የአማራውን ጩኸት የምትሰማ ኢትዮጵያ አልተገኘችም (ጌታቸው ሽፈራው)

በአለም ሰቆቃው ያልተነገረለት ሕዝብ ማለት የአማራ ሕዝብ ነው።

27 አመት ሙሉ በመንግስት መዋቅር ተፈናቅሏል፣ ታርዷል፣ ወደ ገደል ተወርውሯል፣ ቤት ተዘግቶ ተቃጥሏል፣ እርጉዝ በስለት ሆዷን ተወግታ ከእነ ልጇ ተገድላለች።

በተወለደበት ቀየ ሀብት ንብረቱን ተቀምቶ፣ ተገድሎ፣ ተዘርፎ ሲባረር ኖሯል። ሲፈናቀል አማራጭ ቦታ የሚያዘጋጅለት አልነበረም። በመንግስት መዋቅር ሲሳደድ የኖረው ይህ ህዝብ “አማራ ክልል” ተብሎ ወደተከለለው ሲመጣ የሚጠብቀው ተመሳሳይ ማሳደድ ነው!

አንድ የቤንሻንጉል ባለስልጣን የትግራይ ተወላጆችን በአውሮፕላን እንደሸኛቸው፣ አማራውን ደግሞ “ውጣ” ብሎ ስለማባረሩ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለ ምልልሱ ላይ ያሳያል። ከዚህ በላይ መድሎ የለም። ከዚህ በላይ አፓርታይድ የለም። ኢትዮጵያ የአባትና የእንጀራ አባት ሀገር ሆናለች። ለአማራው የሰቆቃ ምድር ከሆነች አመታት አልፈዋል። በየትኛውም መመዘኛ አማራ በመንግስት ጠላት ተደርጎ ከተፈረጀ ቆይቷል።

በዚህ ሁሉ መገደል፣ መፈናቀል፣ መገፋት ውስጥ ሲፈረጅ፣ ሲፈረድበት ኖሯል።

ከምንም በላይ ይህን በደሉን በግልፅ እንዲነገር አይፈለግም። ገዥዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ለሌላ ሕዝብ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነኝ የሚል ሁሉ አማራ ሲገደል፣ አማራ ሲበደል አፉን ይለጎማል። ለሌላው ሰብአዊ መብት የሆነው ለአማራ ሲሆን ዝምታ ይነግሳል።

ስለ ሶርያ፣ ሊቢያ፣ የመን ሕዝብ መከራ ሲያወራ የሚሰማ እንኳን አማራው ላይ ስለሚደርሰው በደል ለማውራት፣ የሚደርሰውን በደል ለማውገዝ አፉን ይይዘዋል!

ዛሬ ከምዕራብ ሸዋ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ኢቲቪ፣ አዲስ ቲቪ ድረስ ሄደው አመልክተዋል። የተቀበላቸው ግን አልተገኘም። የአማራውም ጩኸት የምትሰማ ኢትዮጵያ አልተገኘችም። አማራ እንዲበደል፣ እንዲሰቃይ የፈረደበት፣ የበየነበት መንግስታዊ ተቋም አሁንም ስራውን ቀጥሏል። ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው እየተባለ እንኳ የአማራው ስቃይ ቀጥሏል።

ግንቦት 20 ለአማራ ሕዝብ ያበረከተው ጥላቻን ነው!

ግንቦት 20 ለአማራ ሕዝብ ያበረከተው መበደልን ነው!

ግንቦት 20 ለአማራ ሕዝብ ያበረከተው መገደልን ነው!

ግንቦት 20 ለአማራ ሕዝብ ያበረከተው መፈናቀልን ነው!

ግንቦት 20 የሰራቸው ተቋማት፣ ያበረከታት “ኢትዮጵያ” ፀረ አማራ ነች!