ቋራ በቅኝ ገዥዎች ስር – (ጌታቸው ሺፈራው)

ቋራ በቅኝ ገዥዎች ስር

~”ሱዳን ሳይወጣ ከሞትኩ በነጭ አቡጄዲ አትቅበሩኝ” የቋራ ገበሬ

(ጌታቸው ሺፈራው)

የአጤ ቴዎድሮስ መነሻዋ ቋራ ለምለም ነች። የኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር አካባቢ የምትገኝ በመሆኗ ስትራቴጅያዊ ቦታ ነች። ቋራ ውስጥ በአጤ ቴዎድሮስ ልጅ አልጣሽ የተሰየመ ብሔራዊ ፓርክ ይገኛል። ይህ ፓርክ የኢትዮጵያ ነው ከማለት የሱዳን ነው ማለት ይቀላል። የአካባቢው ገበሬ በርካታ የቁም እንሰሳትን ያረባል። ሆኖም 50 የቀንድ ከብቱ በአጋጣሚ ወደ ፓርኩ ደንበር ቢደርሱ ይወረሳሉ። ይህ የሚደረገው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው። ፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚችለው የግለሰቡ ወንጀለኛ መሆን አለመሆን እንጅ ከብቶቹ የሚወረሱት ቀድመው ነው። ፍርድ ቤት ነፃ ቢለው እንኳ ከብቶቹ አይመለሱለትም። የሱዳን ዘላኖች ግን ፓርኩ ውስጥ ከብቶቻቸውን ይዘው ሲገኙ የሚደርስባቸው ቅጣት ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ለሱዳን ለም መሬት የተሰጠበት ይህ አካባቢ የኢትዮጵያ ሰራዊት በብዛት አይታይበትም። የሱዳን ወታደሮች በቅርቡ ለሱዳን ከተሰጠው ድንበር ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሕዝብ ያሰቃያሉ። ቋራ ውስጥ ሆነው ሕዝብን የሚቆጣጠሩበት ሰፈራ ተሰጥቷቸዋል። የበርካታ ፖለቲካ ኃይሎች መነሃሪያ ሆኖ የኖረው ይህ አካባቢ ሕዝብ እምብይተኛ፣ በፖለቲካም ንቁ መሆኑ ከራሱ አልፎ ለሉአላዊነቱ ቀናኢ ነው። የአካባቢው ገበሬዎች የሱዳን ጦር የሚያደርስባቸውን በደል ለመመከት አይፈሩትም። ገበሬዎቹ የሚፈሩት የሱዳን ጦርን ለመውጋት ሲነሱ ከኋላቸው የሚወጋቸውን የኢትዮጵያ ጦር ነው። የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከሱዳን ወራሪ ጦር ጋር ለመታኮስ የሚፈሩት የ”ኢትዮጵያ” የሚባለውን ጦር ነው። ይህ የኢትዮጵያ የተባለው ጦር ዘመናዊ መሳርያ የታጠቀውን የሱዳን ጦር ደግፎ ገበሬዎች ላይ ይተኩሳሉ።

“ሱዳን ሳይወጣ ከሞትኩ በነጭ አቡጄዲ አትቅበሩኝ”

ቋረ ውስጥ አንድ ከሱዳን ጋር ሲዋጉ የኖሩ ገበሬ አሉ። ሰውዬው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከበስተጀርባ እየተኮሰባቸውም የሱዳንን ጦር ጋር ሲፋለሙ ኖረዋል። ሕዝብ ሉዓላዊነቱን እንዲያስጠብቅ ያነቀሉ፣ ያስተባብራሉ። ገበሬው “መንግስት አስደፍሮናል፣ ሱዳን በመንግስት ጦር ድጋፍ ወሮናል” እያሉ ለሕዝብ ይናገራሉ። በቅኝ ግዛት ውስጥ እንደሚኖሩ ያምናሉ። ይህ የኢትዮጵያ መንግስት የሚባለው መሪነት የሚደርሰው ውርደት እንዲያበቃ የበኩላቸውን ያደርጋሉ። ይህ የሱዳን ቅኝ ግዛት፣ የመንግስት ጦር አስገዥነት እስኪያበቃ ጥቁር (ማቅ) ይለብሳሉ። ነጭ ልብስ ለብሰው አያውቁም። “ሱዳን ሳይወጣ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ከጀርባ ለሱዳን አብሮ እየወጋን ያለበት ወቅት ላይ ከሞትኩ በነጭ አቡጄዲ እንዳትከፍኑኝ። በጥቁር ልብስ ከፍናችሁ ቅበሩኝ” ብለው በቁም ተናዝዘዋል።

ገበሬው ባለፈው አመት የጊዜያዊ አዋጅ ሊታሰሩ ነበር። ነገር ግን በእሳቸው ብርታትና በሕዝብ ድጋፍ ከአሳሪዎች እጅ አልገቡም። ሆኖም ጉዳዩ የቀዘቀዘ ሲመስል ከእስር አላመለጡም። በአሁኑ ወቅት በእስር ቤት ጥቁር እንደለበሱ ይገኛሉ።

በሁለት ቅኝ ገዥዎች ስር!

የሱዳን ገበሬ ከብት ጠፋብኝ ሲል የሱዳን ጦር፣ ወደኋላ ካፈገፈገው የኢትዮጵያ ጦር ጋር ይፈልጋል። የቋራ ገበሬዎችን ያዋክባል፣ የሱዳን ጦር ከብቱን አገኘም አላገኘም የገበሬውን ጎጆ አቃጥሎ፣ ዘርፎ ይመለሳል። የአማራ ገበሬዎች ከብት በሱዳን ሲዘረፍ ግን የሚያስመልስ ጦር የለም። የቋራ ወረዳ ሕዝብ እንደ ቅኝ ተገዥ፣ ሱዳኖች ገዥ ሆነው ይኖራሉ ማለት ይቻላል። ቅኝ ገዥዎቹ ግን የሱዳን ሰዎች ብቻ አይደሉም። የትህነግ/ሕወሓት ባለሀብቶች አንደኛ ደረጃው ባለመብት ናቸው። በፍርድ ቤት ክርክር የተሸነፉትን እንኳ በትዕዛዝ ያስመልሳሉ። የቋራ ገበሬ የሚደርስበት ጫና አስከፊ ነው። ከየትኛውም የጎንደር ወረዳ በላይ መሳርያ እንዲያወርድ ጫና የደረሰበት የቋራ ወረዳ ነው። የቋራ ወረዳ ሕዝብ በሱዳን ቅኝ ግዛት፣ በትህነግ/ህወሓት ጭቆና ስር ይገኛል። የትህነግም ቢሆን ጭቆና ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። ለሱዳን አሳልፎ ሰጥቶታል፣ ከሱዳን ጋር ሆኖ ይወጋዋል። የትህነግ/ህወሓት ባለሀብቶች ይመዘብሩታል። በትህነግም ቅኝ ግዛት ውስጥ ነው! በሁለት ቅኝ ገዥዎች ስር ያለ ሕዝብ ነው!