በአገዛዙ የታነቁ ሕገ መንግሥታዊ የፍትሕ ተስፋዎች (ተሾመ ተስፋዬ እና ሄኖክ አክሊሉ )

በአገዛዙ የታነቁ ሕገ መንግሥታዊ የፍትሕ ተስፋዎች
***
ተሾመ ተስፋዬ እና ሄኖክ አክሊሉ
***

በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ቀደም ሲል የነበረው አሃዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ተቀይሮ በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት መመሥረቱን ተከትሎ የፍትሕ ተቃማቱም በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ተዋቅራል። የፍትሕ ሥርዓት ሲባል ፍርድ ቤቶችን፣ ዐቃቤ ሕግን፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤቶችን፣ ጠበቆችን፣ የሕግ ትምህርት ቤቶችን፣ የሕግ ምርምርና ተያያዥ ተቋማትን የሚያካትት ሲሆን፣ ተቋማቱ የሚመሩበትን የአሠራር ሥርዓት ያጠቃልላል። የፍትሕ ሥርዓት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስከበር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በመደገፍ የማይተካ ሚና እንዳለው ይታመናል። በሕገ መንግሥቱ ላይ የፍትሕ ሥርዓቱን አስመልክቶ በርካታ ተስፋ ሰጪ ድንጋጌዎች የተካተቱ ሲሆን ድንጋጌዎቹን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የታዩ አንዳንድ ችግሮችን በመዳሰስ ለውይይት መነሻ የሆኑ ሐሳቦችን ማቅርብ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ ነው።

በሕገ መንግሥቱ የተገቡ የፍትሕ ሥርዓት ተስፋዎች
***

ሕገ መንግሥቱ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኙ በርካታ የፍትሕ ሥርዓት መርሆዎችን አካቶ ስለመያዙ ብዙ ባለሙያዎች ይስማማሉ። የፍትሕ ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ መሆኑ ይታመናል። የሕግ የበላይነት አገሪቱ የቆመችበት መሠረታዊ መርሆ እንደሆነ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ በግልጽ ተመልክቷል። በፍትሕ ሥርዓት ላይ ትልቅ ሚና አላቸው ከሚባሉ ተቋማት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀዳሚው ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ላይ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ነጻ ፍርድ ቤት የተቋቋመ ሲሆን ዳኞችም የዳኝነት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ ነጻ ሆነው የመሥራት መብታቸው ተጠብቆላቸዋል። የዜጎች እና ሕዝቦች መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ሕገ መንግሥቱ ላይ አንድ ሰፊ ምዕራፍ ተሰጥቷቸው በዝርዝር ሰፍረው ይገኛሉ። ድንጋጌዎቹ ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም እንዳለባቸው ተደንግጓል። በሌላ በኩል በፍርድ ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮችን ዜጎች ለፍርድ ቤት ወይም የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል በማቅረብ ፍትሕ የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ላይ ተደንግጓል።

አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የፍትሕ ሥርዓት ምንና ምን ናቸው?
***

አንድ የፖለቲካ ሥርዓት የሚቀርፃቸው ፖሊሲዎችም ሆነ የሚፈጥራቸው ተቋማት በአብዛኛው ፈጣሪው ባለው አመለካከት፣ ባዳበረው ባሕሉና የኋላ ታሪኩ ላይ የሚመሠረቱ ናቸው። ሆኖም ወቅታዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ግፊቶች የሚያሳርፉትም ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ያምንበት የነበረው ማርክሲስት-ሌኒንስት ርዕዮተ-ዓለም እና ድርጅታዊ አሠራሩን ይመራበት የነበረው የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሕ ከግንቦት በኋላ ለፈጠረው ፖለቲካዊ ሥርዓት መሠረት እንደሆነ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ‹Ethiopia: Beleagured Opposition under a Dominant Party System› በሚለው ጥናታቸው ላይ ይገልጻሉ። ምሁሩ አክለውም ይኽ አስተሳሰቡ እና ባህሉ የጠቅልል (dominant) ዓይነት ባሕርይዎችን በመንግሥትነት ዘመኑ እንዲከተል እንዳደረገው ያስረዳሉ። ሆኖም የቀድሞ ሶቭየት ኅብረት መፈራረስን ተከትሎ የምሥራቁ ጎራ ሲመሽበት ብዙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ሳሙኤል ሃንቲንግተን “ሦስተኛው የዴሞክራሲ ማዕበል” ሲሉ በጠሩት እንቅስቃሴ የሊብራል ዴሞክራሲን እና ተቋማት የመቀበል ጫና ውስጥ ገብተዋል። ኢሕአዴግም በከባድ የምዕራባዊያን ጫና አማካኝነት በርካታ የሊብራል ዴሞክራሲ መርሆች ያካተተ ሕገ መንግሥት እና የመንግሥት አወቃቀር እንዲመሠርት ተገዷል።

ድርጅቱ በትጥቅ ትግል ጊዜ የነበረውን “የቫንጋርድነት” ባሕርይ በመንግሥትነቱ ጊዜም በመከተል በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ሕጋዊ ድንጋጌዎች ቢኖሩም ሁሉንም የፌዴራል እና የክልል መንግሥት ተቋማት በሙሉ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ለማድረግ በሰፊው ተግቷል። ፓርቲው በሕገ መንግሥቱ ተቋማዊና ግላዊ ነጻነት ያለው ፍርድ ቤትን አቋቁሟል። ነገር ግን የፍትሕ ሥርዓቱ ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ነጻነት ቢኖረውም የፖለቲካው ሲስተም ከሚዘወርበት ተጽዕኖ ውጪ ሆኖ ሊኖር እንደማይችል እና ይኼም ቀድሞ በአገሪቱ በነበሩ ሥርዓቶች የቆየውን አካሄድ ተከትሎ ቀጥሏል። ይኽን ሐሳብ የሚያጠነክሩት ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ ‹Constitutional Adjudication in Ethiopia› ሲሉ በጠሩት ጥናታቸው የፍትሕ ሥርዓቱ በኢትዮጵያ እራሱን የቻለ ነጻነት ኖሮት እንደማያውቅ እና ፈጣሪዎቹ የሆኑት ሥርዓት ሞትን ተከትሎ ይፈራርስ እንደነበር አስቀምጠዋል።

ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ የሚከተለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ እና የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብም የመንግሥት እና ፓርቲን ውሕደት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ የጠቅልልነት ባሕርይውን ለማራመድ የሚያስችሉ እንደሆነ የሚነግሩን አቶ አደም አበበ ‹Rule by Law in Ethiopia› በሚለው ሥራቸው ፓርቲው የፍትሕ ሥርዓቱን የራሱን ጥቅሞች ለማራመድ በዓይነተኝነት እንደሚጠቀምበት አስገንዝበዋል።

በእንደዚህ ዓይነት የጠቅልል ሥርዓት የፍትሕ ተቋማት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ስላላቸው የይምሰል ነጻነታቸውን ጠብቀው መቆየታቸው ይፈለጋል። ሥርዓቱን ሕጋዊነት እና ተቀባይነት ማሰጠትን ከማስቻላቸውም በላይ የውስጥ እና የውጭ ተቀናቃኞችን ዝም ለማስባል ትልቅ አገልግሎት ይሰጣሉ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ከተቋማቱ ባሕርይ በመነጨ ለሕልውናው አደጋን ሊፈጥሩ የሚችሉ በመሆኑ ትልቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ናቸው።

የፍትሕ ሥርዓቱን የባለፉት 25 ዓመታት ጉዞ መለስ ብለን ከተቋማቱ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ነጻነታቸው አንጻር ስናይም አንድ ወጥነት ያለው አካሄድ አይደለም። ከግንቦት 1983 እስከ ሕገ መንግሥቱ መፅደቅ ድረስ ያለውን ያልተረጋጋ የፖለቲካ ወቅት ትተን እስከ 1997 ድረስ የነበረውን ሁኔታ ስንቃኝ ተቋማቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አንጻራዊ ነጻነት አግኝተው የቆዩበት ጊዜ ነበር። በእርግጥ በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን ድርጅቱ ከባድ ውስጣዊ የፖለቲካ መተጋገል የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ በገጠመው ጊዜ ሕገ መንግሥቱን በጣሰ መልኩ “የስዬ ሕግ” እየተባለ የሚጠራውን የፀረ-ሙስና አዋጅ በሩጫ በማውጣት ለመጠቀሚያነት ያዋለበት አንድ ማሳያ ነው። እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ የቆየው አንፃራዊ ነጻነት ግን በዚሁ ዓመት የደረሰበትን የምርጫ ሽንፈት እና የተፈጠረውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ ድርጅቱ በከፍተኛ ደረጃ የነጻነትን ምኅዳር የሚያጠቡ እርምጃዎችን የመውሰድ ተግባር ውስጥ ተዘፍቋል። የፍትሕ ሥርዓቱም የዚህ ሰለባ ከመሆን አልዳነም።

የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ፈተናዎች
***

የሕግ የበላይነት የሚባለው ጽንሰ-ሐሳብ ሰፋ ያለ ትርጉም እና በርካታ መገለጫዎች አሉት። በዋነኛነት ግን ዜጎች ልዩነት ሳይደረግባቸው በሕግ ፊት ዕኩል ሆነው መታየታቸውንና ሕግ ጥሰውም ሲገኙም ያለ ልዩነት ተጠያቂ የሚሆኑበት ሕገ መንግሥታዊ መርሕ ነው። የሕግ የበላይነት መርሕ በዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎች በግልጽ ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን በብዙ አገሮችም ተቀባይነትን ካገኘ ቆይቷል። ሕግን እንደ አገዛዝ መሣሪያ በሚጠቀሙና ሰብአዊ መብትን ባለማክበር የሚታሙ አገዛዞች ሥልጣን ይዘው በሚገኙበት አገሮች ጭምር በሕገ መንግሥታቸው አካተውታል። ሆኖም በተግባር ሲታይ ግን ለሕግ የበላይነት ተገዥ ለመሆን ቁርጠኝነት የሌላቸው፤ የፍትሕ ሥርዓቱም ባለሥልጣናቱን ለፍርድ ማቅረብ ሲሳነው ይስተዋላል። ጥናቶች እንደሚያሳዩትም

እነዚህ መንግሥታት ዜጎችን በሕግ ለመግዛት እንጂ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ፈቃደኝነት የላቸውም። በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቷል። የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ “…በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤” ይላል። ይኽም የሕግ የበላይነት ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናን ከማግኘት ባለፈ መሠረታዊ መርሆ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ከሕገ መንግሥቱ በኋላ የወጡ ርዕዮተ-ዓለማዊ እና የፖሊሲ ሰነዶች ላይም ይኽንኑ ከመግለጽ ተቆጥቦ አያውቅም። ለሕግ የበላይነት መከበር ፓርላማ፣ ፍርድ ቤት፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ጠበቆች… እንዲሁም ነጻ ሚዲያና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የጎላ ሚና አላቸው። የሕግ የበላይነት መርሆው ሕገ መንግሥቱ ላይ መስፈሩ መልካም ነገር ሆኖ በተጨባጭ መሬት ላይ ወርዶ እንዲተገበር ከተፈለገ ግን ተቋማቱ ነጻና ጠንካራ ሊሆኑ፣ አገዛዙም ለተግባራዊነቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖረው ያስፈልጋል። በተለይም ከባባድ ባለሥልጣናትና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ሕግ ጥሰው ሲገኙ እንደማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሥርዓት መዘርጋትን ይጠይቃል። የሕግ የበላይነት በተሻለ ሁኔታ በተረጋገጠባቸው አገሮች ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ካደረጃጀት ጀምሮ ሰፋ ያለ ተቋማዊና ሙያዊ ነጻነት ተላብሰዋል። በተለይም ከፖለቲካ ተቋማት አላስፈላጊ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አስፈላጊው ከለላ ይደረግላቸዋል።

በአገራችን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ዐቃቤ ሕግ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር እንደ አንድ ክፍል ተዋቅሮ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመባል እራሱን ችሎ ተዋቅሯል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለብቻ ማቋቋም ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ተቋማዊ ነጻነት እንዲኖረው ለማስቻል መሆኑን ከማቋቋምያ አዋጁ መግቢያ ላይ ለመረዳት ይቻላል። ይኹን እንጂ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ፣ የፖለቲካና የሙያ ሥራዎች ሳይለዩ በአንድ ላይ ተጠቃለው የተሰጡት ከመሆኑ አንጻር የሙያ ሥራው በተለይም ምርመራን የማስጀመር፣ የመምራትና የማቋረጥ ተግባሩ የማከናወን ሒደት በፖለቲካ ተጽዕኖ ሥር ሊወድቅ እንደሚችልና ሙያዊ ነጻነቱ ፈተና እንደሚገጥመው የዘርፉ ባለሙያዎች ከወዲሁ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

እንደሚታወቀው ዋና ኦዲተር በተለይም ላለፉት 3 ዓመታት በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የመንግሥት የገንዘብ አያያዝ፣ ግዥ አፈፃፀም… ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉድለትና ብክነት የተገኘ መሆኑን አሳውቋል። በሌላ በኩል በዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው የስኳር ማምረቻ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም የተጓተተና ለገንዘብ ጉድለትና ምዝበራ በሚያጋልጡ አሠራሮች የተተበተበ መሆኑን መንግሥት በቅርቡ ይፋ ካደረጋቸው መረጃዎች ለመገንዘብ ይቻላል። የሕግ የበላይነት በዳበረባቸው አገሮች ቢሆን ተመሳሳይ ሁኔታ ሲከሰት በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂውን አካል ለፍረድ በማቅረብ ሕዝብም እንዲያውቀው ይደረጋል። በእኛ አገር ግን ይኼ ለመከናወኑ እስካሁን ለሕዝብ ይፋ የሆነ ነገር የለም። ይኽም ከላይ ላነሳነው ነጥብ እንደ አንድ ማሳያ ሊወሰድ የሚችል ነው።

ሥልጣኑና ነጻነቱ እየጠበበ የመጣው ፍርድ ቤት
***

ፍርድ ቤቶች ከተለያዩ ባለጉዳዮች የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች የመዳኘት ሥልጣን ያላቸው ሲሆን ሰብአዊ መብትን እና የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አንጻር ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይታመናል። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ላይ ነጻ ፍርድ ቤት መቋቋሙ እና ዳኞችም ከሙያቸው ጋር በተያያዘ ከማንኛውም ሦስተኛ አካል ተጽዕኖ ነጻ መሆናቸው ተመልክቷል። የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን ወሰን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሰጥቷል። ይኽ ከመነሻው አንስቶ ሰፋ ያለ ክርክር ሲካሄድበት የቆየ ጉዳይ ነው። በመግቢያችን ላይ እንዳመለከትነው የጽሑፉ ዋና ዓላማ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈሩና ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ መርሆዎች በአተገባበር ረገድ የገጠማቸውን አንዳንድ ፈተናዎች ማሳየት ላይ የተገደበ በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የመሰጠቱ አግባብነት ላይ በዝርዝር የምንለው አይኖርም። ነገር ግን ከመነሻው ፍርድ ቤት የተሰጠው ሥልጣን የጠበበ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

የዳኝነት ሥልጣን በመርሕ ደረጃ ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች ብቻ የተሰጠ መሆኑን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 (1) ደንግጓል። ይኹን እንጂ የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን በብዙ መልኩ የሚሸረሽሩ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በቅድሚያ ከላይ እንደተገለጸው በሕገ መንግሥቱ ላይ ሕገ መንግሥትን መተርጎም የፍርድ ቤት ሳይሆን የፌዴራል መንግሥቱ መሥራች የሆኑ ክልሎች የሚገኙበት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የሚልኳቸው አባላት የሚወከሉበት ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። የተቀሩት የዳኝነት ሥልጣኖች በመርሕ ደረጃ ለፍርድ ቤት የተሰጡ ቢሆንም ለሌሎች አካላት በሕግ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 (4) ድንጋጌ ለመገንዘብ ይቻላል። ድንጋጌውን በጥልቀት ስንመለከተውም በሕግ የተደነገገውን የዳኝነት ሥርዓት የማይከተሉ ሌሎች የዳኝነት ተቋማት ማቋቋም እንደማይቻል ተመልክታል። ይኽም የሆነው የዳኝነት ሥራ ፍትሕ ከማስፈን ጋር የተያያዘ ግልጽ፣ ፍትሐዊና ዕኩልነትን መሠረት ባደረገ ለምሳሌ እያንዳንዱ ተከራካሪ ክርክሩን በአግባቡ እንዲያቀርብ፣ በሌላው ተከራካሪ የቀረበበት ክርክርና ማስረጀ ደርሶት እራሱን እንዲከላከል ዕድል መስጠት መሠረታዊው የፍትሕ አሰጣጥ ሒደት በመሆኑ ነው። ስለዚህም ልዩ ፍርድ ቤቶች ሲቋቋሙ የዜጎችን እነዚህን መሠረታዊ መብቶች የማይጥሱ መሆኑን ማረጋገጥ ከባድ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በአገራችን በሕግ አውጪው አካል የተቋቋሙ ከፊል የዳኝነት ሥልጣን (quasi judicial power) ያላቸው አካላት ገቢዎች ሚኒስቴር፣ የቦታ ማስለቀቅ፣ የሸማቾች ማኅበራት፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ አሠሪና ሠራተኛ ቦርድ፣ ማኅበራዊ ዋስትናን… ይጨምራል። እነዚህ ከፊል የዳኝነት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላትን በተመለከተ ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች ቢኖሩም የከተማ ቦታ የሊዝ ቦርድ የተቋቋመበትን ሁኔታና ከሚመራበት ሥርዓት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት። የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 መሠረት የከተማ ቦታ ማስለቀቅና የካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ተቋቁሟል። ጉባኤው አግባብ ያለው የመንግሥት አካል ይዞታውን እንዲለቅ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ሰው የሚያቀርበውን ቅሬታ በይግባኝ የማየት የዳኝነት ሥልጣን ተሰጥቶታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በጣም አከራካሪው ጉባኤው “በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ አይመራም” ብሎ እራሱ አስፈፃሚው በሚያወጣው “የተቀላጠፈ” ሥርዓት ይመራል ሲል ያልተገደበ የሥነ-ሥርዓት አካሔድ መፍቀዱና ይኽም በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ አለመሟላቱን የሚያመላክተው ሲሆን ሌላው ደግሞ ጉባኤው በአንቀጽ 29 (3) ላይ ቦታውን (መሬቱን) እንዲለቅ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ተነሽ “በካሳ ክርክር ላይ ካልሆነ በስተቀር ምትክ ቦታን ጨምሮ በሌሎች በሕግም ሆነ በፍሬ ነገር ክርክሮች ላይ ጉባኤው የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል” በማለት ጉዳዩ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንዳይሄድ ያስቀመጠው ክልከላ ነው።

ይኽ አዋጅ በኢትዮጵያውያን ማንነት ውስጥ እጅግ ትልቅ ስፍራ ስላለው የመሬት ጉዳይና በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ስላገኘው የንብረት መብት በመሆኑ ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ብቻ ቸል ሊባል እንደማይገባውና ትልቅ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ ብዙዎች ያስገነዝባሉ። የዚህ ሕግ ሰለባ ሆንን የሚሉ ወገኖች ጩኸትም በየቀኑ በመገናኛ ብዙሃን መስማት የተለመደ ሆኗል።

ፍርድ ቤቶች በተለያዩ ሌሎች አካላት ሥልጣናቸውን መነጠቃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እራሳቸው ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ባላቸው ፍርዶች በሚሰጠው ውሳኔ (አዋጅ ቁጥር 454/1997 ላይ የተደነገገ) ሕገ መንግሥታዊ እና ተፈጥሯዊ (inherent) የሆነውን የዳኝነት ሥልጣናቸውን በርካታ ጊዜ በራሳቸው ፈቃድ አሳልፈው ሲሰጡም ተስተውሏል። እነዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ናቸው በማለት ግልጽ ድንጋጌ በሌለበት እና በጠበበ ሁኔታ መተርጎም ያለባቸውን ልዩ ሁኔታዎች በፍርድ ሊዳኙ የሚችሉት አይደሉም በሚል የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ፍርድ ቤት ሥልጣኑን በራሱ ውሳኔ እያጠበበ የመጣ መሆኑን ብዙ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ሲሆን፣ ‹A Judicial Branch Growing to a Legislative Oligarchy› የሚል አንድ ጥናት ይህንኑ በማንሳት ይከራከራል።

ፍርድ ቤቶች ባለፉት ዓመታት ያላቸው የዳኝነት ሥልጣን በተለያየ መንገድ መሸርሸሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የፍርድ ቤቶች ነጻነት መገለጫ አንዱ የራሳቸውን በጀት ማስተዳደር መቻላቸው ነው። ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79(6) “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራሉን መንግሥት የዳኝነት አካል የሚያስተዳድርበትን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስወስናል፣ ሲፈቀድም በጀቱን ያስተዳድራል፤” ቢልም በተግባር ግን የፍርድ ቤቶች በጀት በአስፈፃሚው አካል ቁጥጥር ሥር ሆኖ በመገኘቱ የዳኞችን ደሞዝ፣ ጥቅማ ጥቅም እና በአጠቃላይ የፍርድ ቤቶቹን ዕቅድ በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የአስፈፃሚውን አካል በጎ ፈቃድ ማግኘት ግዴታ ሆኖበታል።

የዳኞች አመላመል እና አሿሿም በተመለከተም ነጻነታቸውን ባስጠበቀ መልኩ እስካሁን ወጥነት በሌለው አሠራር የሚካሄድ መሆኑን እራሱ መንግሥት እ.አ.አ. በ2005 ያስጠናው “የተቀናጀ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም” ሪፖርትና ሌሎችም ጥናቶች ያሳያሉ።

በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተጠፍሮ የቆየው ፍርድ ቤት የነቃ ተሳትፎ (Judicial Activism) በማድረግ የሕግ የበላይነትና የዜጎችን መብት የማስከበር አቅሙ በእጅጉ የተገደበ ነው፡፡

ያልሞከርነው ለሕዝብ አጠቃላይ ጥቅም ተሟጋችነት (Public Interest Litigation) ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል በማቅረብ ፍትሕ የማግኘት መብት አለው። ዜጎች በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሌሎች ሕጎች የተጠበቁላቸው መብቶች ሲጣሱባቸው፣ የጣሰውን ሰው ወይም ተቋም ከሰው ወይም እንዲከሰሱ በማድረግ መብታቸውን ማስከበር ካልቻሉ መብቶቹ ዋጋ አልባ እንደሚሆኑ ይታወቃል። አሁን የምንመለከተው ግን ከሕዝብ ወይም ከተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል አጠቃላይ መብትና ጥቅም ጋር በተያያዘ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ጥቅም ወይም መብት የሌለው ሰው ወይም ተቋም ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አደባባይ በማቅረብ የኅብረተሰቡን ጥቅም ለማስከበር መብት ያለው መሆን አለመሆኑንና ይኽም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚኖረውን እንድምታ በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ነው።

በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቀደም ባሉት ጊዜያት በአብዛኛው አገሮች (ኢትዮጵያን ጨምሮ) አንድ ሰው ወይም ተቋም በአንድ ጉዳይ ላይ መብት ወይም ጥቅም ሳይኖረው ክስ ማቅረብ አይችልም። የሕዝብ አጠቃላይ ጥቅም ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ክስ ማቅረብ የሚችለው ዐቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ግለሰቦችና ሌሎች አካላት ክስ የማቅረብ ዕድል ጭራሹኑ የላቸውም ወይም በእጅጉ የተገደበ ነው። በሒደት ግን አገራት በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችንና በደሎችን ማንኛውም ሰው ወይም አካል በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ጥቅም ባይኖረውም እንኳን ለፍርድ አቅርበው ለተጎጂዎች ፍትሕ ማስገኘት እንዲችሉ በመፍቀድ የሕግ ማዕቀፍ አበጅተዋል። በዚህ ረገድ የሕንድና ደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ለእኛም አገር በአርኣያነት ሊወሰድ የሚችል ነው።

በሕንድ በነባሩ ሥነ-ሥርዓት ሕግ መሠረት አንድ ሰው ክስ ለማቅረብ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ጥቅም ሊኖረው ይገባ ነበር። ሆኖም በ1979 የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ነባሩን የሥነ-ሥርዓት ሕግ በማሻሻል በጉዳዩ ላይ አዲስ አቅጣጫ እንዲቀይሱ ያስቻላቸው አጋጣሚ ተፈጠረ። ይኸውም የሕንድ ጋዜጦች “ባሂር” በተባለች ግዛት ለፍትሕ አካላት ሳይቀርቡ ቢፈረድባቸው እንኳን ሊቀጡት ከሚገባ ጊዜ በላይ በእስር ሲማቅቁና በደል ሲደርሰባቸው የነበሩ ግለሰቦችን አስመልክቶ ዘገባ ያቀርባሉ። በዚህ መነሻነት ከነባሩ የክስ አቀራረብ ሒደት ባፈነገጠ ሁኔታ አንዲት ጠበቃ ለግዛቱ ፍርድ ቤት ክስ ያቀርባሉ። ክሱም ተቀባይነትን አግኝቶ በጠቅላላ አገሪቱ ውስጥ ያሉ በሺሕ የሚቆጠሩ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን ቀጥተኛ ጥቅም ባይኖረውም እንኳን አንድ ሰው ወይም ተቋም በሕዝብ አጠቃላይ ጥቅም ላይ የሚፈፀሙ የሕግ ጥሰቶችን ለፍርድ በማቅረብ ፍትሕ እንዲያገኙ የማድረግ መብት እንዲኖረው ተደርጓል። ከዚህም በላይ ሥርዓቱ የበለጠ እየተለመደና እየዳበረ ሲመጣ የክስ አቀራረብ ሒደቱ ከመደበኛው ሥርዓት ቀለል እንዲል አድርገዋል። በዚሁ መሠረት ክሱን በፖስታ ለመመሥረት እስከሚቻልበት ደረጃ ተደርሷል። በርካታ የመብት ጥሰቶችም ለፍርድ ቀርበው መፍትሔ አግኝተዋል። በደቡብ አፍሪካም ይኽ ሥርዓት ከተለመደ የቆየ ሲሆን በአፓርታይድ ሥርዓት ነጮች በጥቁሮች ላይ የሚያደርሱትን መድልዎና የመብት ጥሰት በፍርድ አደባባይ ለመታገል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደነበረውና በአሁኑ ወቅትም በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ሙያቸውንና ተቋማዊ አቅማቸውን በመጠቀም አጠቃላይ የመብት ጥሰቶችን በፍርድ አደባባይ ለመሞገት ዕድል አግኝተዋል። ሥርዓቱ አቅምም ሆነ ዕውቀቱ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር እገዛ ማድረጉ፣ የሕዝቦች መሠረታዊ መብቶችና ጥቅሞች ላይ ጥሰት የፈፀሙ የመንግሥት ተቋማትና ባለሥልጣናትን በፍርድ አደባባይ በመገተር ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ሙስናን በማገዙ፣ በሒደቱም ዜጎች ስለመብታቸው በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙና በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እንዲተማመኑ መርዳቱ፣ በጥቅሉ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥና የመብቶች መከበር ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ ይታመናል። በዚህም የተነሳ ሥርዓቱ በተለያዩ አገሮች ተቀባይነት እያገኘና ምቹ የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኙ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ (በሌሎች አገሮችም ሆነ) ዐቃቤ ሕግ መደበኛ ተግባሩ የሆነውን የወንጀል ክስ ማቅረብና የወንጀል ምርመራን ከመምራት ባሻገር በአጠቃላይ የአገሪቱ ሕጎች መከበራቸውን መቆጣጠር፣ እንዲሁም ከሕዝብ ጥቅም ጋር የተያያዙ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ ክስ የማቅረብ ሰፊ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ከማቋቋሚያ አዋጁና ከፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል። ቀደም ሲል እንደተመለከተው በአገራችን ዐቃቤ ሕግ ከአወቃቀሩም ሆነ ከተግባሩ አኳያ ሲታይ ከአስፈጻሚው አካል ተጽዕኖ ነጻ ነው ለማለት እንደማስደፍር በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ በተለይም ጠንካራ በሆኑ የመንግሥት ተቋማትና ባለሥልጣናት አማካኝነት በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ተከታትሎ ለሕግ ላያቀርብ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። በሌላ በኩል ካለንበት ዕድገትና ሥልጣኔ ደረጃ የመብት ጥሰት የሚፈፀመባቸው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ መብታቸው በቂ ግንዛበ የሌላቸው የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። ግንዛቤው ቢኖራቸውም መብቶቻቸውን ለማስከበር አቅሙም ሆነ ድፍረቱ ላይኖራቸው እንደሚችል ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል።

ደረጃው ይለያይ እንጂ በየትኛውም አገር ቢሆን አናሳ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ድሆች፣ አካል ጉዳተኞች… አጠቃላይ መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን በፍትሕ አደባባይ አቅርበው ለማስከበር ሲቸገሩ ይስተዋላል። ይኽም ከላይ የተጠቀሰው ተሞክሮ ለአገራችን በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል። በሥራ ላይ ያለው የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ መሠረት አንድ ሰው ወይም አካል ክስ ለማቅረብ በቅድሚያ በጉዳዩ ላይ ጥቅም ያለው መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት በአንቀጽ 33 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። በአንጻሩ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ላይ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚችል ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል አቅርቦ ፍትሕ የማግኘት መብቱ ተከብሮለታል። ይኽ ድንጋጌ እንደ ፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ክስ አቅራቢው ሰው ክስ በሚያቀርብበት ጉዳይ ላይ የግድ ጥቅም ሊኖረው የሚገባ ለመሆኑ በግልጽ የሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለም።

እንዲሁም ለሕዝብ ጥቅም የሚደረግ ሙግት (Public Interest Litigation) እንደዳበረባቸው አገሮች የሕዝብን አጠቃላይ ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም ጥቅም ሳይኖረው ክስ ለማቅረብ ስለመቻሉ በግልጽ አላሰፈረም። በሌላ በኩል ይኽ መብት በግልጽ ሰፍሮ የሚገኘው ከአከባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ሲሆን የአከባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995 አንቀጽ 11 ላይ አንድ ሰው ወይም ተቋም ጉዳዩ የሚመለከተው መሆኑን ማስረዳት ሳይጠበቅበት በአከባቢ ላይ ጉዳት ባደረሰ በማንኛውም ሰው ላይ ክስ ለማቅረብ እንደሚችል ተደንግጓል:: ጠበቆችን በተመለከተ ደግሞ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 199/92 አንቀጽ 7 ላይ እንደተደነገገው የሕዝብ ጥቅምን አስመልክቶ ክስ ለማቅረብ ልዩ ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸው ተመልክቷል። እነዚህ ድንጋጌዎችን በጥሞና ስንመለከት ምንም እንኳን ከነባሩ ሥርዓት አንጻር ሲታይ የሕዝብን ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጉዳዩ የማይመለከተው ሰው ወይም ተቋም ክስ ለመቅረብ የሚችልባቸው የተወሰኑ ዕድሎች ቢኖሩም በጥቅሉ ሲታይ ግን በኢትዮጵያ ለሕዝብ ጥቅም ሙግት የማቅረብ መብት ተረጋግጧል ለማለት አይቻልም።

ከላይ እንደተገለጸው ሥርዓቱ በዳበረባቸው አገሮች መብቱን በሕገ መንግሥትም ሆነ በሌሎች ሕጎቻቸው ከማስፈር ባለፈ መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን ይደነግጋሉ። በተጨማሪም ክሱን የሚያቀርቡ ሰዎች በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ጥቅም የሌላቸው መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደማበረታቻ ከመደበኛው ሥርዓት ቀለል ያለ ክስ የማቅረቢያ ሥርዓት ዘርግተዋል:: ፍርድ ቤቶቻቸውም ቢሆን በጉዳዩ ላይ የላቀ ሚና ለመጫወት የሕግ ማዕቀፍና ነጻነት አላቸው። በእኛ አገር ግን ቀደም ብሎ በቀረበው ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደሰፈረው ፍርድ ቤቶች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የነቃ ሚና ለመጫወት ያላቸው ዕድል በእጅጉ የተገደበ ሲሆን፤ በአከባቢ ብክለት ጉዳይ ላይ እንኳን መብቱን ከማስፈር ዉጪ በበቂ ሁኔታ ቀለል ያለ የአሠራር ሥርዓት አልተበጀለትም።

ጠበቆችም ቢሆን ፈቃድ የሚሰጣቸውና የሚቆጣጠራቸው በወንጀል ጉዳይ ተከራካሪያቸው የሆነው ቀደም ሲል ፍትሕ ሚኒስትር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመሆኑ፤ ጠንካራና ሙያውን የመቆጣጠር መብት ያለው የሙያ ማኅበር ስለሌላቻው፣ ቀጥተኛ ጥቅም ለማያገኙበት ጉዳይ ልዩ ፈቃድ እንዲያወጡ መገደዳቸው በመብቱ የመጠቀም ዕድላቸውን ያመነምነዋል። በሌሎች አገሮች የበጎ አድራጎት (ሲቪክ) ማኅበራት የሕዝብ ጥቅም ክስ በማቅረብ ረገድ የላቀ ሚና ያላቸው ሲሆን በኛ አገር ግን ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች አልፎ አልፎ የሰብአዊ መብት ጥሰትን ከማጋለጥና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ከማዘጋጀት ያለፈ ሚና ሲጫወቱ አይታዩም። በዚህ ረገድም ቢሆን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራትን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የወጣ አዋጅ ቁጥር 621/2001 የውጭ ማኅበራት ሙሉ በሙሉ፣ የአገር ውስጦቹ ደግሞ ከ10% በላይ ገቢያቸውን ከውጭ የሚያገኙ ከሆነ በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም የፍትሕና የሕግ ማስፈፀም ተግባር ላይ እንዳይሳተፉ ተከልክለዋል። በዚህም የተነሳ እንቅስቃሰያቸው በእጅጉ የተዳከመ መሆኑ ብዙ የተባለለት የአደባባይ እውነታ ነው።

የባለፉት 27 ዓመታት የፍትሕ ሥርዓቱ ጉዞ ራሱ ፓርቲው ለሕዝብ ከሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት የገባቸውን ቃል ኪዳኖች ማሳካት ተስኖት፣ ይልቁንም የፍትሕ ሥርዓቱ ለፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያ ለበርካታ ጊዜ በመዋሉ ሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እጅጉን ተመናምኖ የሚገኝበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ ይገኛል። የወደፊቱ ጉዟቸው ከዚህ ስለመለየቱ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ይኖር?