ከቢሻንጉል ጉምዝ ከተፈናቀሉ ህፃናት መካከል አንዷ ናት – የሺሀሳብ አበራ

የሺሃሳብ አበራ | የአማራ ክልል የመገናኛ ብዙሃን ባልደረባ
 
በአፍሪካ ረጅሙን የነፃነት ጦርነት ለ 30 ዓመታት ያህል ያካሄዱት ኤርትራዎች ከ1983 እስከ 1991 ቅኝ ገዥ ከሚሏት ኢትዮጲያ በሰላም ኑረዋል፡፡በኤርትራ ትግል ውስጥ ኢትዮጲያ ቅኝ ገዥ ናት፡፡ ሻዕቢያ 1983 ትህነግን (tplf) አግዞ የምኒሊክ ቤተመንግስትን ከተቆጣጠረ በኃላ በርካታ ተቋማትን በቁጥጥሩ ስር አውሎ ቅኝ ገዥ የሚላትን ኢትዮጲያ መርቷል፡፡ለአብነት የፕሮፊሰር አስራዓት የዳኘው የኤርትራ ባለስልጣን ነበር፡፡

ቅኝ ገዥዋ ኢትዮጲያ ኤርትራዎችን እስከ 1991 ድረስ አላፈናቀለችም፡፡፡ሚያዚያ 25 ቀን 1985 ኤርትራ የራሷን ሃገርነት ብታውጅም፣ዜጎቿን ኢትዮጲያ አላፈናቀለችም፡፡እንዳውም የኤርትራ ዜጎች የኢትዮጵያ ቡና ወደ አስመራ እያጋዙ ኤርትራ የዓለም 13 ኛዋ ቡና ላኪ ሃገር ነበረች፡፡የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መነሻ የኢኮኖሚ እንጂ የድንበር አልነበረም፡፡

በተቃራኒው ኢትዮጲያ ደሜ ናት የሚለው አማራው ከ 1983 ጀምሮ መጤ እየተባለ በግፍ መፈናቀል ጀመረ፡፡ከ 1983 ወዲህ ኢትዮጲያ ከአማራው ይልቅ ኤርትራን ታከብራለች፡፡ስለምታከብርም ሰኔ 30 ቀን 1983 ዓም አማራው በያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ መሪነት ኢሳያስ አፈወርቂን እና አስመራን ይቅርታ ጠይቋል፡፡በወቅቱ በትህነግ የፖለቲካ ትርክት ደርግ የአማራ ሰራዊት ይመስል ነበር፡፡በግልፅ ማንፊስቶውም የትህነግ ዓላማ አማራን ማሸነፍ ነው፡፡ከዶክተር አረጋዊ በርሄ እስከ ገብረመድህን አርአያ ይሄን ሃቅ በይፋ ተናዘዋል፡፡የትህነግ መስራች ዶክተር አረጋዊ ኢህአፓን ከኛ ግዛት ያባረርነው አማራ ስለሚመስለን ነው ብለዋል፡፡በኦነግ እና በሻዕቢያ በኩል አማራ ጭራቅ ሆኖ ተስሏል፡፡ለ 60 ዓመታት የአማራ ጥላቻ ተሰበከ፡፡

የስብከቱ ውጤትም መፈናቀል፣መሞት ሆነ፡ 

የቤተክርስቲያን ሰዎች እንኳን በ2004 ዓም አማራው ከጉራ ፈርዳ ሲፈናቀል ከቅድስት ስላሴ ካቴዴራል አላስጠጋም አሉ፡፡ዓለም አሸናፊ ያልሆነውን ትጠየፋለች፡፡ከ 1984 እስከ 1994 ዓም አካባቢ መአህድ ከ 1994 እስከ 2007 ዓም ድረስ ደግሞ መኢአድ በብቸኝነት ስለ አማራው መግለጫ ያወጣል፡፡በ 2004 ዓም ከቤንች ማጅ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ስለተፈናቀሉት አማራዎች አፈር ይቅለላቸው ና የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር” የተፈናቀሉት ደን አውዳሚዎች ናቸው፡፡፡ደግሞ የአማራ ተወላጆች ናቸው ተፈናቀሉ የሚባለው ውሸት ነው፡፡ የተፈናቀሉት የምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶአደሮች ናቸው” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ጠቅላዮ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት አማራው ዝቅ ሲል በዞናዊ እሳቤ ከፍ ሲል በኢትዮጵያዊነት የታሰረ ጀሌ በመሆኑ በአማራነቱ አይቆጭም ብለው ይመስለኛል፡፡ አማራው ለወቀሳ ጊዜ ተስፋፊ፣ ሞፈር ዘመት፣ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ ሆኖ ስሙ ጠቁሮ ይነሳል፡፡ በደህናው ቀን የኢትዮጵያ ታሪክ ሲወሳ “አማራ የለም” የሚል ክህደት ይመጣል፡፡ፕሮፊሰር አስራት ” አማራው የለም ብትሉም ስትገሉን ታገኙናላችሁ” ያሉት ለዚህ ክህደት ነበር፡፡

አለም ያሸናፊዎች ብቻ ናት፡፡እንደዚህ በሆነች ዓለም ውስጥ በመሸነፍ ፍትህን እና እኩልነትን መጠበቅ አይቻለም፡፡እንኳን ዲሞክራሲ የሃይማኖት ተቋማትም ለአሸናፊው የመስገድ ግዴታ አለባቸው፡፡ፍትህ የሚመጣው በማሸነፍ አሊያም አቻ በመሆን ብቻ ነው፡፡

ከ 1966 ጀምሮ ባለው ፖለቲካ በብዛት አማራ የለበትም፡፡ የሊሂቃን መምከን አጋጥሞታል፡፡ የነቁ ሊሂቃን ቀድመው እንዳይኖሩ ስለተደረገ፣አማራው በታሪኩ ልክ መቆም ተስኖታል፡፡

ከጉያው ያሉ ሊሂቃን( የፖለቲካ ሰዎች) ተሸናፊ እና ተንበርካኪ፣ሆድ አደር፣ከመብላት በላይ ዓለማየሌላቸው፣ያሸነፈው ሁሉ የሚልካቸው ጀሌ ሆነዋል፡፡ አማራው የራሱ ልጆች ማንዋል አዘጋጅተው እንዲንበረከክ ሰብከዋል፡፡አንገቱን እንዲደፋ በዳይ ሆኖ ኤርትራን ይቅርታ እንዲጠይቅ ተደርጓል፡፡

ዳሩ እስካሁን በአማራው የደረሰው ችግር ከአቅሙ በላይ አይደለም፡፡በአንድ ጀምበር እስካሁን የደረሰበትን ችግር እንዲያስወግድ ልምዱ እና ሃብቱ በቂው ነው፡፡፡ብቸኛ መፍትሄውም የአማራ ብሄርተኝነት ነው፡፡ያልተደራጀ ህዝብ ይጠፋል፡፡ዮጎዝላቪያ ከዓለም ካርታ የጠፋችው በዮጎዝላቪያነት ፖለቲካዋን ስላልሰራች ነው፡፡የሞሶፖታሚያ ስልጣኔ ባለቤት ተጋሪ የሆነው የኩርድ ህዝብ ተቅበዝባዥ እና ሃገር የለሽ የሆነው ባለመደራጀቱ ነው፡፡አይሁዳውያን በሂትለር የተገደሉት በፖለቲካ ተደራጅተው ራሳቸውን ማቆም ስላልቻሉ ነው፡፡ለአማራውም መፍትሄው በራሱ ላይ ቁሞ መገኘት ብቻ ነው፡፡ለአዲስ ችግር አሮጌ መፍትሄ ለመስጠት ኢትዮጵያ ኢትዮጲያ ብሎ መዘመር ብቻ 60 ዓመት ተሞክሮ አዋጭ አይደለም፡፡ኢትዮጲያ የ 80 ብሄር ና ህዝብ ፌዴሬሽን እንጂ ለአማራው ብቻ በሃላፊነት የተሰጠች ሃገር አይደለችም፡፡ ለአማራው አክሲዮን የሌለበት ሃብቱ አማራነቱ ብቻ ነው፡፡

ከቢሻንጉል የተፈናቀሉት አማራዎች ዛሬም ባህርዳር አሉ፡፡ ሂዶ መጠየቅ፣ ችግራቸውን መጋራት፣ የሞራል ግዴታ ይመስለኛል፡፡ ከንፈር መምጠጥ እና መቆዘም መፍትሄ አይደለም፡፡ ማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ለመፍትሄው ቅርብ መንገድ ነው፡፡