ታስረዉ የሚበሉ (ምስጋናዉ ታደሰ)

ታስረዉ የሚበሉ

(ምስጋናዉ ታደሰ)
ቀበሮ እና ዉሻ የዘር ሀረጋቸዉ ከአንድ ግንድ የሚመዘዝ እንደሆነ የሥነ ሕይወት ሳይንስ ያረጋግጣል፡፡ ቀበሮ በዱርና በጫካ ዉስጥ መኖርን ስትመርጥ ዉሻ ደግሞ ከሰዎ ችጋር ተላምዳ የቤት እንሰሳ ሆነች፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ቀበሮና ዉሻ በአንድ የከተማ ዳርቻ አካባቢ ተገናኙ፡፡ ተሳስመዉ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ወሬያቸዉን ቀጠሉ፡፡ ዉሻ ቀበሮን “ከስተሻል፣ ጠቁረሻል፣ ተጎሳቁለሻል . . . ምነዉ ምነዉ?” አለቻት፡፡ ቀበሮም “የእኛ ነገር ሲገኝ ሲበላ ሲታጣ ጦም ሲታደር ነዉ፡፡ የእኛ ሕይወት ሁል ጊዜ ድካም ሁል ጊዜ ሩጫና መንከራተት ነዉ” በማለት መለሰችላት፡፡ ቀበሮም በተራዋ ዉሻን “አንቺ ግን ወፍረሻል፣ ቀልተሻል፣ ሰዉነትሽም ለስልሷል፣ አምሮብሻል ምንድን ነዉ ነገሩ” ስትል የተሰማትን ገለጸች፡፡ ዉሻዋም “አዎ እኛ ጋር የሚበላ ሞልቷል የሚጠጣም ሞልቷል፡፡ ስጋ በልተን ወይን ጠጥተን፣ በመኪና ሄደን ሶፋ ላይ ተኝተን ነዉ የምንኖረዉ” በማለት የኑሮዋን ደረጃ ገለጸችላት፡፡ በመጨረሻም ዉሻ ቀበሮን እንዲህ አይነት አሳዛኝና የተተጎሳቆለ ሕይወት ከምትኖሪ ለምን ከኔ ጋር ሄደሽ ጥሩ ሕይወት አትኖሪም (ላይፍሽን አትቀጭም) አለቻት፡፡ ቀበሮም በሀሳቡ በመስማማቷ ዉሻ ከፊት እየመራች ቀበሮም ከኋላ እየተከተለች ጉዞ ጀመሩ፡፡
ትንሽ እንደተጓዙ ቀበሮ የተሰለሰለዉን የዉሻዋን አንገት ተመልክታ ጉዞዉን ገታ አደረገችና እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠየቅሽ አለቻት ዉሻን፡፡ ጥያቄዋን በማስከተልም “ለመሆኑ እንዲህ አምሮብሽ ወፍረሽ ሳለ አንገትሽ ሊቆረጥ እስኪደርስ ድረስ እንዲህ የተሰለሰለዉ ምን ሆኖ ነዉ?” ዉሻም መለሰች “ይኼማ የምታሰርበት ነዉ፡፡ እንዲህ እስክወፍር ምበላዉ እኮ ታስሬ ነዉ፡፡” በማለት መለሰች፡፡ ቀበሮም ታስሬ ከምበላ ታስሬ ከምጠጣስ ነጻነቴ ይበልጥብኛል፡፡ ነጻ ሆኜ በነጻነቴ ሳገኝ በልቼ ሳጣ ጾሜን ባድር ይሻለኛል ብላ ዉሻን በቆመችበት ቦታ ጥላት ወደ ጫካዋ ሮጠች፡፡
ሀገር እንዲህ የምትታመሰዉ እንደ ዉሻዋ ታስረዉ በሚበሉ (ለእንጀራ ሲሉ ህሊናቸዉ በሸጡ) ፖለቲከኞች፣ ወታደሮች፣ የተቃማዊ ፓርቲ መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ዳኞች፣ ፖሊሲ አዉጭዎች፣ አርቲስቶች፣ ካድሬዎች፣ . . . ለጥቅም ሲባል በማዕሰረ ህሊና በታሰርን በሁላችን ዜጎች ነዉ፡፡
ተሿሚዎቹ ታስረዉ የሚበሉ – ያመኑበትን የማይሰሩ (ያመኑበትን ለመሥራት ነጻነት የሌላቸዉ)፣ ኧረ ይኼ ነገር አይበጅም ከህዝብ ጋር ያጋጫል፣ ለትዉልድም ለታሪክም ጥሩ አይደለም የማይሉ፣ ሲጠሯቸዉ አቤት ሲልኳቸዉ ወዴት ብቻ የሚሉ . . .
በተቃማዊ ፖለቲካዉ ጎራም ታስረዉ የሚበሉ – ተቃዋሚ ሳይሆኑ ህሊናቸዉን ታስረዉ የተቃዋሚ ፓርቲ ካባ ለብሰዉ “ሀገራችን ይኧዉ እንደፈለጉ መቃመም የሚችሉባት ሀገር ናት” የሚል ሀሳዊ አርማ ይዘዉ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ህይወት፣ በዜጎቻቸዉ ላይ ቁማር የሚጫወቱ፣ ብሶቱን ለመናገር አደባባይ ላይ በመዉጣቱ ብቻ በግፍ በተገደለዉ ዜጋቸዉ ደም እጃቸዉን የሚታጠቡ . . .
በእምነት ተቋማቱ ታስረዉ የሚበሉ – መንፈሳዊ ያልሆኑ ህሊናቸዉን ተሸብበዉ በመሪነት ደረጃ የተቀመጡ፣ መንጋዉን የማያዉቁ እረኞች፣ በጎቹን ሳይሆን የፖለቲካዉን ስልጣን ለመጠበቅ የተቀመጡ አንጃዎች . . .
የሚበሉት ሳያጡ፣ የሕዝብ ኪስ እና ልብ ገንዘባቸዉ የሆነላቸዉ ኪነጥበብን የፖለቲካ አሽከር ለማድረግ የሚተጉ አርቲስቶችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች . . . እንዲህ እንዲህ አያልን ሰፈሩን ስንቃኘዉ የሀገሬ ችግር ታስረዉ በሚሉ ሰዎች ታስራ መያዟ ይመስለኛል፡፡
ሀገር ነጻ የምትወጣዉ እኛ ዜጎቿ እንደ ቀበሮዋ ታስሬ ከምበላስ ነጻነቴ ይሻለኛል ብለን ከታሰርንበት ማዕሰረ ህሊና ስንፈታ ነዉ፡፡ በመሆኑም ፖለቲካዉም፣ ሃይማኖቱም፣ ኪነ ጥበቡም፣ ትምህርቱም፣ ፍትህ አካሉም፣ የጸጥታ አካሉም ባጠቃላይ ሀገሩ ባልታሰሩ ሰዎች የሚመራበትን ዘመን እናፍቃለሁ፡፡
መጭዉ ዘመን ሁላችንም ከታሰርንበት ማዕሰረ ህሊና የምንፈታበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

የአንባቢያን አስተያየቶች

 1. Yohannes Maekel says:

  This is well explained article about our current Ethiopia ,
  But ,due to the burden of living conditions ( expenses) people have chosen to become lchained dogs . As you all know that , it’s looks like the county belongs to few people who lives on comfortable zone , but most people ( 85% )are live in under poverty. For this reason only people become …

 2. Mu'uz says:

  My dear brother well said. Wonderful insight on our predicaments. True, better to be unsatisfied (wo)man than a satisfied pig. Your metaphor of the wolf and the chained dog fits well to the politics of the belly which is distroying our country. In that spirit, we better be wolf of the mountain than a badly domesticated dog. Thank you Misge! We expect more bro!

 3. Mu'uz says:

  My dear brother well said. Wonderful insight on our presicament. True, better to unsatisfied (wo)man than a satisfied pig. Your metaphor of the wolf and the chained dog fits well to the politics of the belly which is distroying our country. In that spirit, we better be wolf of the mountain a badly domesticated dog. Thank you Misge! We expect more bro!

Leave a Reply

Please answer this math question before submitting your comment: