የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ (መስከረም አበራ)

የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ (መስከረም አበራ)
*******************
ስህተት ስህተትን ይወልዳል! ስህተቶች ተዋልደው የሃገራችንን የፖለቲካ አየር ሲያጣብቡ፣ የፈውስ መንገዳችንን ሲያስቱን ኖረዋል፨ የአፄው ስርዓት ሊወድቅ ሲንገዳገድ ውድቀቱን ያፋጠነው የተማሪዎች/የህዝቦች እንቅስቃሴ የሰራው አንድ ትልቅ ስህተት በበሰለው ትግል ላይ ድንገት ዱብ ያለውን የዝቅተኛ መኮንኖች(በሃላ ደርግ) ቡድን ህይወትም መንገድም አድርጎ በመቁጠሩ ነው፨ ራሱ ባበሰለው ትግል ላይ በአናት መጥቶ በአላዋቂ እጁ የሚያቦካውን ወታደር ድርጊት ዳር ቆሞ እንደ ትርኢት ተመልካች እያፏጨ እና እያጨበጨበ በመመልከቱ ወታደሮቹ ግርታቸው እንዲለቃቸው እና ያልሆኑት የትግሉ ባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ሆነ፨

ይህ ስሜት ሲውል ሲያድር የወታደር እብሪት እና ድንፋታን አመጣ፨ የጠላት ጠላት ሁሌ ወዳጅ ላይሀቀን ይችላልና በሃላም ደርግ የሚባል አውሬ ተፈጥሮ ባጨበጨበለት ህዝብ ላይ የጠመንጃውን ላንቃ ከፈተ፨ ከዛ በሃላ የተፈጠረው ለማን ይጠፋዋል ??!! ሳልናገር የማላልፈው ግን የደርግ መምጣት ለኢህአዴግ መምጣት መንገድ እንደጠረገ ነው ፨ ሃገር ለመምራት ከጠመንጃ በላይ የእውቀት ስንቅ ያስፈልጋል፨ ደርግ ደግሞ የነበረው ጠመንጃ ብቻ ነበር፨ ሃገርን ያክል ሸክም በጠመንጃ አፈሙዝ ጫፍ ላይ ሰክቶ ‘ግደል ተጋደል’ ማለት የባሰውን አምባገነን መጋበዝ ፤ የበለጠውን መከራ መጥራት ነው!

ለዚህ ነው ሃገርን የሚያክል ግዙፍ ነገር ያለ አቅሙ ተሸክሞ ሲንገዳገድ የኖረው ደርግ የባሰውን አምጥቶብን ውልቅ ያለው! የዚህ ሁሉ ስህተት ጅማሮ ደግሞ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ስፍራውን ለደርግ ለቆ ዳር መሆን የሚገባውን ወታደር ከነ ግርታው ወደ መሃል ገብቶ እንዲያቦካ ለቆለት ከዋናነት ወደ አጨብጫቢነት ማነሱ ነው፨

ደርግ ገና ከሃገር ዳርቻ ተሰብስቦ ሲመጣ በግርታ ውስጥ ባለበት ሰዓት ተማሪው(ሌላው ሲቪሊያን ታጋይ) ስፍራውን ሙሉ በሙሉ ለደርግ ለቆ የዳር ተመልካች ከሚሆን ይልቅ ተማሪው አብዮቱን እንዲመራ ደርግ ደግሞ (የሚመጥነው ይሄው ነውና ) ጠመንጃውን አንግቦ አብዮቱ የሚመከርበትን አዳራሽ በር እንዲጠብቅ ቢደረግ ፤ ይህ ካልሆነ እንኳን የተማሪዎችን(የህዝቦችን) እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ነጥቆ በጠመንጃው ስር ማድረግ እንደማይችል ፣ይልቅስ ነገሩ በጋራ መሪነት መሄድ ነበረበት እንጅ ወታደሩ ብቻ መድህን ተደርጎ ሙሉ እምነት ሊጣልበት አይገባም ነበር !

ታሪክን መከለስ ፣ ወደ ሃላ ማምጣት አይቻልም፨ የሚቻለው መዝገብ አገላብጠበ ከታሪክ መማር ነው፨ ለዚህ ደግሞ ታሪክን ማገላበጥ ያስፈልግ ይሆናል፨ እኛ ኑሮ የሚያዋክበን ኢትዮጵያዊያን ደግሞ እንኳን ኑሮ ተጨምሮበት እንዲያውም ማንበብ ላይ እስከዚህም ነን ! በዘመኑ የኖሩ ታላቆች ሲነግሩንም ልንሳደብ እንነሳለን ፨ ስለዚህ መመሪያችን ሃቅ ሳይሆን ሞቅታ ሆኗል፨ እውቀት የሚፈጥረው እርጋታ ያንሰናል፨ አንሰማማም ፨ በመንጋ ከምንነዳበት የሚያናጥበን የተለየ ሃሳብ አንፈልግም ፤ጭራሽ በጨለምተኝነት እንከሳለን፨ ኢህአዴግን በሚያስንቅ ሁኔታ ፕሮፖጋንዳ እናደንቃለን፣ በዛው እንወሰዳለን ፣ ራሳችን በፈጠርነው ፕሮፖጋንዳ ወለድ እውነት ርርርቀቀቀን በሄድን ቁጥር ከእውነት እንፋታለን፨ ካልሆነ ቦታ መድህን እንፈልጋለን፣ ተስፋ በማይደረግበት ቦታ ተስፋ እናደርጋለን ፣ራሱን እንኳን የማያድን ሸንበቆ ተመርኩዘን ሸክማችን ሲበዛበት ተሰብሮ መልሶ ይወጋናል፨

የራሳችንን ስራ እርግፍ አድርገን ትተን እኛ እንደ ህዝብ ባበሰልነው ትግል በአናቱ ላይ በመጣ ካድሬ ተስፋ ስናደርግ ከላይ የጠቀስኩትን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ቀደም ብለው ከሰሩትን ስህተት የባሰውን እንደግማለን ፨ የስልሳዎቹ ታጋዮች ተስፋ ያደረጉት ደርግ እንኳን እውቀት ባይኖረው ጠመንጃ ነበረው ፨ ሃይል በሚገዛበት ሃገር ጠመንጃ ያለውን ተስፋ ያደረጉት እነሱ ከእኛ ምንም የሌለው አፈጮሌ ተመርኩዘን ሶስት አራቴ ከምንሳሳተው የተሻሉ ተስፈኞች ይመስሉኛል ! ያልሆነው ተስፋችን በ1997 እንደሆነው ግራ መጋባት ፣ረዥም ድንዛዜ ፣ ብዙ መከራ ማስከተሉ አይቀርም! ቀድሞም “ተስፋ አድርጉብኝ ፤እኔ አለሁላችሁ” ያላለ ካድሬ የሚወቀስበት ምክንያት አይታየኝም ፨ እኛው ዘለን ተስፋ አድርገንበት እኛው ውርጅብኝ ጀመርን ! ካድሬ ምን ተዳው ? ! ሂሱን ሰልቅጦ ፣ “አመለካከቱን አሰስተካክሎ” ፣ ጌታ በማንጓጠጡ ‘ተፀፅቶ’ ብቅ ይላል ! ይሄው ነው …..

(መስከረም አበራ)