በአማራ ክልል ኦሮሞኛ መሰጠት የለበትም የሚሉ በስሜት ሳይሆን በመረጃ ይከራከሩን – ግርማ ካሳ

 

በቅርቡ እኔም ያለሁበት የምሁራንና አክቲቪስቶች ስብስብ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአማራ ክልል ከአማርኛ ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ሶስተኛ ቋንቋ እንዲሰጥና ሶስተኛው ቋንቋም አሮምኛ ከሆነ በላቲን ሳይሆን በግእዝ ፊደል እንዲጻፍ የሚጠይቅ ፣ ከአባሪ ሰነዶች ጋር በማያያዝ ደብዳቤ ጽፏል። ደብዳቤው ከቀድሞ የኦህዴድ አመራርና የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት የተከበሩ  ግርማ ወልደጊዮርጊስ ይፋዊ ድግፍ ያገኝ ሲሆን ከሁሉም ማእዘናት ኢትዮጵያዊያን አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡበት ነው።

ሆኖም ከተወሰኑ፣ ብርቅዬ ኤትዮጵያ ልጅ የነበሩት ፕሮፈሰር አስራት የፈረንጅ ጥቁሮች ካሏቸው፣ ላቲን አፍቃሪ  አካራሪ ኦነጋዉያንና፣ በሌላ ጽንፍ ደግሞ ከተወሰኑ የአማራ ብሄረተኞች ተቃዉሞ ተነስቷል። የላቲን አፍቃሪዎች የሚያቀርቡትን ተቃዉሞ  በተመለከተ በሌላ ጽሁፍ የምንመለስበት ሲሆን፣ በአማራ ብሄረተኞች ዘንድ ለሚነሱ ትችቶች ግን እንደሚከተለው፣ ስብሰቡን ወክዬ ሳይሆን ፣እንደ አንድ የስብስቡ አባል መልስ መስጠት ፈለኩ።

ለዚህም እንዲረዳኝ የማክበረው ጋዜጠኛ አያሌው መንደር አስራ ሶስት ጥያቂዎች በመጠየቅ ላቀረበው ትችት መልስ በመስጣት አንባቢያን ግልጽ መረዳት እንዲኖራቸው ለማድረግ እሞክራለሁ።

«በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለሚኖሩ አማራዎች እንግልትና ስቃይ “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ፤ በአማራ ህዝብ ላይ ኦሮምኛ ቋንቋን ለመጫን ፊርማ ማሰባሰብ ከስህተትም በላይ ነው፤ ቋንቋውን ጠይቃችሁን ሳይሆን ፈልገነው ነገ እንማረዋለን፤ ዛሬ ግን ስለህመመችን መጮህካልቻላችሁ ለቀቅ አድርጉን!!!.» ሲል ነው አያለው ጽሁፉን የጀመረው።

ላለፉት በርካታ አመታት በኦሮሚያ ውስጥ በሌላው ማህበረሰብ ላይ ስለሚደርሰው የዘር አድልዎ ፣ የሌላው ማህበረሰብ መብት እንዲከበር፣ ዘረኘነት እንዲቀር፣ አሁን ነገሮች ሲጋጋሉ ሳይሆን፣ ከጅምሩም ሳይታክቱ ፣ከፊት ሆነው፣ ግፊት ሲያደርጉና ሲታገሉ ከነበሩ ወገኖች መካከለ ሰነዱን ባዘጋጀው ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በቀዳሚት የሚጠቀሱ ናቸው። ከማንም፣  አለ ከሚባል የአማራ ብሄረተኛ ባልተናነሰ፣ እንደዉም በበለጠ፣ በኦሮሚያ ውስጥ መብታቸው ለተረገጠ ወገኖች ጮኽናል። መጮሃችንንም እንቀጥላለን። አያሌው መንበር «በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለሚኖሩ አማራዎች እንግልትና ስቃይ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው”  በሚል አስተያየት ከመስጠቱ በፊት ቢያንስ የሰብስቡ አባላት ላለፉት 27 አመታት ያደረጉትንና የጻፉትን ጉግል አድርጎ ቢመረምር ጥሩ ይሆን ነበር።

«እናም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አንስቼ እንደ አንድ የጉዳዩ ባለቤት ወጣት ልሞግታቸው ወደድኩ ሲል አያሌው መንበር  አሥራ ሶስት ጥያቄዎችን አቅርቧል።የሰለጠነ በመረጃ ላይ ያተኮረ ሙግት ይመቸኛል። ምላሽም ለመስጠት የተነሳሁት ከዚህ የነተሳ ነው።

አያሌው መንበር ምን ያህል ስብስቡ ያዘጋጀውን ሰነድ እንዳነበበ አላዉቅም። ባልሳሳት ያነበበ አይመስለኝም። ለምን ቢባል የጠየቃቸው ጥያቄዎች አብዛኞች በሰነዱ ላይ ግልጽ ፣ ዝርዝርና አሳማኝ ምላሽ የተሰጠባቸው ናቸው። አያሌውና እንደ አያሌው ሳያነቡ ላይ ላዩን በአይምሯቸው ጥያቂዎች ላጨቁ ወገኖቼ በሚከተለው ሊንክ በመሄድ አስራ ስድስት ገጽ ያለውን ትምህርት ሰጪና መፍትሄ ጠቋሚ ሰነድ እንዲያነቡ በአክብሮት እየጠየኩ አያሌው ወዳነሳቸው ጥያቄዎች ልመለስ፡

http://www.ethiomedia.com/1000dir/oromigna-be-amara-kilil-be-geez-fiddel-endiset.pdf

ጥያቄ አንድ – 1.ኦሮምኛ ቋንቋን በአማራ ክልል ለማስተማር ለምን አስፈለገ?ለዚያውም በግዕዝ?የአማራ ህዝብ ተቻችሎ የሚኖር ማንኛውንም ጎሳ አክብሮ የተቀበለ ህዝብ መሆኑ ልብ ይሏል።በቤኒሻንጉል፣ደቡብ፣ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል ብሄርን መሰረት ያደረጉ መፈናቀሎች ሲከሰቱ በአንፃሩ በአማራ ክልል ግን እስካሁን በውስጡ የሌላ ጎሳ ላይ ጥቃት ተፈፅሞበት የማያውቅ፣ የሌላን ጎሳ መብትም ያልገፋ ነው።የቋንቋም ይሁን የባህል ብዝሀነት ችግር የሌለበት፣ቋንቋ ባለመማሬ ተጎድቻለው ብሎ ሌላ ቋንቋ ለመማር ጥያቄ ያላቀረበ ህዝብ ነው።ታድያ የዚህ ጥያቄ intention/motive ምንድን ነው?

መልስ – አላማው የክልሉን ሕዝብ መጥቀም ነው። ሶስተኛ ቋንቋ ማወቁ በምንም መሰፈርት የሚጠቅም እንጂ የሚያከስር አይደለም።፡

ጥያቄ 2. አሁን ሀገራችን የገጠማት ችግር የቋንቋ ነው ወይስ የስርዓት? እኔ እስከሚገባኝ የስርዓቱ ችግር ቋንቋን አይደለም ነፍስን እየነጠቀ ነው። 

መልስ – በአገራችን ያለው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው። በዋናነት ሰርአቱ ነው። ሰርዓቱ ደግሞ የስርዓቱ ቁንጮ የሆኑት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አስተሳሰባቸው፣ ፖለቲካቸው፣ ፖሊሲዎቻቸውም ናቸው። የስርዓቱ ትልቁ አጀንዳና ፖሊሲ ደግሞ ዜጎችን በዘር መከፋፈልና እንዳይግባቡ፣ እንዳይስማሙ፣ እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ ማድረግ ነው።ስርዓቱን ማሻሻል ወይም ማስወገድ፣ ማሸነፍ የሚቻለው በዜጎች መካከል ያለው የዘር ሆነ ሌሎች የክፍፍል ግድግዳዎችን ማፈራረስ ሲቻል ነው። ስርዓቱ ዜጎች በቋንቋ እንዳይግባቡ አድርጓል። የኦሮሞ ወጣቶች አማርኛ ማንበብና መጻፍ አይችሉም። በዩኒቨሲቲዎች ከሌላው ጋር መነጋገር መግባባት ይከብዳቸዋል።አማርኛ መጻፍና ማንበብ ባለመቻላቸው፣ በቋንቋ ምክንያት ስራ የማግኘት እድላቸው የመነመነ ነው። በቋንቋ ምክንያት መግባባት አልተቻለም። የምንጽፈውን አያነቡም፣ የሚጽፉትን አናነብም። ስለዚህ ስርዓቱ ቋንቋን ለመከፋፈል እየተጠቀመበት ስለሆነ፣ ቋንቋ የመከፋፈል ምክንያት እንዲሆን መፍቀድ የለብንም።

ጥያቄ 3 – ኦሮምኛ ቋንቋን በአማራ ክልል እንዲስያተምሩ ከመጠየቃቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል በየጊዜው ስለሚፈናቀሉ፣ ውክልና ስለተነፈጉ፣ባህል ወግና ማንነታቸውን ተነፍገው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ስላልተፈቀደላቸው አማራዎች ለምን ፊርማ ማሰባሰብ እና ኦሮሚያ ክልልን መጠየቅ ተሳናቸው? ይህ ጥያቄ የጠያቂዎችን ከጀርባ የረጀም ጊዜ ፍላጎት ይዘው የመጡ ይመስላሉ የሚል ግምት ላይ እንድናርፍስ አያስገድደንም? ከቋንቋ ሳይንሳዊ ውልደትና እድገት ጋርስ አይጣረስም?

መልስ- በኦሮሚያ ክልል ኦሮምኛን በግእዝ ፊደል እንዲጻፍ ዶር ፍቅሬ ቶሎሶ ለአቶ ለማ መገርሳ ግልጽ ደብዳቤ መጻፋቸው የሚታወስ ነው። ለአቶ ገዱ አንዳርጋችው የተጻፈውም ደብዳቤ ግልባጭ ለአቶ ለማ መገርሳና ለዶር አብይ አህመድ እንዲደርሳቸው ተደርጓል። በቅርቡም ዶር ፍቅሬ ቶሎሶ የጻፉትን በማጠናከር በርካታ ታዋቂ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላትን በማቀፍ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አፋን ኦሮሞን በግእዝ ማስተማር እንዲጀመር የሚያበረታታ፣ ያለዉን ጥቅም አጎልቶ የሚያሳይ በሰነድ የተደገፈ ግፊት ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው። ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተጻፈው ደብዳቤ አንዱ ጥረት እንጂ ብቸኛ ጥረት አይደለም።

በቀድሞ የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪዎች ላለፉት 27 አመታት በአማራው ማህበረሰብና “ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው” በሚሉ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ስቃይና መከራ እንደተፈጸመ ሁላችንም በግልጽ የምናወቀው ነው። ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ።

  • ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዜጎች መጤ፣ ነፍጠኛ፣ አማራ ተብለው ተገድለዋል። በሃይልናበጭካኔ ተፈናቅለዋል። ከሃያ ሰባት አመታት በፊት በአርባ ጉጉ በኦህዴድ፣  በበደኖ በኦነጎች ያለቁትን ንጹሃን ዜጎች፣ በቅርቡ በኢሊባቡር መጤ ተብለው በቆጨራ የተገደሉ ወገኖቻችን  ጨምሮ ላለፉት 27 አመታት ሳይቋረጥ በአማርኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ላይ ግፍ ተፈጽሟል።
  • በአማራው ክልልኦሮሞዎች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ልዩ ዞን ተሰጥቷቸው አፋን ኦሮሞን እየተጠቀሙ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው። ሆኖም ግን በኦሮሚያ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት በሚኖርባቸው አካባባዊች ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር አልተፈቀደለትም። ለምሳሌ በአዳማ ልዩ ዞን ከ80% ነዋሪዎች አፋን ኦሮሞ የማያናገሩ ሆኖ፣ በከተማ መንግስት ተቋማትና መስሪያ ቤቶች፣ በቀበሌዎች የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል። ዜጎች በቋንቋቸው አገልግሎት እንዳያገኙ ተደረጓል።ይሄ ዘረኝነት ነው።
  • በኦሮሚያ ክልል መንግስት ኦሮምኛ ከሚናገሩ ውጭ ተቀጥሮ መስራት አይቻልም። ያ ብቻ አይደለም ለኦሮሚያ ክልል ሆነ ለዞኖች ለወረዳዎች ሃላፊነት መመረጥ አይቻልም።
  • በኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት መሰረት የክልሉ ባለቤት፣ ሌላዉን ማህበረሰብ የሚጨምረው የክልሉ ነዋሪዎች ሳይሆኑ ኦሮሞዎች ናቸው። በአዳማ/ናዝሬት የተወለደ ፣ እናት አባቱ በዚያ የተወለዱ አንድ ዜጋ ፣ በአዳማ ውስጥ ካለው መብት ይልቅ፣ አዳማን አይደለም ሸዋን ረግጠው የማያወቁ ከአወዳይ ሃረርጌ ወይም ነጆ ወለጋ የመጡ ፣ ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ የበለጠ መብት አላቸው።
  • ኢሕአዴግ ስልጣን እንደጨበጠ ለብዙ አመታት አዳማ አካባቢ ሕዝቡ በማመጹና በመጠየቁ ተፈቀደ እንጂ፣ በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች አማርኛ እንደ ትምህርት አይሰጥም ነበር። በኋላ ግን በኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ ያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ ማሻሻይዎችን በማድረግ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ አማርኛ እንደ አንድ ትምህርት እንዲሰጥ ተደርጓል።

በአጠቃልይ በኦሮሚያ የሌሎች ማህበረሰባት መብት የተረገጠበት፣ ሌሎች ሁለተኛ ዜጋ የሆኑበት፣ እኩልነት ሽታው እንኳን የሌለበት አፓርታይዳዊ አሰራር ያለበት ክልል መሆኑ የሚያከራከር አይደለም።

ሆኖም ግን የነ አቶ ለማ መገርሳ አመራር  በኦሮሞ ስም፣  በኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ የተዘረጋውን፣ ሌላውን ማህበረሰብ የማግለል  ፖለቲካ ከማንም በላይ ኦሮሞዉን እንደጎዳ የተረዳ ይመስለኛል። ያለፉት የ27 አመታት እነ አባ ዱላ፣ እነ ጁናዲን ፣ እነ አለማየሁ አቶምሳ፣ እነ ሙካታር ከድር፣ በሕወሃት እየታዘዙ የመሩት ኦህዴድ፣ ኦሮሞዉን ከሌላው ማሀበረሰብ ጋር አቃቅሮታል። ለመዝናናት፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስተመንት ወደ አሳሶ፣ ወደ ባህር ዳር፣ ወደ አዋሳ እንጂ ወደ ነቀምቴ፣ ወደ ጎባ፣ ወደ መቱ የሚያቀና የለም። የንግድ እንቅስቃሴ በመዳከሙ ደግሞ የኦሮሚያ ከተሞች እየሞቱ ነው። ሆቴል ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች ከስረዋል። በኦሮሚያ ከተሞች ያሉ ቀበሌዎች የገበሬ ማህበር እየሆኑ ነው። ትንሽ በሸዋ የተለየ ነገር አለ። እርሱም ለአዲስ አበባ ቅርብ በመሆኑ ነው።

ይሄን አሳዛኝ የኢኮኖሚ ገጽታ ለመቀየር ፣ የለማ ቡድን በቀዳሚነት አጀንዳው አድርጎ የተነሳው በኦሮሞና በሌላው ማህበረሰብ መካከል ያለውን ግድግዳ ማፈራረስ ነው። መቀራረብን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን ማስፈኑን ነው። ዜጎች በነጻነት በኦሮሚያ እንዲሰሩ፣ እንዲነግዱ ፣ እንዳፈሩ፣ እንዳይሸማቀቁ ፣ የኦሮሚያ ከተሞች እንዲያድጉ ማድረጉ ላይ ነው። ከዚህም የተነሳ ኦህዴድ.ና ኦነግ ሲያራምዱት ከነበረው የጸረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ መቶ ሰማኒያ ዲግሪ በመዞር የኢትዮጵያዊነት ጠበቃና ዘብ ሆነው የአገሪቷን ፖለቲካ በአዎንታዊነት እየነቀነቁት ነው።

ኦያለውም መንበር ሆነ ብዙ የአማራ ብሄረተኞች እንደሚገልጹት፣ አዎን፣ በኦሮሚያ ችግሮች አሉ። ግን የ27 አመታት ችግሮች በአንድ ጀንበር አይፈቱም። ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ፍቃደኛ የሆነ አመራር አሁን መጥቷል።፡ከነርሱ ጋር በመስራት የሚነሱ ጥያቄዎችን በንግግር ማስተካከል ይቻላል። በነ አባ ዱላ፣ በነ ሙካትር ከድር አይን እነ ለማን ማየት ተገቢ አይደለም።

ጥያቄ – 4.ኦሮምኛ ቋንቋ መማር አለብን የሚል ፍላጎት ከየትኛው የአማራ ግዛት ነው የመጣው? ለጥያቄው መነሻ የሚሆን ምን ምክንትያ አለ?

መልስ –  ምሁራናና አክቲቪስቶች ክልሉን ይጠቅማል በሚል ነው ሐሳብ ያቀረቡት። ሕዝብ ካልፈለገ ከሕዝብ ፍቃድ ዉጭ የሚሆን ምንም ነገር አይኖርም። ሕዝብ ግን አዋቂ ነው። ቋንቋ ጥቅም እንዳለው ይረዳል። አፋን ኦሮሞን በግእዝ መማሩን ይቃወማል ብለን አናስብም። በመሆኑም ሰነዱን አስተማሪ ፣ አቅጣጫ አሳዪ ከመሆን ባለፈ ሌላ ሚና እንዳለው ባናስብ ጥሩ ነው። ማንንም ለማዘዝ፣ በማንም ላይ ለመጫን አልተሞከረም።

ጥያቄ 5.ቋንቋው መሰጠት ያለበት ለመላው አማራ ወይስ አማራ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ኦሮሞዎች? ለምንስ በግዕዝ?

በሰነዱ በግልጽ እንደተቀመጠው የቀረበው ጥያቄ ከአማርኛና ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ሁሉም ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ እንዲማሩ የሚጠይቅ ጥያቄ ሲሆን ኦሮምኛ የሚሰጥ ከሆነ ግን ፊደሉ በግእዝ እንዲሆን የሚያሳስብ ነው። «የአማራው ክልል የትምህርት ፖሊሲ የሚሻሻልበትና ከአማርኛና ከእንግሊዘኛ ቀጥሎ በዜጎች ወይንም በወረዳው አስተዳደር ምርጫ ሶስተኛ የአገራችንን ቋንቋ የሚማሩበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ሊሆን ይችላል ብለን እሳስባለን» ብለን ለአቶ ገዱ በተጻፈው ደብዳቤ ላይ በግልጽ አስቀምጠናል።

ኦሮምኛ ለምን በግእዝ ለተባለው አሳማኝ ነጥቦች በሰነዱ ላይ ተቀምጠዋል። አንደኛ ከኢኮኖሚ አኳያ ግእዝ ከላቲን ይሻላል ። ሁለተኛ ከታሪክ አኳያ – ኦሮምኛ በግእዝ ከጥንት ጀምሮ ይጻፍ ነበር ። ሶስተኛ ከአገራዊ ስነልቦና፣ ከአመችነትና ከቅለት አኳያ ግእዝ ከላቲን ይሻላል። አራተኛ ከሳይንስ አኳያ – ኦሮምኛን በኮምፒተር በተሟላ መልኩ መጻፍ ይቻላል።

ጥያቄ- 6.አማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞዎች “በኦሮሚያ ልዩ ዞን” ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በቋንቋቸው እየተማሩ፣ ባህላቸውን እያበለፀጉ ባሉበት እና ምንም አይነት የአስተዳደር ቅሬታ በማያነሱበት ወቅት አማራ ክልል ላይኦሮምኛን ለማስተማር ጥያቄ እንዲነሳ የተፈለገበት ምክንያት የተደበቀ ፖለቲካዊ ፍላጎት ወይስ ዝም ብሎ ቋንቋን ማሳደግ ሌላ?

መልስ- ላለፉት 27 አመታት የነበረው ፖለቲካ የመፈራራት፣ ያለመተማመን ፖለቲካ ነው። ይሄ አይነቱን ፖለቲካ አልፈን መሄድ መቻል አለብን።፡ለአቶ ገዱ ያቀረብናቸው አስተያየቶቻችን፣ ምክንያቶቻችንን፣ መረጃዎቻችንን ለሕዝብ በግልጽ ይፋ አድርገናል። በየሜዲያው ወጥቷል። በግልጽ በይፋ የሚደረግን ነገር በግልጽና በይፋ መረጃን በመያዝ መምገት ነው እጂ የሚገባው ከበስተጀርባ ነገር አለ ብሎ መጠርጠር ተገቢ አይመስለኝም። ሰነዱን ያዘጋጀነው ኢትዮጵያዉያን በግልጽነት የምናምን ወገኖች ነን። ሳንፈራ ሳንሸማቀቅ ያመንበትን የምንጽፍ ነን። ለመወደድ ብለን የምንሰራ፣ ለመወደድ ብለን ያለመንበትን የምናራግብ አይደለንም።

ጥያቄ 7.የኦሮምኛ ቋንቋ በኦሮሚያ ክልል ቁቤ በሚባል እየተሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት አማራ ክልል ላይ በግዕዝ ይሰጥ ማለት ግዕዝን ለማሳደግ ወይስ ኦሮምኛን ለማሳደግ? ወይስ የኦሮሚያ ክልል የሚሰጥበትን ቁቤ ለመቃወምና ቅሬታ ለመፍጠር?

መልስ- ሁለቱንም ነው። አንደኛ ግእዝ፣  የኛ፣ የኢትዮጵያዉያን ሁሉም፣  የጥቁር ህዝብ ቅርስ ነው። ሌሎች ያላቸውን ትንሹና እንኳን ሲንከባከቡ እኛ ያለንን ትልቁን መሬት ላይ መጣል ተገቢ አይደለም። ሁለተኛ ላቲን ኢትዮጵያንም ኢትዮጵያዊ የሆነን ነገር በሚጠሉ ፣ ፕሮፌሰር አስራት የጥቁር ነጮች ባሏቸው አካራሪዎች ያለ ሕዝብ ፍላጎት በሕዝቡ ላይ የተጫነ ነው። በመሆኑም ከጣሊያንና ከጀርመን የመጣውን የነሙሶሊኒ ፊደል መቃወም ተገቢ ነው። እኛ የሌለንን፣ ወይም ካለን ከኛ የተሻለን ከሌሎች ብንወስድ ችግር የለውም፡ ተገቢ ነው። ግን ብቃት ያለውን የኛን ጥለን፣ በሁሉም ነገር ፈረንጆች ከኛ በላይ እንደሆኑ የመቁጠር ስነ-ልቢናዊ በሽታ ታመን፣  የሊሎችን ማግበስበስ ግን ስህተት ነው።

ጥያቄ 8- ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግዕዝ ይስጥ ብሎ ከመጠየቅ በፊት በኦሮሚያ ክልል በቁቤ የሚሰጠው ኦሮምኛ በግዕዝ እንዲቀየር የኦሮሚያ ክልል እንዲተገብረው ማደረግ መቅደቀምስ አልነበረትበም? የቋንቋው የመጀመሪውያ ባለቤት የኦሮሞ ህዝብ ያላደረገውን ሌላውን መጠየቅ ጤነኛ ጥያቄስ ነውን?

መልስ- ከላይ እንደጠቀስኩት ዶር ፍቅሬ ቶሎሳ በቀዳሚነት ለአቶ ለማ መገርሳ የጻፉት ደብዳቤ አለ። ለአቶ ገዱ የተጻፈውም ግልብጫ ለአቶ ለማ መገርሳና ለዶር አባይ ደርሷቸዋል። በተጨማሪ ለአቶ ገዱ ጻፈው የምሁራንና የአክቲቪቶች ስብስብ በድጋሚ ለአቶ ለማ በመጻፍ በኦሮሚያ በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ አንዳንድ ስራዎችን ለመስራት ጀመሯል።

“የቋንቋው የመጀመሪውያ ባለቤት የኦሮሞ ህዝብ ነው” የተባለው ፍጹም የተሳሳተና የኦሮሞ አክራሪዎችን ስለ አፋን ኦሮሞ እኛ ነን የሚያገባን የሚለው አይነት መልእክት የሚያንጸባርቅ ነው። ይሄ ቋንቋ የዚህ ዘር፣ ያ መሬት የዚያ ዘር የሚለው፣ የኛና የነርሱ የሚል አመለካከት ከፋፋይ አመላካከት ነው።፡ኦሮሞኛ የኦሮሞዎችን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ቅርስ ነው። አማርኛ የአማራዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትይጵያዊያን ቅርስ ነው። በኦሮምኛ ጉዳይ ኦሮሞ ነን የሚሉት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ያገባቸዋል። በተለይም ደግሞ ቋንቋም የፌዴራል ቋንቋ ፣ የአዲስ አበባ የስራ ቋንቋ ይሁን ከተባለ የሊሎችን ፍላጎት የሌሎች ስሜት መታየት አለበት።

ጥያቄ – 9.ኦሮምኛ ቋንቋ መማር የማይፈልገውን ወይም ያልጠየቀውን ህዝብ እኔ አውቅልሃለው መማር አለብህ ብሎ መብቱን መጋፋትስ የአማራን ህዝብ መናቅ ወይም እንደ የዋህ መቁጠር አይደለምን?

መልስ- ዜጎች አስተያየት የመስጠት መብታቸው የተጠበቀ ነው። ለሕዝቡ ይጠቅማል የሚለውን ሐሳብ አቅርበናል። ሕዝቡን ሐሳባችንን ይደግፋል ብለን እናስባለን።ለአማራ ክልል ህዝብ ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ እንዲያውቅ ሐሳብ መስጠት ህዝቡን ማዋረድ ተደረጎ ከተወሰደ የ”ዉርደትን” ትርጉም አዛብተነዋል ማለት ነው። ኦሮምኛ ማወቅ አማርኛን ማሳነስ ወይንም አማራን ማዋረድ አይደለም። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ የሚመነጨው ለአማራ ጥቅም ከማሰብ ሳይሆን ኦሮምኛን ከመጥላት ነው። ጥላቻ ደግሞ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ነው።

ጥያቄ – 10.የ ዚህ ጥያቄ ዓላማ በኦሮምኛ ቋንቋ ስም አንድነትን፣ መተባበርም፣ መግባባትን በጥቅሉ ኢትዮጵያዊነትን ማስፋፋት /መገንባት ከሆነስ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደርን የአማራ ህዝብ ቤተ ሙከራ ለማደረግ ለምን አስፈለገ?ራሱ ኦሮሞውን ወይም ሌላውን ክልል ቤተሙከራ ማደረግ ለምን አልተቻለም?

መልስ- ለፍቅር፣ ለአንድነት ቀዳሚ መሆን ያስከብራል እንጂ አያሳንስም። በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የአማራ ክልል መንግስት ፍቅርን አንድነት ለማጠናከር ቀዳሚ የሆኑ ስራዎችን ለመስራት ተዘግጅቷል። በባህር ዳር የኦሮሞ የማእከል እንደሚገነባ ተገልጿል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኦሮምኛ ተምህርት እንዲሰጥ ተወስኗል። ሙሶሊኑ በመስኮት ባህር ዳርን ከማጥለቅለቁ በፊት ጥንቃቄዎች መደረግ አለባቸው። ህዝቡም በዚህ ረገድ ግፊቱን እንዲያደርግ ለማበረታታ ነው ለአማራው ክልል ደብዳቤ ያስገናባነው። ለአማራ ክልል ጻፍን ማለት ሌላው ቦታ ምንም አልተደረገም ማለት አይደለም። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ላቲንን ጥሎ ግእዝን እንዲጠቀም እዚያም ግፊት እየተደረገ ነው።

እኛም ደግሞ መስራት ያለበን ያልሰራነው ነሀር አለ ከተባለ ደግሞ ያን ሳትሰሩ ይሄን ለምን ሰራችሁ ከማለት፣ እናንተ ይሄን እየሰራችሁ ነው፣ እና ደግማ ያን እንሰራለን ብሎ መነሳቱ ደግሞ የበለጠ የሚያስከብር ነበር።

ጥያቄ – 11.ከላይ ያለው ዓላማ ኢትዮጵያዊነትን ማጠንከር ከሆነ ለዚህ ሲባል ወደ ባህር ዳር የተደረገን ጉዞ ለምንስ ናዝሬት ወይም ደብረዘይት ወይም ወለጋ ላይ አልተደረገም? እኛ የኢትዮጵያዊነት ችግር ስላለብን ነው ወይ? የሚል ጠንከር ያለ ህዝባዊ ጥያቄ እየተጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅትስ በድጋሚ ይህንን አጀንዳ ማምጣት የአማራና ኦሮሞን ህዝብ አብሮነት አያሻክርምን?እንዴት ቢገምቱን ነው? የሚል ጥቄቃ አያስነስምን?

መልስ – እንዴት ተደርጎ ነው የአማራ ክልል ሕዝብ ኦሮምኛ እንዲማር መጠየቅ ኦሮሞውን የሚያስከፋው ? እንዴት ተደርጎ ነው ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነውን ቁቤ/ላቲን እንጣል ማለት አማራዉን የሚያስከፋው ? በዚህ ሰነድ የቀረቡት ሐሳቦች እንደዉም የበለጠ የሚያቀራረቡ፣ የልዩነት አጥሮችን የሚያፈራረሱ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ናቸው። ሊቀየሙና ሊያኮርፉ የሚችሉት የጥቁር ነጮች የሆነ የኦነግ ርዝራዦችና አክራሪ የአማራ ብሄረተኞች ናቸው።

አንድ ሌላ ነገር አንርሳ የላቲን ጉዳይ እልባት ካላገኘ አሁን ላቲንን ካላሽቀነጠርን ላቲኑ የግጭት መንስኤ መሆኑ አይቀሬ ነው። እኛ በአስተማማኝ ሁኔታ የኦሮሞዉን እና የአማራ ማሃበረሰብ መቀራረብ ነገ ፈተና ውስጥ እንዳገባ ከወዲሁ ይሄ ችግር እንዲፈታ ነው፣ ያለ ሕዝብ ፍላጎት በሕዝቡ ላይ የተጫነ ላቲን እንዲቀር እየሰራን ያለነው። አላማችን ፍቅር፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት ነው።

ጥያቄ – 12.የኦሮሚያ ክልል መንግስት በክልሉ ውስጥ ስለሚኖሩ አማራዎች ደህንነትም ይሁን የወደፊት ኑሮ ዋስትና ምንም አይነት ፍንጭ ባልሰጠበት እና አሁንም ጥቃቶች አልፌ አልፎ በሚታዩበት ወቅት የአማራን ህዝብ ቋንቋ ተማራ ማለት ተግባራዊነቱ ላይ ጥያቄ ውስጥ አያስገባውም?

መልስ – ይሄ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። እኛ ሐሳብ አቅርበናል። የክልሉ መንግስት ነገሩን አጥንቶ ፣ ህዝብን በማማከር የሚወስነው ይሆናል። በሁሉም የአማራ ክልል ወረዳዎች አሮምኛ ላይሰጥ ይችላል። ህዝቡ በውረዳ ደረጃ የሚማረዉን ቋንቃ ራሱ መርጦ ቢፈለግ ቅማንትኛ፣ ቢፈልግ ትግሪኛ፣ ቢፈልግ አገዉኛ.፣ ቢፈለግ አርጎብኛ ቢፈልግ ደግሞ ኦሮሞኛ፡መማር ይችላል። አሰራሩ በሂደት የክልሉ የትምህት ቢሮ የሚወስነው ነው የሚሆነው። ሐሳባችንንም የክልል መንግስቱ ከጅምሩም ዉድቅ ሊያደረገው ይቻላል። ያ የነርሱ ዉሳኔ ነው።

ጥያቄ – 13.በሁለቱ ህዝቦች መካከል የጥላቻ ሀውልት ተገንብቶ መሀል ላይ ቁሞብን እያለ ስለ ቋንቋ ከማውራት በፊት የጥላቻ ሀውልት ስለማፍረስ መሰባሰብ አይሻልምን?

መልስ- ከላይ በተራ ቁጥር ሶስት እንደገለጽኩት በኦሮሚያ የሌሎች ማህበረሰባት መብት በማክበር አንጻር ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ኦህዴዶች ላለፉት 27 አመታት ሲሰሩ የነበሩት ጥላቻን ማራገብ ነው። ከሕወሃት ጋር አብረው አማራውንና አማርኛ ተናጋሪዎች ሲጨፈልቁ ነበር። ለዚህም ነው ለሕዝብ ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤት መገንባት ሲቻል በሚሊዮች የሚቆጠር ወጭ በማፍስስ በአኖሌና በጨለንቆ የጥላች ሃዉልት ያቆሙት።

ሌላው ቢቀር ሃዉልት ማቆም አለብን ካሉ በኦሮሞ ታሪክ ትልቅ ገድል የፈጸሙ በርካታ የኦሮሞ አባቶች አሉ። እነ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ጀነራል ታደስ ብሩ፣ጀነራል ጃጋማ ኬሎች ፣ ደጃዝማች ጆቲ ቱሉ…የመሳሰሉት። ሌላ ብዙዎች የማያውቋቸው ብዙ አስተዋጾ ያደረጉ አባ ገዳዎች ይኖራሉ። ለነርሱ ሃዉልት በማቆም ሌላው የበለጠ የኦሮሞን ባህልና ታሪክ እንዲያውቅ፣ እንዲማር ማስደረግ ይችሉ ነበር። ያን ቢያደረጉ ጅማ እንዳለው የጂማ አባጂፋር ቤተ መንግስት ለመጉብነት እንሄድ ነበር። አሁን ግን እንኳን የአኖሌ ሃዉልት ሄደን ልንጎበኝ አካባቢዎችም አንደርስም።

ሃዉልቶቹ ከማንም በላይ የሚጎዱት የኦሮሞ ማሀብረሰብን ነው። ያንን ተረድተው ኦህዴድ ያቆማቸውን ሃውልቶች ሕዝቡ ራሱ ያፈርሳቸዋል ብዬ ነው የምጠብቀው። ምንም ጥርጥሬ የለኝም። ሁሉም በጊዜው ይሆናል። ሆኖም ግን እዚያ ማዶ ያሉ ድንጋዮች መቆማቸው መደረግ ያለበትን እንዳናደርግ እንቅፋት እንዲሆን መፍቀድ የለብንም።