ዝም ብለን ካሳለፍን ይዘገይና ትልቅ ሆኖ በኋላ ላይ መጋፈጡ ይከብዳል ይላል። ትክክለኛ አባባል ነው።እርግጥ የመጀመሪያ እርምጃችን በቀጥታ ባይሆን የሚመለከተው በሚገባው(ባ ይላላል) መንገድና ቋንቋ መልእክታችንን ማስተላለፉ አስፈላጊነው።ያለበለዚያ ይህች ባቄላ ካደረች ዓይነት ይሆናልና።

በመሠረቱ ለመሪዎቻችን፤ አሁን ላሉትም ሆነ ላለፉት፤ ወደ አምባገነንነት መለወጥ የእኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አምናለሁ ፤መሪዎቻችንን የማምለክ ባህሪይ ያለን መሰለኝ። እርግጥ ሁሉም ሰው መሪ ሊሆን አይችልም የመምራት ችሎታና ዕውቀት ያለው ሰው እንጂ ።ችግሩ ግን ስልጣን ከጨበጡ በሗላ ልዩ ሰዎች ወይም መለኮታዊ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። መሪዎቻችንም ይህንን መሠረት በማድረግ የስልጣን ጥማታቸው እያየለ ሲመጣ ያለነሱ ሌላ ለዚያ ህዝብ እንደሌለ ይሰብካሉ። የመሰረቱትም መንግሥት ከተወገደ ህዝቡ እንደ ሚበተን ሀገሪቱ እንደ ሀገር ሆና እንደ ማትኖር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፕሮፓጋንዳቸውን በመንዛት ህዝቡ እንዲያምናቸው ደፋ ቀና ይላሉ። በተጨማሪም በተቻላቸው መጠን ተተኪ እንዳይኖር ከስፈለገም ካምሳያቸው እንዲሆን ሌት ተቀን ይሰራሉ።ስለዚህ እኛው ነን ያለችሎታቸው ክበናቸው ሲያጠፉ ዝም ብለናቸው የአምባገነንነትን መንገድ ጨርቅ ያርግላቸው ብለን በሗላ ላይ የምንቸገረው ።

የአቶ መለስ ባለቤት ታዋቂ በሆነችው የድህነት ማስተባበያ ቃለመጠይቃቸው ላይ “እኔም ሆንኩ መለስ ደሃ አይደለንም አልኳቸው ገንዘብ የምንፈልግ ቢሆን የመለስ ጭንቅላት በየትኛውም ሌበር ማርኬት (Labour market) ተሽጦ ሊያኖረን ይችላል” ብለዋል። ይህ ከቀጥተኛው ፕሮፖጋንዳዎች አንዱ ነው። ሲተረጎም አቶ መለስ “ለህዝቡ ሲሉ” እንጂ ለስልጣን ወይም ለገንዘብ ብለው አይደለም 20 ዓመት እየገዙን ያለው፤ እሳቸውን የሚተካ ሰለጠፋ ነው።አቶ መለስ በበኩላቸው ለምን ስልጣን አያስረክቡም ሲባሉ “እኔ ብለቅ ደስይለኛል ግን ፓርቲዬ ስለፈለገኝ ነው” ብለዋል ይህም እኔን የሚተካ የለም እኔው ብቻ ነኝ ለዚህች 90 ሚሊዮን ህዝብ ለሚኖርባት ሀገር እንድመራት የተፈጠርኩት ከማለት በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም።

ሌላው ቀርቶ ገና በትረ ስልጣን ያልጨበጡ የአንዳንድ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት መሪዎቻችን እንኳን ሳይቀሩ በተለይም መተራረምና መወቃቀስ ባህል በሆነበት በሰለጠነው ዓለም ውስጥ ያሉትን ጨምሮ እነሱ የሚሉትን የማይቀበልን እንደ ጠላት ይፈርጃሉ። ስለዚህ ከዚሁ ነው ከኔ መንገድ ሌላ የሚያዋጣ የለም በማለት ለአንባገነንነት እጩ የሚሆኑት።እነ አቶ መለስም በዚሁ ሁኔታ ነው ለዚህ ለለየለት አንባገነንነት የበቁት።በኛው ትብብር ማለት ነው

በተቃዋሚው ጎራ ትብብር ማነስ ወይም አለመኖር የዚህን አይነት ባህርይ የሚያንጸባርቁት መሪዎቻችን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ድርጅቶቻቸውን እንወክለሃለን ከሚሉት ህዝብ የሚያስቀድሙ እንዳሉ ነው። ይህ ደግሞ በአባሎቻቸው መሃከል ሃሳብ እንዳይንሸራሸርና አፋቸውን ለጉመው በጭፍን ሁሌም ለመሪዎቻቸው ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።ይህ በበኩሉ ደግሞ የህዝባችን ነፃ የመውጣት ጊዜ የሚያራዝም ከመሆኑም በላይ ለሃገሪቷ ህልውናም አስጊ ሁኔታን ይፈጥራል።

በእንደነዚህ አይነት መሪዎቻችን ምክንያት አብሮ መስራት አይቻልም ብለው ተስፋ ቆርጠው ከማንም ሳይወግኑ ቤታቸው የተቀመጡና የግል ኑሩአቸውን በመግፋት ላይ ያሉ ይኖራሉ።በእነዝህ ዓይነት ሰዎች ላይ መፍረድ ቢከብድም እኔ ግን ይልቁንስ ሌላ አማርጭ የሚፈልጉና አሊያም የራሳቸውን ድርጅት መስርተው ለትግሉ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚሞክሩ ይሻላሉ ነው የምለው። ምንም አለመስራት ከህሊና ተወቃሽነትም ሆነ ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንምና።

ለትግሉ መሳካት ለአንድ ዓላማ፤ ከተቻለ ግንባር በመፍጠር ወይም ወደ ውህደት በመሸጋገር አሊያም ሁሉም በየድርጅቱ የነደፈውን እስትራቴጂና ታከቲክ በመጠቀም ህዝቡን አሳምኖ ከጎኑ በማሰለፍ ለተሻለ ስርዓት መታገል ይበጃል። ለዚህም የመሪዎቻችን ሚና ከፍተኛውን ቦታ የያዘ ቢሆንም ለስኬቱ ግን የሁላችንም የያገባኛል ተሳትፎ ይጠበቃል።

እዚህ ላይ የወያኔን ዘረኛና አምባገነናዊ መንግስትን ለመጣል በየአቅጣጫው በመደረግ ላይ ያለው ትግል ከግምት ካለማስገባት አይደለም ይልቁንም ለተሻለ ውጤት ካሁኑ እያሰብንበት ከጥራትና ከጥንቃቄ ጋር ወደፊት መራመድ አለብን ለማለት ነው። ይህም በበኩሉ ከእሳት ወደረመጥ እንዳንገባ ያግደናል። ካለፈው ውድቀታችን መማራችን የሚገለጸው መጥፎ ታሪካችን እንዳይደገም ጥንቃቄና ጥረት ስናደርግ ብቻ ነው።

ሃገርራችን ከላይ የተጠቀሱትን ለመሪነት የሚያበቁ ነጥቦችን የሚያሟሉ መሪዎች እንደነበሯትና እንዳሏትም እሙን ነው።ሀገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ በህወሃት ግፊት የተሰደዱ ይህንን አምባገነናዊ ስርአት በተሻለ ለመተካት የሚደርገውን ትግል በመምራት ላይ የሚገኙ መሪዎቻችንን ፍፁም አድርገን መቁጠር የለብንም። ስዎች ናቸውና ይሳሳታሉ፤ ልናርማቸው ይገባናል። እርግጥ አንዳንዴ መሪዎች ለጊዜው ተቀባይነት የሌላቸውና ለዘላቂው ግን ወሳኝ በሆኑ ጉዳዎች አቋሞችን ይወስዳሉ፤ በድርጅቶቻቸው አማካይነት ውሳኔዎችን ያስተላልፋሉ።በዚህን ጊዜ ከትችት በፊት ቆም ብሎ ማሰብና የድርጅቶቻቸው አባል ከሆን ለአብላጫው መገዛት፤ ካልሆን በግለሰብም ሆነ በቡድን ስለ አቋሙም ሆነ ስለ ውሳኔው ማብራሪያ ጠይቆ የራስን አቋም መውሰድ የበጃል።

እኛም ሆን መሪዎቻችን እርስ በርስ ከመጠራጠር መተማመንን፤ ከመናናቅ መከባበርን፤ እኔ ብቻ ልናገር ከማለት መደማመጥን፤ ከመቃረን መቻቻልን፤ ከመተራረብ መተራረምን፤ ከመቀያየም መታረቅን ስናስቀድምና ልማዳዊ ስናደርግ ብቻ ነው የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት የምንችለው። ለዘለቄታ ውጤት አማራጭ መንገድ የኔ ብቻ ነው። ስለሆነም ይህንን የማይቀበል ለኢትዮጵያ ህዝብ ያልቆመ ነው በሚል መደምደሚያ ላይ ከመድረሳችን አስቀድመን የሌላኛውን አማራጭ መገምገም ያስፈልጋል። በአንድ ድርጅት ውስጥ አብረን ስንሰራ ቆይተን በዓላማ ሳይሆን በሥራ ሂደት ላይ ለሚፈጠሩት ልዩነቶች በመተማመን ልዩነቶችን ማጥበብ፤ ሃይልን የሚከፋፍል አንጃ ከመፍጠር ወይም ሌላ አዲስ ድርጅት ከመመሥረት ውጣ ውረድ ያድነናል።ይህ ደግሞ በበኩሉ ከህዝብ ለህዝብ በህዝብ ለሚፈጠረውና ፍትህ እኩልነትና ነፃነት የሚያሰፍን በህግ የበላይነት የሚመራ መንግሥትን የመመስረቺያ ጊዜን ያቃርባል፤ የህዝባችን ስቃይም የሚያበቃበትን ጊዜ ያሳጥራል።
አላህ ኢትዮጵያን ከነህዝቦቹዋ ይባርካት!!!

ባሕር ከማል
bahirk@hotmail.com► To receive breaking news and important updates from Mereja.com, please subscribe to our email newsletter. CLICK HERE እዚህ ላይ ይጫኑ

► Post your comment below


Leave a Reply

Please answer this math question before submitting your comment:

Loading Facebook Comments ...