የገቢዎች ሚንስቴር ካቀድኩት በላይ ታክስ ሰበሰብኩ ማለቱ ተሰማ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በአምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ እንደተፈለገ የሚሽከረከረው የገቢዎች ሚንስቴር በዓመቱ ታቅዶ ከነበረው በላይ ከታክስ ገቢ አገኘሁ ካለ በኋላ ካቀድኩት በላይ ታክስ የሰበሰብኩት ታክስ ከፋዩ ሕብረተሰብ ታክስ የመክፈል አስፈላጊነት ግንዛቤው በመጨመሩ፣ ህብረተሰቡን ታክስ እንዲከፍል ማንቀሳቀስ በመቻላችንና ሕብረተሰቡ ለህጉ ታማኝ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ለዚህ ታክስ ገቢ ከፍ ማለት አስተዋጽኦ ያደረገው ከታክስ ጋር በተያያዘ ወደ ፍርድ ቤት የወሰድናቸውን ክሶች በሙሉ ማሸነፍ በመቻላችን ነው ብሏል።

ይሁን እንጂ የታክስ አሰባሰቡን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለግንቦት ሰባት ዘጋቢ የሰጡ በንግድ ስራው ዘርፍ የተሰማሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እውነታው ፍጹም ከዚህ የተለየ ነው፤ የንግዱ ህብረተሰብ እንዲከፍል በሚጠየቀው የታክስ መጠን እጂግ በጣም እያማረረ መሆኑንና ማናቸውም የንግድ ድርጅት ትንንሽ ሻይ ቤቶች እንኳን ሳይቀሩ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመክፈል እንዲመዘገቡ እንደተገደዱም መግለጻቸውን ዘጋቢያችን ገልጾልናል።

ከዚሁ ጋር በማያያዝም የወያኔው አገዛዝ በተለይም በመካከለኛ የገቢ አቅም ላይ የሚገኘውን የንግድ ህብረተሰብ ክፍል በተለያዩ መንገዶች የሚፈጽምበት ግፍና በርካቶችም ከንግድ ስራ ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉ ሳያንሰው አሁንም ፍጹም ፍትሃዊነት በጎደለው አሰራር ታክስ የመሰብሰብ ተግባሩን መቀጠሉ ምን ያህል ህብረተሰቡን እንደናቀና ምንም አያመጡም በማለት መተበቱን ያሳየናል ብለዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ ከመርካቶ በርግጥ ማንም ሰው ከሚያገኘው ገቢ ለመንግስት ተገቢ በሆነ መልኩ ታክስ መክፈል እንዳለበት ብናምንም ወያኔ እያደረገው ያለው አሰራር ግን በፍጹም ከዚህ የወጣ ነው በማለት በምሬት ገልጸዋል። በመቀጠልም እንዲህ አይነቱ ወያኔዎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ልጆቹን ለማቆየት እየደከመ ያለውን ነጋዴ እንዴት እንደሚዘርፉትና እንደሚያምገላቱትም የሳያል ብለዋል።

የወያኔው የገቢዎች ሚንስቴር የሰጠው መግለጫ ርስ በርሱ ይጋጫል ያሉ ሌላው አስተያየት ሰጪም እንደተናገሩት ባንድ በኩል ህብረተሰቡ ግብር እየከፈለ ያለው ለህግ ተገዢ በመሆኑ ነው እያለ በሌላ በኩል ግን ከግብር ለተሰበሰበው ገቢ ከፍተኛ መሆን አስተዋጽኦ ያደረገው በፍርድ ቤት የተከሰሱ ነጋዴዎችን በማሸነፋችን ነው ማለቱ አሳፋሪ ነው ካሉ በኋላ ፍርድ ቤትም ቢሆን የወያኔውን አገዛዝ ቃል የሚጠብቅ በመሆኑ ፍርዱ ትክክል ነው ወይንም አይደለም ብሎ መናገሩ ትርጉም የለውም በማለት አስተያየታቸውን ቸርሰዋል።