‹‹ከክልላዊ አስተሳሰብ ወጥተን ኢትዮጵያን እንዴት እንደምናደራጅ ማሰብ አለብን›› አቶ በላይነህ ክንዴ

በኢትዮጵያ በንግድና በኢንቨስትመንት ሥራዎች ጉልህ ሥፍራ ካላቸው ጥቂት ባለሀብቶች መካከል አቶ በላይነህ ክንዴ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ በላይነህ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ግሼ ዓባይ አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት፡፡  ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ዘለቀ ደስታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፍኖተ ሰላም በመሄድ ዳሞት ትምህርት ቤት እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ተከታትለዋል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ያመጡት ውጤት ለኮሌጅ ትምህርት ስለማያበቃቸው በሁርሶ ወታደራዊ ጦር ትምህርት ቤት ወታደራዊ ሥልጠና ተከታትለው፣ በሐረር የመኮንንነት ትምህርት ወስደው የምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ተሃድሶ ሥልጠና ወስደው በቀን ሥራ ሕይወታቸውን ገፍተዋል፡፡ በኋላም ወደ ንግድ ሥራ በመግባት በ4,600 ብር መነሻ ካፒታል ቅቤና ማር በመነገድ ዛሬ ያሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡  በአሁኑ ወቅት በዓመት ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅስ ድርጀት ባለቤት የሆኑት አቶ በላይነህ፣ በ1980ዎቹ የተለያዩ የቀን ሥራዎችን በመሥራት አልፈዋል፡፡ በኋላም ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ በመግባት የጀመሩትን ንግድ አጠናክረው ከመቀጠል ባሻገር፣ ከወዳጆቻቸው ጋር በአነስተኛ የኤክስፖርት ሥራ ውስጥ ገቡ፡፡ በዚህ የኤክስፖርት ሥራ አቅማቸው እያደገ በመምጣቱ ወዳጆቹ ተለያይተው የየራሳቸውን ሥራ ሲጀምሩ፣ አቶ በላይነህ በ1994 ዓ.ም. ‹‹በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ›› የተሰኘ ኩባንያ በማቋቋም ወደ ንግድ ሥራ በጥልቀት ገብተዋል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራው የበላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑት አቶ በላይነህ ጋር ውድነህ ዘነበ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት ላለፉት አሥር ዓመታት እየገዘፈ የመጣ ኩባንያ ነው፡፡ በምን ያህል ዘርፎች ውስጥ ትሠራላችሁ? የወደፊት ዕቅዳችሁስ ምን ይመስላል?

አቶ በላይነህ፡- በንግድና በኢንቨስትመንት ላይ በተለይም በስድስት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርግን እየሠራን ነው፡፡ የመጀመርያው በአስመጭና በላኪነት ዘርፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ትራንስፖርት ነው፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ የደረቅና የፈሳሽ ጭነት የሚሠሩ ከባድ ተሽከርካሪዎች አሉ፡፡ በሕዝብ ትራንስፖርት ውስጥ በመግባት ጎልደን ባስ አክሲዮን ማኅበር አቋቁመን አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ሦስተኛው የሆቴል ዘርፍ ነው፡፡ ከቀድሞው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኤጅንሲ ኢትዮጵያ ሆቴልንና አዳማ ራስ ሆቴልን በመግዛት ዘርፉን ተቀላቅለናል፡፡ ከሁለቱ ሆቴሎች በተጨማሪ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል እየገነባን ነው፡፡ ይህንን ሆቴል ሒልተን ዓለም አቀፍ እንዲያስተዳድር ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ አራተኛው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በአማራ ክልል ቡሬ ከተማ የአገሪቱን 50 በመቶ የዘይት ፍላጎት የሚያሟላ ትልቅ ፋብሪካ እየገነባን ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ለአካባቢው አርሶ አደሮችም ትልቅ ገበያ ይፈጥራል የሚል እምነት አለን፡፡ ከዘይት ፋብሪካ በተጨማሪ ከባድ ተሽከርካሪዎችን እዚሁ አገር ለመገጣጠም ዕቅድ ይዘን እየሠራን ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ፋብሪካውን እየገነባን ነው፡፡ ሥራውን ከአይቪኮ ጋር እየሠራን ነው፡፡ ፒፒ ባግ ፋብሪካም አለን፡፡ አምስተኛውም የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው፡፡ ደረጃ ሦስት የኮንስትራክሽን ኩባንያ አለን፡፡ ይህ ኩባንያ እስካሁን በራሳችን ሥራዎች ላይ ተጠምዶ ቆይቷል፡፡ አሁን ሌሎች ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ በጨረታዎች ለመወዳደር ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ስድስተኛው እርሻ ነው፡፡ በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን 2,750 ሔክታር መሬት ላይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎ እናመርታለን፡፡ የምናመርተውን ምርት ወደ ውጭ እንልካለን፡፡ ለክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅትም ዘር እናቀርባለን፡፡ ሌላኛውና ሰባተኛው ዘርፍ የምንለው የፋይናንስ ዘርፍ ነው፡፡ ፀሐይ ኢንዱስትሪ የተሰኘ ኩባንያ አለን፡፡ ይህ ኩባንያ ቃሊቲ ብረታ ብረት ላይ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በሌሎች የፋይናንስ ኩባንያዎች አክሲዮኖች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለፋይናንስ ካነሱ በቅርቡ ቤተ ክህነት ያለችበት አንድ ባንክ ‹‹ዳሎል›› በሚል ስያሜ እየተቋቋመ ነው፡፡ እርስዎ የዚህ ባንክ መሥራች መሆንዎ ይነገራል፡፡ በሚመሠረተው ባንክ ላይ ያለዎ ድርሻ ምንድነው?

አቶ በላይነህ፡- አክሲዮን እንድገዛ ተጠይቄ ፈቃደኛ አለመሆኔን ገልጫለሁ፡፡ ድርጅታችን ብዙ ሥራዎችን ጀምሯል፡፡ የተጀመሩትን ሥራዎች ወደ አንድ ምዕራፍ ሳናሸጋግር ወደ ሌላ ኢንቨስትመንት መግባት አልፈለግንም፡፡ እኔም በባንኩ ውስጥ እንዳለሁበት ተደርጎ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን እኔ በአዲሱ ባንክ ውስጥ የአንድ ብር አክሲዮን የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በላይነህ ክንዴ ኮርፖሬት በገባባቸው ዘርፎች ገንኖ ይታያል፡፡ ያከናወናቸው ሥራዎችም ሆኑ አዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች ሰፋፊ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ይኼ ሥራ በአንድ ሰው የሚሞከር አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ ተወዳዳሪዎችዎ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹ከበላይነህ ጋር አብሮ የሚሠራ አካል አለ እንጂ፣ በላይነህ ብቻውን ይህን ሁሉ ኢንቨስትመንት አይወጣውም፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ከእርስዎ ጋር የሚሠራ ሥውር አካል አለ?

አቶ በላይነህ፡- አንዳንድ ሰው ገንዘብ ካገኘ፣ ራሱንና ቤተሰቡን ይዞ የተሻለ ሕይወት ለመኖር ይፈልጋል፡፡ የእኔ እምነት ያገኘዃትን ሳንቲም ከሕዝቡ ጋር፣ ከወገኔ ጋር አብሬ ሠርቼ ዳቦ መብላት ነው፡፡ እኔ ያገኘሁትን ሳንቲም ወደ ቤተሰቦቼ ብል ደሃ እህትና ወንድሞች አሉኝ፡፡ ብዙ ያልተለወጡ ወዳጅ ዘመዶች አሉኝ፡፡ እኔ ግን ከሕዝብ ጋር እንለወጥ፣ ሕዝቡን እናገልግል የሚል አቋም አለኝ፡፡ መጀመርያ ቅድሚያ የምሰጠው ፕሮጀክቶችን ሠርተን ለሕዝቡ የሚታይ ነገር እናቅርብ፡፡ ከዚያ በኋላ ከፕሮጀክቶቹ እንጠቀማለን፡፡ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የምንበላውና የምንጠጣው ከተሟላልን ከሕዝቡ ጋር ብንኖር ይሻላል፡፡ አለበለዚያ ከሕዝብ ተነጥለን አንኖርም ብዬ ቤተሰቤን በማሳመን እየሠራን ነው፡፡ እኛ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንኑር፣ ግን ፕሮጀክቶቻችን ብዙ ኢትዮጵያዊ ይጥቀሙ ከሚል ሐሳብ በመነሳት እየሠራን እንገኛለን፡፡ እንግዲህ አንዳንድ ሰዎች ውድድርና ሥራ ሲያቅታቸው ሰው ሠርቶ አይለወጥም የሚል ገዳይ የሆነ፣ አዲሱን ትውልድ የሚገድል፣ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ሠርቶ ተለውጦ ትልቅ ነገር አይሠራም የሚል አስተሳሰብ እንዲይዝ እያደረጉ ነው፡፡ የሰው ልጅ በቀጥተኛ መንገድ ራሱ ሠርቶ፣ አድጎ ተለውጦ ሊሄድ አይችልም ብሎ እንዲያስብና ወጣቱ ይኼ ገዳይ አስተሳሰብ እንዲሰርፅበት እያደረጉ ነው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ባለሀብት ጥሮ ግሮ እንደሚያድግ ማወቅ አለብን፡፡ ከተሠራ ዕድገት እንደሚመጣ ወጣቱ መገንዘብ አለበት፡፡ ሁሉም ሰው ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ ድጋፍ እየተደረገለት ነው የሚል አስተሳሰብ በወጣቱ ዘንድ መስረፅ የለበትም፡፡ ከተሠራ በ26 ዓመት አይደለም በአሥር ዓመት ውስጥ ለውጥ ይመጣል፡፡ እኔ 26 ዓመት ከሥራዬ ውጪ ሌላ ነገር አላውቅም፡፡ ለመዝናናት ጊዜ የለኝም፡፡ ለሌሎች ነገሮች ጊዜዬን ሳላከፋፍል ሥራዬን ብቻ በመከተል ነው የኖርኩት፡፡ ሠራተኞቼ ደግሞ ቁርጠኛ መሆናቸው ለዕድገታችን ጠቅሞናል፡፡ እኛ ገና ከድክ ድክ ያልወጣን ነን፡፡ ባንክ እየተበደርን እንሠራለን፡፡ በእርግጥ ካለው ማኅበረሰብ ሲነፃፀር የተሻልን ነን ለማለት ይቻል ይሁን እንጂ፣ ሀብታም ነን ለማለት ስንት ቢሊዮን ዶላር ኖሮን ነው? እኔ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሠርቶ እንደተለወጠ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ፎርብስ መጽሔት እርስዎንና አምስት ሌሎች ባለሀብቶችን ኢትየጵያዊ ቢሊየነሮች ሲል ይፋ አድርጓል፡፡ እኔ እስከማውቀው የእርስዎ ድርጅት በዓመታዊ ከኤክስፖርት ብቻ እስከ 75 ሚሊዮን ዶላር ያስገባል፡፡ ፎርብስ በቂ መረጃ ነበረው?  ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ከሼክ መሐመድ አል አሙዲ ቀጥሎ ትልቁ ሀብታም ነኝ ብለው ያስባሉ?

አቶ በላይነህ፡- ይኼ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡ እኔ ሀብታምነቴ ሲነገር ነው የምሰማው፡፡ እኔ ገና ከባንክ ብድር ያልወጣሁ፣ አብዛኛው ሥራዎቼ በባንክ ብድር ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ በእርግጥ ድርጅቱ ሀብት የለውም ለማለት አይደለም፡፡ የተወሰነ ሀብት አለው፡፡ ከባንክ ጋር የሚያያዙ ብዙ ሥራዎች ውስጥ ገብተናል፡፡ ከዚያ ውስጥ ከሼክ አል አሙዲ አይደለም እኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 100 ሀብታሞች ውስጥ አንዱ እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ፎርብስም ሲያወጣ ከምን መረጃ ነው ያወጣችሁት ብዬ ጥያቄ አንስቻለሁ፡፡ እንግዲህ በማንቀሳቅሰው ገንዘብ ከሆነ፣ ሥራ አስፍቶ ከመሥራት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሀብታሞች ውስጥ አንዱ መባል ይቻላል፡፡ እኔ ግን አላምንበትም፡፡ በሀብት ደረጃ ብዙ ሀብት የፈጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ እንደዚህ ነኝም ብዬ አስቤም አላውቅም፡፡ ይኼ የተሳሳተ መረጃ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ምክንያቱም መረጃው ከየት እንደተሰጠና ማን እንደሰጠ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ለሚያካሄዷቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች የራስ ፋይናንስ እንዳለ ሆኖ፣ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችም ያስፈልጋሉ፡፡ ከባንኮች ከፍተኛ ገንዘብ የማይገኝበት ጊዜ ነው፡፡ እርስዎ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እያካሄዱ ስለሆነ በቀላሉ ብድር እንደሚያገኙ ተደርጎ ይነገራል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ በላይነህ፡- ብድርን በተመለከተ ይኼንን ትልቅ ኢንቨስትመንት ይዞ ቀርቶ ትንሽ ሥራም ለመሥራት ዛሬ ብድር አስፈላጊ ነው፡፡ በሌሎች የሠለጠኑ አገሮችም ሀብታም ናቸው የሚባሉ ሰዎች ጭምር ከባንክ ጋር ነው የሚሠሩት፡፡ ሌላው የእኛ አገር ለብድር ያለው አስተሳሰብ ይለያል፡፡ በሌላው ዓለም እየሠራ ብድር የሚፈልግ ሰው በባትሪ ተፈልጎ ነው የሚሰጠው፡፡ እዚህ ብድር መውሰድ ሁልጊዜ እንደ ኃጢያት ተደርጎ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ኃጢያት የሚሆነው ብድር ሲወሰድ አይደለም፡፡ ብድርን ወስዶ መክፈል አለመቻል ነው ኃጢያት፡፡ ከዚህ አንፃር በቂ የሆነ ብድር አለ ብሎ ለማለት ይቸግራል፡፡ እዚህ አገር ውስጥ በቂ የሆነ ብድር ለማግኘት ከባድ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በላይነህ ትልቁ የብድር ተጠቃሚ ነው፣ ባንኮች ይደግፉታል ይላሉ፡፡ መታወቅ ያለበት ባንኮች ራሳቸው ነጋዴዎች መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ ባንኮች ራሳቸው አትራፊ ናቸው፡፡ ባንኮች አትራፊ የሚያደርጋቸውን ቢዝነስ ይደግፋሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛም ድርጅት በተከታታይ ለአሥርና ለአሥራ ሁለት ዓመታት በኤክስፖርት ሥራ ላይ በትልቁ ያለ ስለሆነ፣ ከባንኮች ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት ስላለው ብድር የማግኘት ዕድል አለው፡፡ ግን አሁን ላሉት ኢንቨስትመንቶች በጣም ትልቅ የሆነ ፋይናንስ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ለፕሮጀክቶች ሁሉ ብድር ታገኛላሁ ካልከኝ መልሴ አናገኝም ነው፡፡ ይኼ ፋይናንስ በአገር ውስጥ ይሟላል ወይ ካልከኝ፣ እኔ አላውቅም፡፡ የባህር ዳሩን ሒልተን ሆቴል ግንባታ ብንወስድ ለማጠናቀቅ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል፡፡ እንግዲህ በጥሩ ደረጃ አገር የሚያስከብር፣ የፈለግነውን እንግዳ የምናስተናግድበት ሆቴል እናዘጋጅ ካልን ፋይናንስ ያስፈልጋል፡፡ የቡሬ ፋብሪካ አለ፣ እዚህ ገላን ከባድ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ አለ፣ አዳማ የሆቴል ፕሮጀክት አለ፣ እነሱ ብዙ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ እኔ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ግን ባለው ሁኔታ ባንኮች አይደግፉንም ማለት አይደለም፡፡ ለኤክስፖርት ሥራ በደንብ ይደግፉናል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አዳዲስ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በአገር ደረጃ መገንባት ያለበትን ገንብተዋል? የባህር ዳሩን ሒልተን ግንባታ ብንመለከት እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቅ የማጠናቀቂያ ሥራ ይቀራል፡፡ የቡሬው ምግብ ዘይት ፋብሪካም እንዲሁ 17 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል፡፡ ሌሎችም የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ፕሮጀክቶች ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር አለ፡፡ ከዚህ አንፃር እንዴት ይኼን አስቸጋሪ ጊዜ ማለፍ ይቻላል?

አቶ በላይነህ፡- እነዚህ ፕሮጀክቶች የተጀመሩት ከሦስት ዓመት በፊት ነው፡፡ የመንግሥትን ፖሊሲ ተከትለን በቱሪዝም ሴክተር፣ በኢንዱስትሪ ሴክተር፣ በተለይ ደግሞ ዘይት ለአገሪቱ ወሳኝ ነው በሚል ወደዚህ ሥራ ገብተናል፡፡ ለኢንዱስትሪ 15 በመቶ ካዋጣችሁ 85 በመቶ መንግሥት ይደግፋል የሚል የመንግሥት ፖሊሲን ተከትለን ነው የገባነው፡፡ እንግዲህ አገር ውስጥ ካልተሳካ ከውጭ ባንኮች ጋር የምንነጋገርበትን መንገድ መፍጠር ካልሆነ በስተቀር፣ እነዚህን ፕሮጀክቶች ወደፊት ማስኬድ እንችላለን ወይ? በራስ አቅም ብቻ የሚቻል አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ ማንኛውም ፕሮጀክት በቱሪዝም ዘርፍ ያሉን ፕሮጀክቶች እንዲታገዙ እንፈልጋለን፡፡ እርግጠኛ ነኝ የመንግሥትን ድጋፍ እናገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በእርስዎ ድርጅቶች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ምን ይመስላል?  ከዚህ ችግር ለመውጣት ምንድነው መደረግ ያለበት?

አቶ በላይነህ፡- እንግዲህ የውጭ ምንዛሪ ችግር የአገራችን ዋናው ተግዳሮት ነው፡፡ ይኼ ተግዳሮት እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ኩባንያ የእኔንም ኩባንያዎች ይገዳደራል፡፡ አሁን ሁሉንም ፕሮጀክቶች በያዝንላቸው ጊዜ ላለመጨረስ ዋናው ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ እንደ አገር እንዴት ይፈታል ለሚለው ምርታችንን በመጨመር ነው፡፡ አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ለአገሪቱ ገቢ እያመጡ ያሉት የግብርና ምርቶች ናቸው፡፡ የግብርና ምርቶችን ምርታማነት እየጨመርን፣ ያልታረሱ መሬቶችን እያረስን፣ የታረሱ መሬቶች ደግሞ ብዙ ከመስጠት ትንሽ ወደ መስጠት የመጡትን የአፈር ለምነት ሁኔታ በመመርመር፣ ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ የጎደላቸውን ንጥረ ነገር በማዳበሪያ በማሟላት ዝም ብሎ ዳፕና ዩሪያ ከማድረግ ይልቅ፣ የእኔ ሙያ ባይሆንም የጎደላቸውን ንጥረ ነገር በማየት ምርቱ እንዲጨምር ማድረግ ያሻል፡፡ የሁመራና የመተማ መሬት በፊት አሥር ኩንታል ሰሊጥ በሔክታር ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ሁለት ሦስት ኩንታል በሔክታር ሆኗል፡፡ እሱን ለመለወጥ መሥራት አለብን፡፡ አሁን በዓመት የምናመርተውን አነስተኛ የሰሊጥ ምርት ወደ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ብናሸጋግር፣ ያልታረሱ መሬቶችን በስፋት ብናርስ፣ የታረሱትን መሬቶች ደግሞ ምርታማነት ብንጨምር፣ የመስኖ አሠራር ብንከተል ጥሩ ውጤት ይገኛል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ከረዥም ጊዜ አንፃር ይኼ ነው፡፡ ከአጭር ጊዜ አንፃር የፋይናንስ ፖሊሲያችንን ማየት አለብን፡፡ በውጭ ከሚኖረው ማኅበረሰብ የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበትን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ሁሉ አገሩ ገብቶ ይሥራ ተብሏል፡፡ በውጭ አገር የሚሠራውም አገሩን ይደግፍ ተብሏል፡፡ ዳያስፖራው ከውጭ የሚያገኘውን ዶላር አገር ቤት ቢያመጣ፣ እኛ ኤክስፖርተሮች ደግሞ ጠንክረን ጥሬ የግብርና ምርቶችን ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምረን ብንልክ የተሻለ ዋጋ እናገኛለን፡፡ እንደዚህ ካደረግንና ሁሉም ሰው ከተረባረበት አገር ሊለወጥ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአጭር ጊዜ ፖሊሲያችንን ማየት፣ ከውጭ ማኅበረሰብ የውጭ ምንዛሪ እንዴት ማግኘት እንችላለን የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ትንሽ ጥብቅ ያለው ፖሊሲያችን ፈታ፣ ላላ ቢደረግ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዘይትና ከበቆሎ ንግድ ጋር በተገናኘ የበላይነህና ክንዴ ስም ይነሳል፡፡ በእርግጥ መንግሥት የዘይት ፋብሪካ እየገነቡ ላሉ ኩባንያዎች የዘይት ንግድንም  ሰጥቷል፡፡ ግን ደግሞ በሌላ በኩል የዘይት ንግድ ሊሰጠን ይገባል ብለው የሚያምኑ ነጋዴዎች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ለምንድነው የዘይት ንግድ ነፃ የማይሆነው? ከዘይት በተጨማሪ የበቆሎ ወጪ ንግድም እንዲሁ በእርስዎ ነው እየተከናወነ ያለውና ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

አቶ በላይነህ፡- እኔ የምነግርህ እውነቱን ነው፡፡ ከአንድ አቅጣጫ የሚነሳ የተዛነፈ አስተሳሰብ አለ፡፡ ቡሬ ላይ ዘይት ፋብሪካ ስጀምር መንግሥት ነበር ዘይት የሚያስመጣው፡፡ በጂንአድ በኩል እያስመጣ የሚያከፋፍለው መንግሥት ነበር፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ዘይት በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች ሽርክና መሠራት አለበት፣ የዘይት ችግር በግሉ ዘርፍ መያዝ አለበት፣ የሚል አቋም በያዘበት ወቅት ነው ግንባታ ውስጥ የገባሁት፡፡ ግንባታ ውስጥ ገብቼ እየሠራሁ ሳለ ከንግድ ሚኒስቴር ተደውሎ ‹‹ዘይት ፋብሪካ እየገነባ መሆንህን ሰምተናል፡፡ ስለዚህ ይኼንን ለማበረታታት ልምድም እንድትወስዱ አሁን የሚመጣውን ዘይት እንድታከፋፍሉ እንፈልጋለን፤›› የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ እንዲያውም በስልክ ሲነገረኝ ውጭ አገር ነበርኩ፡፡ አዎ ማድረግ እችላለሁ ብዬ መልስ ሰጠሁ፡፡ ስመጣ ቢሮዬ ደብዳቤ ተጽፎ አገኘሁ፡፡ ፈቃደኛነቴን በደብዳቤ ገለጽኩኝ፡፡ ስብሰባ ተጠርተን እንደ ማናቸውም ጓደኞቼ ሥራ እንድጀመር ተደረገ፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ማየት የሚቻለው ለምን ተመረጠ የሚለውን መንግሥት ነው የሚያውቀው፡፡ የመንግሥት መመዘኛ የነበሩትን ለመግለጽ ፋብሪካ የሚሠሩ፣ በሌሎች ሥራዎች ጠንካራ የሆኑ፣ ለሕዝቡ በአግባቡ ሊያቀርቡ የሚችሉ የሚል መመዘኛዎች እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡ መመዘኛውም ቢታይ የእኔ ድርጅት ባለፉት አሥር ዓመታት ከፍተኛ ዶላር ካመጡ ድርጅቶች የመጀመርያው ዕርከን ላይ የሚቀመጥ ነው፡፡ አንድ ሰው ይመረጥ ቢባል እኔ ብመረጥ ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራችንን በትክክል ነው የምንሠራው፡፡

በመሠረቱ ግን ዘይት መቸርቸር ይሻለኛል ሳልል ፋብሪካ ግንባታ የጀመርኩኝ ስለሆነ ለእኔ ቅድሚያ ቢሰጥ ምንም አይደንቅም፡፡ እኔ የማረጋግጥልህ በተለያዩ ጊዜያት እነዚህ ሐሳቦች ሲነሱ በይፋ እኔን አስወጡኝ፣ ለሌላ ሰው መስጠት ከተፈለገም ብታስወጡኝ እኔ ችግር የለብኝም ብዬ በተደጋጋሚ ተናግሬአለሁ፡፡ ዘይት ማስመጣት እንደ አትራፊነት ብቻ መታየት የለበትም፡፡ ብዙ ኃላፊነት አለው፡፡ አንድ ቀን ሥራው ከጎደለ ማኅበረሰቡ አንተ ላይ ነው የሚያነጣጥርብህ፣ አለቃህ ብዙ ነው፡፡ ቀበሌ፣ ወረዳና ዞን፣ እንዲሁም ክልል ድረስ አለቃህ ብዙ ነው፡፡ በሥነ ሥርዓት መሥራት ይኖርብሃል፡፡ ብዙ ክትትል ነው ያለው፡፡ ሌላው መደበኛና መደበኛ ያልሆነው ገበያ በጣም የተለያየ ነው፡፡ ያንን ተቆጣጥሮ መንግሥት ባስቀመጠው ዋጋ መሸጥም፣ መከታተልም ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ብዙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ሊኖሩህ ይገባል፡፡ ገዝቶ ማምጣቱ፣ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ ለሌሎችም ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ትልቅ ፋይናንስ ነው የሚጠይቀው፡፡ የምታስመጣበት፣ እዚህ የሚኖርህ፣ ክምችት የምትይዘው፣ የምታከፋፍለው ብዙ ችግር ያለው ነው፡፡ እኛ ብዙ ዓመት የሠራን ድርጅት ሆነን እያለ የዘይት ሥራ ባይሰጣቸው ኖሮ ሀብት አይፈጥሩም ብሎ የሚያስብ ካለ በጣም የተሳሳተ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም የዘይት ንግድ ደግሞ አክሳሪ ነው፡፡

ሌላው የምነግርህ ድጎማ የሚያደርገው መንግሥት ነው፡፡ ብራችን ለሁለት ለሦስት ወራት እጃችን ሳይገባ ተይዞ ይቆያል፡፡ ዘይት ብዙ ትጋት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ ያው በዕዝ ሥር የሚተዳደር ስለሆነ ብዙ ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ሌላው በችግር ጊዜ ማድረስ አለብህ፡፡ ያኔ ረብሻው እያለ ሕዝቡ ዘይት እንዳያጣ መኪኖቻችን ይቃጠሉ ብለን የምንልክበት ጊዜም ነበር፡፡ የእኛን አይደለም የሌሎችንም ኮታ ስንሸፍን የነበርንበት ጊዜ አለና ሕዝባዊነት ያስፈልገዋል፡፡ ይኼ ስለገንዘብ ብቻ ሳይሆን አርቆ ማሰብንም የሚጠይቅ ኃላፊነት የሚፈልግ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለዚህ ይኼ የዘይት ሥራ የተሰጠን በአግባቡ ነው፡፡ ፋብሪካ ከመክፈት አንፃር ድጋፍ ከተደረገልን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ከተገኘ፣ የውጭ ምንዛሪው ከተገኘ ፋብሪካውን አምጥቶ ገጥሞ ሥራ መጀመር ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በተሰጠን አቅጣጫ እየሄድን ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ በላይነህ ከዘይት ንግድ ውጣ አታስፈልግም ካለ አንድ ደብዳቤ ነው የምፈልገው፡፡ መውጣት እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በበቆሎ ወጪ ንግድ እንዲሁ የድርጅትዎ ስም ይነሳል፡፡ ለበላይነህ አድልኦ ይደረጋል፣ ለሌላው ላኪ ሥራው አይሰጥም የሚል ቅሬታም ይቀርባል፡፡ ለዚህ ምላሽዎ ምንድነው?

አቶ በላይነህ፡- በቆሎ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ነው ተብሎ እንዳይወጣ ከታገዱ ምርቶች አንዱ ነው፡፡ መንግሥት ግን ትርፍ ምርት አለ ብሎ ሲያስብ ይፈቀዳል፡፡ ከዚህ አንፃር እኔ ከራሴ መሬትና ከኢትዮ አግሪ ሴፍት አራት መቶ ሺሕ ኩንታል በቆሎ ገዝቼ ነበር፡፡ መንግሥት ምርት ያላቸውና የተጠራቀመ እህል ያላቸው ቢያወጡ መልካም ነው በማለቱ፣ ኬንያ ድርቅ ገብቶ ስለነበር የኬንያ መንግሥት ለኢትየጵያ መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ከዚህ አንፃር እያጠራቀምን እኔ፣ ዩኒየኖችና ሌሎችም ነጋዴዎች ጥያቄ አቅርበን በጥያቄው መሠረት ምርት ያላቸውን እያየ የንግድ ሚኒስቴርና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተነጋግረው ፈቃድ ተሰጠ፡፡ በተፈቀደው መሠረት እኔ ሰፊ የገበያ ዕድል አገኘሁኝ፡፡ በጥንካሬ ምርት አወጣሁ፡፡ ከዚያ የተለየ ነገር የለውም፡፡ በቆሎ ለማውጣት የተፈቀደላቸው ዩኒኖችና የግል ባለሀብቶች ስምንት እንሆናለን፡፡ ከእኔ ጋር የተፈቀደላቸው ዩኒየኖችና የግል ባለሀብቶች አሉ፡፡ እኔ ግን የገበያ ዕድል አግኝቼ አንድ ቶን ስንዴ በ275 ዶላር እየተገዛ እኔ እስከ 388 ዶላር በቶን በመሸጥ በቆሎ ከስንዴ በላይ እንዲሸጥ አድርጌ ለአገሬ ከፍተኛ ዶላር አስገብቻለሁ፡፡ አገሬን ደግሞ በኬንያ ሕዝብና መንግሥት ዘንድ ከፍተኛ ሞገስ አሰጥቻለሁ፡፡ ኬንያዎች በጋዜጦቻቸው ጭምር ኢትዮጵያ ረዳችን፣ ኢትዮጵያ በችግራችን ጊዜ ደረሰች እያሉ ሁለት ሦስት ጊዜ አትመዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ለእኔ የኬንያ መንግሥት የምስክር ወረቀት ሰጥቶኛል፡፡ ያለ አንድ የውል ጥሰት በሥነ ሥርዓት በቆሎ ለኬንያ በማቅረቤ ያንን የሚገልጽ ደብዳቤ በሚኒስትር የተፈረመ ተሰጥቶኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ገበያ አፍንጫችን ሥር እንዳለና ምን እንደሚመስል አይቻለሁ፡፡ የሁለቱንም መንግሥታት ዓይን የከፈተ ግብይት ነው፡፡ የሁለቱንም ሕዝቦች ዓይን የከፈተ ነው፡፡ በኮንትሮባንድ ይሄድ የነበረውን በቀጥታ መንገድ እንዲሸጥ አድርገናል፡፡

ስለዚህ በቆሎም ላይ የሠራነው ሥራ በጥሩ ሁኔታ እንጂ በመጥፎ የሚመዘገብ አይደለም፡፡ በጥንካሬያችን የሚመዘገብ ነው፡፡ ይኼንን ሁሉ የታጠረ ነገር ከፍተነዋል፡፡ አሁን ጥሩ በቆሎ ካመረትን ኬንያ ጥሩ ገበያ አለ፡፡ በቆሎ ካመረትን ሁልጊዜ ገዥያችን ልትሆን እንደምትችል፣ የአፍሪካ ኅብረት ያስቀመጠው አፍሪካ ለአፍሪካ ንግድ እናበረታታ ከሚለው አንፃር ዓይን የከፈተ ነው፡፡ አንድ ዓመት ብቻ አይደለም አገርና ሕዝብ የሚኖረው፡፡ ይኼ መልካም ተሞክሮ ተወስዶ ሌላው በዚያ መንገድ መጓዝ አለበት፡፡ እኔ የአገር ሀብት አላባከንኩም፡፡ ትልቅ ዶላር አመጣሁ እንጂ፡፡ እኔ የአገር ስም አላጎደፍኩም፡፡ ትልቅ ጥሩ ስም ከኬንያ ሕዝብና መንግሥት ዘንድ አመጣሁኝ እንጂ፡፡ ስለዚህ ይኼንን የሚሉ ሰዎች ሥሩ ሲሏቸው መሥራት የማይችሉ፣ ደግሞ ሰው ሲሠራ ማስቆም የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢሰጡዋቸውም አይሠሩም፡፡ እኔ ከዚህ አልፎ የኬንያ መንግሥት ያለኝን አፈጻጸም በማየት፣ ከሜክሲኮ መርከብ ሙሉ በቆሎ ገዝቼ እንዳመጣ ሥራ ሰጥቶኛል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ድርጅታችን ያለውን ጥንካሬና ቁርጠኝነት ነው፡፡ ስለዚህ እኔ የሠራሁት ሥራ አገሬን የሚያስከብር፣ አገሬን የሚያኮራ፣ ሕዝቤን የሚያኮራ ስለሆነ የምኮራበት ነው፡፡ ይኼ ሥራ ደግሞ በዚህ ዓመት ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ ድርጅታችን የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ ለጣሊያን መንግሥት ሁለት መርከብ ሙሉ ወደ ስምንት መቶ ሺሕ ኩንታል በቆሎ አቅርቧል፡፡ በዚህ ጊዜ አገራችንን የሚያስከብር፣ ኢትዮጵያ ለዚህ ደረሰች ወይ የሚያሰኝ ስም ያሰጠ ድርጀት ነው፡፡ እና የግብርና ምርቶች በመላክ ከስመ ጥር ድርጅቶች ጋራ የሚሠራ የመጀመርያው መስመር ላይ ያለ ድርጅት በመሆኑ የምኮራበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትየጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበረችም፡፡ እዚያም እዚህም የፀጥታ መደፍረስ ነበር፡፡ መንግሥትም ይኼን ነገር በማብረድ ተግባር ላይ ተወጥሮ ነበር፡፡ እርስዎም ብዙ ክልሎች ውስጥ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችና ንግዶች የሚያካሂዱ እንደ መሆንዎ ተፅዕኖው እንዴት ነበር? ከዚህ በኋላስ በምን ዓይነት አኳኋን መጓዝ አለበት?

አቶ በላይነህ፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት እዚህም እዚያም ያለው ረብሻ ለኢንቨስትመንት ከፍተኛ ችግር ነበር፡፡ ችግሩ የከፋ ቢሆንም በተቻለን መጠን እየሠራን፣ ኢንቨስተመንቱ እንዳይቆም፣ ለሠራተኞቻችን ደመወዝ መክፈል እንዳይቆም የራሳችንን ጥረት አድርገናል፡፡ ወቅቱ ፈታኝ ቢሆንም አሁን ያ ሁሉ አልፎ አገሪቱ ወደ ሰላም  ገብታለች፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ያ ችግር ደግሞ ባይመለስ ሁላችንም መሥራት ይኖርብናል፡፡ ባለፈው በረብሻው ኢንቨስትመንቱን የማስቀጠል ሁኔታው ከብዶን ነበር፡፡ አሁን ሰላም በመምጣቱ ይኼንን ለውጥ ተጠቅመን ወደ ሥራ እንገባለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ያሉን ኢንቨስትመንቶቻችን በሰፊው እንቀጥላለን ብለን እናስባለን፡፡ ለማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጥሪ ተላልፏል፡፡ አገሩ ገብቶ ሥራውን መሥራት አለበት፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን፣ እንደ አንድ ተደምረን ሠርተን አገራችንን መለወጥ አለብን፣ ከዚህ ችግር መውጣት አለብን፣ ከረብሻ መውጣት አለብን፡፡ እንግዲህ ረብሻውን ማስቆም የሚቻለው ተባብሮ በመሥራት፣ ኢኮኖሚውን በማሳደግ፣ ሰላምና ዴሞክራሲን በማስፈን፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሠርቶ እንዲበላ ዕድል በመፍጠር ነው፡፡ ለዚህ ኃላፊነት እኛ በተሻለ ቦታ ያለን ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል፣ የትኛውም ያገባኛል የሚል ሰው ይኼን አገር በመለወጥ ላይ ትኩረት ቢያደርግና ሥራ ብንሠራና ከረብሻ ብንወጣ ደስ ይለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ገና ብዙ ይቀራሉ፡፡ ግን አማራ ክልል የራሱን ኢንዱስትሪ አብዮት ለማካሄድ ትልቅ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ኦሮሚያም እንደዚሁ የኢንዱስትሪ አብዮት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይኼ ነገር ከግሉ ዘርፍ ጋር አይደራረብም? በባለሀብቶቹ የሚሠሩ ሥራዎች በመንግሥት ደረጃ ሲሠሩ ወይም ደግሞ ክልላዊ ባህሪ ያላቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ሲስፋፋ አድሏዊነት አይፈጠርም ወይ? ውድድሩ ፍትሐዊ ይሆናል ወይ? የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር ለመወዳደር ሊያስቸግረው አይችልም ወይ?

አቶ በላይነህ፡- እኔ ለብሔር አደረጃጀትም ሆነ ለብሔራዊ እንቅስቃሴ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ እኔ እንደ አገር ኢትዮጵያ ጠንክራ እንድትወጣ ነው የማስበው፡፡ እሱን ለማድረግ ከክልላዊ አስተሳሰብ ወጥተን ኢትዮጵያን እንዴት እንደምናደራጅ ማሰብ አለብን፡፡ በልማቱ በኩል ያው የጊዜው ሁኔታ ሆነና ሁሉም ወደ ክልሉ ማየት ሲጀምርና ክልሉን የማልማት ነገር ሲታሰብ፣ እዚህ ፌዴራል አካባቢ ያለው ባለሀብትም በየክልሎቹ እየተሳተፈ ይሠራል፡፡ በክልሎቹ ተሳትፎ መሥራቱ አይደለም ችግሩ፡፡ በክልሎቹ ተሳትፎ መሥራቱ አገርን ያለማል ጤናማ ውድድር ከሆነ ማለት ነው፡፡ መጥፎ ሰይጣናዊ ውድድር ከሆነ ግን የመጠላለፉ ነገር ይመጣል፡፡ እና አማራ ክልል ውስጥም እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲታሰብ መጀመርያ የክልሉ ተወላጆች ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር ባለድርሻ ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡ አንድ ሆነን ከሠራን አማራ ክልል ለማ ማለት ኢትዮጵያ ለማች ማለት ነው፡፡ እኔ ባይገርምህ ሁሉም ጋ እሳተፋለሁ፡፡ ድርጅታችን አምስት ክልል ላይ ልማት አለው፡፡ ስለዚህ ይኼ አስተሳሰብ መጥፎ ጎን የሚኖረው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚዞር ከሆነ ነው፡፡ ክልሎችን እየተባበሩ ማልማት የኢትየጵያ ልማት ማለት ነውና በዚህ ውስጥ እኔ የቦርድ አባልም ነኝ፡፡ በዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ አሁን ሥራው እየተቀላጠፈ ለውጥም እየመጣ ይመስለኛል፡፡ በትኛውም ኮሪደር ልማት አለ ማለት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ አማራ ክልል ውስጥ ያለ ልማት ለአማራ ሕዝብ ብቻ ነው ከተባለ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ አሁን ጊዜውም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ እስካሁን ብሔረተኝነት እየጎላ መጥቶ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን እስቲ እናንሳ የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ እኔም የምደግፈው ነገር ነውና ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በላይነህ ክንዴ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ በላይነህና ክንዴ በውጭውም ዓለም እንደዚሁ ስሙ ይነሳል፡፡ እየተነሳም ያለ ትልቅ ድርጅት ነውና ከዚህ አንፃር የጀመራቸው ሥራዎች አሉ? ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በኩል ሌሎችም ኩባንያዎች ከእናንተ ተሞክሮ ሊወሰዱ ይችላሉና ከድርጅቱ ትርፍ ምን ያህል ለፋውንዴሽን ትመድባላችሁ? ወይስ መደበኛ አሠራር አትከተሉም? ድጋፍ የምታደርጉት የትኞቹ አካባቢዎች ነው?

አቶ በላይነህ፡- እንግዲህ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በተመለከተ በድርጅታችን አሁን በመርህ ደረጃ በያዝነው ከማኅበረሰቡ ጋር በጤናና በትምህርት፣ ለአገር ቁልፍ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህም አንፃር ትልቁ ቁልፍ የዚህ አገር ፕሮጀክት የዓባይ ግድብ ነው፡፡ የዓባይ ግድብ ሲነሳ መጀመርያ ድጋፍ ካደረጉ ባለሀብቶች አንዱ ነኝ፡፡ እንዲያውም አቅማችን በሚፈቅደው ማለት ይቻላል መጀመርያ 25 ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛት፣ ጓደኞቼንም እያስተባበርኩ ሠርተናል፡፡ ሌላው እንግዲህ በትምህርት ዘርፍ ስናየው ትምህርት ቤት ሠርተናል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ሠርተናል፡፡ ተማሪዎችን በትንሹም ቢሆን ደግፈናል፡፡ ብዙ ሠርተናል ማለት አይቻልም ገና ነን፡፡ እንደምታውቀው ድርጅታችን እነዚህን ፕሮጀክቶች አስፋፍቶ ይዟል፡፡ ፕሮጀክቶቹም አፋቸውን ከፍተው የሚጠብቁት ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ደግሞ ኢኮኖሚው ተዳክሞ የማትረፉ ሁኔታ በቀዘቀዘበት፣ የባንክ ወለድ ሰማይ በወጣበት ሁኔታ ኢንቨስትመንቶችን ማካሄድ ፈተና ሆኗል፡፡ ግን ባለችን ውስን ሀብት  ትምህርት ቤቶችን ሠርተናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ለተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም አሥር ሚሊዮን ብር ቃል ገብተን በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ብር እየከፈልን ነው፡፡ ጎበዝ ተማሪዎችን እንሸልማለን፡፡ ገቢ የሌላቸውን ሴት ተማሪዎችን እንደግፋለን፡፡ እናትና አባት የሌላቸው እንዲቋቋሙ የመንጃ ፈቃድ ማውጪያ ገንዘብ እንሰጣለን፡፡ በጤና ዘርፍ ብዙ ባንሄድም ክልሎች ሲሠሩ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ አምቡላንሶችን ገዝተን ሰጥተናል፡፡ ለተፈናቃዮች ደግፈናል፡፡ ለጣና እምቦጭ አረም ማስወገጃ በተቻለ መጠን ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ በስፖርት በኩል የአትሌቲክስ ቡድን አለን፡፡ በዓመት አንድ ሚሊዮን ብር እናወጣለን፡፡ ጥሩ ጥሩ አገር የሚያስጠሩ ልጆች እየወጡበት ነው፡፡ እየሞከርን ነው፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደግዴታ የወሰድነውና እየሠራንበት ያለ ጉዳይ ነው


ይህንን ሥራ በፋውንዴሽን ደረጃ የምናካሂደው ይሆናል፡፡ ግን ማኅበራዊ ኃላፊነት ገና ነው፡፡ ምክንያቱም ድርጅቱ ገና እየተመሠረተ ያለ ነው ማለት ይቻላል፣ ብዙ ፕሮጀክቶች አሉት፡፡ እነዚህን ፋይናንስ አድርጎ ከሠራ የሚመጣው ገቢ ሌላ አይደለም ዓላማው፣ ከኅብረተሰቡ ጋር ተካፍሎ መብላት ነው፡፡ ባይሆን ኖሮማ በዚህ ሁሉ ስቃይ ብዙ ኢንቨስትመንት ማለት ብዙ ስቃይ ማለት ነውና ከዚህ አንፃር እንዲታይ እፈልጋለሁ፡፡

Source – Reporter Amharic