የእስክንድር ነጋ የውጪ ሃገር ጉዞ ! ( ይድነቃቸው ከበደ )

የእስክንድር ነጋ የውጪ ሃገር ጉዞ !

ከዛሬ 12 ዓመት በፊት በህወሃት መራሹ የኢህአዴግ “መንግስት” የደህንነት ተቋም አንድ አስገራሚ ገጠመኝ በቦሌ ሃየር መንገድ ተከስቶ ነበር ፤ ነገሩ እንዲህ ነው የደህንነት ተቋሙ ከያዘው ጥቁር መዝገብ ውስጥ “እስክንድር ነጋ” የሚል ስም ተጽፎ ይገኛል ።በወቅቱ የደህንነት መስሪያ ቤት አለኝ ባለው መረጃ “እስክንድ ነጋ” ያሳፈረው አውሮፕላን ጉዞውን ለማቅናት ማኮብኮቢያውን ለቆ ሃየር ላይ መሆኑ ይደረስበታል፤ በወቅቱ ተሳፋሪ የጫነው አውሮፕላን በአስቸኳይ ወደነበረት መሬት እንዲያርፍ በደህንነት ሰዎች በሬዲዮ ግንኙነት ይገደዳል ፤ “እስክንድር ነጋ” ያሳፈረው አውሮፕላን በተሰጠው ቀጭን ትእዛዝ ወደ ነበረበት ይመለሳል ።

በወቅቱ በተሳፋሪዎቹ ዘንድ ድንጋጤ እና ወከባ ይፈጠራል፤ እነዚያ “ጎበዝ” የደህንነት ሰዎች በመጣደፍ መሳሪያቸውን አቀባብለው ፣ የሬዲዮ ግንኙነት እያደረጉ በከፍተኛ የጀብደኝነት ሰሜት በአውሮፕላን ውስጥ “እስክንድር ነጋ” ፍለጋ ይጀምራሉ ጊዜም አልፈጀ ወዲያውኑ በእነኚሁ “ጎበዝ” የደህንነት ሰዎች ተፈላጊው ሰው መያዝ እሁን ይሆናል ። በተደረገው ጥብቅ ፍተሻ እና ክትትል ” እስክንድር ነጋ” ሳይሆን ‘እስከዳር ነጋ” የተባለች ሴት ተጓዥ ሆና ትገኛለች ። የቸኮለች አፍሳ ለቀመች አለ የሃገሬ ሰው መባሉ ለምን ሆነና ?! የእለቱ በረራ በዚህ ምክንያት ተስተጓጉሎ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የዚህ ጽሁፍ አንባቢያን ይህ ከላይ የተገለጸው ምናባዊ ተረት እንዳይመስላችሁ በሃገሬ እሁን የሆነ ክስተት እንጂ ።

ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መበት አቀንቃኝ የሆነዉ እስክንድር ነጋ ! በአገዛዙ ስርዓት በተደጋጋሚ ለእስር እና ለከፍተኛ እንግልት የተዳረገ ብርቱ አገር ወዳድ ዜጋ ነው። በዚያው ልክ ተደጋጋሚ አሰቃቂ የእስር ጊዜ አሳልፎ የደረሰበት በደል እና መከራ ወደ ጎን በመተው “ከእኛ የሚጠበቀው በትግላችን ጽናት ፣ በአካሄዳችን መቻቻል፣ በመንፈሳችን ፍቅር፣ በአስተሳሰባችን ሚዛናዊነትና በተግባራችን ሠላምን ይዘን ወደፊት መጓዝን ነው ” በማለት በቅርብ ከእስር መፈታቱን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልእክት አጽኖት በመስጠት ፤ መቻቻልን ፣ ፍቅርን፣ እና ሰላምን እንዲሁም ይቅር ባይነት እየሰበከ ይገኛል ። ከእስር ከተፈታ በኋላ በተገኘው አጋጣሚ ይህን ሃሳቡን በተደጋጋሚ ከመግለጽ ወደኋላ ብሎ አያቅም ።

ይሁን እንጂ ለሰላም ፣ለፍቅር እና ለይቅር-ባይነት እጅን የዘረጋው ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ እስክንድር ነጋ ፤ በአገዛዙ ስርዓት በኩል አሁንም የተሰጠው ምላሽ ከወትሮው የተለየ አይደለም ። ” ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳም ” እንደሚባለው በዶ/ር አብይ አህመድ “የሚመራው” መንግት አሁንም የዜጎች የመንቀሳቀስ እና ከሃገር ወደ ሃገር የመዘዋር መብት እየገታ ይገኛል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አስፈላጊውን የውጪ ሃገር ጉዞ ሕጋዊ ሰነድ ያሟላ ቢሆንም ከሃገር እንዳይወጣ ታግቷል ፤ ይህ ደግሞ መንግስታዊ ውንብድና ነው ። እርግጥ ነው የዚህ አይነት መሰል መንግስታዊ አሻጥር ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በሌሎች ሰዎችም ላይ ደርሶ እንደነበር የሚታወቅ ነው።

ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ለዜጎች መብት መከበር ጠንክሬ እሰራለው የሚሉት ዶ/ር አብይ አህመድ ፤ እሳቸው የሚመሩት የሚንስትሮች ምክር ቤት አቶ አባዱላ ገመዳ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አድርጎ በሾመ ማግስት ፤ የብሔራዊ ደህንነት ተቋም የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የውጪ ሃገር ጉዞ በማስተጓጎል ሥራውን እንደቀድሞ በይበልጥ አጠናክሮ ቀጥሏል ። ይህም የደህንነት ተቋሙ የሚመራው ወይም እየተመራ ያለው በማን እንደሆነ የሚያመላክት ከመሆኑ ባሻገር ፣ ተቋሙ አሁንም የዜጎችን ደህንነት እና የአገር ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ይልቅ ፤ ከአገዛዙ ስርዓት በፖለቲካ አመለካከት ብቻ የተለዩ የሰብዓዊ እና የዲሞክራሲ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሰላማዊ እና ሕጋዊ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ማወክ ዋንኛ ሥራው እንደሆነ የሚያመላክት ጭምር ነው ።

” ድል ለዲሞክራሲ !! ”
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!

( ይድነቃቸው ከበደ )