አብዮቱና ትዝታዬ (ኮ/ል ፍሥሓ ደስታ)-አዲስ መጽሃፍ – አዲስ ምስጢር (ቅኝት ክንፉ አሰፋ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


TP_Fisseha-Cover-1084-Manipal.indd

የመጽሐፉ ርእስ፣                     አብዮቱና ትዝታዬ

ደራሲ፣                                   ፍሥሓ ደስታ (ኮ/ል)

አሳታሚ፣                               ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት

የገጽ ብዛት፣                            598 ገጾች

ዋጋ፣                                      $44.95

(ቅኝት ክንፉ አሰፋ)

ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ከዚህ ቀደም ሁለት የአብዮቱ መጽሃፍቶችን አበርክቶልናል። የኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም – “ትግላችን” እና ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ – “እኛና አብዮቱ”። የኮ/ል ፍሥሓ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” ከቀድሞዎቹ ትንሽ ለየት ይላል። ኮ/ል ፍሥሓ ደስታ ተድበስብሶ የቆየውን የወታደራዊ መንግስት ውስጣዊ ገመና ብቻ ፈልፍለው አላቀረቡም። በአብዮቱ ሂደት ለተከሰቱ ጥፋቶች ከራሳቸው ጀምረው ተጠያቂው የሆነው ወገንን ከማመልከትም አልታቀቡም። ደራሲው ብዙ ምስጢሮችንም ያስነብቡናል።

መጽሃፉ ዳጎስ ያሉ ምዕራፎች ይዟል። በአምስት ክፍሎች የተመደቡ አስራ አምስት ምእራፎች ተካትተውበታል።   ከቅድመ 1966 ዓ.ም. ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ፣ በደራሲው አገላለጽ – እስከ የ”መጨረሻዋ እራት” የነበሩትን ሂደቶች በስፋት ይቃኛል። ባጭሩ በአፄው መንግሥት ላይ የተነሱ ዓመፆችን በቀላል አማርኛ እያስነበበ የአብዮቱን አፈጣጠር፣ “የየካቲት አብዮት ከነገሌ እስከ መሿለኪያ” በሚል ምዕራፉ ያስነብበናል። ስለ አብዮቱ ውስብስብ ሂደት፤ ስለ ነጭና ቀይ ሽብር፣ የሶማሊያ ወረራ፣ የሕወሓት እንቅስቃሴ፣ የኤርትራ ችግር፣ የግንቦት 8 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ … በስፋት ያወጋና በመጨረሻዎቹ ምዕራፍ ግዙፉ ሠራዊት ለምን እንወደቀ ይነግረናል።

ጸሐፊው ኮ/ል ፍሥሓ ደስታ ከ1967-1983 ኢትዮጵያን ባስተዳደረው ወታደራዊ መንግስት እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት የዘለቀ ሥልጣን ነበራቸው። ከ1983 በኋላ ለሃያ ዓመታት በእስር ቆይተዋል። በመጽሐፋቸው ረጅሙ የህይወት እና የሥራ ተመክሯቸውን በመንተራስ፤ በቡድን ለስላጣን ባለቤትነት ከተደረጉ ሽኩቻዎች እስከ ሀገራዊ የመሪነት ግዴታዎችን መወጣት፣ ከግድያና የጥልፍልፎሽ ሴራዎች እስከ የሥር ነቀል አዋጆች ውጥንና አተገባበር፣ ከሙያ ጓዶቻቸው ድብቅ ስብዕና እስከ የውስጥና የውጭ ጣልቃ ገብነቶች፣ የአገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የተደረጉ እልህ አስጨራሽ ትግሎችና የውድቀቶቻቸው መንስኤዎች ወዘተ በስፋት ዳስሰዋል።

አብዮት ራስዋን እየበላች በነበረበት ሰሞን የእነ ጀነራል ተፈሪ ባንቲ የአገዳደል ሁኔታ የሚገልጸው ክፍል የአንባቢን ቀልብ ከሚስቡት ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው። ኮ/ል ፍሥሓ ደስታ ሁኔታውን በዚህ መጽሃፋቸው እንዲህ በማለት ይተርኩታል።

“…ኮ/ል መንግሥቱ ጠመንጃቸውን እንዳነገቱ ብቅ ብለው በደንብ ከተመለከቱን በኋላ “ትክክል ነው” ብለው ተመለሱ። የመጡትም ቀደም ብለው ማን መቅረት ማን መገደል እንዳለበት በወሰኑት መሠረት ስህተት እንዳይፈጠር ለማረጋገጥ እንደነበር ግልፅ ነው።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ መጀመሪያ ወደነበርንበት የስብሰባ አዳራሽ ተጠራን። ወደዚያ ስናመራ ኮ/ል ተስፋዬ ገብረኪዳንን “ባለፈው ጄኔራል አማን ተገደሉ አሁን ደግሞ ሥራቸውን ከሚሰሩበት ቦታ አምጥተን፣ ራሳችን ሾመን እንዴት እኒህ ሽማግሌ [ጄነራል ተፈሪ] ይገደላሉ? ስለዚህ ለመንግሥቱ እንንገራቸው” አልኩትና ተያይዘን ወደቢሯቸው ገባን። እኛም የመጣንበትን ስንነግራቸው “እውነታችሁን ነው” በማለት የውስጥ ስልክ አንስተው ከደወሉ በኋላ መነጋገሪያውን እያስቀመጡ “አዝናለሁ ጓዶች አልቋል” ብለው ነግረውን እያዘንን ወደ ስብሰባው አመራን። እንደገባን ኮ/ል መንግሥቱ መጥተው “ስለሁኔታው ለጦሩ ማስረዳት ስላለብኝ ኮ/ል ተስፋዬ ገብረኪዳን ከኔ ጋር እንድትሄድ” በማለት ጠየቁ። ኮ/ል ተስፋዬም “በማዛቸው ወታደሮች ፊት እጄን ሰቅዬ ወጥቼ ጦሩን ለማነጋገር ፈጽሞ ሕሊናዬ ሊቀበለው ስለማይችል አልሄድም፤ እንደውም ወደክፍሌ እመለሳለሁ” አለ። እኔም “ከእንግዲህ በዚህ ዓይነት እዚህ ግቢ ለመሥራት ፍላጐት የለኝም እኔም እንደተስፋዬ ወደክፍሌ መመለስ እፈልጋለሁ” አልኩ። መንግሥቱም ሽጉጣቸውን በማውጣት “ይህን እርምጃ ባልወስድ ኑሮ ሁላችንም አልቀን ነበር፤ በድያችሁ ከሆነ ግን ግደሉኝ” በማለት ሽጉጡን ጠረጴዛው ላይ ወረወሩት…”

 

በወቅቱ ከነበሩት ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች፤ በኢሕአፓ እና በመኢሶን ላይ ጸሃፊው የሰጡት አስተያየት ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም እና ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ ካስነበቡን ትንሽ ለየት ይላል። ኮ/ል ፍሰሃ፤ የሁሉንም ፓርቲዎች ብቃት ያወድሳሉ፣ የአመራሩን ችግሮች ደግሞ ይወቅሳሉ። እንዲህ በማለት፣

“…የኢሕአፓ ቆራጥነት፣ የመኢሶን የርዕዮተ-ዓለም ብስለትና የደርግ ሀገር ወዳድነት ተጣምሮ አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያደርስ ይችል የነበረ ኃይል በአመራሮቹ ስህተት ያለአግባብ እርስ በርሱ ተጨራርሷል።”

ደራሲው በወታደራዊው መንግስት አመራሩ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወቱ የነበሩ በመሆናቸው በወቅቱ በነበሩ ስህተቶች ከሃላፊነት ነጻ ያለመሆናቸውንም እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል።

“… ኢትዮጵያ ትቅደም! ያለምንም ደም!’ ብለን በተነሣን ማግሥት… እነዚያ ለሀገራቸው የለፉትንና የደከሙትን አዛውንቶች መጦር ስንችል ገደልናቸው።”

ይህንን መጽሃፍ ከቀድሞዎቹ የአብዮቱ መጽሃፍት ለየት የሚያደርገው ደራሲው እንደ ጲላጦስ ከደሙ ነጻ ለመሆን የሌሎቹን ጥፋቶች ብቻ እየኮነኑ የጻፉት አለመሆኑ ነው። ራሳቸውን ከመውቀስ፣ ይቅርታ እስከመጠየቅ መድረሳቸው ደግሞ ከወገንተኝነት የራቁ መሆነቸውን ያሳየናል። ለዚህም ነው “… በማወቅ፣ በድፍረት፣ ባለማወቅና በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ ሙሉ ሃላፊነትን በመውሰድ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።…” ያሉት።

ከመጽሐፉ ድንቅ ትረካዎች መካከል የተወሰኑት ማቅረቡ ሰለ መስጽሃፉ ለአንባብያን ፍንጭ ሊሰጡ ይችላሉ። አንዳንዶቹ መረጃዎች ከዚህ ቀድመው አልተሰሙም። ፍጹም አዲስ ናቸው። ለምሳሌ የፓትሪያርኩን ማምለጥ በተመለከተ ከዚህ ቀደም የሰማነው ነገር አልነበረም። መጽሃፉ እንዲህ ይላል፣

… ፓትርያርኩ እንደሌሎቹ እስረኞች ሳይሆን ብሔራዊ ቤተመንግሥት በሚገኘው የአድሚራል እስክንድር መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደረገ። በታሰሩ በጥቂት ቀናት ግን ጠባቂዎቻቸው መነኩሴ ስለሆኑ የትም አይሄዱም ብለው ሲዝናኑ ቆባቸውን አውልቀው፣ ጺማቸውን ተላጭተውና ልብሳቸውን ለውጠው በግዮን ሆቴል በኩል ወጥተው ጠፉ። መጥፋታቸው እንደተነገረም በደርግ ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጠረ። …

ደርግ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት የወቅቱ የደርጉ ሊቀመንበር ጀ/ል ተፈሪ ባንቴ በአብዮት አደባባይ ንግግር አድርገው ነበር። በንግግራቸውም ለኢሕአፓ ጥሪ አድርገዋል። አብዮት አደባባይ የነበረው አከባበር እንዳለቀ የሕዝብ ድርጅት አባላት ኮ/ል መንግስቱን እንዴ እንዳዋከቡዋቸው ሲጽፉ፣

…የሕዝብ ድርጅት አባላት መስፍን ካሡ፣ ነገደ ጐበዜ፣ እንዳርጋቸው አሰግድ፣ ሰናይ ልኬ እና ሌሎችም ወደተቀመጥንበት ቦታ እያለከለኩና እየሮጡ መጡ፤ ኃይሌ ፊዳም ተከተለ። ምነው ጓድ መንግሥቱ እርስዎን አምነን ተሰብስበን ኢሕአፓ አየገደለን አላስጣላችሁን፤ ይባስ ብላችሁ ደግሞ እኛን የበለጠ ለማስመታት ለኢሕአፓ ጥሪ እንዴት ታደርጋላችሁ ብለው ከግራ ከቀኝ ያዋክቧቸው ጀመር። መንግሥቱም አንዴ ይቅርታ አድርግልኝ ብለው ኃይሌ ፊዳንና የተቀሩትን ይዘው ቡና ቤት ውስጥ ወደምትገኘው አነስተኛ ሣሎን ገቡ። በዚያች ቀንና ሰዓት መንግሥቱ የተነጠቁትን ስልጣን ለማስመለስ መኢሶን ደግሞ ኢሕአፓን በማስመታት ለሥልጣን መንገዱን ለመጥረግ ሴራ ሳይጠነሰስ አልቀረም።…

ቀይ ሽብርን መኢሶኖች እንደጀመሩት እና የጀመሩትም ከኢሕአፓ ነጭ ሽብርና ግድያ ራሳቸውን ለመከላከል እንደሆነ ጽፈዋል። ‘ብሳና ይነቅዛል ወይ ቢሉት ለዛፎች ሁሉ ማን አስተማረና’ እንደተባለው በአብዮቱ ሰፈር ደግሞ ቀይ ሽብር የሚለውን መፈክር በቲዎሪም በተግባርም ለደርግ ያስጨበጠው መኢሶን መሆኑ አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ሀቅ በመሆኑ ቃላትን በማውገርገርና ነገሮችን በማድበስበስ ከዚህ የታሪክ እውነታ ለማምለጥ መሞከር ትርፋ ትዝብት ነው።…’ ይላል።

ይህንን በመኢሶኖች ተጀመረ ያሉትን ቀይ ሽብር ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም እንዳስቆሙት “አብዮቱና ትዝታዬ” ይነግረናል። እንዲህ ሲል፣

 

… መንግሥቱ ፊታቸው ተለዋወጠ። “ግድየለም እኔ መንግሥቱ ብቻዬን አስቆመዋለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ ሳላውቅና ሳልፈቅድ አንድም ሰው አይገደልም” በማለት ከስብሰባው ወጥተው አንድ ሁለቴ ሲጋራቸውን አቦነኑና ወደ ቢሮአቸው ሄዱ። እውነትም እንዳሉት ከመጋቢት 30፣ 1970 ጀምሮ ቀይ ሽብርም ሆነ ነፃ እርምጃ ቆመ። ኮ/ል መንግሥቱ ይህንን ማድረግ የቻሉት በኢማሌዲህ ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢነታቸው እንዲሁም በርዕስ መንግሥትና የርዕሰ ብሔር ሥልጣናቸው ተጠቅመው እንደሆነ ግልፅ ነው። ዛሬ አንዳንዶች ሊመፃደቁ አንደሚሞክሩት ሳይሆን ቀይ ሽብርን ሊያስቆም የሚችል ከሳቸው ውጭ አንዳችም ኃይል አልነበረም።…

መጽሃፉ እንዲህ እያለ የአስራ ስባት አመቱን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሂደት በአዳዲስና አስገራሚ መረጃቆች እያዋዛ እስከመጨረሻዋ ሰዓት ያዘልቀናል። የመጨረሻዋ እራት በምትለው ምእራፍ ኮሎኔል መንግስቱ በሚስጥር የያዙትን ስንብትና ከሃገር ጥለው የመሄድ ምስጢር፣

… ግንቦት 10፣ 1983 ቅዳሜ ማታ በጡረታ የተገለልነውን፣ በአዲሱ ካቢኔ ያልተካተቱት፣ እንደዚሁም አዲስ የተሾሙት በተገኙበት በፕሬዚደንቱ መኖሪያ ቤት ለኛ መሸኛ ለአዲሶቹ መቀበያ የእራት ግብዣ ተደረገ። … በዚህ ግብዣ ላይ ከወትሮው በተለየ የታዘብኩት ቢኖር ፕሬዚደንቱ አምቦ ውሃ ብቻ ሲጠጡ ስላየኋቸው ለምን እንደማይጠጡ ስጠይቃቸው ጤንነት ያልተሰማቸው መሆኑን ገለፁልኝ። ወደኋላ ተመልሸ ሳስበው ግን ሆድ ያባውን ብቅል ስለሚያወጣው አገር ጥለው ስለመሄዳቸው ሚስጢር እንዳያመልጥ ለጥንቃቄ ያደረጉት ነበር። ግብዣው እንዳለቀ ቤታቸው በራፍ ላይ ቆመው አንድ በአንድ እየጨበጡ አሰናበቱን። ዳግም ላንገናኝ የመጨረሻዋን እራት በልተን ተለያየን።…ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አብዮት ሰፊና ውስብስብ የነበረ ቢሆንም በግላቸው ተካፋይ የነበሩበትን፣ በዓይናቸው ያዩትንና በማስረጃ ያረጋገጧቸውን እውነታዎች በተቻለ መጠን ከወገናዊነት በፀዳ መልኩ በዚህ መጽሐፍ ለማቅረብ ሞክረዋለሁ።

ጸሃፊው የታሪክ ባለሞያ አይደሉም። ታሪክን፤ በተለይ ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች ሲጽፉ ወገንተኝነት ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም።   ከሰው ስህተት አይጠፋምና መጽሐፉን በሚገባ አንብበው በጭፍን ሳይሆን በገምቢ መልኩ የሚሰጡትን ማንኛውን ምአስተያየትና ሂስ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ኮ/ል ፍሰሃ በመግቢያው ላይ ገልጸዋል።

ጸሃይ አሳታሚ ድርጅት በኢትዮጵያ ጥንታዊ እና ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ጉዳዮች ላይ በርከት ያሉ መጽሃፍት እያሳተመ ለአንባብያን እያቀረበ ይገኛል። ይህም የታሪክ ቅርስን እየጣለልን የሚያልፍ ስራ ነው።   ሊበረታታም ይገባዋል። እነሆ ዛሬም “አብዮቱና ትዝታዬ” ጀባ ብሎናል። ግንዛቤ ለመግኘት ያንብቡ – መጽሃፉ መተቸት ካለበትም ይተቹ። … በመጀመርያ ግን ያንብቡ! መልካም ንባብ!