በመንጋ ማጨብጨብ እርግማን ነው። ለማጨብጨብ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል

አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ ። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ ። ለማጨብጨብ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል። ስሜታዊነትና ምክንያታዊነት ሲደበላለቁ ደግሞ አደጋው የከፋ ነው። በስኬት የሚጓዘው የዲያስፖራው ፖለቲካ በክምር ወሬ ተከፋፍሎ ለክሽፈት እንዳይዳረግ ከፍተኛ ስጋትን አጭሯል። መንገኝነት እርግማን ነው። ነገ ላይ ሆነን ዛሬን መመለስ የማንችልበት ጸጸት ውስጥ ከመግባት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ሊተገበሩ የሚገቡ ጉዳዮችን ማጤንና ወደ ተግባር እንዲለወጡ መታገል ዋናና አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

  1. በፖለቲካ ጥላቻ የታወረው ኢሕአዴግ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በወሕኒ እየማቀቁ ነው። እነዚህ የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች ተፈትተው ወሕኒው ነጻ መውጣት አለበት።
  2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እኩል ስልጣን አለው። ይገላል ያፈናቅላል ፣ ያስራል ፣ ያንገላታል ወዘተ ፤ የስርዓቱ ቁንጮ የደህንነትና የጦር ባለስልጣናት የሚመሩት ኮማንድ ፖስት ከሕግ በላይ ሆኖ በሕዝቦች ላይ መንግስታዊ ሽብር ይፈጽማል። ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶ ኮማንድ ፖስቱ መበተን አለበት።
  3. ሌላው በዋናነት የሚያስፈልገው ዐለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ኮንቬክሽንን ኢትዮጵያ እንደመፈረሟ ሁሉ የሰብዓዊ መብቶች ሊከበሩ ፣ የዜጎች በገዛ አገራቸው ተዘዋውረው የመኖር የመስራት መብታቸው እንዲረጋገጥ ፣ የመደራጀት የመሰብሰብና ዜጎች ከመንግስታዊ ሽብር ስጋት ተላቀው በነጻነት እንዲኖሩ ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ስርዓቱን የመቃወም መብቶች እንዲፈቀዱ ፣ በግልና በቡድን አመለካከቶች ላይ መንግስታዊ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር መደረግ አለበት።

ነገ ላይ ቆመን በቁጭትና በጸጸት ዛሬን ከምንረግም ፤ በተግባር ሊተረጎሙና ልናያቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ጠንክረን ብንሰራ ተመራጭ ነው። በመንጋ ማጨብጨብ እርግማን ነው።