የቤተ ክርስቲያን ዕርቀ ሰላም ጉዳይ (ዳንኤል ክብረት)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውንና ከ25 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን መለያየት ለመፍታት በድጋሚ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በሀገር ቤትና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሽማግሌዎች የተጀመረው ጥረት የሁለቱን ወገን አባቶች ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ይህ ጥረት ከግብ ደርሶ የመለያየቱ ግንብ እንዲፈርስና አንድነቱ እንዲመጣ የሚመኘውና የሚጸልየው ብዙ ነው፡፡

ችግሩን ለመፍታት የተነሡት ሽማግሌዎች ያጓኟቸውን አራት ዕድሎች በመጠቀም ካለፈው በበለጠ ሊሠሩ ይገባል፡፡ እነዚህ ዕድሎችም፡-

  1. ሁለቱም ወገኖች ሽምግልናውን ለመቀበልና በውይይቱ ለመቀጠል መስማማታቸው
  2. በሀገርና በውጭ ሀገር የሚገኙ የምእመናንና የካህናት ማኅበራት ለዕርቅና አንድነቱ ጠንካራ ድጋፍ መስጠታቸው
  3. ሀገሪቱ ያጋጠሟትን የልዩነት ፈተናዎች በመግባባትና በአንድነት ለመፍታት መነሣሣት የጀመረችበት ወቅት መሆኑ
  4. የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና መንግሥታቸው ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ መደገፋቸው፣ ናቸው፡፡

እነዚህን ዕድሎች በመጠቀም ሁለቱም ወገኖች የዕርቅና የአንድነት ሂደቱን ለመጀመር ብቻ ሳይሆን ለመቀጠልና ከፍጻሜውም ለማድረስ መትጋት አለባቸው፡፡ ጊዜው እየሄደ ነው፡፡ ችግሩ ሲከሠት የነበሩት አበው በሁለቱም ወገኖች ዐረፍተ ሞት እየገታቸው ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ ጳጳሳትን ካጣን በታሪኩ ላይ የምናደርገው ንትርክ ራሱ ከዕርቁ ሂደት በላይ ይፈጃል፡፡ በሌላ በኩልም ሰው የተሰላቸበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ የምእመናንን ፍላጎት የሚያረካ፣ የዓለምን ሂደት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የተሰለፈ ቤተ ክህነት የትም ማግኘት አልተቻለም፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ መለያየቱን የሚፈልጉት ቀሳጥያን ይህንን ችግር ማትረፊያ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡

በአንድ ጀንበር ያልመጣ ችግር በአንድ ጀምበር አይፈታም፡፡ የሽምግልና ጥረቱ ችግሮችን ሁሉ ለመፍታት ከሆነ አይሳካም፡፡ ነገር ግን ዋና ዋና የሚባሉትን ችግሮች በመፍታትና ሌሎቹን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል መደላድል በመፍጠር መሄዱ አዋጭ ነው፡፡

አሁን ሽማግሌዎቹ እየሄዱበት ላለው መንገድ አማራጭ መፍትሔዎቹ ስድስት ናቸው፡፡

  1. ውግዘቱን ያለ ቅድመ ሁኔታ በተመሳሳይ ጊዜ ማንሣት
  2. የሁለቱን አባቶች (የአቡነ መርቆሬዎስንና የአቡነ ማትያስን) ጉዳይ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ልምድ (ሩሲያ፣ አርመን) በመነሣት የሚያቀርብ የሊቃውንት ጉባኤ መሰየምና በአስቸኳይ (ከአንደ ወር ባልበለጠ) እንዲያቀርብ ማድረግ፤
  3. በመለያየት ወቅት ያጋጠሙትን የዶግማ፣ የቀኖና፣ የባህል፣ የአስተዳደር፣ ወዘተ ችግሮች አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ የጋራ የሊቃውንት ምክር ቤት ማዋቀር
  4. ከሁለቱ ወገኖች የተውጣጣ በ‹ፓትርያርኮቹ› የሚመራ ልዑክ በአንድ በተመረጠ ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝቶ እንዲነጋገርና አብሮ እንዲጸልይ ማድረግ (ንግግሩ መተማመንን ለመፍጠር፣ የልዩነትን ግንብ ለማፍረስና ለሕዝቡ መቀራረብ ትእምርታዊ ዋጋ እንዲኖረው ነው፡፡)
  5. ከኢትዮጵያ መንግሥት በሚሰጥ ዋስትና መሠረት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣና የተሥፋ ብሥራት እንዲያበሥር ማድረግ
  6. የሊቃውንቱ ጉባኤ/ምክር ቤት በሚደርስበት መሠረት ሁለቱ ‹ሲኖዶሶች› የተስማሙበትን በየጉባኤያቸው አጽድቀው የአንድነቱን ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ማድረግ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሁለቱን አባቶች የዕርቅና የአንድነት ሂደት በግልና በመንግሥት ደረጃ እንደሚደግፉት፣ አስፈላጊውን ሁሉ መንግሥታቸው እንደሚያደርግ፣ በቅርብም ሂደቱን እንደሚከታተሉ ገልጠዋል፡፡ ለዕርቀ ሰላሙ ሲባል ከዚህም ያለፈ ርቀት ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ሐሳባቸውን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩ ጊዜ በጽኑዕ ገልጠውላቸዋል፡፡

አንዳንዶቹ ችግሮች ከዕርቀ ሰላሙ በፊት ባለው ሂደት ሊፈቱ የሚገባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ምንም ከባድ ቢመስሉ ግን ጥቂት ናቸው፡፡ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናትም ተከሥተው መፍትሔ ያገኙ በመሆናቸው ያንኑ አጣጥሞ መጠቀም የተሻለ ነው፡፡ ሌሎቹ ችግሮች ግን (ለምሳሌ ሁለቱን ቤተ ክህነቶች ማጣጣም፣ በየጊዜው የተሾሙ ጳጳሳትና ተመሳሳይ ስሞችን ያዙ አባቶች ጉዳይ፣ የተፋለሱ ቀኖናዎች ጉዳይ፣ የኑፋቄ ጉዳይ፣ በሁለቱም ወገኖች የወጡና የማይጣጣሙ ሕጎችና ደንቦች ጉዳይ፣ የኢኮኖሚ ውሕደት ጉዳይ፣ ወዘተ) የሊቃውንትን ምክረ ሐሳብ የሚፈልጉ፣ ጥናት የሚጠይቁ፣ ማስረጃ የሚሹ፣ ጊዜ-ጠየቅ ናቸው፡፡ እነዚህን በጋራ ሆኖ መፍታቱ የተሻለ ነው፡፡

ምናልባት ሁኔታዎቹ ተለዋውጠው የዕርቁ ሂደት የሁለቱን ወገኖች ተሳትፎ የማይፈልግበት ደረጃ የሚደርስበት ጊዜ እየመጣ ነው፡፡ ያ ሂደት በሌሎች አካላት ምክንያት ከመጣ ከመሥመር ውጭ ቀርተን የተበላ ዕቁብ እንዳንሆን ልንሠራበት የምንችልበት ጊዜው አሁን ነው፡፡