እርሙ እና የአንድ ሰሞኑ የቲም ለማ ትያትር ማብቂያው ሰአት (መንግስቱ ሙሴ)

እንደሚመስለኝ አሁንም ቲም ለማ የተባለውን የኦሕዴድ አመራር ቡድን እንደየለውጡ አካል አርገው የሚያዩ ተራ ዜጎች ብቻ አይደለም የሚዲያም ሰወችም እንዳሉ ለመረዳት ችያለሁ። ከዚህ በፊት ጄኔራል ጻድቃን ወ/ተንሳይ በጻፉት ላይ አስተያየት እና ነቀፋም አቅርቤ ስለነበር “የቲም ለማ” ተብየው የመድረክ ቅንብርን ገና ከመጀመሪያው የጻድቃን ወ/ተንሳይን ውትወታ የተከተለ ለመሆኑ ብዙ አመላካች ነበርቱ እና የቲሙ የቶሎ ቶ ሎ ኢትዮጵያዊነት ያልጣመኝን ያክል። ከመሀላቸው አንደኛው ሰው ለጠቅላይሚኒስቴርነት ሲመረጥም የነበረኝን አቋም ባለመቀየሬ እና አስተያየቴን በዚሁ በማህበራዊ ሚዲያ ገጼ በማንጸባረቄ የአካባቢው የዳላስ ሬዲዮ ከአንድ ወዳጀ ጋር በጉዳዩ እንድከራከርበት ጋብዞኝ እንደነበር ወዳጀም ሀሳቤን አክብሮ መለያየታችንን አስታወሰኝ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት እየሞቱ እየታሰሩ መጠነሰፊ ችግርም በስርአቱ እየደረሰባቸው ታግለዋል። የዜጎች ደም በየጎዳና ፈሷል። በባህርዳር የ70 ወጣቶች ደም የፈሰሰ ቀንን ያህል ከባድ ወንጀል አላየሁም። በጎንደር በሰላም በወጡ ዜጎች ላይ የበአዴኑ የባንዳ ቡድን ከህወሓት አጋዚ ጋር ተደምሮ ያደረሰው እስራት፣ ግድያ እና ሽብር የሚረሳ አይደለም። በአንቦ ወጣቶች ላይ ድፍን ሁለት አመታት መብትን በሰላም ወጠው በመጠየቃቸው የተፈጸመባቸው መንግስታዊ ወንጀል ለአፍታ የምንረሳው ጉዳይ አይደለም። በአለማያ፣ በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲወች የተፈጸመው በደል እና ወንጀል አሁንም ፍርድ ይፈልጋል። በአጭሩ በኦሮሞ እና አማራ ሕዝባችን ላይ የወረደውን መከራ የሚስተካከል የታሪክ ገጠመኝ ከዘመነ ህወሓት ውጭ የለም አይኖርምም።

እናም የ OPDO ቲም በድንገት ብቅ ማለት ብዙ አነጋጋሪ ቢሆንም ዜጎች እየታደኑ ባለበት ወቅት የታየ phenomena በመሆኑ እየተጠራጠሩም ቢሆን ግዜ እንስትጥ ወደማለት የዞሩ መባዛታቸው ለትያትሩ የሚያስገርም አይደለም። በኦሮሚያ የተጀመረው ትግል አሁን ጋብ ያለበት ሁኔታ ሲሆን። በእርግጥ በአማራ አካባቢ ከሰሜን ወሎ ፍጅት በኋላ ትግሉ ግዜን የሚጠብቅ እንጅ እሳቱ እንደፋመ መሆኑን የመቀሌው የካድሬ ስብሰባ እና የተሰጠው ምላሽ አንጸባራቂ ገጽ ነው።

ስልጣኑን ከተረከበ ብዙ ያልቆየው ጠቅላይ ሚኒስቴር ከሶማሌ እና አንቦ ጉብኝት በኋላ ወደትግራይ በመሄድ ስለየወልቃይት ሕዝብ የተናገረው ቀዩን መስመር ማለፍ ብቻ አይደለም የጠላት ጥቅል መሆኑን ያስረገጠ ንግግርም አስደምጦናል። በህወሓት ጥይት የተለበለበው ወልቃይት እና መላ የአማራ ክልል ሕዝብ የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስቴር አነጋገር በቸልታ አላለፈውም። በአጭሩ ባለ ጉዳዩ ሕዝብ ትግሉ ገና ብዙ አቀበት እንደሚጠብቅ የተዘጋጀበት እንጅ አብይ ይፈታልናል ብሎ እንዳልተዘናጋ ገልጽ ነው። የለውጥ ኀይል ነው በሚል ጭንብል ግዜ ሰጠው ለማየት የተዘጋጁ እና በአንድ ሌሊት ከቲም ለማ እና ከበአዴን ጋር ወደፊት ያሉ ብዙ በውጭም በውስጥም መኖራቸው እየታዘብን ያለነው ኩነት ቢሆንም። ማንም ግዜ ሰጠው ወይንም ተስፋ ጣለበት እየታዘብን ያለው የጫጉላ ግርግር እና የቲያትሩ ጉዳይ በዛሬው የሚኒስቴሮች ምርጫ ከመጋረጃው ጀርባ ምን እየተሰራ እንደነበር ለመማር አስችሎናል።

ለውጥ አለ ብለው ላመኑት ከመርዶው ሁሉ ክፉ የሽፈራው ሽጉጤ አሁንም ወደስልጣን ማማ መሰቀሉ አይን ጨፍነው ቆዩን ግዜ ስጡልን፣ ያሉንን ቢያንስ የክርክር ዳፋውን ያስቸገረባቸው ፈጣን ለውጥ እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን። ሽፈራው ሽጉጤ የጉራ ፈርዳው ፋሽስታዊ ወንጀል ከመለስ ዜናዊ ጋር በግንባር ቀደም የአካሄደ ወንጀለኛ ሰው ነው። ምናልባት ልክ መለስ እንዳለው “ትቂት የምስራቅ ጎጃም ሰወች በሰሩት ስራ ተፈናቀሉ ብላችሁ ነው” ካልተባለ ማለት ነው። የአባ ዱላ ገመዳ፣ ፈተወርቅ ገ/እግዚያብሔር፣ የወርቅነህ ገበየሁ ወዘተ በዚህ አስተዳደር ውስጥ መኖር እና መቀጠል ብቻ አይደለም በአዲስ የተሾሙት ሳይቀር ልክ እንደቲሙ ሁሉ በህወሓት ተጠፍጥፈው ነፍስ የተዘራላቸው በድናት መሆኑ በአንድ ገጽ ገሀድ ሲሆን። በሌላ በኩል ከአሁን በኋላ ለለውጥ የታገሉም ሆነ ለውጥን የሚመኙ ሁሉ እንደገና ቀበቶን አጥብቆ አይቀሬውን የማስወገድ ትግል ማስቀጠሉ መሆን ያለበት ስለሆነ በሕዝብ ልቦና የተጫረውን ተስፋ በትግል እንጅ ከወያኔ ሰራሽ ስብስብ እንደማይገኝ ማስረገጥ እና ትግሉን ማፈፋሙ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።

አሁንም በተቃዋሚ ሚዲያወች መነገር ያለበት የተመረጠው ጠቅላይ ሚኒስቴርም ሆነ ቲሙ የለውጥ አካል ነበሩ የሚለው ሳይሆን ትግል ገዳይ ህወሓት ሰራሽ መሆኑን እውነተኛውን የህወሓት ከመጋረጃ ጀርባ የሰራችውን ሕዝብን እያሳዩ መቀጠሉ የተሻለ አማራጭ ነው።

በህወሓት ታሪክ፤ እርሷ የታጠቀ ሰራዊት እየመራች፣ የተደራጀ እና ማንም የማይገባበት የደህንነት መዋቅር ተቆጣጥራ ቀርቶ ገና በለጋ የድርጅት ዘመኗ አገር ለማፍረስ ከምንም እና ማንም ጋር ለድርድር ግዜና ቦታ እንደማትሰጥ ሁሉም ሕዝብን ማስተማር/ማሳየት ይገባል። የህወሓት ተፈጥሮ ለአገራዊ እርቅም ሆነ ለለውጥ ፈጽሞ ክፍት ልቦና የሌላትን ያህል። አሁን ጠፍጥፋ የሰራቻቸው እና ተንከባክባ ያሳደገቻቸው ልጆቿን በመጨረሻዋ ጠባብ ሰአት ማውጣቷ የሚጠበቅ ሲሆን። ይህን ሁሉም እንዲገነዘበው በተቃዋሚ ሚዲያ ዙሪያ ያሉ ከአዚም ወጥተው የቆየ ስራቸውን እንዲሰሩ ይገባል።

ኢትዮጵይ ለዘላለም ትኑር!!!