እግር ተወርች የታሰረው የአገራችን ቱሪዝም

ከሙሉጌታ ገዛኸኝ

ባለፈው ሰሞን ‘የቱሪዝሙ አባት’ እየተባሉ የሚጠሩት ክቡር አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ከዚህ ዓለም በሞት የመለየታቸው አሳዛኝ ዜና ተሰምቷል፡፡ ‘ኢትዮጵያ የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ አገር’ የሚል ጥልቅ መርሕ አንግበው ለበርካታ ዓመታት ለፍተዋል፡፡ በአበው አነጋገር መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላል ነውና አቶ ሀብተ ሥላሴ ለዘመናዊው የኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ፈር-ቀዳጅነት ውለታቸው ምንጊዜም በታሪክ ይታወሳሉ፡፡

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እስከዛሬ ድረስ በስራ ላይ የቆየውን መለያ ማለትም ‘የአስራ ሦስት ወር ፀጋ’ የተሰኘውን በአዲስ ማለትም ‘ምድረ ቀደምት’ (ላንድ ኦፍ ኦሪጅን) መገለጫ መተካቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በቱሪዝም ኮሚሽን እውቅና ያገኘው የቀድሞው መለያ ያስገኘው ፋይዳና ጉዳቱ ምን እንደሆነ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በባለሙያ ጥናት አስገምግሞ ይሁን በበላይ ሹማምንቱ ፍላጎት በግልፅ ባይታወቅም የወቅቱ የአገሪቱ መገለጫ ምድረ ቀደምት የሚል መሆን እንዳለበት ተወስኗል፡፡ ለአብነት የአገር-በቀል ብቸኛ ምርት የሆነው የጤፍ ዝርያችን በምእራባውያን ከነአካቴው ተነጥቆ ተሟጋች ያጣው ኢትዮጵያዊ በዚህ አዲሱ ምድረ ቀደምት መፈክርነት ከማንነቱ ጋር የተቆራኘውን የጤፍ ባለቤትነት መብት ያስጠብቅ ይሆን የሚለው ግምት አጠያያቂነቱ ቀጥሏል፡፡

አገራችን ያላትን እምቅ ባሕል፣ ቅርስና ታሪካዊ እሴቶች የማንነት መገለጫ መስህቦች የሚዳሰሱ እና የማዳሰሱ በሚል ለጎብኚዎች ታስተዋውቃለች፡፡ የቱሪዝም ዘርፍ ዘላቂነቱ መጠበቅ ሲቻል ውጤታማነቱ ይልቃል፡፡ ለዚህም ቤተመዛግብትና ሙዝዬሞችን ማደራጀት፣ የቱሪዝም ሙያ ማሰልጠኛዎችን፣ ባሕላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የገፀ በረከትና ጌጣጌጥ መሸጫዎችን ማስፋፋት፣ የመዳረሻ ቦታዎችንና የጎዞ ማሳለጫዎችን ማመቻቸት ይጠይቃል፡፡ የዘላቂ ቱሪዝም ወይም ኤኮቱሪዝም ለአንድ አገር ብሔራዊ ጥቅም ማጎልመሻ ሲሆን በእርስ በርስ የባሕል መወራረስ፣ በሥራ እድል መፈጠርያነት፣ ለድህነት ቅነሳ እንዲሁም የተረጋጋ ሰላም መስፈን ጥቅም ዓይነተኛ ማሳያም ነው፡፡

ጉብኝት በአብዛኛው በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ጉዞና ከእንግዶች ቆይታ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የተሟላ የትራንስፖርት፣ ጉዞ ወኪሎች፣ የምግብና መኝታ መስተንግዶ አገልግሎት፣ የባንክና ኢንሹራንስ አቅርቦት የመሳሰሉት በተሻለ ሁኔታ መሟላትን በእጅጉ የሚሻ ዘርፍ ነው፡፡ እነዚህ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች ዓነታቸው አያሌ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የቅድመ ታሪክ ቅሪተ አካልና መካነ ቅርስ ሥፍራዎች(ፓሊዎንቶሎዥና አርኪዮሎጅ)፣ ጥንታዊ የዋሻና ፍልፍል አለት ቤተመቅደሶች፣ ጥንታዊ የመገበያያ ቦታዎች፣ ክብረ በኣላት መከወኛዎች፣ ባሕላዊና ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ፓርኮችና ጥብቅ ሥፍራዎች፣ ብርቅዬ አዕዋፍትና የዱር እንስሳት፣ የሰው ሰራሽ ቅርስ ወይም ሔሪቴጂ ማሰባሰቢያዎች፣ የኪነ ሕንፃ አሻራዎችና  ፍርስራሾች፣ የሸክላ ማድጋዎች፣ የመንፈሳዊ ጉዞ በዓለ ንግስ ሥፍራዎች ወይም ፒልግሪሜጂ፣ ትምህርታዊ ጥናትና ምርምር እንቅስቃሴ ጉብኝቶችን ያካትታል፡፡

የጪስ አልባው ኢንዱስትሪ(ቱሪዝም) ዘርፍ ጠቀሜታው የጎላ እንደመሆኑ መጠን በጥንቃቄ መያዝ ካልተቻለ ከፍተኛ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ማናቸውም ሰው ልማዱን ይከተላልና በተለይም ከቅርስ ዝርፊያ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ለባሕልና ወግ መበረዝና መፋለስ፣ አደገኛ አደንዛዥ እፆች ንግድንና ባዕድ የሆኑ አጉል ልማዶችን፣ የሴተኛ አዳሪነት መስፋፋትን፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳትን፣ የገበያ ዋጋ መናርን፣ የአገር ደህንነት መናጋትን የመሳሰሉትን አሉታዊ ጥፋቶች ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡

በልዩ ልዩ አገም ጠገም ምክንያት የተነሳ የጎብኚዎች ፍሰት ከፍና ዝቅ እለ ሲዋዠቅ አጠቃላይ የነበረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም የሆቴሎችንና መዳረሻ ሥፍራዎችንና የጉዞ ወኪሎችን ሁለገብ እንቅስቃሴ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ጥሎት ነበር፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በኋም አገልግሎት ሰጭዎች ብቻም አይደለም በቱሪዝም ሥራ ዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ቋሚ ገቢ እንዳያገኙ አሰናክሎ ከጨዋታ ውጭ አድርጓል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁና መተግበሩ በመንግስት ዘንድ የሚፈልገውን ፀጥታ ወደነበረበት በማስፈን አስተማማኝ ውጤት አስገኝቷል የሚል ሪፖርት የቀረበ ቢሆንም የቱሪዝም ዘርፍ አላንሰራራም ሰቅዞት የሰነበተው ደብዛዛ ድባብ ውሎ አድሮም ጭራሽ የለቀቀው አይመስልም፡፡ አዋጁ በጥብቅ የሚመለከታቸው በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች የቱሪስቶች(ጎብኚዎች) መዳረሻ ሥፍራዎች የሚገኝባቸው የሸፈነ በመሆኑ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይዘቱ ሲቃኝ አዋጁ የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ በእጅ አዙር መገደብ የራሱን ተፅዕኖ አሳርፏል ለማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጣለው እገዳ የተነሳ ቢሆንም የአገሪቱ ቱሪዝም ወደ መልካም ገፅታው እንዲመለስ ከሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጠንካራ ጥረት መደረግ እንዳለበት ሁኔታው ያመላክታል፡፡

ጤናማ የቱሪዝም እድገትና ልማት አስጠብቆ ለመዝለቅ ምን መደረግ እንዳለበት በብዙዎች ዘንድ ግራ መጋባት ይስተዋላል፡፡ በመንግስት በኩል ለዘርፉ ልዩ ልዩ ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን ቢገልፅም በተጨባጭ ግን የአንድ ወገን እንቅስቃሴ ብቻ መሆኑ ስኬታማ አያደርገውም፡፡ መናበብ የጎደለው የተናጠል ጉዞው ችግር አሁንም አልተቀረፈም፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ የሆቴሎች ማሕበር፣ የቱር ኦፕሬተሮች ማሕበር፣ የመኪና አከራይ ባለቤቶች፣ የአስጎብኚዎች ማሕበር ወዘተርፈ አግድምና ሽቅብ ግንኙነትስ ምን ይመስላል? ተቀናጅተው የሚሰሩበት አግባብስ አለ ወይ ? ትኩረት ያጣውና በስሩ ቁጥራቸው በዛ ያሉ አባላትን ያቀፈው የአዲስ አበባ የግለሰብ አስጎብኚዎች(ቱር ጋይዶች) ማሕበር  ሙያዊና ሣይንሳዊ እገዛ እየተደረገለት በቂ እውቅናስ ተሰትቶታል ለማለትስ ይቻላል ወይ? ትኩረት የተነፈገው የዚሁ ማሕበር ሥራ አስፈጻሚዎች ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በቋፍ የሚገኘውን ማሕበር ህልውና ለመታደግ ወደፊት ምን መደረግስ እንዳለበት አስጨንቋቸዋል፡፡ የተጠናከረ ድጋፍ ለማሕበሩ እንዲደረግ በተለይም ቋሚ የራሱ ጽሕፈት ቢሮና አድራሻ እንዲኖረው፣ የፋይናንስ፣ የቁሳቁስና ተሸከርካሪ መሟላት፣ የኮምፒውተርና ፕሪንተር ግብዓቶች ማሟላትን ይሻል፡፡ የማሕበሩ አባላትም ጊዜው ከሚጠይቀው የዘመናዊ ቱሪዝም መስፋፋት ጋር በዓለማቀፍ ተወዳዳሪነት ሙያቸውን ማዳበር እንዲችሉና ከመብትና ግዴታ ጋር በተያያዘ አጠቃላይ ክንዋኔዎችን በተመለከተ በልዩ ልዩ መንገድ ጥረት ቢያደጉም እስከአሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ምላሽ ያማግኘታቸውን በምሬት ይናገራሉ፡፡ በሂደቱም ተስፋ ወደመቁረጥ ደረጃ መድረሳቸውን ያወሳሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱ ሆቴሎችና መዳረሻዎች ቢሟሉም አገናኝ ድልድይ በመሆን የማናይናቅ አስተዋፅዖ ያላቸው ብቁ ባለሙያ አስጎብኚዎች(ጋይዶች) ካልተሳተፉበት ስራው ፈፅሞ ፈቀቅ ሊል እንደማይችል ለማንም ግልፅ ነው፡፡

የቱር ኦፕሬተሮች ማህበር ግን ከግለሰብ አስጎብኚ ማሕበር በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከመንግስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን ስራቸውን የሚያካሂዱበት የሙሉ ሰዓት ማናጀር እንዲሁም በተሻለ ቢሮና አድራሻ ነው፡፡ ነገር ግን ከአዲስ አበባ አስጎብኚዎች( ቱር ጋይዶች) ማሕበር ጋር የስራ ግንኙነት ፈፅሞ የላቸውም፡፡ ምንም እንኳ ሥራው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው ሳለ ተቀናጅቶ የመስራት ግንኙነት የላቸውም ለማለት ያስደፍራል፡፡ በየፊናቸው ተደጋግፎ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖርና ውጤታማ ለመሆን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ሰነድ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ይጠቁማል፡፡

የአስጎብኝ ድርጅቶችም በዚህ ረገድ ልዩ ትኩረት ቢሰጡ ይበጃል፡፡ በተለይም ሥራውን በዘመድ አዝማድ ተብትቦ ወደ ኢንዱስትሪው ለመቀላቀል የሚፈልጉትን ብቁ አስጎብኚ ባለሙያዎች(ቱር ጋይዶች)ን ለማሳተፍ ፈቃደኛ ቢሆኑና እድልም ቢሰጡ አይከፋም፡፡ የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ በዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራር ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና ስላላቸው የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ቱሪዝም በመዳረሻ አካባቢዎችም ጭምር ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ሕይወት መሻሻልና ብልፅግና የላቀ ድርሻው የማይካድ ነው፡፡

እንግዲህ ቱሪዝም ባለቤቱ ሁሉም ነውና የጥቂቶች መዋዕለ ነዋይ ትርፍ ማግበስበሻ መሆን የለበትም፡፡ በሁለገብ መንገድ ባሕሉንና ታሪካዊ እሴቶቹን ለሽያጭ የሚያቀርብበት ነውና አገርንና ሕዝብን  አሳታፊ ብሎም በባለቤትነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ምቹና ጤናማ አሰራርን መፍጠር የግድ ይላል፡፡ ለዛሬው በዚህ አበቃሁ፡፡ ቸር ይግጠመን!