BBC በኦሮሚፋም ስርጭት እንዲጀምር የሚደረገው ዘመቻ ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባዋል::


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ኦሮሚፋ በቢቢሲ ስርጭት አድማስ እንዲያገኝ የተጀመረው ዘመቻ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ እንጂ ከዜጎቻችን መካከል ለአንዱ የኦሮሞ ማኀበረሰብ አሊያም ደጋፊ ብቻ ተብሎ የሚተው አይመስለኝም፤ መሆንም የለበትም፡፡ ምክንያቱም በዚህ አንዱ ብቻ ተጠቃሚ ሌላው ዝም ብሎ ለሌላው ሲል በወገናዊነት ድጋፍ ያደረገ ያስመስለዋል፡፡ ቢቢሲ በኦሮሚፋ ስርጭት ቢጀምር ከአማርኛ እና ትግርኛ ተናጋሪና አድማጭ በተጨማሪ ኦሮሚፋ ብቻ ለሚችለው ወገናችን አማራጭ የመረጃ ምንጭ ማግኘቱ ጥቅሙ የሁላችንም ነው፡፡ በአንድ ደረጃ የሀገራችንን ህዝብ ንቃተ ህሊና በማሳደግ በመረጃ የበለፀገ፣ ከአንድ ወገን መረጃ ጥገኝነት እና አስተሳሰብ ነፃ፣ ንቁና ምክንያታዊ ማኀበረሰብ እንዲፈጠር በማገዝ ኢትዮጵያችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማምጣት ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

ሌላው በዚህ ጉዳይ መረዳት ያለበትን በሀገራችን አማራጭ ሚዲያ በመዳከሙ ምን ያህል ወገኖቻችን በመረጃ ድርቅ እየተመቱና ክፉና ደጉን እንኳን እንዳይለዩ በአንድ ርዕዮተ ዓለማዊ አሊያም በሌላ ፅንፍ የሚቀዳላችሁን ብቻ ስሙ በሚባልበት ሀገር ቢቻል አማርኛ፣ ኦሮሚፋ፣ ትግርኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሀገራችን ቋንቋዎች አማራጭ የመረጃ ምንጭ ቢኖረን በታደልን ነበር፡፡ በመረጃ የበለፀገ ማኀበረሰብ ነፃና ምክንያቲዊ በመሆኑ ማንም ግለሰብ ሊነዳውም ሆነ ሊያታልለው አሊያም በስሙ ሊነግድም ሆነ ሊያስመስል አይችልም፡፡ ይሄ ደግሞ ለሁላችንም ከዛም ሲልቅ ለመላው ዓለም እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን በእኛ ሀገር አፋ አውጥቶ በማይናገረው ድህነት ሁሉም ነገር እየተመኻኘ ዓለም በሰለጠነበት ዘመን በመረጃ በኩል እኛ ዛሬም እዚሁ ነን፡፡

ከ96 ሚሊዮን ህዝብ መሃል የኢንተርኔት አገልግሎት ቴክኖሊጂን በመጠቀም ማኀበራዊ ሚዲያውን እንኳ የሚገለገለው ህዝብ 2 ሚሊዮን አልሞላም፡፡ ስለዚህ አማራጭ የመረጃ ምንጭን እንኳን ባለፀጋ ሀገሮች አስበውልን ቀርቶ ቢቻል ተረባርበን ራሳችን ማስፋፋት ይጠበቅብን ነበር፡፡ በሀገራችን በመረጃ የበለፀገ ማኀበረሰብ ተፈጥሮ የሰለጠነችና የታፈረች ሀገር ትኖረን ዘንድ የምንመኝ ሁሉ የድጋፍ ፊርማችንን ብናኖር ጥቅሙ የሁላችንም ነው፡፡ ስለዚህ ከሚጠበቀው በላይ የድጋፍ ቁጥር ለማስመዝገብና ተግባራዊ እንዲሆን የድጋፍ ፊርማችንን እንቀጥል፡፡

https://www.gopetition.com/petitions/bbc-consider-afan-oromo-for-new-broadcasts-to-ethiopiaeritrea-as-a-matter-of-priority/sign.html#se

Bisrat Woldemichael