አማርኛ ተናጋሪው በኦሮሞ ክልል ኢንቨስት እንዳያደርግ ይፈለግ ይሆን ? #ግርማ_ካሳ

አፋን ኦሮሞ ከላቲን ፊደል ጋር በታሪክ፣ በባህልም፣ በምንም ግንኙነት የለውም። ቁቤ የሚባለው ላቲን የመጣው በቅርቡ ነው። አንድ ጀርመናዊ ሚሲዮናዊ፣ “ጥቁሮች ባሪያና አናሳዎች ናቸው፣ የነርሱ ስልጣኔ ከነጭ ስልጣኔ ጋር የሚወዳደር አይደለም” በሚል፣ የአስተሳሰብ ድሃ የሆኑና በራሳቸው የማይተማመኑ የፈረንጅ ጥቁሮች አታለለ። እነርሱም የሰለጠኑ መስሏቸው፣ ላቲንን ለአፋን ኦሮሞ መጠቀም ጀመሩ። ወያኔ በሰጣቸው አጋጣሚም ላቲንን በአገር ቤት ያለ ሕዝቡ ፍላጎት ጥቅም ላይ እንዲውል አደረጉ።

ከዚህ በታች ያለው ፣ በኦሮሞ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተዘጋጀ በኦሮሞ ክልል ኢንቨርስተሮች ኢንቨስት ማድረግ ከፈለጉ ተግባራዊ የሚሆን የመሬት ሊዝ ስምምነት ሰነድ የተወሰደ ነው። ከዚህ የተወሰኑ ነጥቦችን ቀስመን ማውጣት እንችላለን፡

አንደኛ – ሰነዱ የተጻፈው ሙሉ ለሙሉ በላቲን ፊደል ነው። ግማሹ በእንግሊዘኛ ስለሆነ መጻፍ ያለበት በላቲን ነው። ግማሹ ግን ኦሮምኛ ነው። ምንም ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚሸት ነገር የለውም። መቶ በመቶ ላቲን።

ሁለተኛ – በእንግሊዘኛና በላቲን/ቁቤ መጻፉ ፣ የኦሮሞ ክልል፣ ምን አልባት ከዉጭ አገር ዜጎችና ኦሮምኛ በላቲን ከሚያነቡ ወገኖች ውጭ፣ ሌሎች አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያን ወደ ክልሉ እንዲመጡ፣ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፍላጎት እንደሌለውም አመላካች ሊሆን ይችላል።

ከ75% በላይ የአዳማ ህዝብ አፋን ኦሮሞ አይናገርም። አዲስ አበባን ጨምሮ 45% የሸዋ ህዝብ አፋን ኦሮሞ አይናገርም። 20 በመቶ የአርሲ ዞን ሕዝብ አማርኛ ተናጋሪ ነው። ግን የኦሮሞ ክልል መንግስት አማርኛን እንደ ክልሉ መንግስት ቋንቋ አድርጎ የመጠቀም፣ ከአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ውጭ ያለው ማህበረሰብ ጥቅምና አገልግሎት እንዲያገኝ የማድረግ ፍላጎት ያለው አየመስልም። ምንም አይነት መረጃ በአማርኛ በክልሉ ላሉ ሌሎች ማህበረሰባት አያስተላልፍም። አቶ ለማ መገርሳ ጨምሮ የኦሮሞ ክልል መንግስት ባለስልጣናት በክልሉ ያሉ ሌሎች ማህበረሰባት ሰብስበው በሚናገሩት ቁንቋ፣ በአማርኛ ያናገሩበት ሁኔታ የለም።

የክልሉ መንግስት ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉትን፣ ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ አምጥቶ ሲያሰፍር፣ ለነርሱ ትልቅ እንክብካቤ ሲያደርግ፣ ማድረግም ነበረበት፣ በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ሌሎች ሲፈናቀሉና ሲጎዱ ግን ዝም ማለትና ነገሩን ማድበስበስ፣ ነው የሚመርጡት። እንደዉም የክልል መንግስት ታችኛዎቹ አመራሮች፣ ራሳቸው ሆን ብለው የዘር ማጽዳቱን ወንጀል የሚያቀነባብሩት እንደሆነ ነው የሚነገረው።

በፌዴራል ደረጃ አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ ጋር የሥራ ቋንቋ ይሁን ይላሉ። እነርሱ በፌዴራል አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ግፊት በሚያደረጉበት መጠን አማርኛም በአፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን መፈለግ ነበረባቸው። ግን ያ አልሆነም። ለነርሱ እንዲሆን የፈለጉት ለሌላው ሲሆን እምቢ ማለት ወገንተኝነት ብቻ ሳይሆን የለየለት ዘረኝነት ነው።

እንደዉም አንዳንዴ ሳስበው፣ አማርኛን የሥራ ቋንቋ ከሚያደርጉ፣ አረብኛን ወይንም ቻይንኛ ጨምሩ ብትሏቸው እሺ የሚሉ ነው የሚመስለኝ። ለምን እንደሆነ አላውቅም አማርኛን መናገር ኦሮምኛኝ ማሳነስ ነው የሚመስላቸው።

አንድ ጊዜ ቺካጎ ከአንድ የነጆ ልጅ ጋር እናወራለን። አንድ ሌላ የወለጋ ልጅ ተቀላቀለን። እኔን በአማርኛ ያዋሩኛል። እነርሱ ግን በኦሮምኛ ነበር የሚናገሩት። እኔን እዚያ አስቀምጠው። በጣም ጥሩ ሰዎች ናቸው። ግን እርስ በርስ ከኦሮምኛ ውጭ ከተናገሩ ኦሮምኛን ማሳነስ ስለሚመስላቸው፣ እኔ መሃላቸው ሆኜም እንኳን ለኔ ሲሉ፣ አማርኛ እየቻሉ፣ በአማርኛ መናገር አልፈለጉም። እነዚህ ሰዎች እኔ ጋር ችግር የላቸውም። አማርኛም ላይ ችግር የላቸውም። ግን ኦሮምኛን የማንነት መለኪያ ስላደረጉት፣ እርስ በርስ ኦሮምኛን ካልተናገሩ ማንነታችን ያሉትን ያሳነሱ ነው የሚመስላቸው። ይህ አይነቱ የተሳሳተ፣ መስመር የሳተ አመለካከት በፖሊሲ ደረጀ በኦሮሞ ክልል ስር ሰዶ ገብቷል። ለዚህ ነው የኛ ክልል ነው በሚሉት በኦሮሞ ክልል አማርኛን ከኦሮምኛ ጋር የክልሉ የስራ ቋንቋ ማድረግ የማይፈለጉት። አማርኛ የስራ ቋንቋ ከሆነ ማንነታቸው የተደፈረ ይመስላቸዋል። አይ ደካማነት !!!!!

በነገራችን ላይ ይህ ፖሊሲ ከማንም በላይ የጎዳው የኦሮሞ ማህበረሰብን ራሱ ነው። ብዙ አማርኛ ተናጋሪ የግል ባለሃብቶች እንደነ ጂማ፣ መቱ፣ ነቀምቴ ያሉትን ጥለው ሂደዋል። ለመዝናናት፣ ለንግድ፣ ለኢንቨርስትመንት ፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከሸዋ ውጭ ወዳሉ የኦሮሞ ክልል ከተሞች የሚሄድ የለም። በነዚህ የኦሮሞ ክልል ከተሞች ምግብ ቤቶች፣ ሆቴል ቤቶች.. ወና እየሆኑ ነው። ከተሞቹም ወዳድቀዋል። በአንጻሩ ሂዱ ባህር ዳር፤ ሂዱ አዋሳ ..እስቲ በአዲስ አበባአ ዙሪያ ወዳሉ ወደነ አዳማ፣ ቢሾፍቱ ተመልከቱ …እያደጉ ነው። ቡራዮ ለአምቦ፣ ሰበታ ከወሊሶ በልጠዋል።፡ ያን ምን ትሉታላችሁ ?

እንግዲህ አሁንም ከጠባብነትና ከዘረኝነት ተላቀው ብልጥ፣ አዋቂ ይሆኑ ዘንድ እመክራለሁ። የክልሉን ነዋሪ ህዝብ የኢኮኖሚ እድገት ማሻሻል ከፈለጉ፣ ኢንቨርስተሮችን መሳብ ከፈለጉ፣ሰው ለንግድ፣ ለመዝናናት አዋሳና ባህር ዳር እንደሚሄደው ጎሬና አሰላም እንዲሄድ ከፈለጉ ፖለቲካቸውም መቀየር አለበት።