ኦብነግ የሶማሊያ መንግስት ያወጣውን መግለጫ አጣጣለ

ኦብነግ የሶማሊያ መንግስት ያወጣውን መግለጫ አጣጣለ

BBN
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የሶማሊያ መንግስት ማስታወቂያ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ አጣጣለ፡፡ የኦብነግ አመራር የሆኑትን አብዲካሪን ሼህ ሙሴ ለህወሓት መንግስት አሳልፎ የሰጠው የሶማሊያ መንግስት፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ውገዘት እየገጠመው ይገኛል፡፡ ይህን ተከትሎም ኦብነግን በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የሶማሊያ መንግስት፣ ኦብነግን ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው በማለት ጥፋቱን ለመሸፋፈን እየሞከረ ይገኛል ተብሏል፡፡ ኦብነግ ለሶማሊያ መንግስት ምላሽ ለመስጠት ባወጣው መግለጫ ላይም ‹‹የተፈጸመውን ህገ ወጥ ድርጊት ህጋዊ ለማስመሰል የተደረገ ሙከራ ነው፡፡›› ሲል፣ ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው መባሉን አጣጥሎታል፡፡

Image may contain: 3 people, suit and closeup

የኦብነግ አመራር የሆኑት አብዲካሪን ሼህ ሙሴ በሶማሊያ ለሶስት ዓመታት የኖሩ ሲሆን፣ ከቤተሰብ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ወደ ሞቃዲሾ ማምራታቸውን ተከትሎ፣ በሶማሊያ መንግስት ታፍነው ለህወሓት መሰጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ድርጊቱን የፈጸመው የሶማሊያ መንግስት፣ ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር በማበር የሶማሊያን ጨምሮ የጎረቤት ሀገራትን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አድርጎ ያወጣው መግለጫ፣ በድርጅቱ ተብጠልጥሏል፡፡ የሶማሊያ መንግስት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ባወጣው መግለጫ ላይ፣ ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው ሲል የገለጸው ጉዳይን ድርጅቱ አጣጥሎታል፡፡ ከአልሸባብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው አጽንዖት ሰጥቶ የገለጸው ኦብነግ፣ በሶማሊያ መንግስት በኩል የቀረበውን ክስም ከእውነት የራቀ ብሎታል፡፡
የሶማሊያ መንግስትንም ሆነ ህዝብ አደጋ ላይ በሚጥል ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ አድርጎ እንደማያውቅ የገለጸው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ ህወሓት ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ የሚያናፍሰው ፕሮፓጋንዳም ነጭ ውሸት መሆኑን አስምሮበታል፡፡ ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ቀርቶ ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ደም መቃባታቸውን ያስታወሰው የኦብነግ መግለጫ፣ አልሸባብ በ2009 ወደ ኦጋዴን ዘልቆ በመግባት አምስት የኦብነግ አባላትን መግደሉንም በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ ኦብነግ አልሸባብን ከኦጋዴን ማስወጣቱን ተከትሎ፣ አልሸባብ በሶማሊያ ያገኛቸውን የኦብነግ አባላት ለመግደል መወሰኑንም ድርጅቱ በመግለጫው ላይ አስፍሯል፡፡ አልሸባብ እና ኦብነግ ካላቸው የደም መቃባት ታሪክ አንጻር፣ የሶማሊያ መንግስት የህወሓትን ፕሮፓጋንዳ በመያዝ ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ መፈረጁ ከእውነት የራቀ መሆኑንም ኦብነግ አስታውቋል፡፡

ለህወሓት ተላልፈው የተሰጡት አብዲካሪን ሼህ ሙሴ የሶማሊያ ዜግነት እንዳላቸው በመግለጫው የጠቀሰው ኦብነግ፣ ሶማሊያንም በውትድርና ማገልገላቸውን ያትታል፡፡ በዚህም የተነሳ በሀገራቸው ህዝብ እና መንግስት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ጠቅሷል፡፡ አክሎም ሼህ ሙሴ የፈለጉትን የፖለቲካ አጀንዳ የማራመድ መብት እንዳላቸው የገለጸው ኦብነግ፣ ሼህ ሙሴ በሶማሊያ ደህንነቶች በሚያዙበት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ከተለቀቁ የቪዲዮ ምስሎች መመልከቱንም ጠቅሷል፡፡ ይህ ድርጊትም የሶማሊያን ህገ መንግስት አንቀጽ 3 እና 10 የሚጻረር መሆኑንም አክሏል፡፡ በተጨማሪም የሶማሊያ ደህንነት አብዲከሪን ሼህ ሙሴን ለህወሓት መንግስት አሳልፎ የሰጠው ያለ ፍርድ ቤት ሒደት መሆኑም፣ ህግን የሚጥስ ድርጊት እንደሆነም ኦብነግ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ኦብነግ በመግለጫው መጨረሻም የሶማሊያ ፓርላማ እና የሀገሪቱ ህዝብ ከአብዲካሪን ሼህ ሙሴ ጎን በመቆሙ ምስጋናውን አቅርቦ፣ ሶማሊያ ሉዓላዊነቱን የጠበቀ መንግስት እስክታገኝ ድረስ ድጋፉን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

Save■ Subscribe to mereja.com's email newsletter. ⇒ CLICK HERE እዚህ ላይ ይጫኑ ⇐

► Post your comment below
የአንባቢያን አስተያየቶች

  1. Sammy says:

    Yechi nech chewata..
    Terrorist demo ikul bet huno
    mels mesxt jemere ?

Leave a Reply

Please answer this math question before submitting your comment: