“እህትክን እንድንፈታልህ ከመንግስት ጋር ስራ” ተብሎ የተሰቃየው የንግስት ይርጋ ወንድም

“እህትክን እንድንፈታልህ ከመንግስት ጋር ስራ” ተብሎ የተሰቃየው የንግስት ወንድም

ሚኪያስ የንግስት ይርጋ ታናሽ ወንድም ነው። ንግስት ከመታሰሯ በፊት ታናሽ ወንድሟ ሚኪያስ ከጎኗ አይጠፋም ይባላል።

ንግስት ይርጋ ከተከሰሰችበት የአማራ ሕዝባዊ ንቅናቄ በፊት ወደአርማጭሆ(ደብረሲና) ተመልሶ በግል ስራ ተሰማርቶ ነበር።

ንግስት መስከረም 5/2009 ዓም ታሰረች። ንግስት ከታሰረች ከወር በኋላ ታናሽ ወንድሟ ሚኪያስ ስራው ላይ እያለ ታፍኖ ታሰረ። የተወሰደው ወደ ጎንደር ወይንም ወደ አዲስ አበባ ሳይሆን ወደ መቀሌ ነበር።

ሁለት ወር ከ17 ቀን በመቀሌ ታፍኖ ከቆየ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተወሰደ። አዲስ አበባም ሕጋዊ የሚባል ተቋም አልተረከበውም። ለአንድ ወር ያህል ድብቅ እስር ቤት ውስጥ ከታሰረ በኋላ ንግስት ተከስሳ ወደ ቃሊቲ ከተዛወረች በኋላ በጥር ወር 2009 ዓም ወደ ማዕከላዊ ይዛወራል። ማዕከላዊ በታሰረበት ወቅት “እህትክን እንድንፈታልህ ከእኛ ጋር አብረህ ስራ” እየተባለ ስቃይ ደርሶበታል። በወቅቱ ሚኪያስን ይመረምሩት የነበሩት ዋነኛዎቹ የማዕከላዊ ሰዎች እንደነበሩ ተገልፆአል።

ከማዕከላዊ የቀረበለትን መደራደሪያ አሻፈረኝ ቢልም፣ አብረውት ታስረው ከነበሩት “ወጥተህ የምትሰራውን አንተ ነው የምታውቀው” የሚል ምክር ያገኘው ሚኪያስ የማዕከላዊን ጥያቄ ይቀበላል።

“የምሰራውን አውቃለሁ” ብሎ የማዕከላዊን መደራደሪያ የተቀበለው ሚኪያስ ያሰበው አልሆነለትም። ከእስር አልተፈታም። ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር በመኪና አመጡት። ከእናቱ ውጭ ማንንም እንዳያገኝ ተገለፀለት። ሁለት ቀን ብቻ ከእናቱ ቤት እንደቆየ የት እንደገባ አልታወቀም።

እህቱ ከተፈታች ከቀናት በኋላ የሚኪያስ በሕይዎት መኖሩ ተሰማ። ሳንጃ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ። የታሰረበት ምክንያት ከአርበኞች ግንቦት 7 አባል ሆኖ ከኤርትራ ደርሶ ተመልሷል የሚል ነው። ሆኖም በወቅቱ የደብረሲና ቀበሌ አመራሮች ምህረት እንዳስገቡት ለማወቅ ተችሏል። ሚኪያስ ከታሰረ በኋላ ምህረት ያስገቡት የደብረሲና አመራሮችም ለእስር ተዳርገው ነበር። ከሶስት ቀናት በፊት የተፈቱ ሲሆን ሚኪያስ አሁንም በእስር ላይ ይገኛል።

ሚኪያስ የታሰረው ኮማንድ ፖስቱ ከመታወጁ በፊት ሲሆን ፍርድ ቤቱ ዋስ አቅርቦ እንዲፈታ ፈቅዶለት ነበር። መጀመርያ የሰው ዋስ፣ በኋላም የገንዘብ ዋስትና ተፈቅዶለት የነበር ቢሆንም ሁለቱንም በ”ኮማንድ ፖስቱ “ስም ተከልክሎ በእስር ላይ ይገኛል።

ሚኪያስ ይህ ሁሉ ግፍ እየደረሰበት የሚገኘው ከስርዓቱ ጋር አልሰራም በማለቱ እንደሆነ እና በዚህ ምክንያትም ህይወቱም አደጋ ውስጥ ነች ተብሏል።