የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት ፈተናዎች (ተስፋዬ ሽብሩና መሐመድ አሊ)

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት ፈተናዎች
(ተስፋዬ ሽብሩና መሐመድ አሊ)

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “ፌደራሊዝምና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ አምስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ነበር፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ያቀረቡት የዩኒቨርስቲው ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት፣ የሕግና አስተዳደር ትምህርት ክፍሎች፣ አንጋፋ ምሁራን ነበሩ፡፡ “ፌደራሊዝም ብዝሃነትና ልማት” በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት የሕግና አስተዳደር መምህሩ ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ “ኢትዮጵያ ብዝሃነትን ባለመቀበል አንድ አገር አንድ ሕዝብ (Nation State) በሚል አስተሳሰብ ለበርካታ ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ባለት ዓመታት ግን በአገሪቱ የፌደራል አወቃቀር ተግባራዊ በመሆኑ እና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድል በመስጠቱ በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የነበረውን ዓይነት ጫፍ የወጡ ብሔር ተኮር ንቅናቄዎች የሚፈጠሩበትና የሚጎለብቱበት ዕድል ጠቧል፤” ሲሉ ይሟገታሉ፡፡

አሁን ያለው የፖለቲካ ገጽታ ግልጽ ቅርቃር ውስጥ እንደገባ የምትገልጸው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሯ አለን ሎቪስ በተቃራኒው ሥርዓቱ ከዴሞክራሲ መርሖ ውጭ ቆሞ እያለ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸውን የብሔር ቡድኖች በተስማማ ዘላቂና ከግጭት በጸዳ መልኩ የፌደራል ሥርዓቱን ለማስተዳደር መሞከሩ የማይቻል ነው ስትል ትከራከራለች፡፡ ሌላው መከራከሪያ ነጥቧ “ከብዙኃኑ ሕዝብ ዕውቅና ውጪ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ለብሔር ቡድኖች ማመቻቸት፣ የመገንጠል መንገድን መፍቀድና በመጨረሻም የፌደራል ሥርዓቱ እንዲበተን ማመቻቸት ይሆናል፤” የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የጠበበ አስተሳሰብና (Parochialism) መከፋፈል (Fragmentation) ለማስወገድ ከብሔር ማንነት ባሻገር ሁሉን አካታች የማንነት ጥያቄዎችን የማንሸራሸሪያ ዕድል መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ethnic federalism and self-determination for nationalities in a semi-authoritarian state: the case of Ethiopia በሚል ርዕስ ባሳተመችው ጽሑፏ ታብራራለች፡፡

ሌላው የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አስናቀ ከፋለ “ፌደራሊዝም፣ ዲሞክራሲና ሕዳጣን ሕዝቦች (ማይኖሪቲስ) በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በዕለቱ ባቀረቡት ጽሑፍ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት አገሪቱ ውስጥ ጫፍ የወጡ የብሔር ንቅናቄዎችን ማርገቡን እና ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቱን ያስረዳሉ፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን እና ቋንቋቸውን እንዲጠቀሙ፣ በቋንቋቸው እንዲማሩ እና እንዲዳኙ ዕድል ፈጥሯል በማለት የብሔር ተኮር ፌደራሊዝም በረከቶችን ጠቅሰዋል ዶ/ር አስናቀ፡፡ ይሁን እንጂ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት በተግባር የታየው የአገሪቱ የፖለቲካ ብዝሃነት በጣም ደካማ መሆኑን ሳይተቹ አላለፉም፡፡

የፖለቲካ ብዝሃነት እየተዳከመ መምጣቱን ለማሳየት ከሽግግር መንግሥቱ ጀምሮ የነበረውን የኢሕአዴግን በፓርላማ 36 በመቶ መቀመጫ ቁጥር ለማመልከት ሞክረዋል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል፣ በሽግግር መንግሥት ወቅት ኢሕአዴግ በፓርላማ 36 በመቶ መቀመጫ ነበረው፤ በወቅቱ ይህ ቁጥር አሳታፊና ብዝሃነትን ያሳይ ነበር፤ አሁን ግን መቶ በመቶ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ ተይዟል፡፡ ይህም አሳታፊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ያሳያል፡፡ “ገዢው ፓርቲ ከአውራ (dominant) ፓርቲነት ወደ አንድ ፓርቲ (defector one panty ) ሄዷል” የሚሉት ዶ/ር አስናቀ፣ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ያለው መስመር በጣም የሳሳ በመሆኑ የፓርቲው የውስጥ ሥርዓት አደረጃጀቶች እና አካሄዶች ወደ መንግሥት ሥርዓት በመግባታቸው ለመንግሥትም ለፓርቲም ፈታኝ ሁኔታ መፈጠሩን ይገልጻሉ፡፡ የአንድ ለአምስት የፓርቲ አደረጃጀቶች ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመውረዳቸው በፓርቲ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት በማደብዘዝ የፖለቲካ ብዝሃነት በመፍጠር በኩል አሉታዊ ገጽታ መታየቱንም ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ያልተማከለ አሳታፊ ፓርላሜንታዊ ፌደራሊዝም ወደ ወደ ተማከለ (Centralized) ፌደራሊዝም ተቀይሯል በማለት ተችተዋል፡፡

የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች በሙሉ ተግባራዊ አለመደረጋቸው ሌሎች መመሰቃቀሎችንም ፈጥሯል፡፡ የፌደራሊዝም አንዱ ጥቅም ፖሊሲዎች በተለያዩ ክልሎች እና ፓርቲዎች ውስጥ ሊተገበር መቻሉ ነው የሚሉት ዶ/ር አስናቀ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፈለገው ደረጃ ባለመጎልበታቸው ይህ ሊሳካ እንዳልቻለ አብራርተዋል፡፡ ይህም የፖለቲካ ብዝሃነት አለመኖር (መዳከም) የፌደራላዊ ሥርዓቱን ዕድገት እንዲቀጭጭ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የማን ነው?
***

ዶ/ር ያሬድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አሁን በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው “ስማዊ ፌደራሊዝም” (pseudo federalism) ነው፤ አቀራረቡም ከላይ ወደ ታች የሆነ አካሄድን የተከተለ ነው፡፡ ዶ/ር ያሬድ “በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው ፌደራላዊ ሥርዓት በተግባር ግን አሐዳዊ (unitary) ሆኗል፤” በማለት ሕገ መንግሥቱን እና ብሔር ተኮር ፌደራላዊ ሥርዓቱ አለመጣጣሙን ያስረዳሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከሞላ ጎደል ጥሩ መሆኑን የጠቀሱት እኝሁ ምሁር፣ ሰነዱ ሲወለድ ሁሉም ሕዝቦች እና ሕዝብን የሚወክሉ አካላት ተሳትፈውበት ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የሚታየውን ችግር በተወሰነ መልኩ ይቀንሰው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ “ሕግ መንግሥት የሁሉም ሕዝቦች ነው፤ የአሸናፊዎች ብቻ ሊሆን አይችልም” ይላሉ ምሁሩ፡፡ አያይዘውም “ሕዝቡ የራሱን ሕገ መንግሥት (በእርግጥም የራሱ ከሆነና የእኔ ነው ብሎ ከተቀበለው) ሊንድ አይችልም፤ ይጠብቀዋል እንጂ፡፡ መንግሥትም የሕገ መንግሥቱ ጠባቂ (ሞግዚት) ሊሆን አይችልም፡፡ ባለፈው ዓመት የተከሰተው ትርምስና ወጣቱን ወደ አመጽ የገፋፋው ነገር የሚያሳየው እኮ አንድ ችግር እንዳለ ነው፤” ሲሉ ከአፈጻጸም ችግሮቹ ባለፈ ማሻሻያዎች ሊደረጉበት እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

በፌደራላዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ዋነኛ ምሰሶ የሆነው ሕገ መንግሥቱ በሚገባ በተግባር ካልዋለ ቅሬታ እና ግጭት እንደሚያስነሳ በጥናታቸው ያመለከቱት ፕሮፈሰር ካሳሁን ብርሃኑ፣ ሕገ መንግሥቱ በአግባቡ ወደመሬት አለመውረዱ (አለመተርጎሙ/አለመተግበሩ) በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ግንባታ ውስጥ ዋነኛ ተግዳሮት ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ጋር ከሦስት ዓመት በፊት ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ብለው ነበር፡- “ዛሬ ድረስ ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙና ሕገ መንግሥቱን ወደ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት መወርወር አለበት የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን አሉ፡፡ ያም ብቻ አይደለም፤ ሕገ መንግሥቱ የተቀረፀው ከ21 ዓመት በፊት ነው፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ለውጦች ተከስተዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ በዚህ ሕገ መንግሥት ላይ አልተወያየበትም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ምን እንደሆነ እንኳ አያውቅም፡፡

ስለዚህ በዚያን ጊዜ የቀረጽነው ሕገ መንግሥት አሁንም ድረስ ተቀባይነትን ለማግኘት የሚችል ነው ወይስ አንዳንድ ለውጦች ሊደረጉበት ይገባል? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬም ድረስ የተከራከርንባቸው ያሉት ጉዳዮች ወይ ከሕገ መንግሥቱ ከራሱ ጋር ወይም ከአፈጻጸሙ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት ላይ አንድ ነገር ካልተደረገ ሕገ መንግሥቱ አገሪቱን አስተሳስሮ ይዞ ላይቀጥል ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ በሂደት ሕዝቦች ይህ ሕገ መንግሥት ምን ይሠራልናል የሚል ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራሉ፡፡ አሁን ያሉ ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ ውዝግቦቹና ክርክሮቹ ከእጅ አምልጠው የአገሪቱን አንድ ሆኖ መቀጠል አደጋ ላይ እንዳይጥሉት እሰጋለሁ፡፡”

አሁንም አንቀጽ 39
***

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የክርክር ምንጭ ሆነው ከቀጠሉት ጥያቄዎች መካከል አንቀጽ ሠላሳ ዘጠኝን የሚመለከተው ቀዳሚ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ዶ/ር ኢዮብ ይህን አንቀጽ አስመልክተው ሲናገሩ፣ “አንቀጽ 39 ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ባይካተት ይሻል ነበር፣ ነገር ግን ቢገባም ቤቱን የተመቻቸ ማድረግ ከተቻለ፣ “ተገንጠል፤” ቢባል የሚያጣው ነገር ስላለ የትም አይሄድም፤ የእኛ ግን የዚህ ተቀራኒ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ችግሮችን እየፈታ ያለው በጠንካራ መዳፉ ይመስለኛል፤” ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት ላይ ሰፊ ጥናት ያደረገችው አለን ሎቪስ በበኩሏ “ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ሚዛናዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልን የሚያካትት ሕገ መንግሥት ቢሆንና የመገንጠል መብት ቢጨመር ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ሆኖ የመገንጠል መብት ሲካተት አስገራሚ ነው፤” ትላለች፡፡ “ፌደራሊዝምና መገንጠል አብረው አይሄዱም” የሚለው ሮናልድ ዋትስ በበኩሉ፣ አንድ አገር የፌደራሊዝም ሥርዓት ሲያዋቅር ሦስት ነገሮችን ቀድሞ ማሰብ እንደሚገባ ያስታውሳል፡፡ የመጀመሪያው የቀድሞው ችግር ምንድነው? ዛሬ ያለውን ችግርስ እንዴት እንለፈው? በሦስተኛ ደረጃ ለወደፊትስ ችግሮቻችንን የምንፈታው እንዴት ነው? የሚሉት ጥያቄዎች በቅጡ መመለስ እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ የተዘረጋው ፌደራላዊ ሥርዓት የዜጎችን የፖለቲካና ኢኮኖሚ መብት ያረጋገጠ፣ በሕዝቦች መካከል ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ያመጣ፣ ለሠላም መሠረት የሆነ … መሆኑን ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡ የአገሪቱን ዘርፍ ብዙ ችግሮች ከመፍታት አንጻር ወቅታዊው ሥርዓት ወሳኝ መሆኑንም ግንባሩ አጥብቆ ይከራከራል፡፡ ነገር ግን ይህ ብሔር ተኮር (ዘውጋዊ) የፌደራል ሥርዓት ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በልሂቃኑ መካከል የከረረ የሙግት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡

ከፍ ብሎ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አንዱ የፌደራላዊ ሥርዓቱ ውጤት መሆኑን የመንግሥት ኀላፊዎች ሳይናገሩ አያልፉም፡፡ ግንባሩ ይህንን ይበል እንጂ፣ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም የብሔር ግጭት ከመቀነስ ይልቅ የመጨመር አዝማሚያ እንዳለው በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ፌደራላዊ ሥርዓት የመገንጠል ጥያቄን እንደማያስቀር፣ እንዲያውም ነጻ አገረ መንግሥት ማቋቋም የሚፈልጉ ኀይሎች እንደ መንደርደሪያ መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ የሚያስገነዝቡ በርካታ ምሁራን ናቸው፡፡

“በፌደራላዊ ሥርዓት ሕዝቦች ራሳቸውን ማስተዳደር አለባቸው ሲባል ራስን ማስተዳደር አንድ ነገር ሆኖ፣ በሕዝቦችም መካከል የተሳሰረ ማንነት እና አዎንታዊ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፤” የሚሉት ዶ/ር አሰፋ በበኩላቸው፣ “ፌደራሊዝምን ለአገር ግንባታ እንደ መሣሪያ መጠቀም ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአገራዊ ማንነት ይልቅ ክልላዊና የብሔር ማንነቶች ጎልተው መታየት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች በጊዜ ካልተረሙ አደገኛ ናቸው” በማለት ያስረዳሉ፡፡

ሕዝቦች ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ አብረዋቸው የሚኖሩ “ህዳጣን” ሕዝቦችን (minorities) በማቀፍ ለሚያነሷቸው ተገቢ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት የግድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን አየታየ ያለው በክልል ደረጃ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ሕዝቦች ከእነሱ ሥር ባሉ አናሳዎች ላይ አግባብ የሌለው የፖለቲካ እርምጅ እየወሰዱ ይገኛሉ ያሉት ዶ/ር አሰፋ ራስ ከማስተዳደር ጋር ተያይዞ በሕገ መንግሥቱ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” የሚለው ፖለቲካል ጽንሰ-ሐሳብ ወይስ የብሔር ማንነነት (ethnic) ጽንሰ-ሐሳብ? የሚለው ጉዳይ አወዛጋቢነቱ እንደቀጠለ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ብሔር ብሔረሰብ የሚለው የፖለቲካ ጽንሰ-ሐሳብ ከሆነ ለአንድ ዜጋ የዘር ሐረጉ ከየትም ይሁን ከየት የአካባቢውን ቋንቋና ባሕል ካወቀ በክልሉ በሁሉም ጉዳዮች የመሳተፍ ዕድል ይሰጣል፡፡ የብሔር ጽንሰ ሐሳብ ከሆነ በተለይ ለሹመት የዘር እና የብሔር ሐረግ ይመዘዛል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ጽንሰ-ሐሳብ ሆኖ እያለ በአንድ ክልል ከሌሎች ክልሎች አያቶቻቸው ሄደው በኖሩባቸው አካባቢ የሚኖሩ እና የአከባቢውን ባሕል እና ቋንቋ የሚችሉ ሆነው ሳለ የመሾም መብታቸው መነፈጉን ያነሳሉ፡፡ ይህም በዋነኛነት በአገሪቱ አምስት ክልሎች እንደሚታይና አካሄዱ አደገኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ሰሎሞን አየለ የተባሉ የሕግ ምሁር ከሪፖርተር ጋዜጣ (ግንቦት 2009) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ተክስቶ ስለነበረው ችግር ሲያስረዱ “በድኅረ 1983 ዓ.ም. የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ከሆነው የፌደራል ሥርዓት አፈጻጸም ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ሲሆኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፌደራል ሥርዓቱ ችግር ውሰጥ ገብቶ ነበር” ብለዋል፡፡ ከመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ጋር የተገናኘ ችግር አለ የሚሉት ምሁሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሥርዓቱ ራሱ ስለመኖሩ ጥያቄ እየቀረበበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እሑድ፣ ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የግንቦት 20 የመዝጊያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በሕዝቦች መስዋዕትነት የተገኘውን ድል ወደ ተግባር የመነዘረው ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የሕዝቦችን ያልተገደበ ተሳትፎ በማሰተባባር በመምራት ፈጣን ተከታታይና ፍትሐዊነት ላይ የተመሠረተ ልማት ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የተመዘገበው ዕድገት የዜጎችን ሕይወት ከመሻሻሉም በላይ ሁሉም ሕዝቦች አገሪቱ ከምታመነጨው ሀብት በግልፅና ፍትሐዊ ቀመር የሚከፋፈሉበት የትኛውም ሕዝብ የበይ ተመልካች የማይሆንበት እና የሚጠቀምበት ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ ይህን ይበሉ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዝሃነት ባለበት አገር ፓርላማውም የአገሪቱን የፖለቲካ ብዝሃነት የሚወክል ስለመሆኑ ጠንካራ ጥያቄዎች ሲቀርቡበት እንደቆዩ ግልጽ ነው፡፡ በአገሪቱ የብሔር ብዝሃነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ብዝሃነትም አለ፤ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ስለ ብሔረሰቦች መብት መጠበቅ አበክሮ የሚናገረውን ያህል ስለ መድበለ ሐሳብ ወይም ስለ ሐሳብ (ርዕዮተ ዓለም) ብዝሃነት ሲናገር አይደመጥም፡፡ በእርግጥ አገዛዙ ስለ ብሔረሰቦች መብት መጠብቅ አብዝቶ ይናገራል እንጂ የብሔረሰቦች ብዝሃነት እየተስተናገደ ነው ለማለትም ያስቸግራል፡፡ ለነገሩማ የዜጎች የሐሳብ ልዕልና ሳይከበር የብሔረሰቦች መብት ሊከበር የሚችልበት ምን ዕድል አለ?

ከፌደራላዊ ሥርዓት ውጪ ምን አማራጭ አለ?
***

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር አስናቀ ከፋለ እና ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ ኢትዮጵያ ከፌዴራላዊ ሥርዓት ውጪ የሚበጃት የአስተዳደር ሥርዓት እንደሌለ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በእርግጥም “ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፌደራላዊ ሥርዓት ነው፤” በሚለው ሐሳብ ላይ በሚበዙት ምሁራን ዘንድ ስምምነት አለ፡፡ ልዩነቱ፣ ምን ዓይነት ፌደራላዊ ሥርዓት? በሚለው ጥያቄ ላይ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መሪዎች አሁን በሥራ ላይ ካለው ፌደራላዊ ሥርዓት ውጪ ምንም ዓይነት ምርጫ የለም፤ በሥራ ላይ ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት ከተቀየረ ኢትዮጵያ ያልቅላታል፤ ትበተናለች ሲሉ አበክረው ይናገራሉ፡፡ ከኢሕአዴግና አጋሮቹ ውጪ ያሉት የብሔረሰብ ድርጅቶችም ቢሆኑ፣ የአፈጻጸም ጉድለቱን ካልሆነ በስተቀር አሁን ባላው ፌደራላዊ ሥርዓት ላይ ጥያቄ የላቸውም፡፡

ከዚህ በተቃራኒው አሁን በሥራ ላይ ያለው ብሔረሰብ ተኮር ፌደራላዊ ሥርዓት በሕዝቦች መካከል አላስፈላጊ ፉክክር፣ ጥላቻና ቂም የሚፈጥር በመሆኑ ለአገር ህልውና ጠንቅ ነው የሚሉ አካላትም አሉ፡፡ እንደነዚህ ወገኖች እምነት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ተመጣጣኝ መጠን ያላቸው (symmetric)፣ ብሔረሰባዊ ማንነትን ብቻ ሳይሆን፤ የባህልና የሥነ ልቦና ተቀራራቢነትን፣ መልክዓምድራዊ አመችነትን ወዘተ. ከግምት ውስጥ ያስገቡ እና በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተቋቋሙ ክልሎችን የያዘ ፌደራላዊ ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች በየጊዜው መፈናቀላቸው፣ በፖለቲካ ኤሊቱ በተለይ በወጣቱ መካከል የሚታየው አስፈሪ ጽንፈኝነት፣ የሚያስገነዝበው ብሔረሰብና እና የቋንቋ ተኮር የሆነው ፌደራላዊ ሥርዓት ዜጎች በጠባብ ብሔረሰባዊና ክልላዊ ማንነት ላይ እንዲያተኩሩ፣ ሌሎችን ዜጎች በጥላቻ እንዲመለከቱ፣ ከዚህም አልፎ አዳዲስ አገሮችን ለመፍጠር እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረላቸው ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡