ታዬ ደንደኣ አረዶ፡ ምስኪን ኦሮሞ፡ ምስኪን ኢትዮጵያዊ  

ታዬ ደንደኣ አረዶ፡ ምስኪን ኦሮሞ፡ ምስኪን ኢትዮጵያዊ  

አለቃ ተክሌ ከካናዳ ስለ ታዬ ከፃፈው የቆየ ፅሁፍ የተቀነጨበ


ታዬ ደንዳአ አረዶ። ታዬ ግለሰብ ነው። ግን የብሄርተኝነት አደጋ ላይ፡ በተለይም በኦሮሞ ብሄርተኝነት ጉዳይና አደጋው እኛም እንዴት ብናስተናግደው መልካም እንደሆነ ትንሽ ወረድ ብዬ ስለምሄድበት ታዬን ባነሳው ፍኖተ-ውይይታችንን ያቀልንላል። ደግሞም ታዬ ደንደአ አረዳ ከኛ እንዳንዱ ነው። ታዬ ተክሌ ነው። ታዬ ብርሀኑ ነጋ በልጅነቱ ነው። ታዬ ብርቱካንንም ነው። ታዬ የአ.አ.ዩ. ተማሪ እያለ ከ2003 እስከ 2006 ታሰረ። ከዚያ ተፈታ። አ.አ.ዩ. የሕግ ትምህርቱን ቀጠለና ሊመረቅ ሶስት ቀን ሲቀረው ባለፈው ሀምሌ ወር፡ 2009/2001 ዓ.ም. እንደገና ታሰረ። ታዬ ኦሮሞ ነው። ስለዚህ ታዬ ኢትዮጵያዊ ነው።
ታዬ ባንድ በኩል እድለኛ ነው። በ2003 ከሱ ጋር ከታሰሩት አንዱ አለማየሁ ገርባ በጥይት ተመቶ በሳምንቱ ሞቷል። ኦክቶበር 2006/1998። ሌላኛው ጓደኛው ጋዲሳ ሂርጳሳ በድብደባና ስቃይ ብዛት እስር ቤት ሞቷዋል። ምናልባት ያኔ ታዬ እድለኛ ነበር። አሁን ካልሞተ። ታዬ የምስኪን ልጅ ነው። ልክ እንደኔ። እኔ ሳልሻል አልቀርም። ገብረ ጉራቻን ታውቋታላችሁ? እዚያ ነው የተወለደው። ጠላ ለሚሸጡ ሰዎች ውሀ እየቀዳ እየሸጠ፡ በመልሱም እነሱ እያጎረሱት ነው ትምህርቱን የጨረሰው። በጣም ብሩህ አእምሮ ስላለው፡ በሰቃይነት ትምህርቱን ጨረሰ። አ.አ.ዩ. በመምህርነት ቀጥሮ አስቀረው። የመመረቂያ ጽሁፉ ኤ ፕላስ አስገኝቶለታል። “ፎልስ ኮንቪክሽን በኢትዮጵያ” ይላል ጽሁፉ። ታዬ ራሱ የሀሰት ፍርድ ሰለባ ስለሆነ ይሄንን ርእስ አሳምሮ ያውቀዋል። አሳምሮ ጻፈው። ግን ታሰረበት።
ታዬ ላሳደገው ህ/ሰብ ተቆርቋሪ ነው። ወዳደገበተ ገብረ ጉራቻ እየተመላለሰ ሴቶችን እየሰበሰበ ያስተምራል። ሴቶች ለምንድነው በትምህርት ቤት ከወንዶች ደረጃ እኩል ነጥብ የማያመጡት? ይሄ ችግር የህብለ በራሂ ነው ወይንስ ሰው ሰራሽ? ብሎ በእልህ ሴቶችን ያስጠናል። ከሀምሳ በላይ ቀድሞ በእረኝነት ሙያ የተሰማሩ ታዳጊዎች፡ ዛሬ በታዬ ገፋፊነት ከእረኝነት ወጥተው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ታየን ያመሰግናሉ። እነሆ ታዬ ታሰረ። ለምን? በመመረቂያ ጽሁፉ ሽብር ፈጠረ። ሰው ቀሰቀሰ። ማእከላዊ ታሰረ። እስካሁን ይኑር ይሙት የሚያውቅ የለም። ቤተሰብ ከታሰረ ጀምሮ አላየውም። አሳሪዎቹ ዝም ብለው፡ ስንቅ ብቻ አንጡ እያሉ ይቀበላሉ። ይድረሰው አይድረሰው አይታወቅም። ከዚህ ቀደም ከሱ ጋር የታሰሩ ሰዎች እንደገለጹት፡ በቃ ይደበድቡትና ፊቱም ምኑም ሲያብጥ እስኪያገግም ድረስ፡ ሰው አንዳያው ወደ ውጭ አያወጡትም አሉ፡ በሕወሀት የእስር ባህል። ታዬ ሊታሰር ትንሽ ቀን ሲቀረው አባቱ ሞተዋል። እናቱና ወንድሞቹ ግን አሉ።
በባዶ እግሩ ተምሮ እዚህ የደረሰው ታዬ እሱንና ወገኖቹን ከአማሮች አገዛዝ ነጻ ሊያወጣ በመጣ ነጻ ያልወጣ ነጻ አውጪ ታስሯል። ዶ/ር ቡልቻ ደመቅሳ፡ ስለታዬ መታሰር ሲጠይቋቸው፡ “የሱን ነገር አታንሱብኝ ብለው ያለቅስሉ” ብሎኛል አንድ ጓደኛዬ። ዶ/ር መረራም እንደዚያው። እንባቸው ይመጣል። ስለዚህ ስለሰዎች መታሰር ስለሰዎች መገደል ስለሰዎች መሰደድ ስለሰዎች መታፈን ለመናገር አልተዘጋጀሁም። ምክንያቱም እሱን እኩል እናውቀዋለንና። #MinilikSalsawi