አይረሴዎቹ የወርሃ መጋቢት 1969 ዓም መስዋዕቶች ጀግኖቹ መድፈኛቹና ፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶቹ !

አይረሴዎቹ የወርሃ መጋቢት 1969 ዓም መስዋዕቶች
ጀግኖቹ መድፈኛቹና ፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶቹ !

ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ
ሳክራሜንቶ / ካሊፎርኒያ

የሶማሌው ፕሬዚዳንት የነበሩት ኢንጉልፋቶው ዜያድ ባሬ ፤ በካባድ መሣሪዎች፤ በበርካታ ብረት ለበስና በአየር ላይ ተምዘግዛጊ ሚግ ጀቶቹንና በብዙ አሥራ ሺዎች የሚቆጠሩ እግረኛና ጦሩን አሰማርቶ በሰኔና በሐምሌ ወሮች 1969 ዓም የግልጽ ወታደራዊ ወረራውን በኦጋዴን ፤ በከፊል ባሌና ሲዳሞ ግዛቶች ከመፈጸሙ በፊት፤ በምዕራብ ኦጋዴን ነፃ አውጭ ስም ያደራጃቸውን ሽምቅ ተዋጊ ወታደሮቹን አስቀድሞ አስርጎ በማግባት ፤ ወታደራዊ ኃይላችንን ለማዳከም በተለያዩ ቦታዎች ተኩስ በመክፈት ሠራዊቱን ማዳከሙ የታወቀ ሥልቱ ነበር።

የጥር ፤ የካቲት ፤ መጋቢትና ሚያዚያ 1969 ዓም ወሮች በተለይም በፊቅ ፤ በባቢሌ ዳከታ ዝቅተኛ ሥፍራዎችና በሰላማዊ ፖሊሶች ይጠበቁ የነበሩ የጠረፍ ከተሞች ዓይነተኛ የደፈጣ ውጊያ ጥቃት መስመሮቹ ነበሩ ። የሐረርና አካባቢውም እንደ ማንኛውም የጦር ቀጠና አካባቢ የጦር ሠራዊቱና የፖሊስ ሠራዊቱ ተሽከርካሪዎች ለግዳጅ ወዲያና ወዲህ ሲባዝኑ ፤ ወታደሩ በቅጠልያና የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ተሸክሞ ሰርክ መመልከቱ ለነዋሪዎቿ እንግዳ ነገር ከመሆን አልፎ ፤ ወሬውና ሽኩሽኩታው ስለ ጦርነቱ ነበር ። መላው ሐረርጌን ዓየር ጦርነት ሸቶታል። ያ ጦርነት ታዲያ በውዠንብርም የተሞላ ነበር ።

በጦርነቱ ቆስለው አስቸኳይ ነፍስ አድን ዕርዳታና ፤ በከፋ ሁኔታ የቆሰሉ ወታደሮችን ደግሞ ከውጊያው ሥፍራ በሄሊኮፕተር እየተጓጓዙ በአካዳሚ ወታደራዊ መኮንኖች ማሰልጠኛ ተቋም የሰልፍ ሜዳ ላይም እያራገፉ፤ በቀላድ ዓምባ በሚገኘው የሠራዊቱ ሆስፒታል፤ በአካዳሚው ግቢ በነበረው አነስተኛ፤ በፖሊስ ሠራዊትና በተቀሩትም በከተማው የሚገኘ ሆስፒታሎች ሁሉ የተጣደፈ ህክምና አገልግሎት ሲሰጡም ታዝበናል ።

ከሐረር ከተማ አንዳንድ ሥፍራዎችም በተለይ ባቢሌ ከተማና የዳከታ ዝቅተኛ ሥፍራዎች ጎላ ብለው በሚታዩበት ጠራራ ሰዓትም ላይ፤ ጀግኖቹ የኤፍ 5 ተዋጊ ጀት አብራሪዎቹ የጦር መኮንኖቹም በአየር ላይ እንዲደበደብ የተሰጣቸውን ግዳጅ ሲፈጽሙም ፤ እንደ ትርዒት ፈዘን ቆመን ተመልክተን አድንቀናል ። አየር ኃይላችን የሐረርን ከተማ ተሻግሮ ሲሄድ ድምፁን ሳንሰማውና በአየር ላይ ሳናየው፤ ግዳጁን በአየር ላይ ከፍና ዝቅ እያለና እየተንሳፈፈ ፈጽሞ ሲመለስ ፤ የደስታ ሲቃ የያዘውና የድል ምልክት ማሳያውን ምልክት ጩኸት ዝቅ ብሎ በሐረር ከተማ ላይ እንደ ብራቅ ሲለቀው አንዳንዶቻችን ሮጠን መሸሸጊያ ፈልገናል ። በድምፁም መጠን ከፍታ፤ በከተማዋ የሚገኙ በመስታወት የተሸፈኑ መስኮቶችና የቤት ክዳን መክደኛ ቆርቆሮዎች ለመንቀጥቀጣቸውና ለመሰበራቸው ሕያው ምስክሮች ናቸው ። የድል ብሥራት ትርዒት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቁርጥ ቀን ልጆች ፦

አይበገሬዎቹ ፤ ንስር አሞራዎቹ
አየር ኃይሎቹ ፤ የቁርጥ ቀን ልጆቹ
ተዋጊዎቹ ደፋሮቹ፤ ዐርበኞች ጀግኖቹ።

ፖለቲካ ውለታ አያውቅም ። ሥልጣን ወንበር እንጂ ጭንቁ ፤ የጀግኖችና ዐርበኞች ውለታ ለፖለቲከኞች ፋይዳ የለውም ። በተግባር የተፈተኑና በልምድ የዳበሩ የሃገር ሃብት የፈሰሰባቸው ተቋማቸውም እነርሱም ቤተሰባቸውም እንደ አልባሌ ዕቃ ተበተኑ። ድሮም በኢትዮጵያ ታሪክ ውለታን የሚያውቀው ሕዝብ እንጂ ፤ የመጣ መንግሥት ላለመሆኑ በርካታ አስረጂዎችን መሰብሰብ ይቻላል ።

ይህ በእንዲህ እያለ ነበር በተከታታይ ከባቢሌና ከፊቅ የጦር አውድማዎች እጅግ አሳዛኝና አሰቃቂ የመስዋዕትነት ዜናዎች በተከታታይ የተሰሙትና የተስተዋሉት ። የሠለጠኑና በወጣት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ወታደሮች ቁጥራቸው ከ60 በላይ የሚሆኑ ለግዳጅ ሲጓዙ በፊቅ – ባቢሊ ጥርጊያ መንገድ ላይ በደፈጣ ተዋጊዎቹ ሠርጎ ገቦች በተቀበረ ፀረ – ተሽከርካሪ ፈንጂ ላይ በመውጣቱ ፤ ፈጥኖዎቹ በፈንጂ እሳት ተቃጥለው የሕይወት መጥፋትና በከፍተኛ ደረጃ አካል በእሳት የመቃጠል ዕጣ ፈንታ የተቀበሉት ። የሓረር ከተማ ለቅሶ ደራሾች እናቶችን ከመንደር መንደር ነጠላ አዘቅዝቆና በደረት ዙሪያ በመርፌ ቁልፍ የታሰረ ፎጣ ተጥሎ ማየት የተለመደ ክስተት ሆነ ። በተለይም የቀላድ ዓምባ ፤ የኮንጎ ሠፈር ፤ ቋሚ ሠፈር ፤ አቦከር አራተኛና የሸንኮር ዳርቻዎች በለቀስተኛው ነዋሪዎች ተሞላች።

ጥቂትም ሳይቆይ በወርሃ መጋቢት ሁለተኛው ሣምንት ደግሞ የሞት ጥላ ደመና ያንዣበበባት የሠራዊቱ መንደር ሐማሬሳም የመስዋዕትነት ዕጣዋን ተቀበለች። የ፫ ተኛው ክፍለጦር የ፪ ተኛው መድፈኛ ሻለቃው ጦር ባልደረቦች በዳከታ ዝቅተኛ ሥፍራዎች በእግረኝነት ዘምተው ፤ ሌላ ዙር መስዋዕትነትን በፈንጂ ላይ በመረማመድና በውጊያ መሃል ወደቁ ። ተሰው ። መቃብራቸው ዳከታ ሆነች ። መርዶው መጣ። የሠራዊቱ ቤተሰቦች ተሸበሩ ። እናቶች እንደተለመደው አሸረጡ ። የመስዋዕትነት ዜናቸውን ለመስማት፤ በትንሿ መንደር አማካይ ሥፍራ ሜዳ ተመርጦ ፤ በቀሪውና በእኛ ወጣቶችና በነዋሪዎቿ ትብብር በርካታ ድንኳኖች ከተተከሉ በኋላ የመርዶው ዜና በአስተዳደር መኮንኑ፤ ዛሬ በሕይወት የሌለው ወላጅ አባቴ በሻምበል ታምሩ ዓየለ፤ እንደ ማዕረጋቸው የመስዋዕትነቱ ዜና ተበሰረ። ሐማሬሳ በነዋሪዎቿና በህፃናቶች ዋይታና እሪታ ተናጠች ። ከተማው አበደች ። በለቅሶና ዕሪታ ተሞላች ። ሐማሬሳ አለቀሰች ፤ አዘነችም ተከዘችም። ሃዘኑም ቆየባት ደጋገማትም። በዛን ዕለት ብቻ ቁጥራቸው ወደ 19 የሚጠጉቱ መስዋዕነታቸው ከወታደራዊ ሚስጥርነት ገሃድ ሆነ ።

የመስዋዕቱ ተቀባዮች የልጆች አባትና በ1956 / 57 ዓም በቶጎጫሌ ጦርነት ወቅት የመድፉን ቀለህ እሩምታ ለቀው ወራሪውን ረሚም ( ድባቅ የመቱ) ያደረጉ የጦር ሜዳ ጀግኖችም ነበሩ ፤ የመሠረቱትን ትዳር በቅጡ ጎጆአቸውን ያላቆሙ ፤ የባለቤታቸውን ምጥ ተረድተው የፀነሷቸውን ልጆች ሲወለዱ የመሳም ዕድል የተነፈጉ ፤ የጀመሩትን ፍቅር ደህና አድርገው ያላጣጣሙ ፤ እጮኛቸውን ከንፈር እንኳን አጣጥመው ለመሳማቸው ያልታደሉ ፤ ነዋሪው በሞላ የሚወዳቸው ወጣትና ዐመለ ሸጋ ወታደሮች አንዳንዶቹም የስፖርት ፍቅርና ችሎታ ያላቸው አድናቂያቸውም የበዛ ነበሩ።

የሐማሬሳ አሳዛኝና አስለቃሽ ሁነቶች በዚህ ብቻ አልበቃም ። በዕለተ ሰኔ 21 ቀን 1969 ዓም ከግማሽ ሌሊት በላይ በሠርጎ ገቦቹ ተከባ በተኩስ እሩምታ ድምፅ ስትናጥ አድራለች ። ነዋሪዎቿን አስደንግጣም አሸብራለች ። ዕድሜ ለአባት ጦር አባሎችና የቀሪ ሠራዊቱ ክፍል ወታደሮች ፤ በየምሽጉ አድፍጠው የጠበቁ ባለውለታዎች ፤ የከፋም ችግር ሳይገጥማት ትንቅንቁን በአሸናፊነት ወጥታለች። በተመሳሳይ በቆሬው ግንባርም ከ21 በላይ የሠራዊቱ መድፍ ክፍል ተዋጊዎቻንም መስዋዕት ተቀብላ እንደገና በት/ቤቷ ቅጥር ግቢ ድንኳን ጥላ በጋራ አዝናለች፤ በወረራውም ወቅት በርካታ ወታደሮች ነዋሪዎቿ በኦጋዴን በረሃዎች የማፈግፈግ ሥልት ሲከተሉ አቅጣጫ ስተው ከጠላት እጅ የወደቁና እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ደብዛቸው የጠፉ ወታደሮችም ቤተሰቦች የሚገኙባት ምድር ነች። በሠራዊቱም ውስጥ በቂ አገልግሎት ስጥተው በጡረታ የተገለሉትም ጭምር በቀረበላቸው የዳግም ዘመቻ የእናት ሃገር ጥሪ ዘምተው በአረጋዊ ዕድሜያቸው ቤተሰብ በትነው እስከ ወዲያኛው ሄደዋል። የወደቁበትን ሥፍራ እንኳን ዛሬም ድረስ ሕያው የሆኑ የቤተሰባቸው አባሎች አያውቁትም። ባስታወሱ ቁጥር በሰቀቀን ይኖራሉ። ጩኸቷ በንፋስ ውስጥ የቀረ፤ ሃዘነቶኞቿ እንደባከኑ የኖሩባት ሐማሬሳ ጠባሳ ወሯታል።

ትንሿ መንደር በዚያ የወረራ ጦርነት ወቅት ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሥልት እስከ ተጀመረበት የየካቲት ወር 1970 ዓም ድረስ የጦር ሜዳም አውድማ ነበረች ። በርካታ የጠላት ጦር የታንክ፤ የመድፍና የሞርታር ጥይት ጥቃት ሰለባም ሆናለች ። የሞት ጥላው ዳመና እንዳንዣበበባት ቆይታ፤ በሁሉም የአገሪቱ የጦር ግምባሮች መስዋዕቶቿን እስከ መንግሥት ለውጥ ድረስ ስትሰጥ ከርማለች ።

የዚህችን ታሪካዊ ከተማ መስዋዕቶች በሚገባ መዘከርና የአገሪቱ የሠራዊቲ ታሪክ ትልቅ አካል አድርጎ ማቅረብ ተገቢና ወቅታዊ ነውም ብዬ አምናለሁኝ። ሐማሬሳም ሃዘነተኛ ነዋሪዎቿም የሙት ልጆቿም በምድሪቱ ላይ የወረደው ችግር ግምባር ቀደም ገፈት ቀማሾችና ሰለባዎች ናቸው። ዛሬም ቢሆን የተገፉና ገለል የተደረጉ ናቸው። በሁሉም መስኩ ዛሬ ከሚኖሩት ነዋሪዎቿ መረጃዎችን መሰብሰብና ማደራጀት በተለይም የሠራዊቱን ተጋድሎ ታሪክ እየነቀሱ በመጻፍ ያሉት የጦር መኮንኖችም ጉዳይ መሆን እንዳለበት እመክራለሁኝ ።

ባለፈው ዓመት ላይ ሚያዚያ ወር መሰለኝ ይህንን መፈክር በዋናነት አስምቻለሁ ።

” ለማያውቀው ሐማሬሳም ትንሽ መንደር ነች! ” ፦ ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ

” For whom does not know : Hamaressa is just a simple village. ” – Solomon Tamiru Ayele

ሠሎሞን ታምሩ ዓየለ
ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፱