መምህር ዘበነ ለማ ስለዋልድባ መነኮሳት መፈታት መጮህ ትቶ አልባሌ ጉዳይ ውስጥ ገባ

ፓስተር ወዳጄነህ የተባለ ግለሰብ ጴንጤዎች እያደረጉት የመጡትን እጅግ አሳፋሪና አስደንጋጭ አምልኮ ማጋለጡና መተቸቱ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ በተለምዶ መናፍቃን ከሚሰነዝሩት ስድብ ወጣ ባለ መልኩ አንዳንድ ገንቢ ነጥቦችን ማንሳቱን ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ ከተለቀቁ ቪዲዮዎች ለመረዳት ይቻላል። ከታዋቂ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የወቅቱ መምህራን መካከል አንዱ የሆነው መምህር ዘበነ ለማ ለፓስተር ወዳጄነህ ማበረታቻ መሰል መልእክት በፍጥነት በቪዲዮ ለቋል። ፓስተር ወዳጄነህ የኦርቶዶክስን ቤተክርስቲያን አስመልቶ የሰነዘራቸው መልዕክቶች ገና ትኩስ ከመሆናቸው አኳያ መምህር ዘበነ ለማ የሰጠው ምላሽ ሌላ ታላቅ ጉዳይ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።ይኽውም ለረዥም ዓመታት አለወንጀላቸው ከገዳማቸው ታፍነውና ተዋርደው በእስር ስለሚማቅቁት የዋልድባ መነኮሳት እንዲፈቱ የሚጠይቅ ማንኛውም ዓይነት ቪዲዮም ሆነ የጽሁፍ መልዕክት መምህር ዘበነ አላስተላለፈም። የዋልድባ መነኮሳት ጨለማ ቤት ተቆልፎባቸው እየተደበደቡ ልብሳቸውን ሳይቀይሩ በአንድ ልብስ ብቻ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ቤት ሲሰቃዩ መምህር ዘበነ ስማቸውን እንኳ  አንስቶ የተናገረው አንዳችም ነገር የለም። ህዝብ ማወቅና እርምጃ መውሰድ ያለበት አንገብጋቢው ጉዳይ በእስር ቤት በመማቅቅ ላይ የሚገኙ መነኮሳት ወይንስ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ።

የዋልድባ መነኮሳትና መንንያን የአገርና የትወልድ ቅርስ የሆነውን ታሪካዊውን የዋልድባ ገዳም በወያኔ ለስኳር ፋብሪካነት በግሬደር ሲፈርስና ለዘመናት ተከብሮ የነበረው የመነኮሳቱ መካነ መቃብር በትራክተር ሲታረስ በመቃወማቸው ለእስር እንደተዳረጉ ይታወቃል። መምህር ዘበነና እንዲሁም የአቡነ ማቲያስ ሲኖዶስና ተከታዮቻቸው አሳራቸውን በመቁጠር ላይ ስለሚገኙት መነኮሳት ስለነአባ ገብረሥላሴ ወልደኅይማኖትና ስለነአባ ገብረየሱስ ኪዳነማርያምና ሌሎች ከእስር መፈታት መጮህ ዋጋ የሚያስከፍላቸውና ከወያኔ ጋር የዘረጉትን የጥቅም ገመድ የሚበጣጥስባቸው ስለሆነ ዝምታን መርጠዋል። መምህር ዘበነ በቅርቡም ወልድያ ውስጥ በቃና ዘገሊላ በዓል ላይ በዝማሬና በእልልታ ታቦተ ህጉን አጅበው በዓል ሲያከብሩ የነበሩ ምዕመናን ላይ የትግራይ ሚሊሻዎች የጥይት ዝናብ አውርደው በርካቶችን ህጻናትን ጭምር ሲረፈርፉ የለቀቀው የተቃውሞ ቪዲዮ አላየንም።

ዋርካ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ተለጥፈው እንደ ጅብ ጥላ በቅለው ያደጉና ስርና መሠረት የሌላቸው በራሳቸው ጠውልገው የሚረግፉ ጴንጤዎች ከሁለት ሽህ ዓመት በላይ የኢትዮጵያ መሠረትና አስትንፋስ የሆነች ቤተክርስቲያን ላይ የሚቀባጥሩት ነገር ቁም ነገር ሆኖ አጸፋዊ ምላሽ መስጠት ቤተክርስቲያኗን ማዋረድና ማሳነስ ነው። ጴንጤዎች ስለኦርቶዶክስ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ቢናገሩ በተሳሳተና በተጣመመ መንገድ የሚሄዱ ስለሆነ ኦርቶዶክሶች በእምነት ጉዳይ ከነሱ ጋር ምንም ዓይነት መስተጋብር የላቸውም። የፓስተር ወዳጄነህን ንግግር ቁም ነገር ነው ብሎ መምህር ዘበነ ለማ የፈነደቀበት ምክንያት በወሬውና በጫጫታው ከወቅታዊው የቤተክርስቲያኗ ችግር ለመሸሸግ በመደበቀያነት ለመጠቀም እንደሆነ አያጠራጥርም። መመህር ዘበነ ይህንን የሚያደርገው አፍጦና አግጦ የመጣውን አንኳሩን የቤተክርስቲያኗን ችግር አድበስብሶ ለማለፍ “ከጴንጤዎች ጋር ይፋለማል” የሚል ለጆሮው የሚጥመውን ጭብጨባና ውዳሴ ከምዕመናን ለማግኘት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደበኛ ጠላት በነስብሃት ነጋ የተጠነሰሰው አማራውንና የተዋህዶ እምነትን ለማጥፋት ከ40 ዓመታት በላይ የዘመተው ወያኔ እንጅ ጴንጤዎች አይደሉም። ለጴንጤዎችም ቢሆን ኦርቶዶክሱን እንዲያዳክሙና እንዲያወናብዱ መድረኩን ያመቻቸላቸው እርሱወያኔ እንደሆነ አይዘነጋም።

የዋልድባ ገዳምን አስመልክቶ አቡነ መቃሪዮስ ከ6 ዓመታት በፊት ያስተላለፉ ታሪካዊ መልእክት ለግንዝቤ እንዲረዳ አቅርበንላችኋል።