ባህር ዳር የፖለቲካ አውድማ እየሆነች መጥታለች (ሚኪ አማራ)

በባለፉት 27 አመታት አዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማዕከል፣ መቀሌ ደግሞ የፖለቲካ ማዕከል ሁነዉ ቆይተዋል፡፡ አሁን ባለዉ የፖለቲካ ዳይናሚክስ ባህር ዳር ለሚቀጥሉት ዓመታቶች ከፍተኛ የፖለቲካ ትንቅንቅ የሚካሄድባት ከተማ ትሆናለች፡፡ ባጠቃላይ ኦሮሚያ አካባቢ የከራረመዉ ፖለቲካ በመቀዝቀዝ፣ ነገር ግን የአማራ ፖለቲካ ካለበትም በላይ እየጦዘ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሄን ያዉቃሉ፡፡ ለዚህም ነዉ የአማራ ጉዳይ የራስ ምታት የሆነባቸዉ፡፡ ባህር ዳር የፖለቲካ አውድማ ለመሆኗ የሚከተሉት ምክንያቶች አሉ፡፡

አንደኛ፣ ብአዴን እርስ በርሱ በሚያደርገዉ ፍትጊያ እዚህ ከተማ ላይ መከራረሙ አይቀርም፡፡ በዚህ አመት ብቻ አንኳን ከ10 ጊዜ በላይ ተሰባስበዋል፡፡ በየጊዜዉ በቡድን እየተከፈሉ በሚያደርጉት እሰጣ እገባ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለህወሃትም ራስ ምታት ሁኖታል፡፡ ህወሃት ብአዴን ዉስጥ ያለውን ጉልበት ቢያጣ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀዉስ ይገጥመዋል፡፡ ህወሃት ያን ያህል ጠንካራ ሁኖ አይደለም የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚዘዉረዉ፡፡ ነገር ግን ብአዴን ዉስጥ ባለዉ ስር የሰደደ ድርሻ እንጅ፡፡ ከዛም ባለፈ እራሱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ደርግን የጣለ ጦረኛ አድርጎ ስሏል፡፡ ደርግን ግን የጣለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ኢትዮጵያዊያን እራሱ የረሱት ይመስሉኛል፡፡ ስለ ረሱትም ሙሉ ለሙሉ ለትግራይ ህዝብና ለህወሃት ዉጤቱን አሸክመዉታል፡፡ ከዚህም በመነሳት ህወሃቶች ነገር ከረር ሲልባቸዉ “እኛ ደርግንም የጣልን ነን ማንም አይነካንም” ፉከራ ያሰማሉ፡፡ አቅማቸዉ ጭንቅላታቸዉ ላይ እንደሳሉት አለመሆኑን ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ ለፕሮፖጋንዳነት ግን እየተጠቀሙበት ነዉ፡፡

ሁለተኛ፣ አዲሱ የአማራ ፓርቲም መቀላቀሉ ባህር ዳርን ሌላኛዉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጡዘት የሚካሄድባት ከተማ ያደርጋታል፡፡ አዲሱ ፓርቲ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ይኖረዋል፡፡ ብዙዉ ወጣትና ሙሁር ይሄን ፓርቲ ይቀላቀላል፡፡ ይህ ፓርቲ ትልቁ ተግዳሮት ሊሆን የሚችለዉ ይህን የሰዉ ሃይል እንዴት ያስተናግደዋል የሚለዉ ነዉ፡፡ በአቅም ክፍተት፤ በልምድ እጥረት እና በተደራሽነት ጉዳዮች ይሄን ሁሉ ህዝብ ማስተናገድ ሊከብደዉ ችላል፡፡ በዚህ ዉስጥ ከብአዴን ጋር ፍትጊያዉ ይቀጥላል፡፡ ባህር ዳር በዚህ ፍትጊያ ዉስጥ ዘንባባዎቿ ሊሰባበሩ ይችላሉ፡፡ ብአዴን እስካሁን እንደምንሰማዉ በሁለት ጎራ የተከፈለ ነዉ፡፡ ህወሃትን የሚደግፍና የማይደግፍ ቡድን፡፡ በሚቀጥለዉ ደግሞ ይህ አዲሱ የአማራ ፓርቲ ፖለቲካዉን ሲቀላቀል እንዴት ባለ መንገድ እናስተናግዳቸዉ በሚል ሌላ ንትርክ ዉስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡

በሶስተኛ ደረጃ፣ ኦህዴድ አሁን ባለዉ አቅም ብቻዉን አገር ሊመራ አይችልም፡፡ ፖለቲካውንም፤ ሚሊታሪውን፤ ደህንነቱን እና መሰል አካባቢዎችን እንደ ህወሃት ተቆጣጥሮ ሊያስኬደዉ አይችልም፡፡ የልምድ ማነስ እና የአቅም እጥረት ያጋጥመዋል፡፡ ይህን የልምድ ማነስና የአቅም እጥረት ህወሃት ለመጠቀም ስለሚሞክር ኦህዴድ አጋር ያስፈልገዋል፡፡ አሁን አጋሬ ብሎ ብአዴንን ለይቶ ይዟል፡፡ ኦህዴድም ከብአዴን ወስዶ የሾማቸዉ ሰወች ህወሃትን የማይደግፉ ብሎ ገምግሞ ነው፡፡ ለምሳሌ እነ ዶ/ር አምባቸዉን ጃንጥራርንና ሌሎችንም ሲወስድ በዚህ ቀመር ነዉ፡፡ ባንጻሩ የህወሃት ደጋፊ ያላቸውን እን ጌታቸዉ አምባየን አንስቷል፡፡ አለምነዉን በየአመቱ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር የመለስ ራእይ የሚል የመወያያ ሃሳብ “ትምክህትና ጠባብነት የስራዓቱ አደጋዎች ናቸዉ” የሚል ነገር እየጻፈ እንዲያቀርብ የሆነ ቢሮ ዉስጥ ነዉ የገባዉ፡፡ ሰሞኑንም ይህን ጽፎ አቅርቧል፡፡ ስለዚህም ኦህዴድ እራሱ ወደ ባህር ዳር መመላለሱ አይቀርም፡፡ አንደኛ፣ ፖለቲካዊ ዉሳኔዎችን ለመወሰን። ሁለተኛ፣ በብአዴን ዉስጥ ችግር ሲፈጠር እንደ ሽማግሌ ሆኖ ለማስማማት፡፡

አራተኛ፣ ህወሃትም በተደጋጋሚ ከመቀሌ ወደ ባህር ዳር መመላለሱ አይቀርም፡፡ አንደኛ፣ ብአዴን ዉስጥ ያለዉን ሃይል እንዳያጣ ሽማግሌ በመምሰል በየስብሰባዎቹ መገኘቱ አይቀርም፡፡ ሁለተኛ፣ ኦህዴድ ሀገራዊ የፓለቲካ ጉዳዮችን መቀሌ ሄዶ ከመወሰን ባህርዳር ሄዶ መወሰን ይቀለዋል፡፡ ባህርዳር ላይ ቢያስወስን ተቀባይነት ያገኛል፡፡ ህዝቡ መቀሌ የሚል ሰም ሲሰማ ስለሚያንገሸግሸዉ ትክክል የሆነ የፖለቲካ ዉሳኔ እኳን መቀሌ ላይ ተወሰነ ቢባል ተቀባይነት የለውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በራሱ በተደጋጋሚ መቀሌ አካባቢ ከታየ ህዝቡ በጥርጣሬ እንደሚያየዉና አሁን ያለዉን መጠነኛ ድጋፍ ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለዚህም ዶ/ር አብይ ባህርዳር በተደጋጋሚ መታየቱ አይቀርም፡፡

አምስተኛ፣ የአማራ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት አሁን ባለዉ ሁኔታ ባህር ዳርን እየናጣት ነዉ፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ደግሞ እጅግ ከብዶ እና ገዝፎ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ እየተስፋፋ የመጣዉ የአማራ ብሄርተኝነት የባህርዳርን ፖለቲካ ማዕከል የሚያቀጣጥል ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ በእርግጥ ከዚህ በፊት እንዳልኩት የአማራ ብሄርተኝነት ወደ አዲስ አበባ ቢሻገር የተሻለ ይሆናል፡፡ ከሚታሰበዉ በላይ በፍጥነት የሚፈለገዉን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለዉጥ ማምጣት ከተፈለገ የአማራ ብሄርተኝነት ቁልፉ እና ቆጣሪዉ አዲስ አበባ ላይ መተከል አለበት፡፡

አዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማዕከል እንደሆነች ትቀጥላለች፡፡ ባህርዳር ግን የፖለቲካ ማእከል ሁና መከራረሟ አይቀሬ ነዉ፡፡