የብሔረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ ከየት ወዴት? – ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶ/ር)

የብሔረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ
ከየት ወዴት?
***

ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶ/ር)
***

መግቢያ
***

በዓለማችን የቅርብ ታሪክ በተለይ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች በአጨቃጫቂነታቸው፣ በጭፍንነታቸው፣ በጨለምተኝነታቸው፣ ስሜታዊነታቸውና ከፋፋይነታቸው እንደ ብሔርተኝነት ስማቸው የገነነ እምብዛም ናቸው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የብሔር ፖለቲካ ጽንፍ ከረገጠባቸው ከቀድሞዎቹ ሶቭየት ኅብረትና ዩጎዝላቪያ ተርታ በብቸኝነት የምትመደብ ናት፡፡ ይኽ ተመሳስሎ ከብሔር ጥያቄ አረዳድ፣ አያያዝና ካስከተለውም በጠብና ደም የተለወሰ ኅልውና ድረስ ይሄዳል፡፡ አንድ አብዮታዊ ትውልድ ተነስቶ የወደቀበት፣ አገርንና ሕዝብን ከራሱ ዕጣፈንታ አቆራኝቶ የቀረበት ሰፊ ገድል ነው፡፡ ያ ትውልድ ለግማሽ ምዕት ገደማ የዘራውን የጥላቻ፣ የክፍፍልና የጥፋት ፖለቲካ መኸር ልጆቹና የልጅ ልጆቹ የመሰብሰብ ዕዳ ወድቆብናል፡፡

ሀ. ብሔርተኝነት ምንድነው ?
***

ይኽ ከሁሉ አስቸጋሪው ጥያቄ ቢሆንም በአገራችን ከሁሉ የቀለለ ተደርጎ የተወሰደ ነው፡፡ የአጨቃጫቂነቱ አንደኛው ምክንያት ከራሱ ተፈጥሮ ይመነጫል፡፡ ብሔርተኝነት ወደኋላ እያስታወሰና ወደፊት እያለመ፣ እግሮቹን በጥንታዊነትና በዘመናዊነት አድማሶች አንፈራጦ የቆመ እሳቤ ነው፡፡ በአንድ ወገን ብሔርተኝነት የጥንታዊውን ማኅበረሰብ አፈጣጠር፣ እምነት፣ ማንነትና የሕይወት ውጣ ውረድ የሚያቅፍ ታሪካዊ ፍልስፍና ነው፡፡

በሌላ በኩል በዘመናዊነት ሒደት ውስጥ የሚነሱ ትግሎችና ሙግቶች አካል በመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ ማኅበረሰቦችን፣ ተቋማትን፣ መደባትንና ማኅበራትን ፍላጎቶችና ርዕዮቶች ያንፀባርቃል፡፡ ባለንበት ዓለም ብሔርተኝነት በተለይ ከዴሞክራሲና ፍትሕ ጥያቄዎች ጋር የተቆራኘ አስተሳሰብ ነው፡፡

ለብሔርተኝነት ሁሉን አስማሚና የተሟላ ትርጉም መስጠት አይቻልም፡፡ እስካሁንም ለብሔሮችና ብሔርተኝነት መስፈርትነት የዋሉት እንደ ቋንቋ፣ ዘውግ፣ ባሕል፣ ወዘተ. ያሉት በራሳቸው ያልነጠሩና ሙልጭልጭ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን ብሔርተኝነት መልከ ብዙ ነው፡፡ የፖለቲካ አስተምህሮ ነው፤ አገራዊ ስሜት ነው፤ ማኅበራዊ ንቅናቄ ነው፤ ዘውጋዊ ተቆርቋሪነት ነው፡፡

ለ. ብሔር ምንድነው፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብስ?
***

የብሔረሰቦች ጥያቄ እስስታዊ ባሕሪ ምሥጢር በከፊል ብሔር በሚለው መሥራች ቃል ላይ ጥገኛ በመሆኑና ይህ ደግሞ በተራው ከትውልድ ሥፍራ ጀምሮ መንግሥት፣ ሕዝብ፣ አገር የሚሉትን ሰፋፊ ሐሳቦች ከማጠቃለሉ ጋር ይያያዛል፡፡ ብሔራዊ መዝሙር ማለት አገራዊ ነው፡፡ ብሔረ አማራ ሲል ዘውጋዊ ነው፡፡ ዘብሔረ ቡልጋ ማለቱ ደግሞ አውራጃዊ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ አብዮተኞች የብሔር ትርጉም አንድ ወጥና የስታሊንን ትንታኔ ቃል በቃል የሚደግም ነበር፡፡ አሁንም ጥቂት የይስሙላ ለውጥ ካልሆነ ብሔር ለሚለው ቃል (ጽንሰ ሐሳብ) በአገራችን ታሪክና ተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሠረተ ትንታኔ የለም፡፡ ስለዚህ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የሚሉት የተምታቱ አስተሳሳቦች ተኮርጀው በሕገ መንግሥታችን ውስጥ ስፍራ ይዘው ቀርተዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የማኅበረሰብን ዕድገት ደረጃን የሚያመለክቱ ቢመስሉም በዘፈቀደ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ብሔርነት የክብር ጉዳይም ስለሆነ እነዚህን ማዕረጎች ከራስ ፍላጎት ውጭ ማን እንደሚመድብ መወሰን አይቻልም።

ሐ. ኢትዮጵያዊነት ምንድነው?
***

ይኽም እስከዛሬ አጥጋቢ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል ታሪክ ውስጥ፣ ኢትዮጵያዊነት በጠላትነት ካልሆነ የረባ ቦታ አልነበረውም፡፡ በጥር 1961 የኦጋዴኑ ኢትዮጵያዊ አብዱል መጅድ ሑሴን “ኢትዮጵያዊነት ማለት ከግላዊ፣ ነገዳዊና አውራጃዊ ስሜቶች የላቀ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከሕዝብ አንጻር የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ያለው እምነት ነው” ብሎ ከገለጸው በኋላ የረባ ሙከራ አልተደረገበትም፡፡

አብዮቱ ሊፈነዳ ጥቂት ዓመታት እስኪቀሩት ድረስ፣ የአብዛኛው ተማሪ ጠንካራው የጋራ ማንነት ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊነት ዝቅ ሲል ደግሞ ተማሪነት ነበር፡፡ በተጓዳኝም ራስን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ መፈለግ፣ “ማነው ኢትዮጵያዊ?” የሚል ጥያቄ በከተሜው ምሁር ዘንድ እያቆጠቆጠ ነበር፡፡ ይኽ ጥያቄ በውል ሳይጠራ ማርክሳዊ ሌኒናዊ አብዮተኝነት “የብሔር ጥያቄን” ይዞ መጣ፡፡ አዲሱ የተማሪ ርዕዮተ-ዓለም በብሔር ግንዛቤ ዙሪያ ያለው ውዥንብር ጉዳዩን በተፃራሪ ትርጓሜዎች የታገተ አደረገው፡፡

አብዮተኝነትና ጎሰኝነት፤ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መንታ ገጽታዎች
***

አብዮተኝነትና ጎሰኝነት ከአንድ ዓለም አቀፍ ርዕዮተዓለምና ከአንድ ማኅበራዊ መደብ የመነጩ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኅልውና ተጻራሪ ገጽታዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ቀድሞ የተፈጠረው አገራዊ አድማስ ያለው፣ አዲሱ ትውልድ በአባቶቹ ላይ የሚያምፅበት ትውልዳዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ይኽ ለዘብተኛው አገራዊ ብሔርተኝነት ሚዛናዊ፣ አካታች፣ ተደራዳሪ ነው፡፡ በጋራ ገ”ልና ዕጣፈንታ የሚወሰን ነው፡፡ ተማሪው ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን ከተቀበለና፣ “ለቀለም ብቻ ሳይሆን ለተጋድሎ” እንሰለፍ ማለት ከጀመረበት ከ1960 መባቻ በኋላ ጽንፋዊው አብዮታዊ ብሔርተኝነት ዋጠው፡፡

ዘውጌ ብሔርተኝነት ወይም ጎሰኝነት፣ ከአገራዊ ብሔርተኝነት በተቃርኖ የሚቆምና፣ በተወሰነ ደመነፍሳዊ ማኅበረሰብ ጥቅም ላይ የሚያተኩር ርዕዮት ነው፡፡ በተማሪው መንፈስ ውስጥ ውስጡን የከረመና በ1950ዎቹ በተለይ በትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች መካከል እየጎላ የመጣ ተካራሪ የዘረኝነት፣ ጎሰኝነት ወይም አውራጃዊነት መንፈስ ነበር፡፡ በወቅቱ የአብዛኞች ስጋት የተማሪዎችን ኅብረት ይጎዳል የሚል ነበር እንጂ፣ እንዲህ ጎሰኝነት እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብሎ የጠረጠረ አልነበረም፡፡ ከቀዳሚው አብዮታዊ ብሔርተኝነት ተገንጥሎ ገሃድ የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት በፈነዳበት በ1966 ገደማ ነው፡፡

ሁለቱም አብዮታዊና ዘውጌ ብሔርተኝነቶች ነባሩን ብሔራዊ ታሪክ ለመከለስና የሕዳጣንና ጭቁን አመለካከቶችን ለማሳየት ቢሞክሩም፣ በክፉ ጎናቸው ደግሞ ታሪክን ለርዕዮተ-ዓለም ደንገጡር በማድረግና ግጭትና ውጥረት በማራገብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በተለይ ጎሰኝነት በተፈጥሮው ቀናተኛ፣ ስግብግብና ጠበኛ ነው፡፡ ለራስ ማኅበረሰብ ጥብቅና በመቆም አይመለስም፡፡ ማኅበረሰቡን አለቅጥ ማቆላመጥንና ሌሎችን በተፃራሪነት መመልከት ድረስ ይሄዳል፡፡

የኢትዮጵያ ተማሪዎች አንዱ መለያ ባሕሪ ልኂቃዊነት ነው፡፡ ለልኂቅ አንድ የተቆረጠ ትርጉም ባይኖረውም፣ በአገራችን የብሔረሰቦች ጥያቄ ታሪክ ውስጥ ከ1960ዎቹ በኋላ ተጽዕኖው እያደገ የመጣውን ዘመናዊ ምሁር ይመለከታል፡፡ በተለይ በጋራ ርዕዮተ-ዓለምም ሆነ በጋራ ዘውግ ተቧድኖ በኢትዮጵያ ዕጣፈንታ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ነኝ የሚል አጉል እምነቱና ከዚህ የመነጨው የፖለቲካ አስተሳሰብና ባሕል ልኂቃዊነት ይባላል፡፡ ይብዛም ይነስ በድኅረ አብዮት የተፈራረቁ አገዛዞች ብሔርተኝነትን ለሥልጣን ማደላደያነትና ማስጠበቂያነት አውለውታል፡፡ የፖለቲካ ባሕላችን በከማን አንሼና ማናለብኝነት ተመርዟል፡፡

የብሔረሰቦች ጥያቄ የመርሕ ጉዳይ ብቻ አልነበረም፡፡ ሥር መሠረት የሚያናውጥ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ተግባራዊ አንድምታ ያለው ነበር፡፡ በተለይ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ አደገኛ ውጤቶች ነበሩት፡፡ ይህም ምንጩ ለዘብተኝነት የሆነና፣ በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በምሥራቅ አውሮፓ ዘውጌ ብሔርተኝነት ሲዛመት ዕውቅና ያገኘ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቀላሉ መገለጫው ራስን በራስ ማስተዳደር ሲሆን፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ በዊልሰን 14 ነጥቦች ውስጥ ተካትቶ ዓለም ዐቀፍ ሰውነት አግኝቷል፡፡ ሆኖም ለነገሩ ትልቅ ትኩረት የሰጡት ሌኒኒስቶች ናቸው፡፡

እኛም አገር ሐሳቡ በኤርትራ የመገንጠል ንቅናቄ በግርድፉ ሲወሰድ ውሎ አድሮ ያን ያህል ችግር ያስከተለ አልመሰለም፡፡ ከእናት አገር ለመገንጠል ውጊያ ማለት እኮ በራሱ ተቃርኗዊ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አባቶቹ ወደ እናት አገራችን እንመለስ ብለው ያፈሰሱት ደማቸው ሳይደርቅ፡፡ ተገንጥሎስ ምን? ከዘውዳዊ አሃዳዊ መንግሥት የተለየ ምንም አማራጭ ማሰብ ይከብድ ነበር፡፡ በቅኝ ያልተገዛ ሕዝብስ እንዴት ልገንጠል ይላል፡፡ ለሰሚው ግራ በመሆኑ ከሹክሹክታ በላይ አይወራም ነበር፡፡ ጥላሁን ግዛው በ1960 ለተማሪ ፕሬዚዳንትነት ውድድሩን በመኮንን ቢሻው የተሸነፈው በ‹ተገንጣይነት› አሉባልታ ነው ይላሉ ደጋፊዎቹ፡፡

ጥላሁን ግዛውን የብሔረሰብ ጥያቄ የመጀመሪያው ሰማዕት ልንለው እንችላለን፡፡ በሱ ግድያ ጦስ የተፋፋመው የተማሪ አመጽ፣ በቀጣዩ ዓመት ዋለልኝ መኮንን ሀዱሽ ምንነቱ በቅጡ ያልታወቀ፣ አይነኬዎቹን አገርን፣ ባህልን፣ ማንነትን የመካድ አስፈሪ ርዕስ ይዞ የሚቀርብበት ድፍረት ሰጠው፡፡ በተማሪነቱ ጥቃት ያቆሰለውን ወጣት በውል ላልታወቀ ተልዕኮ የሚያሰልፍ መጽናኛ አቀረበለት፡፡ እስከዚህ ድረስ የተማሪው ገድል ከማኅበረሰቡ ያልተለየ ዝገምተኛና ብዙም ሊወራለት የሚችል ነገር አልነበረውም፡፡

“ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት” የሚለው በቀጥታ የተቀዳ ሌኒናዊ ሽሙጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ለመመርመር ፋታ አላገኙም፡፡ አዲሱን ራዕይ ከነባራዊው ሁኔታ አላገናዘቡም፡፡ በጭፍንና በጥራዝ ነጠቅነት አመለኩት፡፡ ዓለምን ያስደነቀ የአክራሪነት ባሕሪ አሳዩ፡፡ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር የተያያዘ ማናቸውንም ነገር ካዱ፡፡ ወይም ማንነታቸውን ጠሉ፡፡ ክፉ ነገር ሁሉ የተፈጠረው በኢትዮጵያ፣ ደግ ነገር ሁሉ ሌላ አገር ሆነ፡፡ ጭቆና የትውልድ አገሩ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ‹የብሔረሰቦች እስር ቤት›፣ እንዲያውም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ብቸኛዋ ቅኝ ገዥ አገር ናት ብለው ራሳቸውን አዋረዱ፡፡

ከዚህ በኋላ እረፍትና መደማመጥ የሌለበት፣ በጥድፊያ፣ በግርግር፣ በሴራና በጀብደኝነት የተሞላ፣ የአፍለኛን ልብ የሚያቀልጥ ዘመን ነበር፡፡ ያ ትውልድ ማተቡን በጥሶ በጅምላ ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን አምላኪ የሆነበት ምትሐታዊ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የተማሪው አገራዊ አብዮተኝነት ተዳቀለና የብሔረሰቦች ጥያቄ የአብዮተኝነት መለኪያ ቱንቢ ሆነ፡፡ ተማሪው “በመርሕ ደረጃ” ከፀሐይ በታች ማናቸውንም ነገር ለመቀበል ተሰለፈ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ምን ዓይነት ጭቆና ነው ሲል ጠየቀ፡፡ የመደብና የብሔር ጥምር ጭቆና የሚለው፣ ማርክሲዝምንና ስታሊኒዝምን ለማስታረቅ የሚሞክር ድምዳሜ ነው፡፡ ትንታኔውን ከመደብ በተጨማሪ በባሕልና ብሔር ጭቆና ላይ ያደረጋል፡፡ ይህ ክፍል ጥምር ጭቆና ያለበት ስለሆነ ተቃውሞው ይበረታል ተብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን የብሔር ፍልሚያ የተነሳውና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እስከመካድ የተደረሰው በተገላቢጦሹ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል ነው፡፡

“ማነው ኢትዮጵያዊ?” የሚለው አጭር ጥያቄ ሲሆን፣ ይበልጥ ታሪካዊ ይዘት ካለው “ኢትዮጵያ መቼ ተፈጠረች?” ከሚለው ጥያቄ ጋር ይቆራኛል፡፡ የታላቂቱ ኢትዮጵያ አስተምህሮ፣ ሁሉን አካታችና ወግአጥባቂ፣ ዜግነታዊ – ግዛታዊና በአገሪቱ ረዥምና ቀጣይ መንግሥትነት የሚያምን ነው፡፡ ጎሰኞች በቀጥታ ለማጥቃት በደፍጣጭነት ወይም ጠቅላይነት በመወንጀል፣ በተለይ ከአንድ ከአማራ ብሔረሰብ ጋር ሊያቆራኙት ይሞክራሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒና በአፀፋ ዲስኩር መልክ የቆመው ታናሺቱ ኢትዮጵያ አስተምህሮ፣ ደመነፍሳዊ አስተሳሰብ ሲሆን ሐበሻና ኢትዮጵያን በመነጣጠል ይጀምራል፡፡ “አስኳል ሐበሻ” ወይም “ቅኝ ገዥ ኢትዮጵያ” የሚለው ከፍፍል በኢትዮጵያ/አቢሲኒያና በደቡባዊ ሕዝቦች መካከል ልዩነት አለ በሚል የተመሠረተ ነው፡፡ በተለይ የደቡቡን የአገሪቱን ክፍል ከሰሜናዊው ወይም ሐበሻዊው ወይም ታሪካዊ አስኳል ከሚባለው ለይቶ በማየት የመጣ ስህተት ነው፡፡ ከናካቴው ይህ ክፍል በታሪክም፣ በባሕልም፣ በዘርም ከኢትዮጵያ አይመደብም፣ ስለዚህም ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ክህደትን ይጨምራል፡፡ በዚህ ላይ ኢትዮጵያ የደቡባዊው ክፍል ቅኝ ገዥ ናት ይላል፡፡ ሰሜናዊ ወይም ሐበሻ የሚለውንም እንደ አንድ ወጥ ሕዝብ ያያል፡፡ ደቡባዊውንም በውስጡ ልዩነት የሌለው አሃድ አድርጎ ይቆጥራል፡፡

ከተማሪው ንቅናቄ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የወጡ ቡድኖች፣ የጀብደኝነት ድርጊቶቻቸው ወደፊት ምን ያስከትሉ ይሆን ብለው ለመጭው ትውልድ ለማሰብ አይፈልጉም፡፡ ማፍረሳቸውን እንጂ ምን እንደሚያፈርሱና በምትኩ ምን እንደሚገነቡም አያወቁም፡፡ እስከዛሬም አምሳ ዓመት ሙሉ እነዚህን አደገኛ ሐሳቦች በጭፍንነት ማራመዳቸው ከምን የመነጨ እንደሆን ለመረዳት ያስቸግራል፡፡

በተለይ ጎሰኝነትና የአገር ክዳት በዘመነ ኢሕአዴግ መከበሪያ ሆኖ አሁን ለምንገኝበት መስቀለኛ መንገድ አደረሰን፡፡ በዚህ ዘመን የናጠጠውን የከፋፋይነት ፖለቲካ በሁለት ዓይነት መልኩ ማየት እንችላለን፡፡ አንዱ መልክ ብድር መላሽ የሆነና የጎሳ ባላንጣዎችን ዒላማ የሚያደርግ ነው፡፡ “የነፍጠኞች ሴራ ትናንትና ዛሬ” በሚለው መርዘኛ አባባል ይገለጻል፡፡ ሁለተኛው የዳግም ውልደት መልክ ሲሆን፣ በራስ ደመነፍሳዊ ማኅበረሰብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የጎሳ ማንነትን፣ ባህልን፣ ታሪክን በመፍጠር የተሠማራ ቢሆንም፣ በተፈጥሮው በዚህ አይቆምም፡፡ በአንድ በኩል ስለጎሳዬ ከኔ ውጭ ማንም ሊያገባው አይችልም የሚል ጤናማ ያልሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአጎራባች ማኅበረሰቦችን መስተጋብር ቆርጦ የሚጥል፣ ነጥሎ የሚያይና ብሔራዊ ራዕይ የሌለው ከሆነ አደጋ ይደቅናል፡፡

አሮጌውን ትውልድና አሮጌ ሐሳቡን ማለፍ ይቻላል
***

የብሔራዊ ጥያቄ መነሻ፣ ሒደትና ውጤት በተመለከተ የዘውጌ-ብሔርተኛው ትግል አንጋፋ መሪዎች እንኳን የነበራቸውን የተምታታ አመለካከት በፀፀት እየከለሱ ናቸው፡፡ እንደ ተስፋፅዮን መድኅኔ፣ አረጋዊ በርሄና ዲማ ነገዎ የመሳሰሉ ምሁራን ትውልዳቸው የብሔር ጥያቄን መሰሪ ማወናበጃ መሣሪያ በማድረግ፣ ታሪክን በማዛባትና የማጭበርበሪያ ዲስኩር ስለማድረጉ ይስማማሉ፡፡ በተለይ ኢሕአዴጋዊው የዘውግ ፖለቲካ በአገሪቱ አብዛኛ ክፍል ውስጠ-ማኅበረሰባዊ ግጭቶችን ከመጫር በተረፈ፣ ለብሔረሰቦች ፍትሕና ዴሞክራሲን አላመጣም፡፡ ለጥቂቶች የእንጀራ ዘይቤ ሆኖ ቀረ ብለው ያማርራሉ፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ታሪክና እሴቶቸ ያለው ግንዛቤ እጅግ የተዛባና፣ በአመዛኙ በፖለቲካ መድልዎ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ያሳስባል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክና አንድነት ላይ በቅድመና ድኅረ-አብዮት በግልጽና በስውር የተከፈቱ ጥቃቶችና በሕዝብ ላይ የተጫኑ መርዘኛ አመለካከቶች፣ በተለይም ዛሬ በሕዝባችን መካከል እንደዋዛ እየሰረጉ የመጡ ውዥንብሮች አደጋቸው ግልጽ እየሆነ ነው፡፡

መቋጫ የሌላቸው የሚመስሉትን የዚያን ትውልድ ከፋፋይ አመለካከቶች አንጥሮ የድኅረ-አብዮቱ ተተኪ የሚኖረውን አማራጭ አመለካከት ለማቅረብ፣ በአገርና በብሔረሰብ፣ አልፎም በተለያዩ አሰባሳቢ ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት መመርመርና መጥራት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ፣ ብሔረሰቦቿና ታሪኳ በተቃርኖ የቆሙ ሳይሆኑ፣ አንድነትም ልዩነትም ያላቸው፤ አንዱ ያለአንዱ የማይታለሙና የተሟላ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው፡፡

አገራዊና ዘውጋዊ ማንነቶች የግድ አይቃረኑም፡፡ ብዝኃ ማንነት ብዝኃ ታሪኮችን የግድ ይላል፡፡ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ልዩነት እንደ ኢትዮጵያ ባለች ብዝኃነት ተፈጥሮዋ በሆነ አገር የተለመደና በዘመናት ያደረጀውም የተቻችሎ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ በዚህ ላይ ማንነት በርካታ ተጠላላፊ ዘርፎች ያሉት በመሆኑ፣ በአንዱ ያጣውን በአንዱ እየካሰ እንደ ሁኔታው የሚታይ ኅብረት ፈጥሯል፡፡ በአውራጃ ቢለያይ በቋንቋ፣ በቋንቋ ቢለያይ በእምነት፣ በእምነት ቢለያይ በመደብ ይዛመድ ነበር፡፡ ስለዚህም አገራዊነት ወይም ዜግነታዊ ማንነት በጋራ ተሞክሮዎችና እሴቶች ዙሪያ ሊገነባ ይችላል፡፡

ኢትዮጵያዊነት የሞተና የተዘጋ አጀንዳ አድርጎ ማሰብ ራስን ማሞኘት ነው፡፡ ብሔራዊ ግብ የሌለው የመንደር ፖለቲካ ጥቂቶችን በሥልጣን ለማክረም ሊጠቅም ይችላል፡፡ ነገር ግን አብሮ በሠላም የመኖርን እውነታ ስለሚዘነጋ አገር አጥፊ ነው፤ ትውልድ ገዳይ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱ በታሪኩና በማንነቱ የሚኮራና በጋራ ለለውጥ የሚነሳ ኃይል እንዲሆን መታገዝ አለበት፡፡ ወጣቱ አገሩን የሚያስባትና የሚወዳት እንጂ ግድየለሽ የሚሆንባት፣ የሚሸሻት፣ የሚያፍርባት አልፎም የሚጠላት እንዲሆን መገፋቱን መቃወም ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችን የወደፊቷን ኢትዮጵያ በብሩህ መንፈስ የሚጠብቋት፣ ተስፋ የሚሰንቁባት አገር ለማድረግ መጣር፣ ያ ትውልድ ያቆየልንን የቂምና ጥላቻ ባህል መሻር የአያቶቻችን ሳይሆን ዛሬ የኛ ኃላፊነት ነው፡፡