የጫት ኦኮኖሚ (ጌታቸው በቀለ)

ከጌታቸው በቀለ

የዓለም የጤና ድርጅት በ1980 ባደረገው ጥናት ጫትን ከአልኮልና ከትንባሆ ያነሰ ንጥረ ነገር የያዘ ቢሆንም፤ በአደገኛ ዕፅነት የተመዘገበ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ አገራት ጫት ወደ አገራቸው እንዳይገባ ደንግገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን የጫት ተዘውታሪነት ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መጥቶ በለጋ ዕድሜ ያሉ ሕፃናት ሳይቀር በጫት ሱስ መያዝ በርካቶችን እያሳሰበ፣ እያወያየ የሚገኝ ርእሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በተለይ ከምሳ ሰዓት ጀምሮ በአገራችን ከተሞች በጫት መሸጫ ሱቆች ተኮልኩሎ፣ ጫት ገዝቶ በስስ ላስቲክ ሸክፎ ይዞ ሲሄድ የሚታየው ወጣት “አገሪቱ ወዴት እየሄደች ነው?” ያስብላል፡፡

በዘመናችን ለሰው ልጆች ከመጠን በላይ አነቃቂ ከሆኑት በርካታ ዕፀዋቶች አንዱ የኾነውን ጫት መዝገበ ቃላቱ እንደሚከተለው ይፈታዋል፤ “ለጋውን፣ ቀንበጡን…የሚያኝኩት…” ነው፡፡ (ደስታ ተክለ ወልድ፣ 1962፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 629)፡፡ ጫት በሳይንሳዊ ስሙ ካታ ኤዱሊስ (Catha edulis) በመባል ይታወቃል፡፡

ጫት የየት አገር ብቃይ እንደሆነ በርካታ ጸሐፊዎች የየራሳቸውን የጥናትና ምርምር ውጤቶቻቸውን አስነብበዋል፡፡ ከተመራማሪዎቹ አንዳንዶቹ እርስ በርስ የሚቃረኑ ሐሳቦችን ቢያቀርቡም አብዛኛዎቹ ጸሐፍት ግን የጫት መገኛ አገር አቢሲኒያ (ኢትዮጵያ) እንደሆነች ይስማማሉ፡፡ (Al-habeshi and Skaug፣ 2005)፡፡ እንግሊዛዊው ጸሐፊና ተርጓሚ ሰር ሪቻርድ በርተን (Sir Richard Burton) በ1856 በጻፈው መጽሐፍ ጫት ወደ የመንና ሌሎቹ አገራት የሔደው ከኢትዮጵያ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ (Burton፣ 1856):: በ14ኛው መ/ክ/ዘ በዐረብኛ የተጻፉ መረጃዎች፡- የምሥራቁ የአገራችን ክፍል በሆነው በሐረርጌ ደጋማ አካባቢዎች ጫት በብዛት ይመረት እንደነበርና ለየመናውያን ከ6ኛው መ/ክ/ዘ ጀምሮ መግባት መነሻ ይኸው ሐረር ነው የሚሉ የጽሑፍ ማስረጃዎች አሉ (ወልደ አማኑኤል፣ 2007)፡፡ ተሰማ ሰብስቤም ጫት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በኢትዮጵያ መሆኑን “በርጫ (ጫት)” በሚለው መጽሐፉ እንደሚከተለው አስፍሮታል፡፡ “የቡና መገኛ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ እንደ ቡናው መገኛነት ኩራት ብዙም ባይዘፈንላትም የጫት መገኛ ናት”፡፡ (2004፣ 79)፡፡

ጫት በኢትዮጵያ በቀደሙት ዘመን እንደ አሁኑ አይብዛ እንጂ ይቃም እንደነበር ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም “የሕይወቴ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡ ጫት በነገሥታቱ ዘንድ ባለመለመዱ ልጅ ኢያሱ በመቃሙ ችግር እንደደረሰበት ሲያስረዱ፤ “ጫት ያስቀባጥራል፣ ልብ ይነሣል ሲሉ እሰማ ነበር፤ ልጅ ኢያሱም ጫት ይበላሉ በስተኋላም በጣም ማብዛት ጀምረው ነበር…” በዚህ ምክንያት በወቅቱ ከቤተመንግሥቱ እንደተገለሉና ከሥልጣን ለመውረዳቸውም እንደ አንድ ምክንያት መቅረቡን ይዘረዝራሉ፡፡

ጫት በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ በርካታ መጠሪያ ስሞች አሉት፡፡ በእንግሊዘኛ ተናጋሪ አገራት khat፣ በየመን qat and gat፣ በሶማሊያ qaat and jaad፣ በኢትዮጵያ chat (ጫት) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ የአቢሲኒያ ሻይ (Abyssinian Tea)፣ የዐረቦች ሻይ (Arabian Tea) ይባላል፡፡ በማለት ጫት ከኢትዮጵያ ተነሥቶ በአካባቢው ወዳሉት አገራት የመን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ማላዊ፣ ታንዛኒያ፣ የዐረብ ባሕረ ሰላጤ አገራት፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችም አገሮች በስፋት መድረሱንና መብቀሉን ያስረዳል፡፡ (Al-Mugahed Leen፣ 2008)፡፡

ጫት በሚቃምበት ወቅት ውስጣዊና ውጪያዊ ስሜቶችን ሊያነቃቁ የሚችሉ ንጥረ ነገሮች አሉት፡፡ እነዚህም፡- Cathinone, Cathine እና norephedrine የሚባሉ ንጥረ ነገሮች (ቅመሞች) የያዘ ነው፡፡ ትኩስ ቅጠሉን በቀላሉ ማግኘት በሚቻልባቸው አገራት ጫት በቀላሉ እየታኘከ በውኃና በሌሎች ጣፋጭ የፈሳሽ ዓይነቶች የሚወራረድ ሲሆን፤ ትኩስ ቅጠሉ በማይገኝባቸው አገራት እንደ ሲጃራ ተጠቅልሎ አሊያም ፒፓ ላይ ተደርጎ ይጨሳል፡፡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በጫት ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚያደርጉ አገራት እንዳሉ ሁሉ፤ በተቃራኒው በከፍተኛ ሁኔታ የሚሸጥባቸው ደግሞ እንደ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ… ያሉ አገራት መሆናቸውን ይኸው ጥናት ያስረዳል፡፡

የጫት ዝርያ ዓይነቶች
***

የጫት ዝርያ ዓይነቶች የሚመረቱባቸው አካባቢያዊ ሁኔታዎች መለያየት ማለትም የቦታው አቀማመጥ፣ የአየር ጠባዩ፣ የአፈሩ ዓይነት፣ የሚደረግለት እንክብካቤ ወዘተ. መሠረት በማድረግ ቀላል የማይባሉ የይዘት ልዩነቶች እንደሚፈጥሩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ የጫት ዓይነቶችም በኅብረተሰቡ ዘንድ በስፋት የሚታወቅበት ጫቱ የመጣበትን ቦታ፣ እንደሚበቅልበት ከተማ ስያሜ የተለያዩ ናቸው፡፡ ወንዶ፣ በለጬ (የማብለጭለጭ ጠባይ ያለው)፣ አቦ ሚስማር (ቂጡ ላይ ሚስማር የሚመስል ቅርጽ ያለው)፣ ገለምሶ (ማታ ማታ ለቅሶ ይሉታል)፣ አውዳይ፣ የባሕር ዳር እና የጉራጌ ጫት ይባላሉ፡፡ የጫት መጠሪያው ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ በአገሪቱ በተለያየ አቅጣጫ የየራሱ የሆነ ስያሜዎች አሉት (ዝኒ ከማሁ፣ 2004፣ 81)፡፡

ከላይ የተገለጹት የጫት ዓይነቶች በዋጋቸውም ይለያያሉ፡፡ አወዳይ እና ገለምሶ የተባሉት ጫቶች ከሐረር አካባቢ የሚበቅሉ ናቸው፡፡ አወዳይ በጫት የጥራት ደረጃ (በቃሚዎች የወጣ እንደሆነ ልብ ይሏል) ቀዳሚ የተሰኘ ነው፡፡ ዋጋውም ከሌሎች የጫት ዓይነቶች በእጅጉ ይወደዳል፡፡ ይህንን ጫት የሚቅሙት ጥሩ የገንዘብ አቅም ያላቸው ሰዎች እንጂ በሌሎች አይደፈርም፡፡ ይህ ጫት አገራችን ወደተለያዩ አገራት በከፍተኛ መጠን ከምትልከው የጫት ዓይነት ውስጥ ዋነኛው እንደሆነም ይነገራል፡፡ ገለምሶ፣ ወንዶ እና በለጬ በተቀራራቢ የዋጋ ደረጃ የሚሸጡ የጫት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ገለምሶ ከተቃመ በኋላ የሚያመጣው የስሜት ለውጥ (ምርቃና) ኃይለኛ እንደሆነ ሲነገር ወንዶና በለጬ ሰውነት ውስጥ ሙቀት ከመስጠት ባሻገር ብዙም የሚያመጡት የስሜት ለውጥ የለም፡፡ የጉራጌ ጫት የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ በተናጠል እንደሚበቅሉበት ሥፍራ የራሳቸው ስያሜ አላቸው፡፡ “እንድብር፣ ወለኔ፣ ወልቅጤ” ይባላሉ፤ በዋጋም ደረጃ ብዙ ገንዘብ አይጠይቁም፡፡

የመቃም ጦርነቶች ከትናንት-ዛሬ
***

ጫት በየቀኑ ካላገኘ የማይንቀሳቀስ ቃሚ አለ፤ ለሥራ ማነቃቂያ ብሎ ጫት ቤት ሔዶ አልያም ቤቱ ወስዶ የሚቅም አለ፡፡ የዕረፍት ጊዜውን ቅዳሜና እሑድ ጠብቆ ከጓደኞቹ ጋር ሰብሰብ ብሎ የሆድ የሆዱን ለመጫወት የሚቅም አለ፤ በተቃራኒው ደግሞ 24 ሰዓት ከአፉ ጫት ሳትወጣ ኦክስጅን የሆነችለት ቃሚም አለ፡፡ ጫት የዕድሜ፣ የጾታ፣ የትምህርት ደረጃ የኢኮኖሚና የአስተዳደግ ባሕል ልዩነት ሳይገታው ተዘውታሪነቱ ይበልጡኑ እያደገ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጫት ሰው እያየ ፊት ለፊት ይዞ መንቀሳቀስ እንደ ነውር የሚቆጠርበት ሁኔታ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን፤ በአብዛኛው ቃሚ ከመንደር አንሥቶ እስከ አደባባይ፣ በታክሲ ውስጥ፤ በዩኒቨርስቲዎች፣ በመኖሪያ ቤት፣ በማስቃሚያ ቤቶች፣ በመንገድ ላይ፣ በገበያ ቦታዎች፣ በቢሮዎች ሳይቀር ይቃማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዳዲስ የሆኑ የጫት መቃሚያ የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችም እየተፈጠሩ ነው፡፡

በዚህ ዘመን እየተመለከትን ያለነው ወጣቱ የገዛውን ጫት በስስ ላስቲክ ይዞ ሲጓዝ አይሸማቀቅም፤ እንደውም እንደ ዘመናዊነት እየታየ ነው፡፡ በርካታ ሠራተኞች ከጫት የተነሣ ይጠርም ይብዛም የሥራ ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ ጫት ለሠላሳ ዓመት ቅሜያለሁ የሚለው መስፍን አበበ ጫት ቤት ገብተህ ስታይ ጫት ይቃማል ሳይሆን እንደ ምግብ ይበላል ማለት ይቻላል ይላል፡፡ “በጫት ቤቶች ውስጥ ዶክተሩ፣ መሐንዲስ፣ አስተማሪው፣ ባለሥልጣኑ፣ ዘፋኙ፣ ወያላው፣ የታክሲ ሹፌሩ፣ የቤት እመቤቶች ሳይቀሩ በየዕለቱ ከትመው ይበላሉ” ሲልም ያክላል፡፡ ይህ ልማድ አሁን ባለበት የመስፋፋት ፍጥነት ሲታይ ችግሩን በእንጭጩ እንዳይፈታ አሳሳቢ አድርጎታል ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡ አንዳንድ ወላጆችም በልጆቻቸው በጫት ሱሰኝነት መጠመድ ከማዘናቸውም በላይ፤ በአገሪቱ የጫት ቃሚ መስፋፋት ተጠያቂው መንግሥት ነው በማለት ይተቻሉ፡፡ “ከኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር ለያዘው ወጣት መንግሥት በቂ የሥራ ዕድል አልፈጠረላቸውም፤ በቂ የሥራ ቦታዎች ባለመኖራቸው ለጊዜ ማሳለፊያ ጫት ይቅማሉ” በማለት መፍትሔ እንዳጡ ያማርራሉ፡፡

የሚቃመው ጫት በከፍተኛ ደረጃ የስሜት ለውጥን ሲያስከትል “ምርቃና” ይባላል፡፡ በምርቃና ወቅት በቃሚዎቹ ዘንድ የተለያዩ ባሕሪና ስሜቶች ይንጸባረቃሉ፡፡ አንዳንዱ ያለመታከት ያወራል፡፡ ሌላው ባልተጨበጠ ተስፋ በደስታ ይቦርቃል፡፡ ገሚሱ በሌለና በሚያስጨንቅ ሐሳብ ውስጥ ተዘፍቆ ይፈዛል፡፡ በጫት ቤት አግኝተናቸው አስተያየት የሰጡን ወጣቶች “ምርቃና ከመጣ የተወሰነ አልኮል ነክ መጠጥ ተጎንጭቶ ስሜትን ማርገብ የግድ ነው፡፡ ያለ በለዚያ ሌሊት ዐይንህ እንደፈጠጠ ጀንበር ስትወጣ ታያለህ” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “እንዳለማመድህ ነው ጫት ቅመህ መጠጥ የማታዘወትር ከሆነ እንቅልፍ አይነሳህም፡፡” ይላሉ፡፡

በጫት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ከባለፉት ሁለት ሥርዓቶች ይልቅ ከኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ጋር ተያይዞ የጫት ሥርጭት መጨመሩን ተሰማ ሰብስቤ ጥናቶችን መሠረት አድርጎ ሲያቀርብ፡- የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ በአገር ውስጥም በውጭም የመንቀሳቀስ፣ ተዘግተው የነበሩ ኬላዎች መከፈት፣ የጫት ሥርጭትን በሓላፊነት ለመከታተል የወሰደ አካል አለመኖሩ፣ በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣው የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ 2004፣ 79)፡፡ በእነዚህ ዓመታት የመቃም ባሕል በአገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ለዚህም ምክንያት ያለውን ሚኪያስ ሰብስቤ በመጽሐፉ “በአንዳንድ አካባቢዎች ለእህል ሰብልና ለቡና ተክል ይውሉ የነበሩ ማሳዎች በጫት ተክል እየተተኩ በመሔድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ጫት በሚበቅልባቸው የአገሪቱ ክፍሎችና የጫቱ ንግድ በሚዟዟርባቸው ክፍሎች የሚገኙ የፖለቲካና የአስተዳደር ሹማምንት ከጫት ከፍተኛ ቀረጥ ይሰበስባሉ፡፡ ገበሬውም የምግብ እህል ከማምረት ይልቅ በማንኛውም ጊዜ በጥሩ ዋጋ የሚሸጥለት የጫት ምርት መሆኑን ስለተገነዘበ በሰፈረበት መሬት ላይ ጫት ለመትከል ለመንከባከብና ለማምረት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡” (ሚኪያስ ሰብስቤ፣ ማኅበራዊ ጠንቆች እና ያንዣበቡ አደጋዎች፣ 1995፣ 98)፡፡

ጫት- “ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆነ ተክል” ጠቀሜታው ለማነው?
***

በብዙ የዓለም አገራት ጫት “ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆነ ተክል” ተደርጎ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካና በዐረብ አገራት ሕጋዊ ተክል ነው፡፡ ይኽ ተክል ወደ አገራቸው እንዳይገባ እገዳ በጣሉት የምዕራባውያን አገራት ጫት ሕጋዊ ያልሆነ ተክል ነው፡፡ ሕጋዊ ባይሆንም የሕጋዊነትን ያህል በየመንደሩ ኅብረተሰቡ በስፋት አውቆታል፤ እየተጠቀመም ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጫትን በየቀኑ በዓለማችን ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሰው ይቅማል ተብሎ ይገመታል፡፡ እነዚህ ቃሚዎች በብዛት የሚገኙባቸውን አገራት ወልደ አማኑኤል ገድሶ በመጽሐፉ እንደሚከተለው ዘርዝሮታል፡፡ “ የመን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ኢትዮጵያ የሚኖሩ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በሌሎች የዓለም ክፍሎች በአፍሪካ ቀንድ፣ የደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ የመካከለኛ ምሥራቅና ተጎራባች የዐረብ ባሕረ ሰላጤ አገራት ተወላጆች ናቸው፡፡” (ወጣቱና ጫት፣ 2007፣ 23)፡፡

ጫት በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ምርት ነው፡፡ በየዓመቱ ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች ከምትባለው ኢትዮጵያ ጀምሮ፣ በሌሎችም አገራት ጫትን እንዳይቅሙ የሚያበረታቱ ቀጥተኛ ያልሆኑ ተግሳጾች ቢኖሩም፣ “አዛውንቶችና በተለይም ደግሞ ወጣቶች” በተለያዩ ምክንያቶች ከማዘውተር አልተቆጠቡም፡፡ (ወጣቱና ጫት፣ ገጽ 28)፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣም ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ያወጣውን መረጃ በመጥቀስ ጫት ከቡና ቀጥሎ በውጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ምርት እንደሆነ ዘግቧል፡፡ “በኢትዮጵያ ከ15 ዓመታት በፊት በጥቂት ቆላማ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ የነበረው የጫት ምርት በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ መስፋፋቱንና ከግማሽ ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን መጽሔቱ አመልክቷል፡፡” (ጥር 13 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡፡

ኒውዮርክ ታይምስም ጫት ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገባ በመሆኑ ከሃያ ዓመታት በፊት ከነበረው መሬት አሁን ወደ ሦስት እጥፍ የሚጠጋ ለጫት ተክል መመደቡን ገልጿል፡፡ ቡና አምራች የነበሩት አካባቢዎችም በጫት ዋጋ በየጊዜው ማሻቀብና በአመራረቱ ቀላልነት እየተሳቡ ከቡና ምርት በመውጣት ወደ ጫት አምራችነት እየገቡ መሆኑንም አስቀምጧል፡፡ ገበሬውም የምግብ እህል ከማምረት ይልቅ በማንኛውም ጊዜ በጥሩ ዋጋ የሚሸጥለት የጫት ምርት መሆኑን ስለተገነዘበ በያዘው መሬት ላይ ጫት ለመትከል፣ ለመንከባከብና ለማምረት ቅድሚያ ይሰጣል ይላል፡፡

ዘኢኮኖሚስት እንደዘገበው የአገሪቱን የውጭ ገበያን በሁለተኛነት ተቆጣጥሯል የተባለው ጫት በአገር ውስጥም ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ምርት መሆኑን በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የጫት መሸጫ አነስተኛ ኪዮስኮች እንደ አሸን እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል ይላል፡፡ ዋጋውም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እያደገ መሆኑንና ወጣት ተማሪዎችም ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መሆኑ ለአገሪቱ አሳሳቢ መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጫት ትውልድ ገዳይ መሆኑ እየታወቀ ትውልዱን ከዚህ ሱሰኝነት ለማውጣት በመንግሥት በኩል ምንም ጥረት አለመደረጉን በርካታ ሰዎችን ያሳዘነ ጉዳ ሆኗል፡፡ “እውን ለትውልዱ የሚያስብ መንግሥትስ አለን?” እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡

ጫት በሚመረትበትና በሚነገድበት ክልል የክልሉ ባለሥልጣናት ከሚገኘው ቀረጥ ተጠቃሚ ስለሆኑ ሁኔታውን እንደጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አድርገው የወሰዱት ይመስላል፡፡ የፌደራል መንግሥትም ጫት የሚበቅልባቸው ክልሎች ከሚያገኙት ጥቅም በተጨማሪ ተጠቃሚ ነው፡፡ ይህንንም ሚኪያስ ሰብስቤ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው ለምሳሌ፡- ከድሬደዋ ወደ ጅቡቲ በአውሮፕላን በባቡርና በመኪና በየዕለቱ ከሚጋዘው የጫት ምርት መንግሥት ቀረጥ እና የውጭ ምንዛሪ ያገኛል፡፡ ከምሥራቅ ሐረርጌ ወደ ሶማሊያ የሚጋዘው ከፍተኛ ጫት እንደዚሁም መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ወደ ሌሎች አገሮች ከሚጋዘው ጫት የማይናቅ ገቢ ይሰበስባል፡፡ በመሆኑም የማዕከላዊው መንግሥት አካላት የዚህን ዕፅ ጎጂነት በይፋ በማጋለጥ ለሕዝቡ ትምህርት ለመስጠትና እንቅስቃሴውን ለመግታት የወሰዱት የጎላ እርምጃ የለም በማለት ቅሬታውን ይገልጻል፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ 98-99)፡፡

በጫት ንግድ አገሪቱ ከምታገኘው ገቢ በተጨማሪ ለአፈር ጥበቃ ጥቅም እንዳለው በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በአፈር ጥበቃ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ” ለመመርመር በተደረገ የማስትሬት ዲግሪ ጥናት የጫት ተክል በመልካም ጎኑ መታየት እንዳለበት ያስረዳል፡፡ “ጫት ለአፈር ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡ አፈርን ቆንጥጦ ይይዛል፤ መሸርሸርን ይከላከላል፡፡ በትንሽ መሬት ላይ የተሻለ ገቢ ስለሚያስገኝ ገበሬው መሬቱን ይንከባከባል” ይላል፡፡

ጫት የሚቅሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ጫት ጥቅም አለው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ሠራተኞች በሥራችን ምርታማ እንድንሆን፣ ተማሪዎችም በትምህርታችን ውጤታማ እንድንሆን አድርጎናል፤ ያደርገናልም ይላሉ፡፡ ጫት ጥቅሙ ተግተን እንድንሠራ ያደርገናል የሚለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪውን እየሠራ የሚገኘው እስጢፋኖስ ተሰማ “ጫት ስቅም በደንብ አጠናለሁ፡፡ ለመሥራትም ያበረታታኛል” በማለት በመቃሙ እንደተጠቀመ ይናገራል፡፡ ጫት መቃም ከጀመርኩ አንድ ዓመት ይሆነኛል የሚለው ዓለማየሁ መኮንን “እስከ ዛሬ አለመቃሜ ይቆጨኛል፡፡ ስቅም ደስታ ይሰጠኛል፣ የበለጠ ጉልበት አገኛለሁ ዋናው በሱስ አለመጠመድ ነው” በማለት በመቃሙ እንደተጠቀመ ያስረዳል፡፡ ጫት ለረጅም ዓመት በመቃም ላይ የሚገኝ አንድ በጎልማሳነት ዕድሜ ክል የሚገኝ ሰው በጫት ተጠቃሚው መንግሥት እንጂ ትውልዱ አለመሆኑን እንዲህ ነበር የገለጸው “ጫት ተጠቃሚው መንግሥት ነው፡፡ አንደኛ በገቢ ኹለተኛ እኔን ጨምሮ ብዙ ጀዝባና ፈሪ ትውልድ ክምችት ይኖራል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ስለ መንግሥት፣ ስለ ፖለቲካ ማሰብ አይፈልግም፡፡ ሁሉም የሚያስበው ሱሱን የሚያሟላበትን ትንሽ ብር ብቻ ነው፤ እሷን ካገኘ ምንም አይፈልግም”፡፡

በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎችም ጫት ትውልዱን እየጎዳው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሲዮሎጂ መምህር የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ በጫት ላይ ሰፊ ጥናት አካሂደዋል፡፡ “ኢትዮጵያ በጫት ምርት አገኘች ተብሎ ትውልድ እንዲጠፋ መተው ትልቅ ዋጋ ያስከፍለናል” የሚሉት ዶ/ር የራስወርቅ፣ በጫት ንግድ ሀብታም ሆኑ የሚባሉ ሰዎች ልጆች በጫት ሳቢያ አእምሮአቸው ተናግቶ በአእምሮ ሕክምና ተቋማት ውስጥ ገብተዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በጫት ለሚገኝ የአጭር ጊዜ ትርፍ አገኘሁ ተብሎ የትውልድ መጻኢ ዕድልን መሠዋት ተገቢ አይደለም የሚሉት አጥኚው ይህ ሁኔታ አደገኛ ከሚባልበት ደረጃ ሁሉ አልፏል ባይ ናቸው፡፡

ምን ይሻላል?
መወያየት መልካም ነው፤ እስኪ እንወያይ …