“ከመቶ አመት በኋላ ዛሬ የት ነን?” (ያሬድ ሹመቴ)

“ከመቶ አመት በኋላ ዛሬ የት ነን?”
(ያሬድ ሹመቴ)

በ1898 ዓ.ም ተወዳጁ ልዑል ራስ መኮንን በድንገተኛ ህመም በሞቱ ግዜ፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሐዘን ብዛት ተጎድተው፤ ከአልጋ ወርደው መሬት እስከማደር ደርሰው ነበር። በወቅቱም ራስ መኮንን ያስተዳድሩት ከነበረው የሐረርጌ ግዛት መኳንንቱ እና አጃቢዎቻቸው ልጃቸውን ደጃዝማች ተፈሪ (አፄ ኃይለሥላሴ) ይዘው ለለቅሶ አዲስ አበባ ይገባሉ።

የሀዘን ስነሥርዓቱ ቢጠናቀቅም ተፈሪ እና የሐረር መኳንንቶች ሾላ አካባቢ እንደሰፈሩ ወደ ሀረር ሳይመለሱ ረዥም ጊዜ ይቆያሉ። በኋላም እቴጌ ጣይቱ ተፈሪን ወደ ቤተ መንግስት አስመጥተው ያስቀምጧቸዋል። ከሀረር ሹማምንቶችም ሁለቱን ዋናዎች መርጠው ‘ራስ መኮንን ጥሩ ህክምና እንዲያገኙ አላደረጋችሁም’ በሚል ክስ ይዘው ያሳስሯቸዋል።

ለዚህ ሁሉ ሰበብ የሆነው ደግሞ፤ የሐረርጌ ሰዎች “ተፈሪ በአባቱ ግዛት ሐረር ይሾምልን የሚል ጥያቄ በማብዛታቸው እንደሆነ “ተፈሪ ረዥሙ የስልጣን ጉዞ” በሚለው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ ይገኝል።

በአፄ ምኒልክ ህመም ምክንያት የአስተዳደሩ ጉዳይ እቴጌ ጣይቱ እጅ ላይ ወድቆ ነበርና በምኒልክ ስም ሹም ሽር የሚያደርጉት እሳቸው ነበሩ።

እቴጌ ጣይቱ ለሐረርጌ ተሿሚ ያደረጓቸው በትዳር የተዛመዷቸውን፣ ራስ መኮንን ከቀድሞ ባለቤታቸው የወለዷቸውን ደጃዝማች ይልማን ነበር።

መኳንንቱም “ተፈሪ ለምን አልሆነም?” የሚለውን ተቃውሟቸውን አጠናክረው ሲቀጥሉ፤ እቴጌ ጣይቱም “ተፈሪ ለምድነው ሀረር የሚሾመው?” ብለው መልሰው ይጠይቃሉ። “የሐረር ህዝብ፣ ተፈሪ በአባቱ ቦታ ተቀምጦ እንዲያስተዳድረው ይፈልጋል” ሲሉ መልስ ይሰጣሉ።

(እቴጌይቱም ፤ ከ112 አመታት በኋላ ዘንድሮ ፤ ከታች በምስሉ ላይ ያለውን ሀሳብ የሚመስል መልስ በመስጠታቸው ልብ ትሉ ዘንድ ነው ይህ ሁሉ ጨዋታ የመጣው።)

እቴጌ ጣይቱም እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጧቸው። “ህዝቡ ‘ተፈሪ ይሾምልኝ’ አለ ነው የምትሉኝ? ከመቼ ወዲህ ነህ ህዝብ መሪ የሚመርጠው? ህዝብ ስራው የተሾመለትን አሜን ብሎ መቀበል እንጂ፤ ይህ ይሾምልኝ! ያ ይሻርልኝ አይልም። ይልቅ ህጻኑ ተፈሪ እንዲሾምላችሁ የምትፈልጉት እናንተው መኳንንቱ ናችሁ” ሲሉ መለሱላቸው።

ከመቶ አስራ ሁለት አመታት በኋላ፣ ዛሬስ የት ላይ ደርሰን ይሆን?