የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ የነበረበት በ”መንግስት” ላይ ነበር!

አዋጅ መታወጅ የነበረበት በ”መንግስት” ላይ ነበር!

ጌታቸው ሽፈራው

~ዜጎች የግል ሱቃቸውን ዘግተው ዋሉ ተብለው ይታሰራሉ፣ የንግድ ፈቃዳቸውን ይቀማሉ!

~ የታክሲ፣ የባጃጅ፣……የተቋማት ባለቤቶች የግል ጥቅማቸውን “ይቅርብን” ብለው ቢሮ ስላልገቡ እጥፍ ድርብ በደል ደርሶባቸዋል፣ እየደረሰባቸው ነው!

~ዜጎች የግል ስራቸውን ትተው ቤታቸው ስለዋሉ “አግልግሎት አቋረጡ” ተብሎ አዋጅ ታውጆባቸዋል!

ገዥዎቹን የትኛው አዋጅ ይገዛቸዋል?

~ለምሳሌ፣ ዛሬ መጋቢት 9/2010 ዓም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 9 ሰዓት በጎንደር ምንም አይነት የስልክ አገልግሎት አልነበረም። ነጋዴዎች ተደዋውለው ስራቸውን እንዳይከውኑ፣ ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን እንዳያሟሉ “መንግስት ነኝ” የሚል አካል አገልግሎት አቋርጦባቸዋል። ይህን አገልግሎት የሚያቋርጡት በሕዝብ ገንዘብ ደሞዝ ተከፍሏቸው የሚኖሩ ናቸው!

~ዜጎች የራሳቸውን ሱቅ ዘግተው ይውላሉ ብሎ መግደልንም ጭምር የፈቀደ አዋጅ ያወጣ “መንግስት ነኝ” ባይ ዜጎች በሚከፍሉት ግብር የሚሰጠውን አገልግሎት አቋርጦ ይውላል። ይህ “መንግስት ነኝ” ባዩ በዜጎች ላይ የመታው አድማ ነው!

~በእርግጥ የስልክ አገልግሎት ብቻ አይደለም። በክልሎቹ የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ አድማ ካደረገ ወራት አልፈዋል። ቴሌ የሚባል የገዥዎቹ “ጥገት” ከዜጎች በሚያገኘው ገንዘብ እየሰራ ለገዥዎቹ ሲል በዜጎች ላይ የኢንተርኔት እቀባ አድርጎ ቀጥሏል። ለፈረንጆቹ ሲባል ብቻ አለ፣ የለም ለማለት የማያስችል ዋይ ፋይንን አልዘጉትም።

~ በርካታ ዜጎች ስራቸውን በስልክ ይከውናሉ፣ ኢንተርኔትን የገቢ ምንጫቸው አድርገው ኢንተርኔት ካፌ የከፈቱ ብዙዎች ነበሩ። በኢንተርኔት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን የሚያፋጥኑ ብዙዎች ነበሩ። በእነዚህ ላይ መንግስት ነኝ የሚለው የስራ ማቆም አድማ አድርጓል። ከእነሱ በሚሰበሰስበው ገቢ አድማውን ያስፈፅማል!

~መግደልንም መብት ያደረገውና ተጭበርብሮ የታወጀው አዋጅ በሚፈፀመው በደል ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ የግል ስራቸውን በሚየቆሙት ላይ ነው! በአንፃሩ የሕዝብና የሀገር አገልግሎትን ሲዘጋ፣ ለራሱ ሲጠቀም፣ ሲያጓትት የኖረ ትህነግ/ኢህአዴግ ተጠያቂ ሆኖ አያውቅም።

~አዋጁ አስፈላጊ አይደለም፣ ለመፅደቅ የሚያስችል ድምፅም አላገኘም! አዋጅ መታወጅ ከነበረበት ግን ሊታወጅ ይገባ የነበረው በሕዝብ አገልግሎት ላይ አድማ በሚየደርገው “መንግስት ነኝ” ባይ ላይ ነበር!