ፍትህን ፍለጋ ፣ የአጋርነት ጥያቄ ! “ስለ ብላቴናው መሐመድ ፍትህ አንደክምም ! ” የሳምንቱ መሪ ቃላችን ነው

የማለዳ ወግ …ፍትህን ፍለጋ ፣ የአጋርነት ጥያቄ !
=================================
* “ስለ ብላቴናው መሐመድ ፍትህ አንደክምም ! ”
የሳምንቱ መሪ ቃላችን ነው
* ዛሬ ጁምአን ለብላቴናውና ለቤተሰቡ እንስጥ !
* ፕሮፋይላችን በብላቴናው ምስል እንቀይር !
* እስላም ክርስትያኑ ብላቴናውን በጸሎት እንሰበው !
* ስለ ብላቴናው የ12 ዓመት ክልትም መረጃ እናግኝ
* መረጃዎችን ላልሰሙት እናሰራጭ !
* ጁምአን የ12 ዓመቱን የተገፊዎችን እንስጥ !

በጁምአ የአርብ ጸሎት ብላቴናውን እናስበው !
==============================

ወገኖቸ ፣ ዛሬ ጁምአ ነው ። ጁምአ ወይም እለተ አርብ በሁሉም ሐይማኖቶች የተከበረች ቀን ናት ። በሳውዲ ዙሪያና በመላ አለም የምትገኙ የእስልምና ሐይማኖት አባቶች ፣ ኡለማዎች፣ ኡስታዞችና ምዕመናን በጅምአው የህብረት ጸሎት ስለ ብላቴናው ፍትህ ጸሎት ታደርጉ ዘንድ እንማጸናችኋለን ! …በሳውዲ አረቢያ ጅዳና በከባቢው ያለን ጉልበትና አቅሙ የሚፈቅድልን ኢትዮጵያውያን 12 ዓመት በአልጋ ላይ የተሰናከለውን ብላቴናው መሐመድ እንጎበኘው ጸሎት እናደርግለት ስል ጥሪየን በአክብሮት አቀርባለሁ !

በመላው አለም የምትገኙ ይህ መረጃ የሚደርሳችሁ የየትኛው ሐይማኖት ተካታይ ወገኖቸ ሳውዲ አረቢያ መብት የሚያስከብርለት የሚቆረቆር መንግስት አጥቶ 12 ዓመት በተረጋገጠ የህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ የሆነ ታዳጊ ኢትዮጵያዊ ብላቴናው መሐመድ አብድልአዚዝ ተንጋሎ መሽቶ እየነጋበት ፍትህ ተነፍጓልና አልቅሳችሁ ስለ ብላቴናው ጸሎት ታደርጉ ዘንድ እማጸናችኋለሁ!

መንግስት የዜጎችን ድምጽ ይሰማን ዘንድ አማልዱን !
=================================

የብላቴናው መሐመድ ወላጆች ነፍሱ ያልወጣች በድን ልጃቸውን እያገላበጡ ፣ እያነቡ 12 የመከራ ጊዜን ሲገፉ ” ተመስገን ” ከአንደበታቸው አይለይም ። ዛሬ የሁላችንንም አጋርነት ይሻሉ ! ስለ ብርታት ጽናታቸው እያመሰገንን አጋር ሆነን እንደግፋቸው ። … ” ፍትህ ለብላቴናው መሐመድ ” ብለን ፍትህን እናፋልጋቸው ! በመላው አለም የምትገኙ በኢትዮጵያ መንግሰት በኩል ተሰሚነት ያላችሁ አባቶችና እናቶች ፣ ምሁራን ልሂቃን፣ የፖለቲካ ፖርቲዎችና የማህበራት ተወካዮች ብሎም መላው የሀገሬ ሰው ለብላቴናው ጸሎት ከማድግ ጎን ለጎን ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው ለኢትዮጵያ መንግስት ፣ ለሪያድ ኢንባሲና ለጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች ” ፍትህ ለብላቴናው መሐመድ ” በሚል ድምጻችሁን ታሰሙ ዘንድ አደራየ የጠበቀ ነው ! መንግስት የዜጎችን ድምጽ ይሰማን ዘንድ አማልዱን !

ዛሬ አርብ ” ጁምአን” ለብላቴናው እንስጥ !
============================
በሩቅ በቅርቡ አለም ያለን ስለ ሰብዕና ቅድሚያ በመስጠት የብላቴናውን የ12 ዓመት ፈተና ፣ መከራና ሰቆቃ ህዝብ ይረዳ ዘንድ ጁምአን በሁሉም ማህበራዊ መገናኛዎች ምልክት ፕሮፋይላችን ከዚህ መረጃ ጋር ባያያዝኩትን የብላቴናው መሐመድ ምስል በመቀየር አጋርነታችን እናሳይ ዘንድ ወንድማዊ ጥሪየን በአክብሮት አስተላልፋለሁ ! መረጃዎችን ላልሰሙት Share እና Like በማደረግ በማሰራጨት ፣ የ12 ዓመቱን የተገፊዎችን ሸክም እያስብን ሙሉ አርብን ” ጁምአን” ከብላቴናውና ከቤተሰቡ ጋር አገር በመሆን እናሳልፍ ! ግልጽ ላልሆኑ መረጃዎች በመጠየቅና በመለዋዎጥ ፣ ጁምአን ለብላቴናውና ለቤተሰቡ አጋርነት እንድናሳይ ከአደራ ጭምር በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ ! …

ስለ ብላቴናው መሐመድ ፍትህ አንደክምም !

ፍትህ ለብላቴናው
#JusticeForMohamned

ጂምአ ሙባረክ !

ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 7 ቀን 2010 ዓም