የ”ጠላት” ደረጃ የወጣለት የአብይ ጉዞ (ጌታቸው ሺፈራው)

የ”ጠላት” ደረጃ የወጣለት የአብይ ጉዞ

(ጌታቸው ሺፈራው)

~የእነ ለማ ቡድን አብይን ወደጠቅላይ ሚኒስትርነት ያመጣው ተስፋ በቆረጠ ሕዝብ ተስፋ ነው። ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ድጋፍ ሳይቀር! ትህነግ/ህወሓትን ባስደነገጠ መልኩ “ኮንትሮባንዲስቶችን” በመታገል ወደ ሕዝብ ልብ ለመግባት ጥረዋል። ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ አብሮነት ብዙ ብለዋል። የትህነግ ደህንነቶች አማራና ኦሮሞን እያጋጩ እንደሆነ መታወቂያቸውን በሚዲያ በማሳየት ጭምር የትህነግን ድንበር ተጋፍተዋል። ሙሰኛ፣ ስኳርና፣ከሰል፣ ቡና እና ሌሎች ምርቶችን ዘርፈው እንደሚወስዱ በመግለፅ ከቆየው ኦህዴድ የተለየ በመሰለ አቋማቸው ህዝብን አማልለዋል! በአብዛኛው ህዝብ የትህነግ/ህወሓት አቋሞች ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን እንደሚፀየፉ በመግለፅ ባልተለመደ መልኩ ኢህአዴግ ውሰጥ ያለ አካል ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ አስሰንቀዋል። ይህ የእነ ለማ የፕሮፖጋንዳ ይዘት ተቃዋሚዎች ሲጮሁበት ከነበረው ቢያንስ እንጅ የበለጠ ሆኖ አይደለም። ሆኖም ኢህአዴግ ውስጥ ያውም ኦህዴድ ውስጥ መሆኑ ይህ አቋም እንደነብይ እስኪሳሉ ድረስ ተስፋ አስጥሎባቸዋል። ዋናው ግን ትህነግ/ህወሓትን ጋር የአቋም ልዩነት አላቸው ስለተባለ ነው።

~ዶ/ር አብይ አህመድ ሲመረጥ በተደጋጋሚ “የስልጣን ሽግግር” እየተባለ ተወርቷል። ስልጣን ከኢህአዴግ ወደየትም አልተላለፈም። በሀይለማርያም ዘመን የስልጣን ሽግግር ተብሎ ብዙ አልተወራም። ቢበዛ መተካካት ሲሉ ነው የሰማነው! እነ አብይ ኢህአዴግ ውስጥ ሆነው የ”ስልጣን ሽግግር” ሲሉ ትህነግ/ህወሓት ለአመታት የያዘውን ስልጣን ሊቀናቀኑ እንደሚችሉ ለመግለፅ ነው። ኢህአዴግ ውስጥ ሆነውም ምንም አይነት ስልጣን እንዳልነበራቸው፣ ትህነግ/ህወሓት ተቆጣጥሮት እንደቆየ በግልፅ የተናገሩበት ነው። ይህ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚሉት ከምንም የተናገሩት አይደለም። አብይ ወደ ስልጣን ሲመጣ የነበረውን ፍትጊያ ወቅት ከትህነግ ጋር ” እኛ እና እናንተ” ተባብለው፣ገዝና ተገዥ እንደነበሩ ሲናቆሩበት ሲሰነብቱ የለመዱትን በአደባባይ የተናገሩት ይመስለኛል።

~እነ አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ካጋጠማቸው ፈተና መካከል የሶማሊ ክልሉ አብዲ አንዱና ዋነኛው ነበር። እነ ለማ የትህነግን ድንበር ተጋፍተው ወደ ሕዝብ ልብ ለመግባት ሲጥሩ፣ ትህነግም አብዲ አሌ ከበስተጀርባቸው እንዲወጋቸው አድርጓል። አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የኦሮሞ ህዝብ አፈናቅሎ ከትህነግ ጋር የነበራቸውን መገፋፋት አቅጣጫ ለማሰቀየር ጥረት አድርጓል። ከምንም በላይ ትህነግ ስብሰባ ላይ “ህዝበኛ” የሚላቸውን ኦህዴዶች በአብዲ በኩል በመንግስት ሚዲያ “ኦነግ” ብሎ አስፈርጇቸዋል። ኦህዴድና ትህነግ ከምክር ቤት ስብሰባ ባሻገር ሶማሊ ላይም የውስጥ ትግል አድርገዋል። ለዚህም እነ አብይ ወደ ስልጣን ለመምጣት 1ኛ ትህነግ፣ 2ኛ አብዲ አሊ ብለው የጠላት ደረጃን ሊያስቀምጡ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። ከትህነግ የተለየ አቋም ይዘዋል ብሎ ያጨበጨበላቸው ተቃዋሚው ከዛ በኋላ የሚመጣ ነው!

~ዶ/ር አብይ በንግግሩ ከተቃዋሚዎች ጋር እንደሚነጋገር ገልፆ ነበር። የመጀመርያው ንግግር ከኋላው ሲወጋው ከቆየው አብዲ ጋር ነው ያደረገው። ይህን ሲያደርግ የትህነግን ወኪል ጠላት ከጎኑ ለማራቅ ነው። አብዲን ከትህነግ ወኪልነት በማራቅ የጀርባ ውጋቱን ለማስታገስ ነው። አብይ ከተቃዋሚዎች ጋር እንነጋገራለን ያለውን እንዳልረሳው ለማሳየት ብቻ የራት ግብዣ አድርጎ ሸኛቸው። “ከተቃዋሚዎች ጋር እንወያያለን”! ብሎ ለተቃዋሚዎች አብዲና ትህነግን ለማስደሰት ያደረገውን ቅንጣት ነገር አለማድረጉ ለአብይ ከተቃዋሚው በላይ ጠላት ተብሎ የተፈረጀው ማን እንደሆነ ግልፅ ነው።

~በአብይ ስልጣን ዘመንን እጅግ የከበደ የሚያደርገው ትህነግ በመከላከያ፣ ደህንነት እና ካድሬው ያለው መዋቅር ነው። እነዚህ አካላት አብይን ተጠያቂ ለማድረግ የማይቆፍሩት ጉድጓድ እንደማይኖር ግልፅ ነው። በዚህ ላይ አብይ “ትግሬ ይጠላል” የሚል ሰፊ ቅስቀሳ ተደርጎበተል። አብይ ከዚህ አደጋ ለመዳን ዋናውን ተቀናቃኙን ማለዘብ አለበት። ወደ መቀሌም ያመራው ለዚሁ ነው። የትህነግን ሰዎች ለማስደሰት የአዝማሪ ያህል አወድሷል! አስጨብጭቧቸውም ተመልሷል! ዋናዎቹንም ባይሆን አብዛኛውን የትህነግ ካድሬ ልብ ሊገዛ የሚችል ንግግር አድርጓል። ትህነግን ብቻ ሳይሆን የትህነግን ወኪል እነ አብዲንም አስጨብጭቦ ተመልሷል። ይህም ለአብይ የስልጣን ዘመን ትህነግ እና እነ አብዲ ምን ያህል አስቸጋሪዎች እንደሆኑ የሚያሳይ ነው።

~ዶ/ር አብይ የተለየ ያደረገው ጉዞ የአምቦው ነው። ይህኛው ስብሰባ ሲደግፈው በነበረው ሕዝብ የተደረገ ነው። ትህነግ/ህወሓትን ለመዳፈር እነ አብይ ሕዝብን በካርታነት አልተጠቀሙም ማለት ይከብዳል። በአንድ በኩል ተቃውሞው ውስጥ ኦህዴድ እንዳለበት በማስገለፅ፣ በሌላ በኩል ይህን ተቃውሞ ኦህዴድ ሊያበርደው እንደሚችል ሲያሳዩት ቆይተዋል። አሁንም ህዝቡ ከጎናቸው መሆኑን ለማሳየት ጥረዋል። አምቦ ላይ እነ ዶ/ር መረራም ከፍተኛ ድጋፍ እንዳላቸው ታይቷል። ኦህዴድ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚዎች የተሻለ ድጋፍ እንዳለው ፣ ህዝቡም ለኦፌኮ መሪዎች ካሳየው በላይ ድጋፍ እንደሚሰጥ ለማሳየት ሞክረዋል።

~ብአዴን የእነ አብይ ደጋፊ ሆኖ ታይቷል፣ ወደ አማራ ክልል የማይመጡበት አንዱ ምክንያት ብአዴንን በወዳጅነት ከጎን ስላስቀመጡት ነው። በሌላ በኩል “አማራ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵየ! ሲሉት ደስ ይለዋል የሚበለው ትርክትንም አብይ ያመነ ይመስላል። ይህን ትርክት ካመነ መቀሌም፣ ጅጅጋም፣ አዲስ አበባም ሆኖ “ኢትዮጵያ!” ማለት በቂዬ ነው ብሏል ማለት ነው።

~እሳካሁን ባለው ጉብኝት የመጀመርየ ስጋቱ ስልጣን ላይ ሆነው እንቅፋት የሚፈጥሩበትን በማለዘብ ላይ ነው። ቀዳሚ ተደርገው የተወሰዱት አብዲና ትህነግ ናቸው። ከዚህ ውጭ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ልብ ውስጥ ያለው ኦህዴድ ነው ለማለት አምቦ ላይ “ሾው” አሳይቶ ተመልሷል። ብአዴን ጉዝጓዝ እንጅ ውጋት አይሆነኝም ብሏል። በአማራው የተደረጋጀ ተቃዋሚ የለም ተብሎ መታመኑም ሌላው ምክንያት ነው። ከብአዴን ይልቅ የትህነግ ወኪል የሆኑት ቤንሻንጉል፣ አፋር፣ ጋምቤላና መሰሎቹን ማስጨብጨብ ላይ ቀዳሚ ትኩረት የሚያደርግ ይመስለኛል! ከዛ በፊት ዳያስፖራውን የሚያስጨበጭብ ካልሆነ!

ይህ ሁሉ ጠላት ያላቸውን ለማስደሰት የማዝመር ጉዞ መዘዙ ምን ይሆን? የሚለውን ደግሞ ጊዜ ከሰጠን የምናየው ይሆናል።