ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መፈፀም የሌለባቸው ስህተቶች

ዓለም ከኮምፒውተር ጋር ከተዋወቀ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም የብዙዎች የኢንተርኔት አጠቃቀም መስመርን የሳተ ነው።

ከመረጃ ደህንነት ጋር የተያያዙ የትየለሌ እሮሮዎች በተደጋጋሚ የሚሰሙትም ከአጠቃቀም ስህተቶች ጋር በተያያዘ ነው።

የኢንተርኔት አጠቃቀም ስህተት ለአካላዊ ወይም አእምሯዊ ጉዳት እንደሚያጋልጥ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

በስፔን የሚገኘው የበይነ-መረብ ደህንነት ተቋም ኢንተርኔት ሰክዩሪቲ ኦፊስ (ኢኤስኦ) በተደጋጋሚ የሚሰሩ ስህተቶችን ይፋ አድርጓል። ከኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች ራሳችሁን ለመታደግ ስህተቶቹን ከመፈጸም ተቆጠቡም ብሏል።

VIDEO

የማይታወቁ ማስፈንጠሪያዎች

የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች ሰዎችን ከሚያጠምዱባቸው መንገዶች አንዱ የተሳሳቱ ማስፈንጠሪያዎች መላክ ነው። ሰዎችን በቀላሉ ማማለል የሚችሉ ‘የዋጋ ቅናሽ’ ወይም ‘በነጻ የሚታደሉ ምርቶች’ ማስታወቂያ ይጠቀሳሉ።

ማስፈንጠሪያዎቹ ቫይረስ ወደተሸከሙ ገጾች ስለሚወስዱ የተጠቃሚዎችን የመረጃ ደህንነት አደጋ ውስጥ ይጥላሉ። ኢኤስኦ “ማስፈንጠሪያዎች ከመከተልዎ በፊት ቆም ብለው ያስቡ” ይላል።

ያረጁ ሶፍትዌሮች

በስልክ ወይም በኮምፒውተር የሚጫኑ ሶፍትዌሮች በየግዜው መታደስ አለባቸው። ሳይታደሱ ከቆዩ የኮምፒውተር ወንጀለኞች በየግዜው ለሚሰሯቸው አደገኛ ቫይረሶች ያጋልጣሉ።

አጠራጣሪ መተግበሪያዎች

መተግበሪያዎችን (አፕ) ከተለያዩ ድረ ገጾች መጫን ለደህንነት አስጊ ነወ። ትክክለኛ የሚመስሉ ነገር ግን ለቫይረስ የሚያጋልጡ መተግበሪያዎች ብዙ ናቸው። ብዙዎችም ያለማወቅ ይጭኗቸዋል።

ቀላል የይለፍ ቃል

የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ለመስረቅ የይለፍ ቃላቸውን ይሰብራሉ። ስለዚህም ኢኤስኦ “ጠንካራ የይለፍ ቃል ይኑራችሁ” ይላል። ምክንያቱም በቀላሉ የሚገመቱ የይለፍ ቃሎች በርካቶችን ለአደጋ አጋልጠዋል።

የመረጃ ቅጂ አለማስቀመጥ

በኮምፒውተር ወይም በስልክ ላይ ያሚገኙ መረጃዎችን ቅጂ አለማስቀመጥ ሌላው ችግር ነው። የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች የግል መረጃ ካገኙ ለባለቤቱ ለመመለስ ገንዘብ ይጠይቃሉ። ተጠቃሚዎች የመረጃቸው ቅጂ ካላቸው ግን ከመዝባሪዎች ጋር መደራደር አያስፈልጋቸውም።