በኦሮሚያ ክልል ኣማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን፣ ኦሮምኛም በግዕዝ ፊደል ትምህርት እንዲሰጥ ምሁራን ለ አቶ ለማ መገርሳ ደብዳቤ ፃፉ።

በኦሮሞ ክልል ኦሮምኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው ዞኖችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም በክልሉ ኣማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን፣ ኦሮምኛም በግዕዝ ፊደል ትምህርት እንዲሰጥና የሌሎች ማህበረሰባትን መብታቸው ተረግጦ፣ ደህንነታቸው አደጋ ላይ ወድቆ፣ ከኦሮሞው ማህበረሰብ እኩል እንዳያታዩ ያደረጉ  የክልል መንግስቱ አሰራሮች፣ ፖሊሶዎችና ሕጎች እንዲሻሻሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ እንደሆነ የገለጹት ምሁራኑ፣ ኦሮምኛ በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሌላው ህየአገሪቷ ክፍል እንዲነገርና እንዲስፋፋ፣ በአማራ ክልል በትምሀት ቤቶች፣ በግ እዝ እንዲጻፍ ለአቶ ገዱ አንዳራጋቸው መጻፋቸው ይታወቃል። ለአቶ ለማ በጻፊትም ደብዳቤ አፋን ኦሮሞ በላቲን መጻል ትክክል እንዳልነበረና አሁንም እንዳልሆነ በድጋሚ አስምረዉበት፣ ኦሮምኛ እንዲያድግ፣ ሌሎች ማህበረሰባትም የኛ ነው ብለው እንዲቀበሉት፣ እንዲማራትና እንዲያውቁት ለማበረታታ የአገር ቅርስ የሆነው፣ በሙሉም መስፈርት ለኦሮሞኛ ብቃት ያለውን የግእዝ ፊደል መጠቀመ እንዲጀመር አሳስበዋል።

መምህራኑና አክቲቪስቶቹ መምህር ልዑለቃል አካሉ፣  ዶ/ር ኣበራ ሞላ ፣ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣  ፕ/ር ማሞ ሙጬ፣  ፕ/ር ባዬ ይማም ፣ ፕ/ር ኀይሌ ላሬቦ፣ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፣  ዶ/ር አበባ ደግፌ፣ የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አቶ ያሬድ ጥበቡ፣ አቶ ሰይፉ አዳነች ብሻው፣  አቶ ተፈራ ድንበሩ፣ አቶ ብርሃኑ ገመቹ፣  አቶ አብርሃም ቀጄላ፣ አቶ ታደሰ ከበደ፣ ወ/ሮ እስከዳር አውላቸው፣  አቶ ተመስገን መኩሪያ  እና አቶ ግርማ ካሳ  ሲሆኑ ጽሁፋቸውን እንደሚከተለው ከዞኢህ በታች አቅርበናል።

 

ደብዳቤዉ በፒ.ዲ.ኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

=====

ጉዳዩ – በክልሉና ኦሮምኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ኦሮምኛ በግዕዝ ፊደል ትምህርት እንዲሰጥ ስለመጠየቅ

ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.

ለተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ክልል መንግሥት ሊቀመንበር

ክቡር ሊቀመንበር ሆይ፦

በቅድሚያ እርስዎ፣ የክልል መንግሥትዎና ድርጅትዎ ኦህዴድ በአገራችን ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበረሰባዊ ቀውሶችን ለማስወገድ በቀዳሚነት እያደረጋችሁት ስላለው ታሪካዊና አስደናቂ ተግባራት ያለንን ትልቅ ምስጋናና አክብሮት ለመግለጽ እንወዳለን። ቀደም ሲል ከነበሩ አመራሮች በተለየ መልኩ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ መከፋፈል፣ ልዩነት፣ ዘረኝነት ተወግዶ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብና መያያዝን ለማምጣትና የጥል ግድግዳዎችን ለማፍረስ በመነሳታችሁ፣ ዘርና ኃይማኖት ሳይለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፉን እየሰጣችሁ ነው። ሕዝብ በፍቅር፣ በትህትና፣ በፍትህና በእኩልነት ሊያስተዳድረው የተነሳን አመራር ያከብራልና።

የጀመራችሁትን መልካም እንቅስቃሴ ለማገዝ፣ መቀራረቡንና አንድነቱን ለማፋጠን የተነሳችሁለትን አላማ እንድታሳኩ እጅግ በጣም ቁልፍና ጠቃሚ ለሆኑ ጉዳዮች ክቡርነትዎ ትኩረት ይሰጡት ዘንድ ይኸንን ጽፈናል። ከዚህ ደብዳቤ ጋር ግዕዝን በኦሮምኛ መጻፍ በብቃትና በአመችነት አንጻር የተሻለ እንደሆነ የሚያስረዳ ጥናታዊ ሰነድ አካትተናል።

አንደኛማርኛን በኦሮሞ ክልል ትምህርት ቤቶች ስለማስተማር

ቋንቋ መግባቢያ ነው። ቋንቋን ማወቅ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። በኦሮሞ ክልል ብዙ ወገኖቻችን ኣማርኛ የማንበብና መጻፍ ችግር አለባቸው። ለብዙ ዓመታት ኣማርኛ ትምህርት አይሰጥም ነበር። መሰጠት ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሚሰጠው ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ነው። ኣማርኛ  የፊዴራል ቋንቋ ነው። በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በኣማራ ክልል፣ በደቡብ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ክልል፣ በጋምቤላ ክልል ኣማርኛ የሥራ ቋንቋ ነው። በኦሮሞ ክልል ውስጥ እንደ አዳማ ባሉ ከተማዎችም የግል መሥሪያ ቤቶች የሚጠቀሙት በኣማርኛ ነው። ኣማርኛ አለመጻፍና አለማንበብ የኦሮሞ ክልል ነዋሪዎችን ክፉኛ ጎድቷል። ሥራ የማግኘት፣ የመሻሻል፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ የማደግ ዕድላቸውን በጣም አጥብቧል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ባለባቸው ቦታዎች መወዳደርና መሥራት ካልቻሉ ሕይወታቸውን እንዴት ነው ማሻሻል የሚችሉት?

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ለኣማራ ቴሌቪዥን ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በኣማራ ክልል ኦሮምኛ ማስተማር እንደሚያስፈለግ ገልጸው፣ በኦሮሞ ክልል ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ኣማርኛ ትምህርት መሰጠት እንዳለበት ተናግረው ነበር። በኣማራ ክልል ኦሮምኛ በግዕዝ ፊደል እንዲሰጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲደርስ አድርገናል። በኦሮሞ ክልልም ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የኣማርኛ ትምህርት እንዲሰጥ በማድረጉ ትልቅ ትኩረት ይደረግበት ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

ሁለተኛየኦሮሞ ክልል ሕገ መንግሥት ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መሻሻል አስፈላጊነት

ክቡርነትዎና የትግል አጋርዎ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ብዙ ጊዜ ኦሮሞ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ክልል እንደሆነች ገልጻችኋል። የኦሮሞ ክልል ሕገ መንግሥት ግን እናንተ እየደጋገማችሁ በግልጽና በአደባባይ የገለጻችሁትን የሚያንጸባርቅ አይደለም። የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ስምንት፣ የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን፣ የሕዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው ይላል። ይህ ማለት የኦሮሞ ክልል ባለቤት የኦሮሞ ሕዝብ እንደሆነ፣ ኦሮሞ ክልል የኦሮሞዎች እንደሆነች፤ ሌላው በክልሉ የሚኖረው ኦሮሞ ያልሆነው ማሕበረሰብ ደግሞ፣ በኦሮሞ ማሕበረሰብ ፍቃድ እንደሚኖር፣ እንግዳ እንደሆነና የክልሉ የባለቤትነት መብት እንደሌለው የሚያመለክት ነው።

ይህ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ፡ ክቡርነትዎ ኦሮሞ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት ያሉትን የሚጻረር ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ በሆነ መልኩ የዜጎችን የሰብአዊና የእኩልነት መብቶችን የሚገፍ ነው። ዜጎች በማንኛውም የአገሪቷ ክፍል የመኖር፣ የመሥራት፣ የመነገድ፣ የመማር፣ የማስተማር፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ መብቶቻቸው ሊጠበቁላቸው ይገባል። የክልሉ ሕገ መንግሥት ማንም ኢትዮጵያዊ፣ በሁሉም መስፈርት ከኦሮሞው እኩል እንደሆነ የሚያረጋግጥ፣ የሌሎች ማሕበረሰባት በክልሉ የመኖር ዋስትናን የሚሰጥ ሕገ መንግሥት ሆኖ መሻሻል አለበት ብለን እናምናለን። ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ስምንት የኦሮሞ ክልል ነዋሪ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን፣ የሕዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው በሚል ቢሻሻል ጥሩ ሊሆን ይችላል ብለን እንመክራለን።

ሦስተኛየክልሉ እንዲሁም ከመቶ በላይ ኦሮምኛ የማይናገሩ ዜጎች በሚኖሩባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ማርኛም የሥራ ቋንቋ ማድረጉ አስፈላጊ ነው።

የኦሮሞ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፭ ኦሮምኛ የክልሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል። አንቀጽ ፴፫ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ነዋሪ የሆነና የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ወይም ሕዝባዊ ሥራ ተመርጦ ወይም ተቀጥሮ የመሥራት መብት አለው ሲል ለክልሉ መንግሥት ኃላፊነት መመረጥ ወይም በክልሉ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥሮ መሥራት የሚችሉት ኦሮምኛ የሚናገሩ ብቻ መሆናቸውን በግልጽ ያስቀምጣል።

ይፋዊ የሆነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ያለው፣ ከ፲፪ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ መስሪያ ቤት ይፋ የሆነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ነው። በዚህ የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት በወቅቱ ከተሸነሸኑት ሃያ የኦሮሞ ክልል ዞኖች በስምንቱ (ጂማ ልዩ፣ አዳማ ልዩ፣ ቡራዩ ልዩ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ጉጂና አርሲ ዞኖች) ኦሮምኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ከኣስራ አምስት በመቶ በላይ ናቸው። ይህ ቀላል ቍጥር አይደለም። በአዳማና ጂማ ልዩ ዞኖች ኦሮምኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ ሰባ አራት እና ስድሳ በመቶ ናቸው። አዲስ አበባ በአካባቢዋ ከአሉ የኦሮሞ ክልል ዞኖች ጋር የተሳሰረች መሆኗ ይታወቃል። በአዲስ አበባ የሚኖረውን ሕዝብና የኦሮሞ ክልል ነዋሪ አንድ ላይ ብንደምራቸው ከመቶ ኣስራ አምስት የሚሆኑት ኦሮምኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አይደለም። አዲስ አበባ፣ አዳማና ቡራዩ ልዩ በኦሮሞ ክልል የሸዋ ዞኖችን ሁሉ ብናካትት ኣርባ ኣራት ከመቶ የሚሆኑት፣ አዲስ አበባ፣ ቡራዩ ልዩ፣ አዳማ ልዩና ምሥራቅ ሸዋ ዞንን ስንደምር ሰባ ኣንድ ከመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮምኛ አይደለም። ክቡርነትዎ እንደሚያውቁት፣ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፭ እና አንቀጽ ፴፫፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ኦሮምኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያንን የመሥራትና የመመረጥ፣ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብታቸውን የሚገፍ ነው። በአገራቸው እንደ ባይተዋር እንዲሆኑ ያደረገ ነው።

ላቲን፣ ላለፉት ፳፯ ዓመታት እንደ ትምህርት ይሰጥ ስለነበረና በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የሚያውቁትና የተማሩት እርሱን በመሆኑ ብዙዎች ላቲን እንዲቀጥል ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ሆኖም ግን በላቲን መጠቀሙ የአብዛኛው የኦሮሞ ማሕበረሰብና በተለይም በክልሉ ያሉ ኦሮምኛ የማይናገሩ ዜጎችን ፍላጎት ያካተተ ነው ብለን አናስብም።

በላቲን መጠቀም የሚፈልግ ማሕበረሰብ አለ፣ ላቲን የመብት ጥያቄ ነው ከተባለ፣ ቢያንስ ሚዛናዊነትን በማሳየት ኦሮምኛ በግዕዝ መጠቀም የሚፈልጉ የክልሉ ነዋሪዎችን ፍላጎት ማስተናገድ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

ከ፳፯ ዓመታት በፊት ላቲን ለኦሮምኛ ሲመረጥ የሕዝብ አዎንታ አልተጠየቀም። ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ላቲንና ግዕዝን እኩል በጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ በጥናት ላይ የተመሠረተ ንፅፅር አልተደረገም። በወቅቱ በኃላፊነት ላይ የነበሩ፣ ከሌላው ማሕበረሰብ የተለየ የኦሮሞ ማንነትን ለመፍጠር የፈለጉ፣ የኦሮሞ ልሂቃንና ፖለቲከኞች በሕዝቡ ላይ የጫኑት ውሳኔ ነው። በመሆኑም “አንቀጽ ፭ ኦሮምኛና ኣማርኛ የክልሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናሉ። ኦሮምኛም የሚጻፍበት ፊደል በሕዝብ ይወሰናል በሚል፣ አንቀጽ ፴፫ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ነዋሪ የሆነና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ወይም ሕዝባዊ ሥራ ተመርጦ የመሥራት መብት አለው። ለሥራው ብቃት ያለው ማንም ኢትዮጵያዊ በክልል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቀጥሮ የመሥራት መብት አለው” በሚለው ቢሻሻል ጥሩ ይሆናል ብለን እናስባለን።

አንዳንድ ወገኖች ለምን በኣማራ ክልል ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ አይሆንም? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ። ኦሮምኛም ሆነ ሌላ ቋንቋ በኣማራ ክልልም የሥራ ቋንቋ መሆኑ በመርህ ደረጃ ችግር የለውም። አስፈላጊ ከሆነ በሕዝብ ምርጫ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ግን አስፈላጊ ነው ወይ? የሚለው መታየት ያለበት ጥያቄ ነው።

 

በኦሮሚያ የሸዋ ዞኖችና አዲስ አበባ ኦሮምኛ አንደኛ ቋንቋቸው ያልሆኑ ነዋሪዎች ብዛት የሚያሳይ

 

ለንጽጽር ይረዳ ዘንድ የሚከተለውን መረጃ እንመልከት። በኦሮሞ ክልል ከላይ እንደገለጽነው በሁለት ዞኖች ኦሮምኛ ውስጥ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ ኣማርኛ ተናጋሪዎች ከግማሽ በላይ ናቸው። በኦሮሞ ክልል ካሉ ሃያ ዞኖች፣ ኦሮምኛ የማይናገሩ ኣምስት  ከመቶ በታች የሆኑበት ዞን አንድ እርሱም የምእራብ ወለጋ ዞን ነው። ኦሮምኛ የማይናገሩ ኣስር ከመቶ በታች የሆኑባቸው ዞኖች ደግሞ አራት ብቻ ናቸው፦ ቀለም ወለጋ፣ ምእራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋና ኢሉባቦር።

በኣማራ ክልል ካሉ ኣስራ ሁለት ዞኖች ከአንድ ዞን በስተቀር ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከአምስት ከመቶ በታች ናቸው። በኣማራ የኦሮሞ/ከሚሴ ዞን ሰማኒያ ከመቶ፣ በአርጎባ ልዩ አራት  ከመቶ፣ በባሕር ዳር ልዩ ሁለት ከመቶ፣  በደቡብ ወሎ ሁለት  ከመቶ ሲሆኑ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በተቀሩት ስምንት  ዞኖች ከመቶ አንድ በታች ናቸው። እንደዚህም ሆኖ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በበዙበት የኣማራ ክልል የኦሮሞ ዞን፣ የክልሉ መንግሥት የኦሮምኛ ተናጋሪዎችን መብት በማክበር፣ በኦሮምኛ እንዲማሩ፣ በኦሮምኛ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

አራተኛላቲን የኦሮምኛን እድገት ክፉኛ የሚገታ ነው።

ዜጎች ብዙ ቋንቋዎች ባወቁ ቍጥር ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም። ኣማርኛ የኣማራዎች ብቻ ቋንቋ እንዳልሆነ ኦሮምኛም የኦሮሞዎች ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ናቸው። ኦሮምኛ በኦሮሞ ክልል ብቻ መወሰን የለበትም በሚል በዐማራ ክልል ኦሮምኛ በግዕዝ ፊደል እንደ ትምህርት እንዲሰጥ የሚጠየቅ ደብዳቤ፣ ከተያያዥ ጥናታዊ ሰነድ ጋር፣ ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ልከናል። ለአቶ ገዱ የላክነውንም ሰነድ ለክቡርነትዎ ግላባጭ አድርገናል።

ለተከበሩ አቶ ገዱ የጻፍነውን ደብዳቤ ተከትሎ የደረሱን አስተያየቶች አንዱ በኣማራ ክልል ኦሮምኛ ተማሩ ስትሉን፣ ለምን በኦሮሞና የሌሎች ማሕበረሰባት መብት እንዲከበር አትሠሩም? ለምን መጀመሪያ በኦሮሞ ክልል ኦሮምኛ በግዕዝ እንዲጻፍ አትጠይቁም የሚል ነበር። ኣማርኛ የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ነው እየተባለ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ መማር ተትቶ ኦሮምኛን ሌሎች ይማሩት ማለት ብቻ በቂ አይደለም።

ሌላው ኦሮምኛን ለመማር በኣማራ ክልል በሚኖረው ማሕበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ተረድተናል። ሕዝቡ ኦሮምኛን የራሱ አድርጎ ነው የሚቆጥረው። ሆኖም ግን ኦሮምኛን ለመማር ትልቅ ፍቃደኝነት ቢኖርም፣ ካገኘናቸው አስተያየቶች ለመረዳት እንደቻልነው፣ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል፣ በላቲን ፊደል ለመማር ፍላጎት የለም ብቻ ሳይሆን፣ ትልቅ ተቃውሞ ነው ያለው። ኦሮምኛ በላቲን ፊደል የሚጻፍ ከሆነ ከኦሮሞ ክልል ውጭ የማደግ፣ የመስፋፋት ዕድሉ እጅግ በጣም የመነመነ ነው የሚሆነው። ያለ ፍላጎት ደግሞ በዜጎች ላይ ምንም ነገር መጫን አይቻልም። “ኦሮምኛ የእኛ፣ ላቲን የሌላ” ነው እየተባለ ያለው።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ በሕዝብ ይሁንታ ኦሮምኛ ከኣማርኛ ጋር የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ድርጅትዎ እንደሚሠራ ገልጿል። የሕዝብ ይሁንታን አስፈላጊነት ድርጅትዎ ማስመሩ ሊያስመሰግነው ይገባል። ኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ የኢትዮጵያ ፴፭ ከመቶ አካባቢ ነው። ከእዚህ ኦሮምኛ ተናጋሪ በላቲን ፊደል መጻፉን የሚደግፍ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ ባይቻልም፣ ከግማሽ በላይ ይሆናል ብለን ግን አናስብም። ያ ማለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከሦስት አራተኛው በላይ የላቲን ፊደልን የሚቃወም ነው ማለት ነው።  ሦስት አራተኛው ተቃዋሚ በሆነበት በላቲን የሚጻፍ ኦሮምኛን የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የሕዝብ ይሁንታን ማግኘት የማይታሰብ ነው።

ኦሮምኛ በግዕዝ ከተጻፈ ግን በኣማራ ክልል ካገኘነው አስተያየት ለመረዳት እንደቻልነው፣ ብዙዎች ሳይገደዱ፣ ደስ ብሏቸው ቋንቋውን ይማራሉ። ቋንቋውን የሚናገሩ ይበዛሉ። ቋንቋው የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋም እንዲሆን የሕዝብን አዎንታ ለማግኘት ቀላል ይሆናል።

አምስተኛየግዕዝ ፊደላትን መጠቀም የአገር ቅርስ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተሻለም ነው።

ምዕራባውያን ለጥቁር ሕዝብ መሸጥና መዋረድ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሙበት አንዱና ትልቁ መከራከሪያቸው “ጥቁሮች የራሳቸውን ስነፅሁፍና ፊደል መቅረፅ ያልቻሉት በዕውቀት ዝቅተኞች ስለሆኑ ነው” የሚለው ነው። ይኸን ትርክት ውድቅ ለማድረግ፣ የግዕዝ ፊደላችን ወደቀረው አፍሪቃ እንዲስፋፋ መታገል ነበረብን። ሆኖም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች በመወጠራችንና በሃገራችን የሰፈነው የማንነት ፖለቲካና ከኢትዮጵያ የተለየ ማንነት ይፈልጉ በነበሩ አክራሪ ብሔርተኞች አሉታዊ ጫና ምክንያት አላደረግነውም። እንኳን ወደ አፍሪካ አገሮች ግዕዝን ልንወስድ ቀርቶ በአገራችን ምዕራባውያን ፊደል፣ ላቲን፣ ለአንዳንድ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እየተጠቀምን ነው።

አንዳንድ ወገኖች የግዕዝ ፊደልን የአንድ ብሔረሰብ ርስት አድርገው የመቍጠር ዝንባሌ ሲኖራቸው አንዳንዶች ደግሞ የግዕዝ ፊደል ብቃት እንደሌለው አድርገው ያስባሉ። የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው አይጻፉም። የቃላት አጻጻፍን/ሥርዐተ ኆሄያትን ለማወቅ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ፊደላት ግን ሰዉ እንደሚናገረው ስለሚጻፉ፣ የሥርዐተ ኆሄያት/የቃላት አጻጻፍ የፊደል ስሕተት ሊሠራባቸው አይችልም። ስለዚህም ከላቲን ፊደል ይልቅ ግዕዝ የበለጠ ይመረጣል፣ ይልቃልም።

ኤርትራውያን መቼ የግዕዝን ፊደል አንፈልግም አሉ? እንዲያውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር፣ በላቲን እንቸክችከው ቢሉ፣ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በኋላ ግን ግዕዝ መሻሉን ተገንዝበው ወደ ግዕዝ ተመልሰዋል። ግዕዝ የአማራ ማሕበረሰብ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቅርስ ነው። ከአረብኛ ውጭ ብቸኛው ጥንታዊ የጥቁር ሕዝብ ፊደል ነው። አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ፣ ሃዲይኛ፣ ከንባትኛ፣ ኑኧርኛ፣ አኝዋክኛ፣ አገውኛ፣ አደሪኛ፣ ስልጢኛ.. በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ፊደላትን ነው የሚጠቀሙት። አደሪኛ ተናጋሪዎች ለአስር ዓመታት ላቲን ይጠቀሙ የነበረ ቢሆንም ግዕዝ ይሻላል ተብሎ ወደ ግዕዝ ተዙሯል።

ኢትዮጵያ በአባቶቻችንና እናቶቻችን መስዋዕትነት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች አገር ናት። የራሷ ባህል፣ የራሷ ቋንቋዎች፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ቅርሶች አሏት። በአገራችን የሌለን ነገርና፣ ለአገር የሚጠቅም ከሆነ፣ ከባእድ አገር ብንወስድ ችግር አይኖረውም። ሆኖም ግን የተሻለ ነገር ከእኛ ጋር እያለ የሌሎችን ማምጣት ተገቢ አይደለም። ፊደል እንደሌለንና ቅኝ የተገዛን ይመስል፣ የእኛን የተከበረ ፊደል ጥለን ላቲንን ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጠቀም አግባብ አይደለም።

ስድስተኛየግዕዝ ፊደላትን ለኦሮምኛ ስለመጠቀም።

አፋን ኦሮሞ በላቲንም በግዕዝም ይጻፋል። በኦሮሞ ክልል በተለይም ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የተወለዱ ወገኖች አፋን ኦሮሞን በላቲን ነው የሚጽፉትና የሚያነቡት። ሆኖም ላቲኑ በጣም ውስንነት አለው። በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ሌሎች ማሕበረሰባትና ከአርባ ዓመት በላይ የሆኑ ኦሮሞዎች ግዕዝ ፊደልን ማንበብ ነው የሚቀናቸው። ቋንቋው በላቲኑ ምክንያት በኦሮሞ ክልል የከተወሰኑ ወገኖች አጥር ውጭ ሊያድግ አልቻለም።

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ለክቡርነትዎ በታህሳስ ወር ፳፻፲ ዓ.ም. በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ ለኦሮምኛ ከላቲን ይልቅ ግዕዝን መጠቀም ምን ያህል በቃላት ቁጠባ፣ በትምህርት ቅልጥፍና፣ በቋንቋ ጥናት ጥበብ እና በሳይንስ አንጻር የተሻለ መሆኑን አስነብበውናል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የጻፉትን፣ ዶ/ር ኣበራ ሞላ እና ሌሎች በርካታ ምሁራን ያደረጉትን ጥናት በተወሰነ መልኩ ያካተተ ተያያዥ ሰነድ ማቅረባችን ይታወሳል። ይኸው ሰነድ ተሻሽሎ ከእዚህ በታች ቀርቧል።

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጐመው የኦሮምኛ መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ የተወሰዱ ሁለት ገፆችን አብረን አያይዘናል።

ክቡርነትዎ ሆይ!

እርስዎ እንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪቃውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝብ ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም። በእዚህና እላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለ ክብራችንና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ አፋን ኦሮሞ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደመሆኑ በኢትዮጵያዊ ፊደል በግዕዝ እንዲጻፍ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቅዎታለን። በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ፣ በግዕዝ ፊደላት “መጫፈ ቁልቁሉ” የኦሮምኛ መጽሓፍ ቅዱስ ተተርጕሟል። የዛሬ ፻፳ ዓመት እንኳን፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን፣ አሁንማ በዘመነ-ቀመር፣ በቀላሉ ኦሮምኛን በግዕዝ ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለችግር መክተብ የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም። ዋናው ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራትና ፍላጎት ናቸው!!

ከታላቅ አክብሮት ጋር፣

  1. መምህር ልዑለቃል አካሉ
  2. ዶ/ር ኣበራ ሞላ
  3. ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ
  4. ፕ/ር ማሞ ሙጬ
  5. ፕ/ር ባዬ ይማም
  6. ፕ/ር ኀይሌ ላሬቦ
  7. ዶ/ር አክሎግ ቢራራ
  8. ዶ/ር አበባ ደግፌ
  9. የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ
  10. አቶ ያሬድ ጥበቡ
  11. አቶ ሰይፉ አዳነች ብሻው
  12. አቶ ተፈራ ድንበሩ
  13. አቶ ብርሃኑ ገመቹ
  14. አቶ አብርሃም ቀጄላ
  15. አቶ ታደሰ ከበደ
  16. ወ/ሮ እስከዳር አውላቸው
  17. አቶ ተመስገን መኩሪያ
  18. አቶ ግርማ ካሳ

ግልባጭ፣

ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኣአማራ ክልላዊ መንግሥት ሊቀመንበር

ግዕዝና ኦሮሚፋ በሚል ርዕስ ግዕዝ ለኦሮሚፋ ጠቃሚነት የቀረበ ታሪካዊና ሳይንሳዊ ጽሑፍ።

ግዕዝ በዶክተር ኣበራ ሞላ ኮምፕዩተራይዝድ ሆኖ ለኣማርኛ ተመድበው ከተረፉት ሦስት መርገጫዎች ኣንዱ ለኣፋን ኦሮሞ (Afan Oromo) ሲሆን ሌላው ለትግርኛ ተሰጥቶ የቀረው ለኣገው/ቢለን ሥራ ላይ ውለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ጊዜ የኣንድ ድርጅት ኦሮሞ ምሁራን ተሰብስበው ከግዕዙ ይልቅ ላቲን ይበጀናል በማለት ግዕዙን (Ethiopic Oromo syllabary) ስለተዉት የሚከተሉትን መጋራት ሳይጠቅም ኣይቀርም።

፩. ጥንትም ቢሆን ፊደላት በእጅ ጽሑፍ ሲጻፉ ላቲን ከግዕዙ በፍጥነት የተከተበበት ጊዜ ኣልነበረም። ምክንያቱም ግዕዝ ኣንድን ድምጽ በኣንድ ቀለም ሲያሰፍር ለኣብዛኛው የላቲን ድምጾች ሁለት ቀለሞች ስለሚያስፈልጉት ነው።

፪. የላቲንና ግዕዝ ቀለሞች በማተሚያ መሣሪያዎች ሲከተቡ የሁለቱም ቀለሞች መረጣዎች ኣጠቃቀሞች እኩል ነበር። በእዚህ ዘዴ የኦሮምኛ ዓማርኛ መተርጐሚያ (Lexicon) በ1850 ግድም በኣቶ ሓብተ ሥላሴ ታትሟል። [886] መጽሓፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የመተርጐሙንም ሥራ በማስፋፋት ከሌሎች የቋንቋው ተናጋሪዎች ጋር (ዋሬ፣ ሩፎ፣ ሾለን፣ ጀገን እና ገብረሚካኤል) በመተባበር ሙሉውን ኣዲስ ኪዳን ወደ ኦሮምኛ ተርጕመው በሰኔ 1862 ዓ.ም. ኣገባደዱ። ይህም ትርጕማቸው ለኦሮምኛ ሥነጽሑፍ የመጀመሪያው ኣዲስ ኪዳን መሆኑ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ሚስዮኑ ክራጵፍ (J.L. Krapf) በ፲፰፻፸፩ ዓ.ም. በራሱ ስም ያሳተመው ይህንኑ የነኣለቃ ዘነብን ፲፰፻፷፪ ዓ.ም. ሥራ “ቁልቁሎታ መጻፎታ ከኩ ሐረዋ” ነበር። [887] ኣለቃ ዘነብ ወደ ፲፰፻፸ ዓ.ም. ግድም የ“ኦሮምኛና ኣገውኛ መዝገበ ቃላት” ጽፈዋል ይባላል። የኣስቴር ጋኖን የትርጕም መጽሓፍ በመጠቀም በ፲፰፻፹፯ ዓ.ም. የታተመም የኦሮምኛ ሓዲስ ኪዳን[888] መጫፈ ቁልቁሉ በ፲፰፻፺፱ እ.ኤ.ኣ. (፲፰፻፺፪ ዓ.ም.) በቅዱስ ኦነሲሞስ ነሲብ[889] [890] እና ከእዚያም ወዲህ እንደነ በሪሳ የኣሉ ጋዜጣዎች በግዕዝ ፊደል በኦሮምኛ ታትመዋል። ቀደም ብሎም በግዕዝ ፊደል በኦሮምኛ ከቀረቡት መረጃዎች ኣንዱ ጀምስ ብሩስ የወሰደው የ1790 የኦሮምኛ ትርጕምና የኢዘንበርግ ጽሑፍም ኣለ። [891]

፫. በዶክተሩ ኮምፕዩተራይዝድ የሆነው ግዕዝ እ.ኤ.ኣ. በ1987 ለገበያ ቀርቦ በማተሚያ ቤቶች ፊደላት መክተብ ስለተጀመረ ምሁራን ደስ ሊላቸውና ሳይንሱንና ቴክኖሎጅውን ማወቅና ማስተዋወቅ በተገባ ነበር። ይህ በኣለመደረጉ እ.ኤ.ኣ. በ1992 [892] በፕሮፌሰር ጥላሁን ጋሜታ ወደ ላቲን ለማዞር ከቀረቡት የኣማርኛ የጽሕፈት መኪናን የሚመለከቱት ጊዜ ለኣለፈባቸው ምክንያቶች መልሶችም ነበሩ። [893] [894] [895] ስለዚህ በግዕዝ ፊደል በማተሚያ ፊደላት ሲጻፉ የነበሩት በኮምፕዩተር ስለቀረቡ ቴክኖሎጂው ስለተሻሻለና ስለቀለለ ጉዳዩ ይመለከተናል የኣሉት የኦሮሞ ምሁራን ሊደሰቱ የሚገባ እንጂ ወደ ላቲን የሚያስዞር ኣዲስ ምክንያት ኣልነበረም። በጊዜውም በፕሮፌሰር ባዬ ይማም በዓማርኛ መልስ ቀርቦ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽና ፕሮፌሰር ሳሙኤል ክንዴ ወደ እንግሊዝኛ ተርጕመውታል። [896]

፬. ላቲን የእራሱ ችግሮች የኣሉት ፊደል ነው። [897] [898] [899] [900] በዶክተሩ ግኝት እየኣንድኣንዱን የግዕዝ ቀለም በሁለት መርገጫዎች መክተብ ተችሏል። ላቲን ይኸን እየኣንዳንዱን የግዕዝ ቀለም በሁለት መርገጫዎች የመክተብ ችሎታ ስለሌለው ግዕዝን በግዕዝ ፊደል መክተብ ብልጫ ኣገኘ። ስለዚህ ኦሮምኛን በላቲን ፊደል መክተብ (ቁቤ) መሻሻል ኣይደለም።

፭. የኦሮምኛው የግዕዝ ፊደል ከሌሎቹ ጋር በዶክተሩ ኮምፕዩተራይዝድ ስለሆነ [901] ለኣለፉት ፴ ዓመታት በኮምፕዩተር ቀርቦ በኋላም በዩኒኮድ ዕውቅና ቢያገኝም [902] ሁሉም ባይሆኑ ኦሮሞዎች ግዕዙን እርግፍ ኣድርገው ጥለው ወደ ላቲኑ ስለዞሩ የተፈጠሩት ችግሮች ቀጥለዋል።

፮. በእጅ የጽሕፈት መሣሪያ ዘመን ታይፕራይተር ኦሮምኛን ለማስጻፍ ስለኣልቻለ ላቲን ብልጫ ነበረው። የዶክተሩ ግኝት ለእውሸቱ (የፈጠራ) የታይፕራይተር የአማርኛ ነገሮችና ለትክክለኛዎቹ የማተሚያ ቤቶች ፊደላት ኣጠቃቀሞች አጅግ ትልቅ ፈውስ (Breakthrough) ነበር። የታይፕራይተር ፊደል ለታይፕራይተር ሲባል የተሠራ በፍፁም ትክክለኛ በኣለመሆኑና ለብዙ ምዕት ዓመታትም በእጅ ስንጽፈው የነበረው ከኣለመሆኑም ሌላ የማተሚያ ቤት ፊደላችንም ስለኣልሆነ ከቁርጥራጮች የሚሠራውን ብጥስጥስ ዶ/ር ኣበራ እውሸት ፊደል ይሉታል። ስለ ታይፕራይተሩ ድክመት ዶክተሩ እ.ኤ.ኣ. በ1991 [903] [904] ስለኣቀረቡ መሣሪያው ወደ ቁቤ ለመዞር ምክንያት መሆን ኣልነበረበትም። ከእዚያም ወዲህ በኮምፕዩተር የኦሮምኛው የግዕዝ ፊደል በዶክተሩ መከተብ መቻልና የተጠቃሚዎች መኖር ግንዛቤ ውስጥ ሳይገቡ ብዙ ዓመታት ባክነዋል። ቴክኖሎጂ የችግር መፍቻ እንጂ ከችግር መሸሽያ ኣይደለም።

፯. ቁቤ በላቲን ዋየሎች ከሚጠቀምባቸው በተሻለ ኣፋን ኦሮሞ በግዕዙ ሊጠቀም ይችላል። ኦሮምኛን በፊደል ለመክተብ ከላቲኑ ቁቤ የግዕዝ ፊደል ይጠቅማል። [905] [906]

፰. መጽሓፍ ቅዱስ በከፊል እ.ኤ.ኣ. በ1841 በኦሮሞ ቋንቋ በግዕዝ ፊደል ተጽፏል። [907] [908] እንዲሁም እ.ኤ.ኣ. በ1875 የኦሮሞ ሓዲስ ኪዳን በግዕዝ ፊደል ታትሟል። [909] [910] [911]

፱. በልሳነ ግእዝና በኣፋን ኦሮሞ (ግእዚፊ ኣፋን ኦሮሞቲን – Giiiziifi Afaan Oromootiin) የተዘጋጀው መጽሓፈ ቅዳሴ – ክታባ ቅዳሴ – Kitaaba Qiddaasee መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል ተመርቋል። የትርጐማና የኣርትኦት ሥራው 10 ዓመታት የወሰደው ባለ ሦስት ዓምዱ ክታበ ቅዳሴ፦ የመጀመርያው ረድፍ በግእዝ ቋንቋ፣ ሁለተኛው ረድፍ በኦሮምኛ ሆኖ በግእዝ ፊደል፣ ሦስተኛው ረድፍ በኦሮምኛ ሆኖ በቁቤ ፊደል ተጽፏል ይላል ሪፖርተር ጋዜጣ። [912] ይህ የግዕዝ ፊደል ኦሮምኛን ኣይጽፍም ለሚሉት ማፈሪያ ነው።

፲. መጽሓፍ ቅዱስ ሙሉዉን ወይም በከፊል ከ፲፭፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ በግዕዝ ቀለሞች በማተሚያ ቤቶች ከታተሙባቸው ቋንቋዎች መካከል የግዕዝ ቋንቋ (ግዕዝኛ)፣ ዓማርኛትግርኛኦሮምኛ [913] [914] [915]ሃዲያሲዳሞከንባታወላይታጌዴኦ ይገኙበታል። ስለዚህ ለዓመታት በማተሚያ ቤቶች የግዕዝ ፊደላት ሲከተብ የነበረው ኦሮምኛ ኮምፕዩተራይዝድ ሆኖ ዛሬ ሥራ ላይ እየዋለ ግዕዝ ኦሮምኛን ኣይጽፍም ማለት ሳይንስ ኣይደለም።

፲፩. በኣነሰ የኆኄያት ግድፈቶች (Spelling / እስፔሊንግ) እና ስፍራዎች (Spaces) ማስከተብ ብልጫዎች የነበረው የግዕዝ ፊደል በዶ/ር ኣበራ ግኝት የተነሳ የግዕዝ ፊደል ሓሳብን በኣነሰ ጊዜ (Time)፣ መርገጫዎች (Keystrokes) እና ገበታዎች (Keyboards) በኮምፕዩተሮችና የእጅ ስልኮች በማስከተብ ብልጫዎቹ ወደ ኣምስት ዓይነቶች ከፍ ብለዋል። ለምሳሌ ያህል “ዘ ኲክ ብራውን ፎክስ ጃምፕስ ኦቨር ዘ ሌይዚ ዶግ።” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ላቲን በ36 ቀለሞችና በቁቤ በ45 ቀለሞች ከመክተብ ይልቅ በግዕዝ ፊደል በ24 ቀለሞች መክተብ የተሻለ ነው።

፲፪. የቁቤ ሥርዓት እ.ኤ.ኣ. በ1992 ገደማ የተመሠረተው ኣንዱ ቀለም ኣንድን ድምጽ በመወከል ነው ተብሏል። የላቲንም ሆነ የቁቤ ቀለሞች ኣንድን ድምፅ በኣንድ ቀለም ከሚወክለው የግዕዝ ፊደል ጋር የመወዳደር ችሎታ የላቸውም። ላቲን ኣንድኣንድ ድምጾችን የሚከትበው በሁለት ቀለሞች ስለሆነ ሁሉም ቀለሞች ለየብቻቸው ኣንድ ድምጽ እንዲወክሉ እንኳን ተደርጎ መጠቀም ኣይቻልም። ለምሳሌ ያህል “d” እና “h” የ“ዽ” እስፔሊንግ ስለሆኑ “ዲ” እና “ኤች”ን በሁለት ቀለምነት ጎን ለጎን ኣስቀምጦ በ“d” እና “h” ድምጽ ሰጪነት መጠቀም ኣይቻልም። ይህ ምሳሌ የሚያሳየው ቁቤ የተመሠረተው በጥቂት የኦሮሞ ምሁራን ማምታታትም ላይ መመርኰዙን ነው። ሌላ ምሳሌ ግዕዝ ማጥበቂያ (Long Vowels / Germination) የለውም የሚባለው ነው። [916] ለግዕዝ ዋየል ስለማያስፈልገውና ስለሌለው የሚያጠብቀው ዋየል ስለሌለው ኣንድ ቀለም የሚበቃውን የግዕዝ ማጥበቂያ ትቶ ለማጥበቅ ሲባል ወደ ኣሥር የላቲን ዋየሎች መዞር ኣያታርፍም። ለላቲን የሚያስፈልጉትን ረዣዥም ዋየሎች ግዕዝ ስለሌለው ኦሮምኛን በላቲን ለመክተብ መረጥን ለሚሉት ሰበቡ ሳይንሳዊ ስለኣልሆነ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ ዶክተር ኣበራ። የግዕዝ ፊደል በብዛቱ እየተወቀሰ ከእዚያ በበዙ መተካት መሞከር ትክክል አይደለም። የተለያዩ ምክንያቶች በማቅረብ የግዕዝ ፊደል ኦሮምኛን ኣይጽፍም የኣሉትን እንደተሳሳቱ ሳይጠቅሱ ኣሁንም መጥቀስ ስለጉዳዩ ኣሁንም የሚጽፉት ጥቂት ምሁራን እራሳቸውን ማረም እንዳልቻሉ ያሳያል። ወደ ላቲን የተዞረው ያለበቂ ጥናትና ሕዝቡ ሳያውቅና ሳይመርጥ በእውሸት ሕዝብ መረጠው ተብሎ ነው።

፲፫. ማንኛውንም የኦሮሞ ፊደል በሦስት መርገጫዎች መክተብ ነውር ነው። ማንኛውንም የኦሮምኛ ድምጽ በሦስት መርገጫዎች መክተብ ነውር ነው። ምክንያቱም ግዕዝ በኮምፕዩተር ኣይጻፍም ተብሎ የኣማርኛ ታይፕራይተር ማጓጓዝ ችግር ነው ተብሎ በቀረበበት ጊዜ እየኣንድኣንዱ የኦሮምኛ የግዕዝ ቀለም በኮምፕዩተር በሁለት መርገጫዎች እየተከተበ ነበር። ምንም እንኳን ግዕዝ እንከን የማይወጣለት ፊደል ነው ማለት ባይቻልም ለኣንድ ድምጽ ኣንድ ቀለም ለመመደብና ኣንድን ቀለም ለኣንድ ድምጽ ለመመደብ የተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል።

፲፬. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን ዓማርኛ የማጥበቂያ ምልክት የለውም የሚሏቸውን ስሕተቶች ቀጥለውበታል። ዓማርኛ መጥበቅ የኣለበትን ቃል ከማይጠብቀው የሚለይበት ሁለት ዘዴዎች ኣሉት። ከእነዚህ ኣንዱ ከሚጠብቀው ቀለም ኣናት በላይ ኣንድ ነጥብ መክተብ ሲሆን ምሳሌውም በ፲፮፻፺ ዓ.ም. ታትሟል። ለምሳሌ ያህል “ላላ‘” እና “አላላ‘” ገጽ 1 እና “መነ‘ሣት” ገጽ 50 ላይ ቀርበዋል። [917] ይኸንንም ኣጠቃቀም ሓዲስ ዓለማየሁ [918] በ“ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሓፋቸው ኣስፋፍተውታል። በኣዲስ ቅርጽ ለኮምፕዩተር እንዲስማማ መጥበቅ ከኣለበት ቀለም ኋላም እንዲከተብ ተደርጎ ማጥበቂያና ማላልያ በዶክተሩ ፓተንትም ውስጥ ኣ.ኤ.ኣ. በ2009 ተጠቅሰዋል። [919]

፲፭. የቁቤ ዋየሎች “ኤ”፣ “ኢ”፣ “ኣይ”፣ “ኦ” እና “ዩ” (“a”፣ “e”፣ “i”፣ “o” አና “u”) ስለሆኑ በቁቤ “ክታበ”ን ከ“ኪታባ” የመለየት ችግሮች ኣሉት። ይህ በኣዲስ ፊደልነት የቀረበውንም በብዛት ከግዕዝ ፊደል የበለጠውንም [920] ይመለከታል። ግዕዝ ሰባት እንዚራን ሲኖረው ኦሮምኛ 10 ያስፈልጉታል የተባለው ትክክል ከኣለመሆኑም ሌላ ቍጥሩን መጨመርም ስለኣላዋጣም ኣልቀጠለም። ትክክለኛው የግዕዝ ኣጻጻፍ “ኣፋን” እንጂ “አፋን” ኣይደለም።

፲፮. ይህ ግዕዝና ኦሮሚፋ ሳይንሳዊ ጽሑፍ ስለ ፊደላቱ እንጂ ቋንቋዎቹን ኣይመለከትም። የኦሮሞ ቋንቋችን መዳከም ስለሌለበት ስለ ፊደል ስንወያይ ሰለ ቋንቋና ሰለኣልፈጠርናቸው ኦሮሞነት መቀላቀል ሳይንስ ኣይደለም።

፲፯. እነ “ሸ”፣ “ቸ”፣ “ኘ”፣ “ዸ”፣ “ጠ”፣ “ጨ”፣ “ጰ”፣ እንዚራኖቹንና ሌሎች ቀለሞች የኣሉትን ለኦሮምኛ የሚያስፈልጉትን ቀለሞች ትቶ እነዚህን ወደ የሌሉት የላቲን ፊደል መዞር ሳይንስ ኣይደለም። [921]

፲፰. የኦሮምኛ ድምጾችንና እርባታዎችን የሚወክል የፊደል ገበታ (ከኣማርኛ ታይፕራይተር፣ ዓረብኛላቲን) ለጊዜው የተሻለው ላቲን ነው በማለት በስሕተት የቁቤ ኣጻጻፍ ሥራ ላይ ዋለ። ይህ ለዓማርኛው በኣለመደረጉ ዶክተሩ በመፍትሔው የደረሱለት ለኣፋን ኦሮሞ ጭምር ነው። ምክንያቱም ዓማርኛና ኣፋን ኦሮሞ በትክክለኛው የግዕዝ ፊደል ለብዙ ምዕት ዓመታት ተጠቅመዋል። [922] የጄምስ ብሩስና ሌሎች መረጃዎችም ኣሉ። ስለዚህ ዓማርኛውንም ሆነ ሌሎችን ቋንቋዎቻችን ለማይጽፈው የዓማርኛ ታይፕራይተር ሲባል ፊደሉን የተዉት ቋንቋዎች በኣንድኣንድ ተናጋሪዎች ስሕተት እንጂ በግዕዝ ፊደል ሲጠቀሙ በነበሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስሕተት ኣልነበረም።

፲፱. በዶክተሩ ግኝቶች ከ”አ” እና “ኸ” መርገጫዎች ፲፬ የግዕዝ ቀለሞች እየተከተቡ ናቸው። [923] [924]

፳. ቁቤ በ“a”፣ “e”፣ “i”፣ “o” እና “u” በተጠቀመው ዓይነት በ“ኣ”፣ “ኤ”፣ “ኢ”፣ “ኦ” እና “ኡ” የግዕዝ ቀለሞች መጠቀም ይችል ነበር። ኣንዳንድ ኦሮሞዎች “ቢራ” በላቲን ኦሮሚፋ “biirraa” ተብሎ የሚጻፈው ግዕዝ ስለማይችለውም ነው ይላሉ። በ“biirraa” ምትክ “ብኢኢርርኣኣ” ተብሎ በግዕዝ ፊደል መጻፍ ይቻላል። ስለዚህ ቁቤ የተመሠረተው ሳይንሳዊ ጥቅም ላይ ኣይደለም። “ቢ” እና “ራ” ቀለሞችን ዓማርኛ በኣራት ዓይነቶች ማለትም “ቢራ”፣ “ቢ’ራ”፣ “ቢራ’” አና “ቢ’ራ’” መጠቀም ይችላል። ለምሳሌ ያህል “ለቅቆ” የሚለውን ቃል “ለቅቆ” ወይም “ለቆ” ዓይነቶች መክተብና ማጥበቂያዎች መጨመርም ይቻላል።

፳፩. ኣንድኣንድ የኦሮሞ ምሁራን ግዕዝ የኦሮምኛ ቃላትን ኣይጽፍም በማለቱ በኣለማወቅ በስሕተቱ ገፍተውበታል። ጎዸቱ፣ ቶኮፋዸ፣ ዹፌ፣ ዹጉማ፣ ጀዺ፣ ዻባ፣ ዻራርቱ፣ ባዻዻ፣ ዻዻ፣ ጄዼ፣ ዼራ፣ ዽባፍ፣ ዽባ፣ ነንዾከዼስ ምሳሌዎች ናቸው።

፳፪. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን “ዻ” የግዕዝ ኦሮምኛ ቀለም በኣንድ ቀለም በሁለት መርገጫዎች ከመክተብ ይልቅ “dha” በማለት በሦስት ቀለሞችና በሦስት መርገጫዎች በኦሮሚፋ መክተብ የተሻለ ሳይንስ ይመስላቸዋል። ኣንድኣንድ የግዕዝ ቀለሞችን በላቲን ለመለየት ሦስትና ከሦስት በላይ ቀለሞችን መደርደር ያስፈልጋል። ግዕዝ ለኣዳዲስ ድምጾች ፊደል ሲፈጥር ቁቤ ለኣለው ፊደል ሌላ ድምጽና እስፔሊንግ በመጨመር መሻሻል ስለሚፈልግ ችግሩን ያባብሳል። ግዕዝን በላቲን እስፔሊንግ ለመጻፍ የሞከሩትም ጥቂቶቹን እስከኣሁን የኣዋጣቸው የሕዝቡ ስለቴክኖሎጂው በሚገ’ባ ኣለመረዳት ነው።

፳፫. በሚገባ ሳይታሰብበት የግዕዝ ቀለሞች በላጭነትና ጥቅሞች ሳይገለጹ ታልፈዋል። ምሳሌ፦ ግዕዝ ችግር የለውም ማለት ሳይሆን የላቲን ቃላት እስፔሊንግ እድሜ ልክ ቢማሩትም ማስታወስ ኣይቻልም። በእዚህ ላይ “ኦሮሞ” የሚለው ቃል እስፔሊንግ በላቲን “Oromo” በኦሮሚፋ የኣለ በቂ ምክንያት “Oromoo” ነው። ግዕዝ ለኣዳዲስ ድምጾች ኣዳዲስ ቀለሞች እየፈጠረ የማደግ ችሎታ ኣለው። [925] [926]

፳፬. በኣጠቃቀም የላቲን ፊደል ከግዕዝ ሳድሳን ቀለሞች ጋር ኣንድ ዓይነት ነው። ግዕዝ እንዚራኑን በኣንድኣንድ ቀለሞች ሲወክል ላቲን ዋየሎቹን ሳድሳኑ ጎን ማስከተብ ስለኣለበት ከሰባት ጊዜ በላይ እጥፍ ስፍራዎችን ያስባክናል። ይኸንን የግዕዝ ምሳሌ የ“ገ” እንዚራን በላቲን በመክተብ ልዩነቱን መመልከት ይቻላል።

፳፭. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን በስሕተት ኦሮሚፋ 10 እንዚራን ሲያስፈልገው ግዕዝ ሰባት ብቻ ኣለው ይላሉ። ዋየል መደራረብ ትርፉ ስፍራ ማባከን ነው። [927] ለምሳሌ ያህል “ዸ”ን በኣሥር ዋየሎቹ ለመክተብ ለቁቤ ላቲን 35 ቀለሞች ሲያስፈልጉት ለግዕዙ 15 በቂ ናቸው።

፳፮. ጥቂት የኦሮሞ ምሁራን በስሕተት ላቲን 26 ቀለሞች ሲኖሩት [928] የግዕዙ ብዙ ናቸው ይላሉ። የላቲን “a” ዓይነቶች ከ26 በላይ ናቸው።

፳፯. ግዕዝ በእጅ ኣይጻፍ ይመስል ስለላቲኑ የእጅ ጽሑፍ (Cursive) የሚያነሱም ኣሉ። ዶክተሩ ኦሮምኛን በግዕዝ ፊደል በኮምፕዩተር ለመክተብ የሚያስፈልጉትን ከሠሩ በኋላ ለ24 ተነባቢና 10 ዋየሎቹ የኦሮምኛ ፊደላቱ 34 ቀለሞችን መፍጠር ስለሚያስቸግርና ኣስፈላጊ ኣይደለም ተብሎ ወደ ላቲን ዞርን ከቀረቡት ምክንያቶች ኣንዱ ነበር።

፳፰. ግዕዝ እንደኦሮሚፋ የኣሉትን (ኩሻዊ) ቋንቋዎችን [929] ጥሩ ኣድርጎ ኣይጽፍም የሚለው ወይም የግዕዝ ኣንድን ድምጽ በኣንድ ቀለም መወከል እንደችግር ተቆጥሮ ወደ ላቲን ለመዞር የቀረቡት ምክንያቶች ወደ እውነት የተጠጉ ኣልነበሩም። ግዕዝ ለኣንድ ድምጽ ኣንድ ቀለምና ኣንድን ቀለም ለኣንድ ድምጽ በማድረግ የተራቀቀ ፊደል ነው።

፳፱. በግዕዝና በላቲን የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን በየእለቱ እየተራራቁ ናቸው።

፴. ኣይርላንዳዊው በርናርድ ሿው ግዕዝን ዓውቆ ቢሆን ኖሮ ላቲን ቦታ ኣይኖረውም ነበር የሚል ጽሑፍ በሰይፉ ኣዳነች ቢሻው እዚህ ቀርቧል። [930] የላቲን ፊደል ለእየኣንድኣንዱ ድምጽ ኣንድ ቀለም እንዲኖረው ተመኝተው ነበር። ላቲን የኣልተሟላና ኣክሳሪ ፊደል መሆኑንም ሿው ገልጸዋል። [931]

 

(ቀደም ሲል ፕ/ር ፍቅሬ ለሊቀመንበር ለማ የጻፋትን ከእዚህ በታች ኣያይዘናል።)

 

ለፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሁለተኛ ግልፅ ደብዳቤ

 

ጉዳዩ — ኦሮምኛን የእራሱ በሆነው በግዕዝ ፊደል ተጓዳኝ የፌዴራል ቋንቋ ስለማድረግ ተገቢነት

 

ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ

 

ክቡር ፕሬዚደንት ሆይ

 

ክቡርነትዎ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው፣ ከአማርኛ ቀጥሎ ኦሮምኛ በሚሊዎኖች ኢትዮጵያውያኖች የሚነገር ትልቅ ቋንቋ ነው። ሆኖም እስክ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ አያውቅም። ካናዳ የተባለውን ሃገር እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ሁለት ብሄራዊ ቋንቋዎች አሉት፣— እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ። የካናዳ ህዝብ፣ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች ሁለቱን ቋንቋዎች ይችላሉ። ቋንቋዎቻቸው እኩል ተከብረው የፌዴራል መሥሪያ በመሆናቸው የካናዳ ህዝቦች በእዚህ ረገድ የእኩልነት ስሜት የሚሰማቸው እና የረኩ ናቸው። በኢትዮጵያም ደረጃ ኦሮምኛም ከአማርኛ ጋር በተጓዳኝነት የፌደራል ቋንቋ ቢሆን ብዙ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ጥቅም ይኖረዋል። ይህን ግንዛቤዎ ውስጥ አኑረው ኦሮምኛ ተደራቢ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ ይሆን ዘንድ እርስዎ እና የሃገር አስተዳደር ባልደረቦችዎ የሚቻላችሁን ታደርጉ ዘንድ አሳስባችኋለሁ።

ካለፉት 30 ዓመት ወዲህ የተወለዱና የማስተማሪያ ቋንቋቸውን ኦሮምኛ ብቻ ባደረጉ የትምህርት ተቋማት የተማሩ የኦሮሞ ወጣቶች ሥራ ማግኝትን አስመልክቶ ተጎጂዎች ሆነዋል። እነዚህ ወጣቶች በክልላቸው መንግሥት የተነገራቸውን ተቀብለው በኦሮሚፋ ብቻ በመማር የትምህርት ጊዜያቸውን አባከኑ። በርካታዎቹ በትምህርታቸው በጥሩ ውጤት ከተመረቁ በኋላ ግን በፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ስለማያነቡና ስለማይጽፉ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙት የሥራ ዕድሎች ተወዳዳሪና ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። ሌሎች ዜጎች የሚያገኙትን ዕድል ያለጥፋታቸው የኦሮሞ ልጆች አጡ። በወቅቱ የነበሩት የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪዎች ብልሆች ቢሆኑ ኖሮ የሚፈጠረውን ችግር አስቀድመው ገምተው የደቡብ ህዝቦች፣ ተጋሩዎች እና ሌሎቹም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንዳደረጉት ልጆቻቸው አማርኛን እንደ ተደራቢ ቋንቋቸው እንዲማሩ አድርገው የሥራ ዕድላቸውን ባሰፉላቸው ነበር። ያለፈው ቢያልፍም፣ ለዘለቄታው ግን ለእዚህ ሁሉ የተሻለ መፍትሄ የሚሆነው ኦሮምኛ ተደራቢ የማእከላዊ መንግሥት ቋንቋ ቢደረግ ነው።

ከእዚህ ጋር በተያያዘ፣ ይህስ ደግ ነው፣ ዳሩ ግን ኦሮምኛ በምን ፊደላት ይከተብ፣ የሚል ጥያቄ ሊከተል ይችላል፣— በባእዱ በላቲን ወይስ በሃገር-በቀሉ ኢትዮጵያዊ ፊደል? በእኔ እና በሌሎችም ምሁራን ምርምር ውጤት መሰረት፣ ከላቲን ይልቅ፣ በተለምዶ ግእዝ በሚባለው፣ እንደ እውነቱ ግን ኢትዮጵያዊ ፊደል መሰኘት በሚገባው ፊደል ኦሮምኛ ቢፃፍ እጅግ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። ይህን አባባሌን ዝቅ ብዬ በማስረጃ አንተርሳለሁ።

የሚከተለውን የቁቤ ጽሁፍ ወስደን ከግእዝ እና ከላቲን ፊደል የትኛው ይበልጥ ውጤታማና ብቁ እንደ ሆነ እንመለከታለን፡-

Uummanni Oromoo ilmaan namaa biyya lafaa ኡመኒ ኦሮሞ ኢልማን ነማ ብያ ለፋ

Kanarratti Uumaman kessaa tokkodha Biyyi ከነረቲ ኡመመን ኬሳ ቶኮዳ ብዪ

Uumamaa fii jireenya issa Aafrikaa Bahaa ኡመማ ፊ ጅሬኘ ኢሳ አፍሪካ በሃ

Gara kaabaatti Yemmuu ta’u Uummmata ገረ ካባቲ የሙ ተኡ ኡመተ

Akata Sabaatti baay’ina gudda qabu kan አከ ሳባቲ የሙ ተኡ ኡመተ

Baha gaanfa Aafrikaatti argamu keessaa ባሃ ጋንፋ አፍሪካቲ አርገሙ ኬሳ

Isa tokko Seenaan uummata kanaa akkuma ኢሳ ቶኮ ሴናን ኡመተ ከና አኩማ

Sabaaf sab-lammaota Aafrikaa heddu namnii ሳባፍ ሳብ ላሞታ አፍሪካ ሔዱ

Seeraaf sirnaan qulqulleessee barreesse ሴራፍ ሰርናን ቁልቁሌሲ በሬሴ

Jiraachun baatullee uummata seenaa ጂራቹ ባቱሌ ኡመተ ሲና

Gudddaa fii gaarii qabu akka ta’e huba ጉዳ ፊ ጋሪ ቀቡ አከ ተኤ ሁበ።

Chuun nama hin dhiba ቹን ነመ ሕን ድቡ።

ከላይ ከቀረበው ናሙና ውስጥ የተወሰኑ ቃላትን እየጠቀስን የኢትዮጵው ፊደል ኦሮምኛን ለመጻፍ ከላቲኑ እና ከኢትዮጵያው ፊደል የትኛው ብቁ፣ ቀልጣፋ እና ጊዜ እና ገንዘብ ቆጣቢ እንደሆነ እንይ፤

Uummanni Oromoo ilmaan namaabiyya lafaa “Uumamaa” የሚለው ቃል በላቲን ሲጻፍ 7 ሆህያት ፈጅቷል። በኢትዮጵያው ግን “ኡመማ” ተብሎ በ3 ፊደላት ይጻፋል። “oromoo” የሚለው ቃል በላቲን 6 ሆህያት አሉት፤ በግዕዝ ግን “ኦሮሞ” ተብሎ በ 3 ሆህያት ይጻፋል። “ilmaan” የሚለው በላቲን 6 ሆሄያት አሉት፤ በግዕዝ ግን አራት በቂው ነው። “namaa፣ biyya፣ lafaa፣” የሚሉትም ቃላት በላቲኑ እያንዳንዳቸው 5 ሆሄያት ፈጅተዋል። በግዕዙ ቢሆን ግን “ነማ፣ ቢያ፣ ለፋ” ተብለው እያንዳንዳቸወቅ በ 2 ፊደላት ይጻፋሉ። ኡመኒ ኦሮሞ ኢልማን ነማ ብያ ለፋ Kanarratt Uumama kessaa tokkodha Biyyi የሚሉትን ደግሞ ስናይ “Kanarratti” 3 በላቲን ሲጻፍ 10 ሆሄያት ያስፈልጉታል። በኢትዮጵያው ፊደል በግዕዙ ግን በ 4 ሆሄያት ይጻፋል። “Uumaman” በላቲን 7 ሆሄያት ያስፈልጉታል። በግዕዝ ግን 4 ሆህያት ይበቁታል። “kessaa” የሚለው በላቲን 6 ሆሄዎች ያስፈልጉታል። በራሳችን ፊደል ግን “ኬሳ” ተብሎ በ2 ፊደላት ይጻፋል። “Tokkodha” እና “Biyyi” የሚሉትም በላቲን እንደ ቅደም ተከተላቸው 7 እና 5 ሆህያት ሲኖሯቸው በግዕዝ ግን 3 እና 2 ሆሄዎች ብቻ ነው የሚኖራቸው።

ነገሩ በገጽ ሲታሰብ በላቲን 100 ገጽ የሚፈጅ ጹሁፍ በግዕዝ ግን በ40 ገጽ ሊጻፍ ይችላል። ብዙ ሺ ኮፒ ሲታተም በላቲን ሲሆን አላግባብ የሚባክነውንና በግዕዙ ሲሆን ግን የሚቆጠበውን ስንትና ስንት ቶን ወረቀት አስቡት። ጊዜንና ገንዘብን በተመለከተም እንዲሁ ነው። ለምሳሌ ባለ 100 ው ገፅ በላቲን የተፃፈው መፅሃፍ በ 100 ሳንቲም ቢታተም በግዕዙ የተከተበው ግን 40 ሳንቲም ብቻ ይሆናል። ሂሳቡ በሺ ብሮች ቢሰላ በላቲን ቢፃፍ 6000 ብሮች ማዳን ይቻላል ማለት ነው። የእዚህን ሁሉ ትርፍና ኪሳራ ዐይተው እርስዎ ይፍርዱ።

ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ቀለማት ቢፃፉ የተሻለ ነው ሲባል አንዳንድ የድሮ ፖለቲከኞችና የቅድሞ ታጋዮች የሚያቀርቡት ሰበቦች አንዳንድ የኦሮምኛ ቃላት በተለምዶ ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደላት ሊፃፉ አይችሉም፣ ለ ታይፕራይትርም አይመቹም፣ የሚሉ ናቸው። ይህ ግን እውነት አይደለም። ለምሳሌ አይቻሉም ተብለው የነበሩት ፊደላትና ቃላት በኦሮሚያዊትዋ ልጅ፣ በሰንዳፋው ተወላጅ በዶክተር አበራ ሞላ መላ እነሆ ተችለዋል።

ዸዹዺዻዼዽዾዿ ዹፌ፣ ዻባ፣ ዻራርቱ፣ ባዻዻ፣ ዼራ፣

ልክ እንደ ላይኛቹ ፊደላት እና ቃላት የኦሮሞ ቀለማት ሁሉ በኢትዮጵያ ፊደላት ተቀርፀው በተግባር ለመዋል እየጠበቁ ነው። እድሜ ለ ዶክተር አበራ ሞላ ከ እኤአ 1987 ጀምሮ በሶፍትዌር ደረጃ ተዘጋጅተው ገበያ ላይ ውለዋል። የ አንዱን ቃል ከሌላው መለያ የማጥበቂያ ምልክቶችም ተበጅቶላቸዋል። ዶክተር አበራ ሞላ የግዕዝ ፊደላት ለኦሮምኛ እና ለሌሎቹም ዋና ዋና ቋንቋዎቻችን መፃፊያ ብቁ እንዲሆኑ ለ 35 ዐመታት ያህል ለፍቶባቸዋል። ስለእዚህ የኢትዮጵያ ፊደላት የላቲኑን ሊተኩ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም። አውቆ የተደበቀን ቢጠሩት አይሰማም ካልተባለ በቀር። የኢትዮጵያ ፊደላት ኦሮምኛን ለመክተብ ብቁ ከመሆናቸውም በላይ ብዙ ጥቅም ያላቸው መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል። ለጊዜው ዊኪፔድያ ውስጥ ገብተው የዶክተር አበራ ሞላን የምርምር ውጤት ይመልከቱ። አስፈላጊ ከሆነ እኔ እና ዶክተር አበራ ከአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ባዩ ይማም እና ከ ከሌሎች ቋንቋ ተመራማሪዎች ጋራ ሆነን ሰሚናር ተዘጋጅቶልን ልንነጋገርባቸው እና ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥባቸው እንችላለን። ፕሮፌሰር ባዩ ይማምም በበኩላቸው በእዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ብለው ሰፊ ጥናት አካሂደዋል።

ለእኛ ለአሁኑ ዘመን ሰዎች አዲስ ነገር ይመስለናል እንጂ ለኦሮሞ አባቶቻችን በኢትዮጵያ ፊደላት መፃፍ አዲስ እንግዳ ጉዳይ አይደለም። በቅርቡ በደርግ ዘመን እንኳን በሪሳ የሚል ጋዜጣ ነበር። ከ ዛሬ 120 ዐመታት በፊት ቄስ ኦናሲሞስ ነሲብ ሙሉውን ቅዱስ መፅሃፍ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሃንስ ከትበውበት ነበር። ከዛሬ 200 ዐመት በፊትም እንደፃፉበት የሚያሳይ ሰነድ በ ቀጣፊው ጆግራፊ ላጠና ነው ብሎ መጥቶ ብርቅዬውን መፅሃፈ ሄኖክን ይዞ በኮበለለው በጀምስ በሩስ እጅ ተገኝቷል። በመጀመሪያ በኦሮሞው ተወላጅ በታላቁ ፓስተር በ ኦኔሲሞስ ነሲብ በግዝ ፊደላት ከተተረጎመው መፅሀፍ ቅዱስ ለናሙና ያህል ሁለት ገፆች ከእዚህ ፅሁፍ ግርጌ አስፍሬሎታለሁ።

ቀደም ሲል በግዕዝ ፊደላት በኦሮምኛ ስለተፃፉት ሰነዶች ሁሉ ጠቅለል አድርጎ ለመናገር፣1ኛ. ከ16ተኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተከተበ ቅዱስ ቁርአን በሀረር ይገኛል። 2ኛ. በ1845 ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በፊት የመፅሀፍ ቅዱስ ወንጌላት በከፊል የተፃፋበት 3ኛ. እላይ አንደጠቀስኩት 4 ከ120 አመታት በፊት በኦሮሞው ሊቅ በቅዱስ ኦኔሲሞስ ነሲብ (አባገመችስ) ሙሉው መፅሃፍ ቅዱስ በአፋን ኦሮሞ የተተረጎመበት 4ኛ. በ1967 አ.ም. ከ20 በላይ በሆኑ በተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ቋንቋ የመሬት አዋጅን ፈትፍቶና ቁልጭ አድርጎ የተገለፀበት 5ኛ. የኢትዮጵያ የመስረተ ትምህርት ከ30 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋዎች በብቃትና በጥራት ይሰጥበት የነበረ 6ኛ. የበሪሳ ታላቅ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጣ ለዘመናት በበርካታ ቁጥሮች ሲሰራጭበት የነበረ 7ኛ. የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በበርካታ ባብዛኛው ከ 45 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ ቋንቋዎች የተገለጡበት 8ኛ. በበርካታ የእስልምና ዝክሮች፣ መንዙማዎች የተፃፋበት እና የተዘከሩበት 9ኛ. በርካታ የክርስትያን መዝሙራት በኦሮምኛና በሌሎች ቌንቌዎች የተገለጡበት 10ኛ. በአፋን ኦሮሞና በሌሎችም ከረጅም ዘመናት በፊት የመዝገበ ቃላት የተደራጀበት ናቸው። እንኳን ዛሬ ዳብሮ በኮምፒተር ሳይንስ ተደግፎ አይደለም ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ገና ድሮ ተፈትነው ኦሮምኛን ለማስተናገድ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። በ ዶክተር አበራ ጥረት በ ዩኒኮድ ዩኒቨርሳል ኮድ በመግባታቸው ጠቀሜታቸው ተገልፆ ዐለምአቀፍ እውቅናን አግኝተዋል።

ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በኣሁኑ ጊዜ ግዕዝ በዩኒኮድ ዕውቅና ያገኙትን የቢለን፣ ቤንች፣ ምኢን፣ ሙርሲ፣ ሱሪ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ ኣገው፣ ኣውንጂ፣ አማርኛ፣ ዲዚ፣ ዳውሮ፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ጎፋ እና ግዕዝ ቋንቋዎች የሚጋሯቸውን ቀለሞችና ሌሎችንም ያስከትባል። ለእዚህም ተግባር የዶ/ር ኣበራ ሞላ ግዕዝኤዲት ገበያ ላይ ውሏል። ኦሮምኛን ጨምሮ እሱ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች የፈፅመው ተግባር ሁሉ በሚከተለው የዊኪፒዲያ ሊንክ ማግኘት ይቻላል።

https://am.wikipedia.org/wiki/%E1%8A%A3%E1%89%A0%E1%88%AB_%E1%88%9E%E1%88%8B#%E1%8C%8D%E1%8B%95%E1%8B%9D%E1%8A%93_%E1%8A%A6%E1%88%AE%E1%88%9A%E1%8D%8B

የእንግሊዝኛ ወይም የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው ስለማይፃፉ ስፔሊንጉን ለማወቅ የእድሜ ልክ ትግል ይገጥማል። በኢትዮጵያ ቀለማት ግን ሰው እንደሚናገረው ስለሚፅፍ የእስፔሊንግ ስህተት ሊሠራ አይችልም። ስለእዚህም ከላቲን ወይም እንግሊዝኛ ፊደላት ይልቅ እሱን መምረጥ ይገባናል። እኛም እንደተጋሩ ወገኖቻችን ብልጥ መሆን ይገባናል። እነሱ በኢትዮጵያ ፊደላት እንጂ መቼ በላቲን ይፅፋሉ? ኤርትራውያንስ መቼ የግእዝን ቀለማት አሽቀንጥረው ጣሉአቸው? ከኢትዮጵያ ተገነጠሉ እንጂ መቼ ከፊደላችን ተገነጠሉ? እንዳውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር በላቲን እንቸክችከው ቢሉ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በመገንዘባቸው ግን ፊደሎቻችን ይዘዋቸው ሄዱ። የኢትዮጵያ ፊደላት የሰሜን ሰዎች እና የአማራ ብቻ አይምሰለን። ባለፉት 4000 ዐመታት ከሁላችንም አባት ከኢትዮጵ ጀምሮ በነገሥታት ልጅ ልጆቹ እየተቀረፀና እየተሻሻለ ሲወርድ ሲዋረድ እዚህ የደረሰ ነው። ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አጋዝያን መደበኛ ፊደላቱን ኢትዮጵያ ውስጥ አግኝተው ለራሳቸው እንዲመቻቸው አድርገው ሞርደዋቸዋል። አማሮች ዘመዶቻችንም ለእነሱ አፍ የሚስማሙ የተወሰኑ ፊደላትን ቀርፀው እውስጣቸው አካተዋል። ስለዚህ ፊደላቱ የኦሮሞም ናቸው። በእርግጥም ናቸው እንጂ ባይሆኑም እንኳ ከማናውቃቸው ከባእዳኑ ከአውሮፓውያኖቹ ፊደላት ይልቅ የተፈጠርንበት እና የኖርባት የኢትዮጵያ ፊደላት ለኛ ይቀርቡናል።

ከቡር ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሆይ! በኢትዮጵያዊነት ስሜት እና ፍቅር መንደዶን እባህርዳር በነበሩ ጊዜ አሳይተውን ነበር። ኢትዮጥያዊነት የኢትዮጵያን ፊደላትንም ይጨምራል። ስለእዚህ ይህን ጉዳይ አተኩረው ያስቡበት። ከዛሬ 26 ዐመታት በፊት መጫፈ ቁልቁሉን ጨምሮ ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ፊደላት እጅግ ብዙ ፅፎበታል። በእዚህ አጋጣሚ አንድ ጥያቄ እንዳቀርብ ይፈቀዱልኝና ባለፉት 26 ዐመታት በቁቤ ወይም በላቲን ፊደላት ምን ያህል የረባ መፃህፍት ተከትበዋል? ከኦሮሞ ሰፊው ህዝብ ውስጥስ ምን ያህሉ ነው በቁቤ የሚፅፍና የሚያነብ? ነው ወይንስ እንዳው ለወጉ ነው ቁቤ ቁቤ የምንለው? እዚህ ላይ ብርሃን የ ሚረጭ ጥናት ቢኖር እንዴት ሸጋ ነበር። ለማንኛውም ቁጥራቸው በዛም እነሰም ቁቤ የሚችሉ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሁንም በቁቤ እንዳይገለገሉ የሚያግዳቸው የለም። ርስበርሳቸውም ሆነ ለየብቻቸው በቁቤ መጠቀማቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። በሃገር ደረጃ ግን ከላቲን ይልቅ ግዕዝ በጣም በርካታ ጥቅም ስለአለው ነው ኦሮምኛ ተደራቢ የፌዴራል ቋንቋ ሆኖ በግእዝ ፊደላት ይፃፍ ብዬ የምመክረው። ኢትዮጵያዊው ፊደል በሀገር ደረጃ ፀድቆ ከተገበረ ከመዋዕለ ህፃናት እና ከ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሊደርስ ይችላል። በእድሜው የገፋውን አዛውንት ሳያስጨንቁ በህፃናቱ ቢጀመር ከ 20 ዐመታት በኋላ ለመጪው ትውልድ ይዳረሳል። ይህን ጉዳይ ለመተግበር ደሞ ለእርስዎና ለሃገር አስተዳደር ባልደረቦቾ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እሺታ እና ትብብር ያሻችኋል። ይህ በቶሎ የሚፈፀም ነገር ስላልሆነ ለጊዜው ቅዱሱ ሃሳቡ ይንሸራሽር።

ደብዳቤዬን ለመደምደም፣ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ቁጥር በጣም በርካታ ስለሆነ ካናዳ ውስጥ እንግሊዝኛንና ፈረንሳይኛን የሥራ ቋንቋዎች አድርገው እንደሚሠሩባቸው ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥም ከአማርኛ ጎን ለጎን ኦሮምኛ በኢትዮጵያውያኑ ፊደላት እየተከተበ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሊተጋበት ይገባል። ከእዚህም በተጨማሪ፣ ጥቅሙ በተጨባጭ እየተመዘነ፣ አዋጭነቱ በሳይንሳዊ መንገድ እየተረጋገጠ፤ አማርኛን እንደ ተደራቢ ቋንቋቸው በተቀበሉ እንደ ደቡብ ክልል ባሉ ሕዝቦች ላይ ጭነት አለመሆኑም እየተጣራ በጥንቃቄ ሊመከርበት ግድ ይላል፡፡ ኦሮሞ ያልሆኑ የ ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች እና ሌሎችም አያሌ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ሰዐት ኦሮምኛን መማር ይፈልጋሉ። ዳሩ ግን በባእዱ ፊደል በላቲን ተማሩ ከምንላቸው ይልቅ ሁሉም በሚያውቁት በኢትዮጵያ ፊደላት እንዲማሩ ብናመቻችላቸው በቀላሉ ሊቀስሙት ይችላሉ። በግድ በላቲኑ ተማሩ ካልናቸው ግን፣ “ጊዜና ገንዘብ ከሚያባክነው ከላቲኑ ፊደል ይልቅ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ በሆነውና በምናውቀው ባገራችን ፊደል እንጽፋለን” ቢሉ ይህ አቋማቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ክቡር ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሆይ! እርስዎ አንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን በአዎሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እና እናቶቻችን ደም እና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች ቅኝ እንደተገዙትና እንድተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች እድንሆን አይገባም። በእዚህ እና እላይ በተዘረዘሩት የአመክንዮ ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለክብራችን እና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ ይህን የተቀደሰ ጉዳይ ትጉበት። ከዚያም ውጤቱ ለህዝባችን ልብ የሚያኮራ እና ለኑሮም የሚበጅ ይሆናል።

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ፓስተር ኦነሲሞስ ነሲብ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጎመው የኦሮምኛ ቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ የወሰድኳቸውን ሁለት ገፆች ከዚህ በታች አስፍሬለዎታለሁ። የዛሬ 120 እንኳን ቅዱስ መፅሃፍን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራት እና ፍላጎት ከአለን አሁንማ በ ዘመነ-ኮምፒተር በቀላሉ ኦሮምኛን ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለችግር መክተብ እንችላለን።