ወደ ምንመኛት ኢትዮጵያ የሚያደርሰን መንገድ ላይ መወያየቱ የተሻለ፣ ትርፋማም ይመስለኛል

መስከረም አበራ

የአዲሱ ጠ/ሚ ወደ ስልጣን መምጣት የምንፈልጋትን ዲሞክራሲያዊት ሃገር ከማምጣቱ አንፃር የነበረን አተያይ ከሞላ ጎደል ለሁለት ተቃራኒ እሳቤዎች የተከፈለ ነበር፨ ለምን እንዲህ ታሰበ ማለት አይቻልም፨ ዋናው ጉዳይ ከሁለት አንዱን እሳቤ እንድናስብ ያደረገንን የክርክር ስንቅ የቋጠርነው ከየት ጨልፈን ነው የሚለው ነው?

የክርክራችን ማስረጃ አንድም የኢህአዴግ ካድሬዎች ፖለቲካዊ ማንነት ከሚታነፅበትን ፖለቲካዊ ባህል በመመርመር፣ የድርጅቱን አባላት ያሰባሰበውን አላማ ምንነት በማጤን ሊሆን ይችላል፨ ሁለተኛው የክርክራችን ምንጭ ሃገራችን በጎ እንዲሆንላት ከመመኘት፣ የድርጅቱን ገታራ ባህል ችላ ብለን በሰው መለወጥ ተስፋ በማድረግ፣ መልካም ንግግር ደግ ተግባርን ይወልዳል በሚል ቅንነት፣ ከአዲስ ፊት አዲስ ነገር ይመጣ እንደሁ በማለት ፣ የወንዝ ልጅ ዙፋን ላይ መቀመጡን በመናፈቅ ወዘተ ሊሆን ይችላል፨

ያም ሆነ ይህ አሁን ማናችን እንዴት ጎበዝ እና ልክ ማናችን ደግሞ ስህተተኛ እንደነበርን እያወራን የምንጠዛጠዝበት ሰዓት አይደለም፨ የእሳቤ ስህተት የለውም፨ ሰው እንደታየው አስቦ በተግባር ሲያመሳክር እሳቤው ከተግባር ያለመግጠሙ አሳፋሪ ሃጢያት አይደለም፨ የሚያሳፍረው ለሃገር አለማሰብ ብቻ ነው !

አዲሱን ጠሚ ባሞገስንበት አፋችን አይንህ ላፈር ማለቱም አግባብ አይደለም ፨ የሰውየውን መሰረታዊ የፖለቲካ አሰላለፍ መሳት የለብንም፤ ከሩቅ ሆነ ሲያየው ያማረው ውስብስብ ወንበር ያመጣበትን አጣብቂኝ ለመረዳት መሞከር ከስሜታዊነት የሚመልሰን ይመስለኛል፨ ሰውየው በግሉ በሚያስበው (በሚመኘው) እና መስራት በሚችለው ነገር መካከል ያለውን ርቀት መረዳት አለብን! በመናገር እና በመተግበር መሃልም ብዙ ልዩነት አለ – ለአፍ ዳገት የለውምና ! በኦህዴድ እቅፍ መሆን እና አለቃ ምንዝሩ በማይታወቀው ቤተ-መንግስት መገኘት ልዩነቱን እናስብ፨ ይሄ ወንበር በጠመንጃ የተከበበ አደናጋሪ ነው፨ እዚህ ወንበር ላይ አለመቀመጡ ነበር ተሻይ (እኔ ሲመስለኝ)፨

ወጣም ወረደ ተረጋግተን ወደ ምንመኛት ኢትዮጵያ የሚያደርሰን መንገድ ላይ መወያየቱ የተሻለ፣ ትርፋማም ይመስለኛል፨