የእነ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ መለቀቅ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለእስር ተዳርገው የቆዩ ሰዎች ከእስር እየተለቀቁ ነው። የአሸባሪነት ክስን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት ታስረው ከቆዩ በኋላ ክሳቸው ተቋርጦ አለያም የእስራት ጊዜያቸውን ጨርሰው ከተለቀቁ ሰዎች መካከል ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እና የቀድሞው የሀገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል ይገኙበታል። የእስረኞቹን መፈታት ያወደሱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ብዙ ናቸው። የዚያኑ ያህል ግን እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ፤ ግፍ ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጠይቁ ተበራክተዋል።

ማክሰኞ ዕለት የእስረኞች መለቀቅ ዜና እንደተሰማ የበርካቶች አስተያየት ያጠነጠነው የልብ ሕክምና ባለሞያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ላይ ነበር።

ራዲዮ ስዊድን በትዊተር ገጹ ቀጣዩን መልእክት በእንግሊዝኛ አስተላልፏል። «ስዊድናዊው የልብ ቀዶ ጠጋኝ ፍቅሩ ማሩ ከእስር ቤት ተለቀዋል» ያለው ጣቢያው የዶክተር ፍቅሩ ንግግርንም አጣቅሷል። «ወዳልተበረዘው አየር መውጣት እንዴት ደስ ይላል» ሲልም አክሏል።

ለታ ቲ ባይሳ ደግሞ እዛው ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ጽሑፉ፦ «ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ስዊድናዊ የልብ ቀዶ ጠጋኝ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በኢትዮጵያ መንግሥት እስር ቤት ለበርካታ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ተለቀዋል። ለወዳጆቻቸው በመላ እንኳን ደስ ያላቸው» ብሏል።

«ከተፈቱ አይቀር ግን መጀመሪያ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እንዴት ነበር የፓለቲካ እስረኛ የሆኑት? ከቂሊንጦ ቃጠሎ በፊት የታሰሩበት ጉዳይ ሙስና እንደነበር ያስታውሷል። ለማንኛውም እንኳን ለቤቶ አበቃዎ!» ያለው ደግሞ ሚክያስ‏ ነው።

ግንቦት 3 አቃቤ ሕግ ክሳቸውን አቋረጥኩ ካለላቸው 62 እስረኞች መካከል ማክሰኞ ዕለት 5ቱ መፈታታቸው ተረጋግጧል።

«ዶክተር ዐቢይ እግዚአብሔር ይባርክህ፤ እንወድሀለን። ምርጥ ሰው። የእስካሁኑ ብቻ ለማንነትህ መገለጫ ከበቂ በላይ ነው። ኢትዮጵያ አገኘችህ እንደ ተመኘችህ» ሲል ፌስቡክ ላይ የጻፈው ገመቹ ነጋሽ ነው። በኢትዮጵያ የተለያዩ እስረኞች መለቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ አስተያየት ነው።

ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ በበኩሉ፦ «ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ ትልቅ ለውጥ እያሳዩ ነው» ብሏል። ያም ሆኖ ግን ሲል ይቀጥላል ነቢዩ፦ «ያም ሆኖ ገና ብዙ የተገፉ በየወህኒው ይገኛሉ። በዶክተር ፍቅሩ አቀባበል የተሰራ ቲሸርት ላይ እንደተገለጸው እጃችን ከብረት አእምሯችን ከጭንቀት፤ አካላችን ከህመም፤ ዛሬ ቢድንም ሀሳባችን ሁሌም ፍትኅ ካጡ ኢትዮጵያዊያን ጋር መሆኑ እውነት ነው! ፍትኅ ለተገፉት ወገኖች እንላለን!»

ዳንኤል ሺበሺ ግንቦት ሰባት ቀን በጻፈው የፌስቡክ መልእክቱ፦ «በግንቦት-7 የተከሰሱ ግንቦት-7 ቀን ከእሥር ተፈቱ» ብሏል። የልብ ህክምና ባለሞያው ዶክተር ማሩ እና አግበው ሰጠኝ ተቃቅፈው ሁለት ጣቶቻቸውን በድል ምልክት ወደላይ ቀስረው ፈገግ እናዳሉ የሚታዩበትን ፎቶግራፍ ባያያዘበት ጽሑፉ፦ «አባትና ልጅ! አርበኞቻችን» በማለት «እንኳን ደስ ደስስስስስስስ አለን! ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን!!» ሲልም አክሏል።

በምጸታዊ ጽሑፎቹ የሚታወቀው አበበ ቶላ ፈይሳ ከፌስቡክ ጽሑፉ ጋር ዶክተር ፍቅሩ ከልጃቸው ጋር የሚታዩበትን ፎቶግራፍ አያይዟል። ፎቶግራፉ ላይ ዶክተር ፍቅሩ ጺማቸው አደግ ብሎ፤ ፈካ ያለ ጉርድ ቲሸርት ለብሰው፤ ጥቁር መነጽር አድርገው ይታያሉ። እሳቸውን የምትመለከታቸው ልጃቸው ደግሞ የለበሰችው ደማቅ ጥቁር ሠማያዊ ካናቴራ ከጀርባ በቢጫ ቀለም የሚከተለው ተጽፎበታል። «እጄ ከብረት፤ አዕምሮዬ ከጭንቀት ልቤ ከሥጋት፤ አካሌ ከኅመም ዛሬ ቢድንም ሐሳቤ ሁሌም ፍትኅ ካጡ ኢትዮጵያውያን ጋር ነው»

ይኽን ፎቶግራፍ ያያዘው አበበ ቀጣዩን ጽፏል፦ «ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እና ዛሬ ከእስር የተለቀቃችሁ ነፃነት ናፋቂዎች በሙሉ እንኳን ለቤታችሁ አበቃችሁ…አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ይፈቱ!» ብሏል በመልእክቱ።

ከእስረኞች የመፈታት ዜና ጋር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሊፈቱ ነው የሚል መረጃም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል። በተለይ ዋዜማ ሬዲዮ፦ «አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲፈታ ከውሳኔ ተደርሷል» በሚል ያቀረበውን ጽሑፍ በርካቶች ተቀባብለውታል። «መረጃውን ለዋዜማ ያደረሱና ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደነገሩን አቶ አንዳርጋቸው እንዲፈታ ውሳኔ ከተላለፈ በርካታ ቀናት ተቆጥረዋል። በቅርቡ ከእስር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል» ሲል ነበር ዋዜማ የዘገበው።

በዶይቸ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ ክፍል የዋትስአፕ አድራሻ ከደረሱን መልእክቶች መካከል ቀጣዮቹ ይገኙበታል። «እባካችሁ የአዳርጋቸው ፅጌ መረጃ ካላችሁ» ከኢትዮጵያ የተላከ መልእክት ነው። «አንዳርጋቸው ፅጌን ለመፍታት አንዳንድ እንቅስቃሴወች በመንግስት በኩል ተጀምሯል።» ይህም ከኢትዮጵያ የተላከ ነው። «እኔ የምለው፣ በኢትዮጵያ ስንት ሰዎች ታስረው ነበር?» ይኼኛው መልእክት የተላከልን ከእስራኤል ነው።

ከእስረኞቹ መፈታት እና ይፈቱ ውትወታው ባሻገር አደባባይ ያልወጡ የግፍ ሰለቦች ፍትኅ ያሻቸዋል የሚሉ መልእክቶችም በስፋት ተሰራጭተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም፦ ቤንሻንጉል ጉምዝ ውስጥ የተፈፀመ ጭካኔ በሚል እጅግ በአሰቃቂ ሁኔታ ጥርሶቹ የረገፉ፤ ፊቱ የተቦጫጨቀ፣ እንዲሁም ሐፍረተ-ሥጋው የተሰለበ ነው የተባለ ልጅ ፎቶግራፍ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በርካቶች ተቀባብለውታል።

ይህ ግፍ ለአደባባይ የበቃው ፎቶግራፍ ስለተነሳ ነው፤ የሌሎች ግን ተድበስብሰው የቀሩ በርካታ ግፎች አሉና ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ እስረኞችን መፍታት ብቻ ሳይሆን መሰል ግፎችን የፈጸሙትን ሊቀጡ ይገባል ብለዋል።

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ፌስቡክ ላይ ይህንኑ ዘግናኝ ፎቶ አያይዞ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፏል። «ዶ/ር አብይ ስለ ፍትሕ ሲየወሩ ከርመዋል! እውነት ከሆነ ከዚህ በላይ ፍትሕ የሚፈልግ ጉዳይ የለም! ይሕን ነውረኛ ተግባር የፈፀሙ ለሕግ ካልቀረቡ የሚወራው ሁሉ ከማደንዘዣነት አያልፍም!» ሲል።

የጋዜጠኛ ጌታቸው ጽሑፍ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፦ «በአበጥር ወርቁ ላይ የተፈፀመውን ልናይ የበቃነው በቴክኖሎጅ እገዛ ነው። በርካቶች መሰል ጭካኔ ተፈፅሞባቸዋል። እየተፈፀመባቸው ነው! ይህ የጭካኔ ተግባር በግለሰብ ላይ የተፈፀመ አይደለም። ሕዝብ ላይ ነው! መንግስት ነኝ ባዩ ይህን ገሃድ የወጣ ተግባር ወደጎን ብሎ የሚያልፍ ከሆነ ሕዝብ የራሱን አማራጭ መውሰድ አለበት!» ብሏል።

የናይጀሪያው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኃላፊ እና ሁለት ሠራተኞች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተገደሉ የሚለው ዜናም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶች ተቀባብለውታል። ሐዘናቸውንም ገልጠዋል።

የአፍሪቃ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አ አዴሲና በግድያው ማዘናቸውን ትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል። «የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሀገር ውስጥ ኃላፊ ዲፕ ካማራ እና ሁለት ሠራተኞቻቸው መገደላቸው አሳዝኖኛል እጅግም አስደንግጦኛል። ለአሊኮ ዳንጎቴ የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እገልጣለሁ» ብለዋል። አሊኮ ዳንጎቴ የዳንጎቴ ግሩፕ ፕሬዚደንት ናቸው።