ቁጥሮች ይናገራሉ: ማድሪድ በዚዳን ስር ከገባ ወዲህ ሮናልዶ ከሚሰለፍበት ጨዋታ ይልቅ እሱ በሌለበት ቡድኑ ተሽሎ ተገኝቷል።

ቁጥሮች ይናገራሉ: ማድሪድ በዚዳን ስር ከገባ ወዲህ ሮናልዶ ከሚሰለፍበት ጨዋታ ይልቅ እሱ በሌለበት ቡድኑ ተሽሎ ተገኝቷል።

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ| ቅዳሜ ታህሳስ 29, 2009
ባሳለፍነው ረቡዕ በነበረው የኮፓ ዴላሬይ ጨዋታ ዚዳን የአመቱን የፍራንስ ፉትቦል አሸናፊ ክርስቲያኖ ሮናልዶን አሳርፎት ታይቷል። ይህንንም ያደረገው ያሳለፍነው 2016 አመትን ያለምንም እረፍት ከክለቡ እስከ ብሄራዊ ቡድን ድረስ ተከታታይ ጨዋታ ያደረገውን ኮከብ የበጋ እረፍት ለማራዘም በማሰብ ነው።

አንድ በትናንትናው እለት ይፋ የወጣ የቁጥር መረጃም የዚዳንን ፓርቹጋላዊውን የማሳረፍ ውሳኔ ትክክል መሆኑን ደግፏል። እንደ መረጃው ከሆነ ጋላክቲኮሶቹ በዚዳን ስር ከገቡበት ወቅት ጀምሮ ሮናልዶ ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ምንም ጨዋታ አልተረቱም።

ምንም አይነት ውሸት የማያውቁት ቁጥሮች እንዳሳዩት ከሆነ ነጮቹ ማድሪዶች በዚዳን ስር ሮናልዶን ሳይዙ 11 ጨዋታዎችን አድርገው 10 የሚሆኑትን ሲያሸንፋ በአንዱ ብቻ አቻ ወጥተዋል።

ብዙ ቡድኖች ኮከባቸውን ሳይዙ ሊቸገሩ ይችላሉ። ነገር ግን የዚዳንን ችሎታ ባጎላ መልኩ ማድሪዶች ፓርቹጋላዊውን ኮከብ ሳይዙ 11 ጨዋታዎችን በሚገባ መወጣት ችለዋል። ይህ የማድሪድ ሮናልዶን ያላሳተፈበት ጉዞ ስኬት ብዙዎችን እያስገረመ ይገኛል።

ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ማድሪድን ከዋና ከተማ አውጥቶ የቀደመ የአውሮፓ የበላይነቱን እንዲይዝ አድርጎታል። አሁን ያላቸው ያማረ ቅርፅም ዘንድሮ በሀገር ውስጥም ሆነ በአውሮፓ ላይ ዳግም የሚነግሱ አስመስሏቸዋል።

በማድሪድ ቤት ለመጨረሻ ጊዜ የላሊጋውን ክብር ማሳካት የቻሉት ጆሴ ሞውሪንሆ ሲሆኑ ዘመኑም በ 2012 ነበር። ከአምስት አመታት ቆይታ በኃላ ዘንድሮ 15 ጨዋታዎች በተደረጉበት የዘንድሮ ሊግ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው ከምንግዜውም ተቀናቃኛቸው ባርሴሎና በሶስት ነጥብ በልጠው የደረጃው አናት ላይ ተቀምጠዋል።

ምንም እንኳን ሮናልዶ ያልተሰለፈባቸው ግጥሚያዎች ማድሪድ በቀላሉ ያሸንፋቸው ነበር ተብለው የተገመቱ ቢሆንም እግር ኳስ ያልተጠበቀ ውጤት የሚመዘገብበት መሆኑ ሲታሰብ የማድሪድ ያለ ሮናልዶ ያስመዘገበው ስኬት አድናቆት የሚቸረው ነው።

እርግጥ ነው ሎስብላንኮዎቹ ያላሸነፉበት ጨዋታ በመጋቢት 2016 ከማንችስተር ሲቲ ጋር 0-0 የተለያዩበት የቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ነው።

በወቅቱ ማድሪድ ሁለተኛውን ዙር ጨዋታ በፈርናንዶ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት በሮናልዶ ጥንካሬ ሳይሆን በሲቲ ድክመት ታግዞ የፍፃሜው ተፋላሚነቱን ማረጋገጥ ችሏል።

ነጮቹ ለ 38 ጨዋታ ያለመሸነፍ ሪከርድን አሳክተው የላሊጋው ባለክብር ወደ መሆን እያመሩ ይመስላል። ሁኔታዎች እየተጓዙበት ያለው መንገድም በየጊዜው በረባ ባልረባው ነገር አሰልጣኝ መቀያየርን ልምድ ባደረገው ክለብ ዚዳን ለብዙ ጊዜያት መቆየት የሚችል አሰልጣኝ አስመስሎታል።

በሌላ በኩል ግን ዚዳን የቡድኑ ኮከብ ሮናልዶ በሚሰለፍበትም ሆነ በማይሰለፍበት ግጥሚያ ቡድኑ ህልሙን ማሳካት የሚችልና በአንድ ተጫዋች ላይ ያልተንጠለጠለ መሆኑን በደንብ ማረጋገጥ ይፈልጋል።

የአንባቢያን አስተያየቶች

Leave a Reply

Please answer this math question before submitting your comment: