ሰብዓዊ መብቶችና ያገራችን ሁኔታ (ባይሳ  ዋቅ-ወያ)

በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ስለ ሰብዓዊ መብቶች የመከበር አስፈላጊነት በግልጽ መወራትና መጻፍ የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ይሁን እንጂ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ጭቆናን የማይቀበል ግን ደግሞ በአቅም ማነስ ብቻ ለጉልበታሙ ይገዛ ነበር እንጂ፣ እንደ ሰው ማንም ከማን እንደማይበልጥና በተፈጥሮም ከአካልና የአዕምሮ ብስለት መበላለጥ ሌላ፣ ሰው በሰውነቱ እኩል እንደሆነ ሁሉም ያምናል። ለምሳሌ በተለምዶ የሴት ልጅ እንደ ወንዶች ቀስትና ደጋን ይዛ ወጥታና አድና ቤተሰቡን መመገብ አትችልም ተብሎ በወንዶች ስለተወሰነባቸውና ውሎአቸው ቤት ውስጥ መዋል፣ ልጆችን መንከባከብና ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰል ስለሆነ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚደረገው ማንኛውም ውይይትና ውሳኔ ተገልለው ኖረዋል። ይህ ሰው ሰራሽ የሆነ የሥራ ክፍፍል፣ በመብት ደረጃ ወንዶችን የበላይ አድርጎ ያስቀመጠና ለዘመናት በሥራ ላይ የዋለ ስለሆነ፣ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ መብት ቢኖራቸው “ተፈጥሮያዊ” ነው ብለን እስከማመን አድርሶን ነበር። ከሴቶች የነጻነት ትግል በኋላ ግን፣ ዛሬ በብዙ አገራት ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ የመሪነትን ቦታ ወስደው ከወንዶች በበለጠ እንጂ ባላነሰ መልኩ ተልዕኮያቸውን እየፈጸሙ መገኘታቸው፣  ለዘመናት  ሰፍኖ  የነበረው  የሴቶችን የበታችነት ያራመደው አስተሳሰብ፣ ለመጨቆን ሆን ተብሎ በወንዶች የተጠነሰሰ እንጂ ተፈጥሮ ወንድንም ሴትንም እንደማያበላልጥና ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ሰብዓዊ መብት እንደሌላቸው አስመስክሯል።

ሰብዓዊ መብቶችና ተከታታይ መንግሥቶቻችን

ባገራችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረው የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ከላይ የሴቶችን መብት አስመልክቼ ለአብነት እንዳስቀመጥኩት፣ ሰው ሰራሽ መሆኑ ቀርቶ ተፈጥሮያዊ ነው ብለን እንድንቀበልና መብታችንም ሲጣስ እንዳናጉረምርም በህግና በልምድ ተጠፍረን ገዢዎቻችን መብታችንን ሲረግጡ አሜን ብለን እንድንኖር ተገድደን ነበር። ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ካባታቸው ከራስ መኮንንና ከናታቸው ወይዘሮ የሺ ዓሊ በጋራ ሙለታ መወለዳቸውንና፣ ዓፄ ምኒልክ አልጋ ወራሼ ብለው የሾሙትን ልጅ ኢያሱን፣ በሸዋ መኳንንት ብርታት አግልለውት መንገሳቸውን እያወቅን፣ ቤተ ክርስቲያን እንኳ ተደምራ “የይሁዳ አንበሳ” “ሥዩመ እግዚአብሔር” ናቸው ብለን እንድናምን ተደረገ። እግዚአብሔር የሾመውን ደግሞ መብቴን ጥሰሃል ብሎ መክሰስ ይቅርና ማሰብም ራሱ ኃጢአት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ህዝቡ ሰብዓዊ መብቶቹ እንኳ ሲጣሱ “እግዜርን ላለማስቀየም” ብሎ ሰጥ ለጥ ብሎ ተገዛ። ህገ መንግሥት ሲደነገግም ንጉሥ በእግዚአብሄር ስለተሾመ ከህጎች ሁሉ በላይ የሆነና የማይከሰስ በመሆኑ የደንቦቹ ተፈጻሚነት በሰፊው ህዝብ ላይ ብቻ መሆኑን አስተማሩን። ይህን ለዘመናት የተንሰራፋና “የበላዮች” በጉልበት የጫኑብን ሚዛኑ የተዛባና የሰው ልጆችን ተፈጥሮያዊ እኩልነትን የማይቀበለው አሰራር ነው እንግዲህ ተዋህዶን፣ ዛሬም ድረስ ትላልቅ ባለሥልጣናት ፊት ይቅርና የመንግሥት ግብር እንኳ ለመክፈል ተራ ግምጃ ቤት ኃላፊ ፊት ስንቀርብ፣ ነጠላችንን አገልድመን፣ እጃችንን ወደ ኋላ አድርገንና ራሳችንን ዝቅ አድርገን የተወሰነብንን ከፍለን፣ ግብሩንም ለመክፈል “ስለፈቀዱልን” አመስግነንና እጅ ነስተን ወደ ቤታችን የምንመለሰው።

ኢትዮጵያ የጥቁር አፍሪካ ብቸኛ መሥራች አባል የነበረችበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ ገና እንደተመሰረተ ያተኮረው በሰብዓዊ መብቶች መከበር ጉዳይ ላይ ነበር። ድርጅቱ በ 1948 ዓም የመጀመርያውን ዓለም ዓቀፋዊ የሰው ልጆች መብት “ዓዋጅ” (Universal Declaration of Human Rights) ሲያውጅና ከአስራ ስምንት ዓመታት የጦፈ ክርክር በኋላ ደግሞ ሰፋ ባለ መልኩ የሰው ልጆችን መብት ጥበቃን ያካተቱትን ሁለቱን ውሎች (Covenants) ሲያጸድቅ፣ መንግሥታት፣ በተለይም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሰው ልጆች ላይ ያደረሰውን ጥፋት በቅርብ ያዩትና ከሩቅም ሆነው የሰሙት፣ ከልባቸው የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች ካሁን በኋላ እንዳይጣሱ ታሪካዊ ግዴታችንን እናሟላለን ብለው ተስማሙ። እነዚህ የተመድ መግለጫዎችና ውሎች ከሞላ ጎደል ሁሉም መንግሥታት የተስማሙበትና የፈረሙት፣ የውሎቹንም ጽንሰ ሃሳቦች በየህገ መንግሥታቸው ውስጥ ያካተቱ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት መንግሥታት ግን አፈጻፀሙ ላይ ወገቤን እያሉ ነው። አገራችን አብዛኞቹን ዓለም ዓቀፋዊ ውሎችን የፈረመች ቢሆንም፣ እየተከሰተ ያለውን የጅምላ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስንመለከት፣ ባለሥልጣኖቻችን ዉሎችን መፈረሟንና ያለባቸውን የሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ግዴታ ቅንጣት ታህል ግንዛቤ ያላቸውም አይመስልም።

ሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጆች ብቻ ስለሆኑ መንግሥት የአገር ልዕልናን ለማስከበር ህጋዊ መብት እንጂ፣ ሰብአዊ መብት ብሎ ነገር የለውም። በምድራችን ላይ የሰው ልጆችን ሰብዓዊና ህጋዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ የማይጥስ መንግሥት አለ ለማለት አያስደፍርም፣ ሁሉም መንግሥታት መብት ይጥሳሉ ለማለት ይቻላል፥ ልዩነቱ ግን ዲሞክራቲክ መንግሥታት አውቀውም ሆነ

ሳያውቁ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን ሲጥሱ ወይም መብት ጣሾቹን ለፍርድ ካላቀረቡ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራርና ልምድ አላቸው። መብቶች ይጣሳሉ፣ መብታቸው የተጣሰባቸው ዜጎች ግን የተጣሰውን መብታቸውን መልሰው የሚያስከብሩበትና የጣሱባቸውንም ግለ ሰቦች የሚያርም ህጋዊ ደንብና ሥርዓት አለ ማለት ነው። መሰረታዊው በህዝብና በመንግሥት መካከል ያለው የማህበረሰቡ ውል (social contract) የሚያዝዘው፣ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ (action) ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ መብቶች በሌሎች ሲጣሱ የእርምት እርምጃ ባለመውሰዱም (omission) እኩል ተጠያቂ መሆኑን ነው። በሌላ አነጋገር፣ የመንግሥት ድርሻ፣ ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስከበርና ማዳበር ብቻ ነው።

ባገራችን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደ ኢህአዴግ ዘመን አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ አልነበረም፣ በንጉሱ ዘመን የፖሊቲካ ሥልጣን ሁሉ በሳቸውና ባካባቢያቸው በነበሩ ጥቂት ቡድኖች እጅ ቢሆንም፣ ህዝቡ የንጉሱን “ሥዩመ እግዚአብሄርነትንና” የተሾመው ሁሉ የመጨቆን መብት እንዳለው ሳይወድ በግድ “አምኖ” ስለተቀበለ፣ ፊደል ከቆጠሩና ካንዳንድ “ሽፍቶች” በስተቀር፣ መብቴን ተገፍፌያለሁ ብሎ የሚሞግት ተቃዋሚ ባለመኖሩ፣ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች እንደዛሬው የዜጎች የጅምላ ማሰቃያ ገሃነም አልነበሩም። ተቃውሞውን የሚመሩ ተማሪዎችም በፖሊስ ከተያዙ ወደ ሰንዳፋ አባ ዲና ፖሊስ ኮሌጅ ተወስደው ከበድ ያለ ስፖርት ያሰሯቸው እንደሁ እንጂ እንደ ዛሬ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከስሰው ረጅም ቅጣት አይፈረድባቸውም። በታሪካችን ውስጥ የሰውን ልጅ ማሰቃየት (torture) የጀመረው ደርግ ቢሆንም ኢህአዴግ ግን ደርግ እንደ ጀማሪ የተለማመደበትን ሙያ ወደ ኤክስፔርት ደረጃ አሻሽሎና በሰለጠነ መልኩ ሰፋ አድርጎ ዜጎችን ማሰቃየት ብቻ ሳይሆን “አሰቃይ” የሚል የሙያ ዘርፍ ፈጥሮ “አሰቃዮችን” በዚህ ሙያ አሰልጥኖና ማሰቃያ ማዕከልም ፈጥሮ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በሰፊው መጣስ የጀመረው።

የኢህአዴግ የዜጎችን መብት የመጣስ ብቻ ሳይሆን፣ ከጣሰም በኋላ ቅስምን የመስበር ባህል ከየት እንደመጣ በጣም ግራ የሚያጋባ ነው ።  አዎ!  ከልጅነታችን  ጀምሮ  ወላጆቻችን፣  ደብድቦና  አሽንፎ  መምጣት እንጂ ተደብድቦና ተሸንፎ መምጣት “አሳፋሪ” መሆኑን ቢያስተምሩንም፣ ቢያንስ ቢያንስ እኔ ያደግሁበትና ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የነበረው ባህላችን፣ በመጀመርያ ደረጃ መታገል ያለብህ በዓቅም ከሚስተካከልህ ጋር ብቻ ሲሆን፣ በለስ ቀንቶህ ታግለህ ተፎካካሪውን ከጣልከው ግን ደግፈህ ከወደቀበት አንስተህ አቅፈኸው ትንከባከበዋለህ እንጂ በወደቀበት ቦታ ላይ በምንም ተዓምር እጅህን አታሳርፍበትም። ይህ እንግዲህ ከልጅነታችን ጀምሮ በጭንቅላታችን እንዲሰረጽ ወላጆቻችን ያደርጉ የነበረው ካደግን በኋላ ከሰዎች ጋር ለሚኖረን ቅራኔ፣ ተቃራኒን ካሸነፍን በኋላ እንድናከብረው ያዘጋጁን ይመስለኛል። የኦሮምኛው ተረት “ጀግና ባላጋራ የክፉ ቀን አለኝታ ነው” የሚለውም ከዚሁ የመነጨ ይመስለኛል። ዛሬ ዛሬ ግን ነገሮች ሁሉ ተቀያይረው ተፎካካሪን ማሸነፍ ብቻ አልበቃ ብሎ፣ አስሮና አሰቃይቶ፣ አዋርዶና ቅስም ሰብሮ፣ “ከሰቆቃው ለመገላገል ከፈለግህ ደግሞ ያለ ዓቅሜ መንግሥትን ተዳፍሬያለሁ” ብለህ ይቅርታ ጠይቅና እፈታሃለሁ የሚል ጠላትን “የማሸነፍ” ብቻ ሳይሆን የመደምሰስ፣ ቅስም የመስበርና ዳግመኛ እንዳያንሰራራ የሚያደርግ አዲስ የጭካኔ ባህል ባገራችን ሰፈነ።

ያደጉ አገራትና እኛ፣

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ኢህአዴግ “ተቃዋሚ” የሚላቸውን ለማንበርከክ የተጠቀመው ዘዴ ህገ መንግሥቱን የሚቃረኑ ህጎችን በማውጣትና በጊዜው ፋሺን የነበረውን የጸረ ሽብር ዓዋጅን የምዕራብ አገሮችን ፈለግ ተከትሎ በማወጅ ነበር። መኮረጁ ባይከፋም ኢህአዴግ የተሳሳተው ግን በእንግሊዝና በሌሎችም የጸረ ሽብር አዋጅን ባወጁት ዲሞክራቲክ አገራት፣ ዓዋጁ ከመታወጁ በፊት፣ መሰረታዊ የሆኑት የሰውን ልጅ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ የሚከላከል ተቋም በህግ ተመስርተው ህዝቡን እያገለገሉ መሆናቸውን ነው። በሌላ አነጋገር፣ በነዚህ አገራት የጸረ ሽብር አዋጅ በመታወጁ የዜጎች የመናገርና የመጻፍ፣ የማሰብና የማመን፣ የመሰብሰብና የመወያየት መብቶች በምንም መልኩ አልተሸራረፉም ማለት ነው። መሰረታዊ ሃሳቡ፣ ተቃዋሚ መሆንና ሽብርተኛ መሆን የተለያዩ ናቸው፣ ተቃዋሚ መሆን ማለት የተለየ አስተሳሰብ ይዞ ላገሪቱ የሚበጅ ከገዢው ፓርቲ የተሻለ አስተሳሰብ አስተናግዳለሁ ማለት ነው እንጂ ያገሪቷን ህልውና አደጋ ውስጥ እከታለሁ ማለት አይደለም። የፖሊቲካ ሂደት ደግሞ ፎርሙላ ስለሌለው የኔ ሃሳብ ብቻ ትክክለኛ ነው ብሎ መሞገትና ይባስ ብሎም፣ አስተሳሰብህ ያገሪቷን ህልውና አደጋ ውስጥ ይከታል በማለት የአንድን ቡድን ወይም ግለሰብ መሰረታዊ የሆነ የማሰብን መብት መንፈግ ማለት ወንጀል ነው።

ሰብዓዊ መብቶች ማክበርን በተመለከተ እስካሁን ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው ህገ መንግሥቶች ሁሉ የኢፌድሪን ህገ መንግሥት የሚስተካከል  የለም።  በህገ  መንግሥቱ  ከተካተቱት  106   አንቀጾች  ውስጥ  32ቱ  የሰው ልጆችን ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን የሚደነግጉ ስለሆነ፣ ይህ ህገ መንግሥት ከሌላ ከማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር ህገ መንግሥት ጋር በእኩልነት ሊቀርብ የሚችል ህጋዊ ሰነድ ነው ማለት ይቻላል። አፈጻፀሙን ከዳሰስነው ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን መብት በመጣስ በምድራችን ላይ ከሚጠቀሱ መጥፎ አገሮች ተርታ በመጀመርያ ረድፍ ላይ የሚሰለፍ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? አንድ ድርጅት (ኢህአዴግ) ያን የመሰለ ውብ ህገ መንግሥት መንደፍ ከቻለ ለምንድነው ራሱ ያረቀቀውንና ያጸደቀውን ህገ መንግሥት በተለይም አከብራቸዋለሁ አስከብራቸዋለሁ ብሎ እየማለ የለፈፈውን የዜጎች መብትን ለማክበር የከበደው?  ያ ሁሉ አገሪቷ ያፈራቻቸው ምርጥ ልጆቿ የተዋጉለትና የሞቱለት የዜጎች ዲሞክራሲያዊና የሰው ልጆች መብት መከበር ጉዳይ እንዴት