የነዋሪዎች ጥያቄ፣ የሚድሮክ ብዝበዛ እና ኦህዴድ እርምጃ!

አውሮፓውያን ቀኝ ገዢዎች የአፍሪካን አንጡራ ሃብት በበዘቡበት አመታት ”ያልሰለጠነውን ሀገርና ህዝብ ማሰልጠን” በሚል ሽፍን የአፍሪካን ሀብት በመበዝበዝ የራሳቸው ነዋይ ማሳደግና አውሮፓን ማበልጸግ ችለው ነበር፡፡ በዚህ የቀጥታ የአውሮፓዊያን ቀኝ ግዛት ዘመን የአንጡራ ሀብቶቹ ባላቤት የሆኑት አፍሪካውያን እጅጉን አሳዛኝ በሆነ መልኩ ህይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል፡፡ በተቃራኒው ግን አውሮፓ እጅጉን አድጋለች፡፡ ለዚህም ነው በአፍሪካና አፍሪካዊያን ስቃይ አውሮፓ አድጋለች የሚባለው፡፡

ሚድሮክ ኢትዮጲያ ከወርቅ ምርቱ ጋር በተያዘ በተለያዩ ወቅቶች መልካም ያልሆኑ ቅሬታዎች ይነሱበታል፡፡ ይህ ድርጅት ለሼክ መሐመድ አላሙዲን ረብጣ ዶላሮችን የሚያስገኝላቸው ድርጅት ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ መረጃ መሰረት ሚድሮክ በወርቅ ምርት ብቻ በ2006 ዓ.ም. ከ152.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ አግኝታል፡፡ በ2007 ዓ.ም በአመት በኢትዮጲያ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ካስገኙት ሁለት ድርጅቶች መካከል ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን በወርቅ አምራችነት በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በአንደኛ ደረጃ ልዩ ተሸላሚ ነበር::

ሚድሮክ በወርቅ ምርቱ የሚሰበስበው በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ትርፍ ልክ እንደ አውሮፓዊያኑ ቀኝ ገዢዎች በወርቁ ባለቤቶች የአካልና እና ህይወት መስዋትነት የተገኘ ነው፡፡ ላለፉት 20 አመታት በለገደንቢና ሳካሮ ወርቅ ሼኩ እና የኢህአዴግ ግብረ አበሮቻቸው ሲበለጽጉ የለገደምቢና ሳካሮ እናት ግን እዳውን ትከፍላለች፣ ልጇን ታጣለች፣ አካለ ስንኩል ትወልዳለች፣ ወልዳ መሳም እያማራት ታስወርዳለች፡፡ ይህ የኢንቨስትመንት ሳይሆን የቀኝ አገዛዝ ብዝበዛ ባህሪ ያለው ነው፡፡

ሚድሮክ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመሸፈንና ብዝበዛውን ለመጧጧፍ ያስችለው ዘንድ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ድጋፎችን እያደረኩኝ ነው ቢልም ለህዝቡ የሰራው ነገር ግን ከሚያደርሰው ጉዳት ጋር ፈጽሞ አይነፃፀርም፡፡ አውሮፓዊያን ቀኝ ገዢዎችም ለቅኝ ተገዢዎች መሰረተ ልማትን ይገነቡ ነበር እኮ፡፡

ኦህዴድ፣ የህዝብ ጥያቄና ሚድሮክ

ሼክ መሐመድ አሊ አላሙዲን የምንጊዜም የኢህአዴግና የህወሃት ደጋፊነታቸውን በግልጽ በበዙ አጋጣሚዎች ተመልክተናል፡፡ በዚህም ሳቢያ በተለያዩ አካባቢዎች ያለ ተቀናቃኝ የሀገሪቱን ሀብቶች እንዲበዘብዙ አጋጣሚዎችን አመቻችቶላቸዋ፡፡ ነገር ግን “ቄሮ” የሚባለው ጉድ ግን ለእርሳቸው ብዝበዛ የተመቸ አይመስልም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተግዳሮት እየገጠማቸው ይገኛል፡፡

የየለገደምቢና ሳካሮ ግን ተራ ተግዳሮት ብቻ አይደለም የህልውና የሰብሀዊ መብት ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ፡፡ የአፍሪካ ጥቁር ጎረቤቶቻችን ከቀኝ ግዛት ብዝበዛ ነጻ ለመውጣት ብዙ መስዋህትነትን ከፍለዋል ምክንያቱም ቀኝ ግዛቱ ለህልውናቸውና ሰብአዊነታቸው ስጋት ስለነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኦህዴድ በተደጋጋሚ በኦሮሚያና ኦሮሞ ጥቅሞች ዙሪያ እንደማይደራደር በተደጋጋሚ ነግሮናል፡፡ በግልጽም አሳይቶናል፡፡ ኦቦ ለማ በአንድ ወቅት ምንም ይሁን ምን ህዝባችን የማይፈልገውም እኛም አንፈልገውም ብለው ነበር፡፡ እነሆ የለገደምቢና ሳካሮ እናቶች፣ ህጻናት እንዲሁም እንሰሳቶቻቸው የሚድሮክ የወርቅ ምርት እንደማይፈልጉትና የ20 አመት ሰቆቃ እንዲቆም ይሻሉ፡፡ ይህንን የእናቶችና ህጻናት ጩኸት ሰምቶ እናዳልሰማ መሆን ለማንም አይበጅም፡፡

ለ10 አመት ብዝበዛውን መፍቀዱና የህዝቡን ሰቆቃ ማራዘሙ ለኦህዴድም ለዶ/ር አብይም የከፋ ውጤት ይዞ መምጣጡ አይቀርም፡፡ ይህ እንዳይሆን ኦህዴድ የሚድሮክን ቀኝ ግዛት እንዲያበቃ ያድርግ፡፡ ህዝቡም ነጻ ይውጣ፡፡ ሴቶቹም ጤናማ ልጅ ወልዶ ይሳሙ፡፡

ዳንኤል መኮንን ይልማ 
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር

Source: ethiothinkthank.com