እምቢ እንበል! (ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር))

ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ – አዲስ አበባ

በአገራችን፣ የቀበሌ ሹመኞች ያለማንም ጠያቂ ኅብረተሰቡን የሚያሸብሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ሰዎች (በእስር ላይ ያሉት ጭምር) ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ በአደባባይ የሚረሸኑበት ጊዜ ነበር፡፡ አርሶ አደሮች የለፉበትን ሰብል ያለፍላጎታቸው በወደቀ ዋጋ እንዲሸጡ የሚደረግበትና ኮታ እንዲከፍሉ የሚገደዱበት ጊዜም ነበር፡፡ በደርግ ዘመን እነኝህና ሌሎች አስከፊ ጭቆናዎች ነበሩ፡፡

ከደርግ አገዛዝ ውድቀት በኋላ፣ ሕዝቡ የጭቆናን አስከፊነት ከበቂ በላይ ስላየ፣ መብቱን አሳልፎ አይሰጥም፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይታገላል፣ በነጻነት ስለመደራጀትና ስለመጻፍ… መብቶቹ ዘብ ይቆማል፤ መሪዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት እንዲዘረጋና የጭቆና ሥርዓት እንዳያንሰራራ ይዋደቃል ወዘተ. ይባል ነበር፡፡ የሆነው ግን ያ አይደለም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ አሁንም እንደ ትናንቱ ጭቆናውን በፀጋ ተቀብሎታል፡፡ ሕዝቡ ጭቆናንና የጭቆናን አስከፊነት አይተነዋል፤ ጭቆና ሰውን ከሰው በታች የሚያደርግ አስከፊ ነገር ነውና ዳግመኛ ልንሸከመው አንችልም፤ አንፈቅድም ማለት አልቻለም፡፡ በተለያየ ምክንያት ተከፋፍሏል፡፡ መከፋፈሉም ለጥቃት አጋልጦታል፡፡

የሚገርመው፤ ካሉት ዓለም ዐቀፋዊ ሁኔታዎችና ከአገሪቱ ታሪክ አኳያ በአገራችን ሊኖር የሚገባውን የዴሞክራሲ ዕድገት ደረጃ ከማየት ይልቅ ኢሕአዴግ ከደርግ ይሻላል፤” ብለው ሥርዓቱን የሚደግፉ ወይም የማይቃወሙ ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ጭቆና መኖሩን ባይክዱም፣ ጭቆናው ከደርግ ያነሰ ነውና እንታገስ፤ በሂደት መሻሻሎች ይኖራሉ የሚሉ ናቸው፡፡ በሙሉ ልብ ዴሞክራሲ በአንድ ጀንበር አይገነባም፤ ሂደት ነው፤ አሜሪካኖች ዴሞክራሲን ለመገንባት 200 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል ወዘተ. የሚሉም አሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጭቆና መኖሩን ቢቀበሉም መብታቸውን ለማስከበር ራሳቸው የማይሳተፉ ነገር ግን ሁሉንም ሥራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሠሩላቸው የሚፈልጉ ወገኖችም አሉ፡፡ እነኝህ ኃይሎች፣ ራሳቸው የፖለቲካ ተሳትፎ አያደርጉም፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በገንዘብም ይሁን በሌላ መንገድ አይደግፉም፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለውጥ ባለማምጣታቸው ግን ይበሳጫሉ፤ ሁልጊዜም ተቃዋሚዎች እንደማይረቡና ተስፋ እንደማይጣልባቸው ከመግለጽ አይቦዝኑም፡፡ መነሻቸው የተለየ ቢሆንም ልክ አንደ ኢሕአዴግ ምን ፓርቲ አለ? የሚሉ ናቸው፤ ነን፡፡

እንደምናውቀው በኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ መቆየት በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙ ኃይሎች ደግሞ አሉ፡፡ እነኝህ፣ ኢሕአዴግ ምን ያህል ይበልጥ ጨቋኝ እየሆነ ቢሄድም ድጋፋቸውን የማያቋርጡ ወገኖች ናቸው፡፡ ከድርጅቱ ተጠግተው መሬት ሸጠው የከበሩ፣ በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ በሚገርም ፍጥነት ሚሊየነር የሆኑ፣ በየክልሉ በብሔረሰብ መብት ስም እየነገዱ ሥልጣን የያዙ ወዘተ. ዜጎች የደህንነታችን መሠረት ኢሕአዴግ ነው፤ እስከመጨረሻው እንደግፈዋለን ቢሉ [አሳዛኝ ቢሆንም] ሊገርም እይችልም፡፡ ጭቆናን ከመቀበል አልፈው ሌሎች እንዳይታገሉ መሰናክል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

በደርግ የመጨረሻዎቹ ዓመታትና ከዚያ ወዲህ የተወለደውና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣትም አለ፡፡ ይኽ ኃይል ከቁጥሩ መብዛት በተጨማሪ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለው ጉጉት ከፍተኛ ቢሆንም አገዛዙና የተወሰኑ ጽንፈኛ ወገኖች የሚያራግቡት የብሔረሰብ ፖለቲካ ሰለባ እየሆነ በጋራ መታገል አልቻለም፡፡ ሌሎች በፈጠሩት የዘር ፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ የገባ አሳዛኝ ትውልድ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ዛሬ በአገራችን በብሔረሰብ ተዋጽዖ ስም ሥልጣን የሚይዙት ከየብሔረሰቡ የተወጣጡ ታማኝ አገልጋዮች መሆናቸውን ማንም ያውቃል፡፡ ሥልጣንና መወለድ በእጅጉ የተቆራኙበት ዘመን አሁን መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ እነኝህ ምንም ይኼ ነው የሚባል አቅም ሳይኖራቸው የአንድ ብሔረሰብ አባልና ታማኝ ካድሬዎች በመሆናቸው ብቻ ከወረዳ ባለሙያነት ተነስተው እስከ ሚኒስትር ደረጃ የደረሱ ሰዎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚቆሙበት ዕድል አለ ወይ?

እንደ እውነቱ ከሆነ የኢሕአዴግ መሪዎች ለመድበለ-ፓርቲ ሥርዓት ያላቸው ቁርጠኝነት ለዜሮ የቀረበ ነው፡፡ ይኽም በብዙ መልኩ የሚገለጽ ነው፡፡ ኢሕአዴጋውያን ወደ ከበርቴነት ከመቀየራቸው በፊት እንዲፀድቅ የታገሉለትን ሕገ መንግሥት በተለያዩ ዝርዝር ሕጎች መሸርሸር ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ከምርጫ 1997 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ በጣም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በአንድ በኩል ሕገ መንግሥቱን በሌሎች ዝርዝር ሕጎች ያቅቡታል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ፖሊሲዎችን በመጠቀም ብዙ እቀባዎች ይደረጋሉ፡፡ ለምሳሌ አገዛዙ የልማታዊ መንግሥትን ፈለግ እንደሚከተል ካወጀ በኋላ ቅድሚያ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ልማት በመስጠት ሌላውን ወደ ጎን ገሸሽ የማድረግ ወይም ከዚያም አልፎ አገዛዙን የሚተቸውን ሁሉ በፀረ ልማት በመክሰስ ማሳደድ ግብር ሆኗል፡፡

ኢሕአዴግ በስትራቴጂ ሰነዱ ላይ እንዳብራራው በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት የቀረቡት አማራጮች ኹለት ብቻ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ወይ ኢሕአዴግ የሚከተለውን “ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አማራጭ መደገፍ ወይ ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢና የፀረ-ዴሞክራሲ አማራጮችን መምረጥ ይኖርበታል” ይላል ኢሕአዴግ፡፡ ሕገ መንግሥቱ የዜጎችን (በነጻነት) የመደራጀት መብት ቢደነግግም፣ አገዛዙ በፖሊሲ ሰነዱ ከእርሱ ውጪ ያሉትን ሁሉ በኪራይ ሰብሳቢነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ፈርጆ ሊያጠፋቸው ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አገዛዙ አንድ ጊዜ አብዮታዊ ዴሞክረሲ ሌላ ጊዜ ልማታዊ መንግሥት ሌላ ጊዜ ደግሞ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ወዘተ. እያለ ተቃዋሚ ድርጅቶችን በልዩ ልዩ መንገድ ከጥቅም ውጪ አድርጓቸዋል፡፡

ሥርዓቱ በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ዘመናት የተሻለ ሆደ ሰፊና “ዴሞክራት” እንደነበር ከ1997 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ በፊት ይታተሙ የነበሩትን የሕትመት ውጤቶች ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ከነጉድለታቸው አገዛዙን የሚተቹ በጣም ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ነበሩ፡፡ በሰብአዊ መብትና በዴሞክራሲ ዙሪያ የሚሠሩ ብዙ ሲቪክ ማኅበራትም ነበሩ፡፡ ያ ሁሉ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው በምርጫው ማግስት በሚያሳዝን ሁኔታ የተቀጨው፡፡ ከዚያ ወዲህ ያለውን ሁኔታ ደግሞ ማንም ያውቀዋል፡፡ በተለይ ከምርጫ 2002 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ ድርጅቱ አውራ ፓርቲ መሆኑን ካወጀ በኋላ ለሂስና ለተቃራኒ አመለካከቶች ያለው አስተያየት ሲበዛ አሉታዊ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ፣ ሕዝቡን አሸብሮ ለመግዛት የሚያስችል የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ወጣ፡፡ ሲቪክ ማኅበራቱን የሚያኮላሽ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሕግ ወጣ፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቱ ከ1997ቱ ብሔራዊ ምርጫ ሰፊ “ትምህርት” በመቅሰሙ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መብቶችን የሚሽሩ ሕጎች ማውጣት ልማድ ሆኗል፡፡ አሁንም ቢሆን አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ወርዶ በሌላ ተተካና ባለሥልጣናት ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ተዘዋወሩ እንጂ በመሠረታዊነት የተቀየረ ነገር የለም፤ መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ አልተደረገም፡፡

ያለንበት አስቀያሚ ሁኔታ በጥቂቱ ይኽን የመሰለ ስዕል ያለው ነው፡፡ ደግነቱ ፖለቲካ ተለዋዋጭ (ዳይናሚክ) በመሆኑ የማይደፈርና የማይነቀነቅ የሚመስለው አገዛዝ በሕዝብ ትግልና መስዋዕትነት ይሽመደመዳል፡፡ መፍትሔው ሁላችንም የራሳችንና አገራችንን ጉዳይ ለጥቂት የተደራጁ ቡድኖች አሳልፈን ሳንሰጥ መታገል እና እምቢ ለመብቴ፣ እምቢ ለክብሬ ማለት ነው፡፡ የትኛውንም ዓይነት ጭቆና ላለመቀበል እምቢ ባዮች መሆን አለብን፡፡ ትግልና የትግል ውጤት ተደማሪ (cumulative) ነው፤ እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ውጤት አላት፡፡ ጭቆናን እንፀየፍ፤ እምቢ እንበል፤ ለመብታችንና ለክብራችን እንታገል!