የህዝባችን መፈናቀል እና በግፍ መገደል አንገብጋቢነት – በፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ (ፕሮፌሰር)

የህዝባችን መፈናቀል እና በግፍ መገደል አንገብጋቢነት

በፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ (ፕሮፌሰር)

በሀረር ክፍለሀገር ቁጥራቸው ወደ ዐንድ ሚሊዎን የሚጠጋ ኦሮሞዎች እና በሺህ የሚቆጠሩ ሱማሌዎች፣ እንዲሁም በሞያሌ ሻኪሾ እና ጉጂ ክልል አያሌ ለፍቶ አዳሪ ኢትዮጵያውያን ከትውልድና መኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በርካታ ዜጎችም በግፍ ተገድለዋል። አብዲ ኢሌ የተባለ አምባገነን ጂጂጋ ላይ ከትሞ ሱማሌ ኢትዮጵያውያንን አየፈለጠና እየቆረጠ ያለልጓም ይፈነጫል። ህዝቡ ኡኡ! ቢልም የህዝቡን የስቃይ ድምፅ የሚሰማው አጥቶእል።

ፍዳው የበዛበት አማራም በቤንሻንጉል ጉሙዝ በአንድ ቀጭን የወረቅት ትዕዛዝ፣ ባለፉት 20 ዐመታት ላቡን አንጠፍጥፎ ካለማው መሬት እና ካፈራው ሀብት ተነቅሎ አንግልትና ሞት ደርሶበታል። የሚገባበት ስለአጣም በባህርዳር በአንድ ቤተክርትያን ውስጥ ተጠልሎ ተመፅዋች ሆኖአል። ከእነዚህ አማሮች መሀል አንድ አበጥር ወርቁ የተባለ የ 14 ዐመት ብላቴና ብልቱን ተሰልቦና ዐይኖቹ ተጎርጉረው ወጥተው በሞትና ሽረት ጣር ውስጥ ይገኛል። በጋምቤላም በአኝዋኮቼ ኢትዮጵያውያን ላይ እንደበፊቱ አሁንም ጡር እና እንግልት እየተፈፀመባቸው አብዛኛውን መሬታቸውን እንደተነጠቁ ይገኛሉ። ይባስ ይባስ ብሎ፣ ቁጥራቸው ወደ ግማሽ ሚሊዎን የሚደርስ የደቡብ ሱዳን ስደቶኞች የኢትዮጵያ ዜግነት ታድሏቸው በጋምቤላ የእኙዋክ መሬት ላይ ሊሰፍሩ ነው ይባላል። የእዚህም መሰሪ አላማው ለነፃነታቸው የሚታገሉትን እምቢተኞቹን አኝዋኮችን አስለቅቆ በእነሱ ፈንታ ለ መሬት ተቀራማቾቹ ታዝዥና አገልጋይ ለመሆን ዝግጁ በሚሆኑት የደቡብ ሱዳኖች ለመተካት ነው።

ወደ አማራው ስንመለስ፣ ባለፉት 40 ዐመታት አማራው የቁምስቅሉን ማየቱን ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው። ይህ ሁሉ ግፍና በደል አማራው ላይ የደረሰበት ለምንድነው ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ ሌሎች ጎሳዎች ያደረጉት ተጋድሎ አንደተጠበቀ ሆኖ፣ አማራው ከራሱ ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድሞ፣ ደሙን አፍሶ የኢትዮጵያን ነፃነት እና አንድነት በማስቀደሙ ነው። ይህ ታላቅ ድርጊቱ ሊያስሸልመው እና ሊያስመስግነው ሲገባ ነፃነቱን ባስጠበቀው እና ባቀናው ሃገር ላይ እንዳይኖር የሚፈፀምበት የማያቋርጥ ፍንቀላና ግድያ ከማስቆጨትና ከማስቆጣትም አልፎ ለሰሚው ግራ ነው።

ድፍን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን እስከሆነች ድረስ አማራውን ጨምሮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው ቦታ የመኖር መብት አለው። እንዲኖረውም ይገባል። ለምን እዚህ ቦታ ኖርክ በማለት ማንም ማንን ሊገድል፣ ሊያስገድል እና ሊያፈናቅል ስልጣን የለውም። ይህን እኩይ ተግባር የሚፈፅሙና የሚያስፈፅሙ፣ በህዝቦች መከፋፈልና መገዳደል የሚፋፉ ኃይሎች መታገድ እና መገታት ይገባቸዋል። አንዲህ ዐይነቶቹ ፍንቀላና ግድያ ከተገፉት እና ከተራዎቹ ዜጋዎች እንደማይጠነሰስ እና በእነሱም እንደማይፈፀም ሁሉም ዜጎች ተገንዘበው፣ በተለይም ኦሮሞውዎችና አማሮች ወንድማማች መሆናቸውን ተረድተው፣ አሁን በመፋቀርና በሚያስድስት መግባባት ላይ የአሉት እማሮችና ኦሮሞዎች ነቅተው እርስበርስ በጠላትነት ሳይፈራረጁ ተባብረው ራሳቸውን በጋራ መጠበቅ ይገባቸዋል። አውነተኛ ደመኛቸውን በትጋት ለይተው በእጅ-አዙር የሚያፋጇቸውን ከውስጣቸው መመንጠር አለባቸው። ለወደፊት ሊተገበሩ የተሴሩ ፍንቅላዎችና የእርስበርስ ግድያዎችም የእነዚህ መሰሪ ኃይሎች እቅዶች መሆናቸውን ህዝቡ ከወዲሁ ሊገነዘብና ድርጊቶቹ በሚክሰቱበትም ወቅት እራሱን ሊጠብቅ ግድ ይለዋል።

ትንሽ ህሊና ያላቸው ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለስልጣኖች፣ በየክልሉ የተሰናከሉትን እና የተፈናቀሉትን ዜጋዎች ሁሉ በአስቸኳይ ወደ ቀድሞ መሬታቸውና ንብረታቸው በመመለስ በአካላቸው እና በንብረታቸው ላይ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ ማሰጠት እለባቸው። ወንጀሉን የፈፀሙት እብሪተኞችም ለፍርድ ቀርብው መቀጣት ይገባቸዋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አቢይም ቢሆኑ የውጭውን ጉዞአቸውን ቀነስ አድርገው የኢትዮጵያ ህዝብ የውስጥ ስቃይ ላይ አተኩረው፣ አስቸኳይ አዋጁን ለማስቆም እንኳን አቅም ቢያጡ፣ የምስኪን ዜጎች የግፍ ፍንቀላና ግድያ ይገቱ ዘንድ ፈጣን መፍትሄ አንዲዘይዱ ይጠበቅባቸዋል። የግፍ ፍንቀላና ግድያ ሲፈፀሙም በእዛ በአማላይ ልሳናቸው ቅዋሜ ማሰማት የስልጣናቸው ግዴታ ነው። ዝምታቸው ግድየለሽ እንዳያስመስላቸውም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።