ከሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

‹‹ለታላቁ የረመዳን ወር እንኳን አላህ አደረሰን!!››
‹‹ጾሙ መላው ሙስሊም ማህበረሰብ በሁሉም የህይወት ዘርፍ በረከት እና ትሩፋት የሚያገኝበት እንዲሆን አላህን እንማጸናለን!››
አርብ ግንቦት 10/2010
አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

በመጀመሪያ አላህ (ሱወ) ለተከበረው ታላቅ ወር ረመዳን ስላደረሰን ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ረመዳን የሰማያት በር የሚከፈቱበት፣ የጀሐነም በር የሚዘጋበት እና ኢብሊስም የሚታሰርበት የተባረከ ወር ነው፡፡ ረመዳን መላውን የሰው ዘር ከጭለማ ወደብርሃን ለማስገባት ለተላኩት ታላቁ ነቢይ ሙሐመድ (ሰዐወ) መመሪያ የሆነው ቁርአን የወረደበት፣ ኡማውም ለሰዎች ከተገለጹ ህዝቦች መካከል የበላይነትን የተጎናጸፈበት ክብር መገለጫነቱ የሚጎላበት ታላቅ ወር ነው፡፡ ታላላቅ ድሎች የተገኙበት እና በሙስሊሙ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በጉጉት የሚጠበቅ ወርም ነው፡፡

ያለፉት ረመዳኖች ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለዲናቸው ያላቸውን ቀናኢነት ያሳዩባቸው፣ እንዲሁም ለዲን መስዋእትነት የመክፈልን ክብር ያገኙባቸው እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ለዲናችን ክብር ብለን የምንከፍላቸው መስዋእትነቶች ሁሉ በዱንያም ሆነ በአኼራ የሚያስከብሩን እንደመሆናቸው መጠን ሕዝባችን በከፈለው መስዋእትነት ታላቅ ክብር ይሰማናል፡፡ ይህ መስዋእትነት አላህ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ሁላችንንም በጭንቁ ቀን ሐዘን ከማያገኛቸው ባርያዎቹ እንዲያደርገን አጥብቀን እንለምነዋለን፡፡ ወደፊትም ሕዝባችን ለዲኑ መስዋእትነት የመክፈልን አስፈላጊነት ተረድቶ ሁልጊዜም ሙሉ ዝግጁነቱን እንደጠበቀ ሲኖር ማየት ምኞታችን ነው፡፡

አዎን! ለዲናቸው ሲሉ ጊዜያቸውን ከመስጠት አንስቶ ሕይወታቸውን እስከመሰዋት ለደረሱ ሁሉ አላህ (ሱወ) ምንዳቸውን አብዝቶ እንዲከፍላቸው፣ ምህረት እንዲለግሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውም የተሻለ ምትክን እንዲያደርግላቸው አጥብቀን እንለምነዋለን፡፡ ይህ ረመዳንም ትክክለኛ ክብራችንን የምናገኝበት፣ እንዲሁም ለአገራችን ሰላምና ብልጽግና ከማንም በላይ አስተዋጽኦ ለማበርከት የምናደርገውን ጥረት የበለጠ በመጨመር ለተሻለ እርምጃ የምንዘጋጅበት ወር እንዲሆን መጣር ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ከልባችን አላህን መማጸን፣ በሙሉ ስሜታችን መስራት እና ጊዜ ወስደን በጥልቀት ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡

ረመዳን ውስጣችንን አጽድተን ከስሜታችን በላይ የምንሆንበት ወር እንደመሆኑ መጠን ስሜታችንን አሸንፈን ከአላህም ሆነ ከፍጡራን ጋር ያለንን ግንኙነት የምናስተካክልበት፣ ስህተቶቻችንን አርመንም ለተሻለ ምግባር የምንተጋበት ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በተለያየ ወቅት ኃላፊነታችንን ሳንወጣ በመቅረት ቀልባችሁን የሰበርናችሁ ሁሉ ዐውፍ እንድትሉን እንጠይቃለን፡፡ ሙስሊም እንደመሆናችን መጠን እንደማህበረሰብ ከቡድንተኝነት እና ስሜት ተከታይነት ተቆጥበን ለአላህ ብለን ዐውፍ መባባል ይኖርብናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከረመዳን የተሻለ ወቅት የለም፡፡ በመሆኑም እንደማህበረሰብ አንድነታችንን ልንጠብቅ እና ለዘላቂ መፍትሄ መሰረት ይሆን ዘንድ ይህንን ረመዳን የአዲስ ታሪክ ጅማሮ ልናደርገው ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ እንድንችል እና የኢብሊስን ሴራ ማክሸፍ የምንችልበት የስብእና ቁመና ላይ እንድንደርስ ሁላችንንም ከስሜታችን በላይ ያውለን ዘንድ አላህን እንማጸነዋለን፡፡

ረመዳን የተባረከ ወር ነውና ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ በሁሉም የህይወት ዘርፍ በረከት እና ትሩፋት የሚያገኝበት እንዲሆን አላህን እንማጸናለን፡፡ በመጨረሻም አላህ (ሱወ) በትክክል የመጾም ተውፊቁን ሰጥቶን ተቅዋውን ከተላበሱ፣ ረያን በተሰኘው የጀነት በር ከሚገቡ፣ ወንጀላቸው ሁሉ ከተማረላቸውና ከጀሐነም ቅጣት ነጻ ከሚባሉት ባርያዎቹ እንዲያደርገን አጥብቀን እንለምነዋለን! አሚን!

አላሁ አክበር!