ከመተከል (ቤኒሻንጉል) የተፈናቀሉት አማሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ ።

ከመተከል (ቤኒሻንጉል) ተፈናቅለው ለ1 ወር ከሳምንት በባህር ዳር ከተማ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙት ወገኖች ሁለት አማራጭ ቀርቦላቸው ሁለቱንም አልተቀበሉትም። እነሱ ያቀረቡት አማራጭ ደግሞ በመንግስት ተቀባይነት አላገኘም።

የመንግስት አካላት ተፈናቃዮች ወደነበሩበት አካባቢ እንዲመለሱ፣ አልያ ግን ቤተሰቦቻቸው ይኖሩበታል ወደሚባል ቀበሌና ወረዳ እንዲበተኑ ውሳኔውን ነግሯቸዋል። ሆኖም ተፈናቃይ ወገኖች ወደነበሩበት ቦታ ለመመለስ የደህንነት ዋስትና እንደሌላቸው በመግለፅ አልተቀበሉትም።

በሁለተኛነት የቀረበላቸው “አማራጭ” ደግሞ ወደ “ቀደምት” የቤተሰቦቻቸው ቀዬ እንዲበተኑ የሚለው ነው። ተፈናቃዮቹ ሀብት ንብረት ያፈሩበት፣ ወልደው ከብደው የኖሩበት አካባቢ አሁን የተፈናቀሉበት እንደሆነ በመግለፅ ሌላ የሚሄዱበት ቀዬ እንደሌላቸው ገልፀው አማራጩን አልተቀበሉትም።

በሌላ በኩል ግን ተፈናቃዮቹ ለእርሻና መኖሪያ በሚመች ቦታ የአማራ ክልል መንግስት እንዲያሰፍራቸው መጠየቃቸውን በማስታወስ፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ገልፀውልኛል።

ተፈናቃዮቹ አሁን በሚገኙበት ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ የአማራ ህዝብ ድጋፍ ሳይለያቸው ለጊዜው ውሉ ያልታወቀ ጊዜ እያሳለፉ መሆናቸውን ይናገራሉ። “ህዝብ እየደገፈን ነው። ሆኖም ዘላቂ መፍትሄ ተሰጥቶን ሰርተን የምንኖርበትን ጊዜ እንናፍቃለን” ብለውኛል።

ተፈናቃይ ወገኖች የት ይሂዱ??