የትንሿ አፍሪካዊት ሀገር ስዋዚላንድ ንጉሥ የሃገራቸው ስም እንዲቀየር ወሰኑ።

ንጉሥ ምስዋቲ

የትንሿ አፍሪካዊት ሀገር ስዋዚላንድ ንጉሥ የሃገራቸው ስም እንዲቀየር ወሰኑ።

ንጉሥ ምስዋቲ ሦስተኛ ይፋ እንዳደረጉት ስዋዚላንድ መጠሪያዋ ‘ኢሰዋቲኒ’ ወደሚለው እንዲቀየር ወስነዋል።

ንጉሡ የሃገራቸውን የስም ለውጥ ያስታወቁት የስዋዚላንድ 50ኛ ዓመት የነፃነት በዓል በተከበረበት ስታዲየም ውስጥ ነው። የነፃነት በዓሉም ከንጉሡ የልደት ቀን ጋር የተገጣጠመ ነበር።

አዲሱ የስዋዚላንድ ስም ኢሰዋቲኒ ትርጓሜም፤ የስዋዚዎች ሃገር ማለት እንደሆነም ተነግሯል።

የስም ለውጡ ያልተጠበቀ ቢሆንም፤ ነገር ግን ንጉሡ ሃገራቸውን ስዋዚላንድ “ኢሰዋቲኒ” እያሉ መጥራት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ንጉሡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ይህንኑ ስያሜ የተጠቀሙ ሲሆን ከአራት ዓመታት በፊትም የሃገራቸውን ፓርላማ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ኢሰዋቲኒን ተጠቅመው ነበር።

“ወደውጪ ሃገራት በምንጓዘወበት ጊዜ በርካታ ሰዎች የሃገራችንን ስም ስዊትዘርላንድ በማለት ይጠራሉ” ሲሉ ስዋዚላንድ የሚለው ስያሜ የፈጠረውን መደናገር ገልፀዋል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ከስዋዚላንድ እንዳለችው የስም ለውጡ አንዳንድ የሃገሪቱን ዜጎች ያስቆጣ ሲሆን፤ ንጉሡ ከዚህ ይልቅ የተቀዛቀዘው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የበለጠ ቢያተኩሩ ይሻላል ብለዋል።

ለ82 ዓመታት በንግሥና የቆዩት የዳግማዊ ሶብሁዛ ልጅ የሆኑት ንጉሥ ምስዋቲ በአሁኑ ወቅት 15 ሚስቶች አሏቸው። እንደ ንጉሡ የህይወት ታሪክ ፀሃፊዎች መረጃ ከሆነ የአሁኑ ንጉሥ አባትም በዙፋናቸው በቆዩበት ዘመን 125 ሚስቶች ነበሯቸው።

‘ንግዌንያማ’ ወይም ‘አንበሳው’ ተብለው የሚታወቁት ንጉሡ ባሏቸው በርካታ ሚስቶችና በሚያዘወትሩት ባህላዊ ልብስ ይታወቃሉ።

የስዋዚላንድ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ በማድረግና በሴቶች ላይ በሚፈፀም አድልዖ ምክንያት በሰብአዊ መብት ተሟጋቾ ይወቀሳል።

BBC Amharic