ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ በስልክ ማስፈራሪያ ከእጩነት ራሳቸውን ማግለላቸው ጥያቄዎችን ያጭራል።

አቶ ጁነዲን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡበት ወቅት አቶ ተካ አስፋውም ራሳቸውን ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትነት በእጩነት አቅርበው ነበር ….ምርጫዉ ሊደረግ አንድ ሳምንት ሲቀረው አቶ ተካ አስፋው ከእጩነት ራሳቸውን በፈቃዳቸው እንዲያገሉ ከማስፈራራት ጋር ትዕዛዝ በስልክ እንደተሰጣቸው ለአንድ ሚዲያ ይፋ አደረጉ፤በዚሁ ለደህንነታቸው ሲሉ ራሳቸውን ከምርጫው እንዳገለሉ ተናገሩ ….ሌሎች ሚዲያዎች አቶ ተካን ለማናገር መሯሯጥ ጀመሩ

አቶ ተካም ከመጀመሪያው መግለጫ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ቃለምልልስ እንዳይሰጡ እንደተከለከሉና መግለጫም ሆነ ቃለምልልስ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናገሩ ….አቶ ተካን ማን እንዳስፈራቸው እና ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ ትዕዛዝ እንደሰጣቸው ያዉቃሉ፤ግን እስከዛሬ ለህዝብ በይፋ አላሳወቁም….አስፈራሪዉን አካል ግን መገመት ከባድ አይሆንም ….

ዛሬ እንደሰማነው ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል….ከዶክተሩ የኖረ ባህሪ ስንነሳ እንዲህ በዋዛ ከፊታቸው ሞቅ ያለ ወንበር እያዩ የሚተዉ አይነት ሰዉ አይደሉም፤ዶክተር አሸብር የስልጣን ወንበር ይወዳሉ …. ዶክተሩ ለምርጫው ቀላል የማይባል ገንዘብ መድበው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፤በዙሪያቸዉም በርካታ የሚዲያ ሰዎችን አሰልፈው ነበር ወደ ምርጫ ፉክክሩ የገቡት….ዶክተር አሸብር ከምርጫው ራሳቸውን ለማግለል የሰጡት ምክንያትም ዉሀ የሚቋጥር አይደለም….በተለይም ዶከተሩ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ለመሆን በተለያዩ ጊዜ ከገቡባቸው ዉዝግቦች እንዲሁም ለአሁኑ ምርጫ በእጩነት ለመቅረብ ከከፈሉት “መስዋዕትነት” አንፃር በቀላሉ ከምርጫው ራሳቸውን ዞር የሚያደርጉ ሰው ናቸው ብሎ መገመት ይከብዳል ….

በኔ ግምት ዶክተሩም እንደ አቶ ተካ አስፋው የስልክ ጥሪ ደርሷቸዋል፤በአንድ የስልክ ጥሪ ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ ተነግሯቸዋል ….ዶክተር አሸብርን ተከትለው አቶ ተካ አስፋዉም ራሳቸውን ከምርጫው ሊያገሉ እንደሆነ እየተነገረ ነው፤ለሁለተኛ ጊዜ ሳይደወልላቸዉ አይቀርም ….ጉዳዩን ሰብሰብ አርገን ስናየው መንግሥት በጉዳዩ ላይ እጁን እንዳስገባ ግልፅ ነው፤ከነገሩ አሰልቺነት አንፃር እጁን ማስገባቱ የሚጠላ አይደለም….በጉዳዩ ላይ የመንግሥት እጅ ስርአት እንዲከበር የማድረግ ሚና ብቻ ያለው ግን አይመስልም ….ግለሰቦች ራሳቸውን በፍቃደኝነት ከምርጫው እንዲያገሉ ተፅዕኖ ከተደረገ ጎን ለጎንም በመንግሥት የተዘጋጀ እጩ መኖሩን መጠርጠር ይቻላል።