የጠ/ሚ አብይ አህመድ የጎንደር ጉብኝታቸው ሙሉ ንግግር

የመካከለኛው ዘመን ስልጣኔ መሰረት እና የህዝባችን የከፍታ መሰላል፤ የባህል እና ውብ እሴቶቻቸችን ማህተም፤ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ጌጥ እና የትጉሀን ልጆች እናት፣ የኢትዮጵያችን የታሪክ አውድማ እና የኩሩ ህዝብ ምድር፣ የዛሬያችን መሰረት ትላንት በተጣለባት ድንቅ ከተማ ጎንደር ተገኝቼ መልዕክት ማስተላለፍ በመቻሌ የተሰማኝን ልባዊ ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎንደር ጉልህ ድረሻ አላት፡፡ ጠቢባን ልጆችዋ በኪነ ሕንፃ የላቀ እርምጃቸው ዛሬም ድረስ የምንደመምበትን የፋሲል ቤተ-መንግስት አንፀው እንዳቆዩልን ሁሉ አብሮነትን ባካተተ ዝማኔ የመንግስት መቀመጫ ቀደምት ታሪክ አኑረዋል፡፡ ሊቃውንቶቿ አማርኛን ከንግግር ወደ ጽሁፍ ቋንቋነት ያሸጋገሩ ብቻም ሳይሆኑ አሻራቸው ዘመንና ትውልድን በተሻገሩ ስራዎች ህያው ሆነው ይኖራሉ፡፡

ጎንደር ከጃንተከል ጥላዋ ስር በዘመን ሀዲድ ላይ እያኖረች የመጣችው የመነጋገር፣ የመከራከር፣ የመወያየት፣ የመደማመጥ፣ የመቀራረብ፣ የመተሳሰብ እና ያለመናወጥ፤ የአብሮነት ካብ፣ የድንቅና ረቂቅ ባህል ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ባህል መዳበር ያለው አንድምታ ከፍተኛ ነው፡፡

ክቡራትና ክቡራን

ለሀገራችሁ እና ለህዝባችሁ የምታሳዩት ፍቅር፤ ለቃላችሁ የምትሰጡት ክብር እና በሀገር አንድነት ላይ ያላችሁን ፅኑ አቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በውል ይረዳዋል፣ ያከብረዋል፡፡

እንኳንስ ጎንደር ከምድሯ- ከጥቁር አፈሯ ላይ ሆናችሁ ይቅር እና የህይወት እጣፈንታ ሰው ሀገር አድርሷችሁ እንኳን ወገናችሁን፣ ሀገራችሁን፣ እና ትላንታችሁን የማትረሱ እንደሆናችሁ እናውቃለን፡፡

በባህሪና በሁኔታ ቢለያዩም ቅሉ በየዘመናቱ እና በየመንግስታቱ የሚገጥሟችሁን ፈተናዎች የምትሻገሩበት ትእግስት፣ ወኔ፣ እና ጥንካሬ እንዲሁም ከሁሉም ኢትየጵያውያን ወንድሞቻችሁ ጋር ያላችሁ የማትደራደሩበት ዘላለማዊ የአብሮነት ድንቅ እሴት ሁሌም ሁሉንም እንዳስደመሙ ዛሬም አሉ፡፡

ከሁላችንም በፊት ትላንት ላይ ሆኖ ዛሬን ያየውና የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውጥን በምዕናቡ የጠነሰሰወው የመይሳው ልጆች ናችሁና በተለመደው ትእግስታችሁና አርቆ አሳቢነታችሁ ከጎናችን እስካላችሁ ድረስ በምንችለው ፍጥነት እና መጠን ተረባርበን በመስራት በጥበብ የማናቋርጠው የህይወት እክል በፍጹም ሊኖር እንደማይችል አጥብቄ አምናለሁ፡፡

በዘላቂነትም የጎንደር እና አካባቢዋ ወጣቶች ተፈጥሮ ከቸረቻቸው በረከት ተጠቅመው ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን መቀየር እና ማሳደግ አለባቸው፡፡ አካባቢው የዕድገት ኮሪደር ሆኖ እንዲለማ እና ለአገራችን የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርካት ይኖርበታል፡፡

ወጣቱን እና የነዋሪውን ገቢ አስተማማኝ መሰረት ላይ የሚያንጹበትን ሁኔታ ማሰብና በፍጥነት ወደ ውጤት ማስገባት ይኖርባችኋል፡፡ ይህ እንዲሆንም የፌደራል መንግሰት ከክልሉ መስተዳደር ጋር በመቀናጀት ይሰራል፡፡

ክቡራትና ክቡራን

ጎንደር የድንቅ ታሪክ ባለቤት- የዘመነዊቷ ኢትዮጵያ ጽኑ መሰረት- የጥበብ እና ውበትም ቤት- የእምነት እና የድል ተምሳሌት ናት፡፡

ጎንደር የተስፋ ጎህ ብስራት መፍለቂያ፤ የአንድነት ጸሀይ መፈንጠቂያ ተደርጎ ይታያል፡፡ በጦር አበጋዞች ፉክክርና የእርስ በርስ ጦርነት ሀገራዊ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በዚያ ዘመን ጎንደር የሀገራዊ አንድነት ትልም አመንጭታ የተስፋ ብርሃንን ፈንጥቃለች፡፡

አርማጭሆ የነ ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማና ደጃዝማች ብሬ ዘገዬ፣ የነጻነት ተጋድሎና የአልበገር ባይነት ተምሳሌት ናት፡፡

ዛሬም የዚህ አደራ ተረካቢ ሆነን የሀገራችን ዲሞክራሲያዊ አንድነት በፍትህና በነጻነት መደላድል ላይ መስርተን እንደምናስቀጥል እተማመናለሁ፡፡

በጋፋት ብረት አቅልጠውና ቀጥቅጠው መድፍ የሠሩት ያገራችን ልጆች ወኔ፣ ታሪክ የማይረሳው እና ትውልድ የሚቀባበለው ጀግንነት ከመሆኑም ባሻገር ቴክኖሎጂን በማሸጋገር በራስ አቅም ነፃነትን አስጠብቆ ለመቆም ላደረግነው ጥረት መታሰቢያ ነው፡፡ ዛሬም እኛ በእደ-ጥበብና በቴክኖሎጂ ልቀን ወጥተን አዲስ ታሪክ ለመስራት፣ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማሸነፍ ቆርጠን መነሳት አለብን፡፡

ይህ ሕዝብና ይህ ምድር በገዥዎች ጭካኔ በትር ይሳደዱ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማትረፍ መስዋትነት የከፈለ፣ ኢህዲንን የመሰረቱ ያልተንበረከኩ ቆራጥ ታጋዮች ያፈራ ህዝብ ነው፡፡ የአማራ አርሶ አደሮች፣ ምሁራንና ወጣቶች በጎንደር፣ በአዲስ ዘመን፣ በጋይንት፣ በእስቴ ፣በደብረታቦር፣ በጉና ፣በበለሳ በሁሉም የአማራ ክልል ገጠሮችና ከተሞች የከፈሉት ውድ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በክብር የምንዘክረው ብቻ ሳይሆን ዘብ የምንቆምለት ሕያው አደራም ጭምር ነው፡፡

ባሳለፍናቸው ትግሎች በርካታ የአማራ ወጣቶች በአደባባይ ተረሽነው ሬሳቸው ሜዳ ተጥሏል፤ ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፡፡ እጅግ ብዙ የሆኑ ዜጎችም ከተወለዱበትና ካደጉበት ቀዬ ቤተሰባቸውን ጥለው ሀብት ንብረታቸውን በትነው ስደት ገብተዋል፡፡

ይህ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራ ለመሆን ያፈሰሰወን ደም፣ የከሰከሰውን አጥንት፣ እና የከፈለውን ወደር የለሽ መስዋእትነት የሚመጥን ዴሞክራሲ፣ ልማት፣ ፍትህ እና ሰላም እንዲያገኝ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኘነት ይረባረባል፡፡

የሠላምን ዋጋ፣ የዴሞክራሲን አስፈላጊነትና የአብሮነትን ጥቅም ለጎንደር ሕዝብ መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ከመሆኑም ባሻገር ከመይሳው ሩቅ ራእይን፣ ከፋሲል ስነ-መንግስትና እና ኪንን፣ ከአለቃ ዘነብ ቅኔን እና እውቀትን፣ ከገብርዬ ጀግንነትን እና ታማኝነት…. ከእልፍ ተምሳሌቶቹ እልፍ ቁም ነገሮችንና እሴቶችን ለተማረ- ለተቀበለ እና በህይወቱ ውስጥም ላኖረ ህዝብ- ሀገር ማለት ምን እንደሆነች በውል ይረዳልና ይህን ለማብራራት መነሳት ከንቱ ድካም ነው፡፡

የተከበራችሁ የጎንደር እና አካባቢዋ ህዝቦች

ክቡራት እና ክቡራን

ጎንደር የቤተኛው ጎንደሬ ብቻ ሳትሆን የሌላው ኢትዮጵያዊ ቤት፣ የእንግዳው ቱሪስትም መልካም አቀባበል ምታደርግ እንደሆነች ለመመስከር የተመቸው ጥምቀትን፣ ያልሆነለት ሰንበትን አሊያም ደግሞ ለአንድ ቀን ከጎንደር ሰማይ ስር ውሎ ማደር በቂ ይሆናል፡፡ ይሄ ፍቅር እና ሰብዓዊነት ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ያስፈልገናል፡፡

ትላንት የነበሩን መልካም ስም፣ ዝና፣ ታሪክ እና የጀግንነት ገድሎቻችን የበለጠ ጉልበት እና የመንደርደርያ ሀይል እንዲሆኑን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ልንጠቀምባቸው ይገበል፡፡

ንግግሬን ከማጠናቀቄ በፊት ላሳስባችሁ የምወደው ኢትዮጵያ የጋራ ኪዳናችን- መነሻ እና መድረሻችን- ብዙ ስንሆን አንድ የመሆኛ ሚስጥራችን- ኖረን በስሟ መጠሪያችን- ሞተን ምድሯ መሆናችን፣ አብረናትም ሆነን ስስታችን – ተሰደንም ናፍቆታችን ለሆነች ውብ ሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት እና ብልጽግና ሁላችንም እጅ ለ እጅ ተያይዘን በጋራ እንድንሰራ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በዚህ ሂደት ኩሩው የጎንደር ህዝብ አዲስ ታሪክ እንደሚሰራ አምናለሁ፡፡ ጎንደር ማለት ባለፈው ታሪክ የበቃው፣ የደከመና የነጠፈ ሳይሆን ብርቱ፣ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር በመተባበር ዛሬም በስራ ላይ ያለ፣ አኩሪ ገድል የሚፈጽም የጀግና ህዝብ ሀገር ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ መላው የጎንደር እና የአካባቢዋ ህዝብ በዚህች ዕለት ላደረጋችሁልን መልካምና ድንቅ አቀባበል፣ ላሳያችሁን ፍቅርና አክበሮት ታላቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!

አመሰግናለሁ