ሥርዓቱ የገባበት አጣብቂኝ (ጌታቸው አስፋው)

ሥርዓቱ የገባበት አጣብቂኝ (ጌታቸው አስፋው)

ሀ.) የፖለቲካ አጣብቂኝ
***

ኢሕአዴግ ብዙ እውነት ያልሆኑ ነገሮችን ለአዲሱ ትውልድ ስለነገረ በጊዜው የነበርን ሰዎች እውነቱን ተናግረን ወጣቱ በሐሰተኛ ወሬ ውዥንብር ውስጥ እንዳይገባና እንዲያገናዝብ ልንረዳው ይገባል፡፡ አውራ የሆነው የሐሰት ወሬ ደግሞ ደግሞ ከሃያ ሰባት ዓመት በፊት ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ባይቆጣጠር ኖሮ አገሪቱ በብሔረሰብ ብጥብጥ ልትፈራርስ ተቃርባ ነበር የሚለው ነው፡፡ የኢሕአዴግ አባላት ዓይናቸውን በጨው አጥበው ሚዲያ ላይ ቀርበው እኛ ባንገባ ኢትዮጵያ ልትፈራርስ ተቃርባ ነበር ብለው እንደሚናገሩ በቅርቡ በፓርቲያቸው አስገዳጅነት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰብሳቢነትና ከሚኒስትርነት ቁልቁል ወርደው አምባሳደር ሆነው ወደሚጠሉት ኒዮ-ሊብራሎች አገር ኑሮን ለመጋራት ሊሄዱ እንደተነሱ ለ‹ኢ ኤን ኤን› ጋዜጠኛ ቃለ ምልልስ ከተናገሩት ከአቶ ካሳ ተክለብርሃን አንደበት ነው የሰማሁት፡፡

ከ1950ዎቹ በፊት ስለነበረው በዓይን አይቼ ስለማላውቅ ከዚያ በኋላ በተወለድኩበት ከፋ ጠቅላይ ግዛት የማውቀውን እጽፋለሁ፡፡ የዚያን ዘመን ኢትዮጵያ በባላባታዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት የምትተዳደር መሆኑን እና ባላባቶቹ ተወላጆቹ ነበሩ ወይንስ መጤዎች ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት የኢሕአዴግን በሬ-ወለደ የፈጠራ ወሬ ያከሽፋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከፋ ጠቅላይ ግዛት የዛሬን ሁለት ክልሎች ከደቡብ ከዳውሮ እስከ ከፋና ማጂን፣ በሰሜን የምን፣ ከአሮሚያ የጂማ አውራጃን፣ ያካለለ ነበር በ1950ዎቹ የጠቅላይ ግዛቱ ዋናው ባለሥልጣን የንጉሠ ነገሥቱ እንደራሴ የነበሩት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ ነበሩ፡፡ በ1960ዎቹ ደግሞ አማራው ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁሥላሴ ተተኩ፡፡ የጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ የነበረችውን የጂማ አውራጃን ከነ ወረዳዎቿ በበላይነት ያስተዳደሩት የአባ ጂፋር ልጅ ደጃዝማች አባ ጀበል አባ ጂፋር ነበሩ፡፡ በወረዳ አስተዳዳሪነትና በልዩ ልዩ የመንግሥት አካላት ውስጥ በአብዛኛው የአማራ ተወላጅ የሆኑ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከምስለኔ ወይም ምክትል ወረዳ አስተዳዳሪነት ጀምሮ ወደታች እስከ አጥቢያና መንደር መሪዎች የነበሩት የአካባቢው ተወላጆች ባላባቶችና በጂማ አውራጃ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ የሥልጣን ምንጭ ወደላይ ማንበብና መጻፍ ዕውቀት ሲሆን ወደታች የአካባቢ ተወላጅነትና ባላባትነት ነበር፡፡

የጭቆና ዋናው ምንጭ የሆነው የመሬት ሥሪት የሚተዳደረው በየአካባቢዎቹ ባላባቶች ቢሆንም ግብረጠል እየተባለ ግብር ያልተከፈለበትን ሰፋፊ መሬት ከመንግሥት በግዢና በስጦታ እየወሰዱ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ሰዎች ሰፋፊ መሬት ይዘው ነበር፡፡ ደርግ ሥልጣን እንደያዘ የመሬት ይዞታውን ጉዳይ ቢፈታውም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አስተዳደሩ በማንበብና በመጻፍ ችሎታ ላይ ስለሚመሠረት ቅድሚያ ያገኙት ፊደል የቆጠሩት ከየትም ቦታ የመጡ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ስለዚህ ደርግ ሁኔታውን ለመለወጥ የወሰደው እርምጀ የጎልማሶች ትምህርትን እና መሠረተ ትምህርትን አስፋፍቶ የአካባቢው ተወላጆች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባለሥልጣን እንዲሆኑ ነበር፡፡ ለዚህ ሥራውም ከዩኔስኮ ሽልማት አግኝቷል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበርኩበት ከ1960 ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አመጽ በመደገፍ የትግል አጋር ብንሆንም ትምህርቴን እስከመሰዋት የተማሪዎች ትግል እንቅስቃሴ አካል የሆንኩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁበት ከ1964 ጀምሮ ነው፡፡ ውስጥ ውስጡን ማርክሲዝምን ሌኒኒዝምን ያነቡ የነበሩት መሪዎቻችን እነ ዋለልኝ መኮንን ዓላማቸው ለብዙሃኑ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ምሥጢር ቢሆንም መላውን ተማሪ በአንድ ዓላማ ያሰባሰበው ከላይ የገለጽኩት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥልጣን በጥቂት የሸዋ መኳንንት መያዙ እና መሬት በባላባቶች መያዙ ነበር እንጂ የብሔረሰብ ጭቆና ጥያቄ አልነበረም፡፡

ከ1964 እስከ 1967 በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ገባ ወጣ እያልኩ ቆይቼ ሶቭየት ኅብረት ትምህርቴን ለመከታተል የሄድኩት በ1970 ነበር፡፡ እዚያ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጥቂት መንግሥትን የሚደግፉ ተማሪዎች በመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ዙሪያ የተሰባሰቡ ሲሆን ከዘጠና በመቶ በላይ የሆነው ተማሪ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓን) በሚደግፈው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ጥላ ሥር የተሰባሰበ ነበር፡፡ በ1970 አጋማሽ ላይ ግን አንድ እንግዳ ነገረ ተከሰተ፡፡ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር አባል የነበሩት የትግራይ ተወላጆች የራሳችንን ማኅበር አቋቁመናል ብለው ከማኅበሩ ስብሰባ መቅረታቸው ነበር፡፡ ከዚያ በፊትና እስከ 1983 ኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ ጥያቄ እንጂ እዚህ ግባ የሚባል የብሔረሰብ ትግል እንዳልነበረ ኮሎኔል መንግሥቱ በ1982 ከኢሕአዴግ ጋር እንዲደራደሩ ሲጠየቁ “ኮረብታ የያዘ ሺፍታ እንደራደር ብሎ በላከብኝ ቁጥር ለስብሰባ የምቀመጥ ሰው አይደለሁም በማለት” የተናገሩት ማስረጃ ነው፡፡ በስም ይታወቅና በውጭ አገር ይንቀሳቀስ የነበረው ኦነግ ሲሆን እሱም እስከዛሬም እየታገለ ያለና ዛሬም ቢሆን የኢሕአዴግ መንግሥት የብሔረሰብ ነፃነት ታጋይ ሳይሆን አሸባሪ ቡድን ብሎ የፈረጀው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከመግባቱ ከሃያ ሰባት ዓመት በፊት ኢትዮጵያዊነትን ሊያፈራርስ ተቃርቦ ነበር የተባለው ኦነግ እንዴት ነው እስከ አሁን ድረስ ከተራ አሸባሪነት ያልወጣው፡፡

ከዚያ በፊትም ቢሆን የንጉሠ ነገሥቱን አገዛዝ ተቃውመው በጎጃም፣ በባሌ፣ በወሎ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ በማይጨው ቀዳማይ ወያኔ፣ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥም ደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋርያት ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሰበታ ሲሄዱ ፈንጂ አጥምደው ሊገሏቸው እንደ ነበረ ይታወቃል፡፡ የነጄነራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥትም ዘውዳዊ-ባላባታዊ ሥርዓቱን ለማስወገድ የተደረገ ነበር፡፡ በማኅበር ስም ውስጥ ውስጡን የሚታገሉ እንደ የሜጫ ቱለማ ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንደነበሩም አይካድም፡፡ እነኚህ ሁሉም በንጉሠ ነገሥቱና በባላባታዊው ሥርዓት ላይ የተነሱ አመጾች እንጂ አገር የሚያፈራርሱ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቶች አልነበሩም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ነው፡፡ ከቤተሰቦቻቸው በስተቀር መቶ በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በቅርቡ ከሐራሬ ጽፈው በላኩት መጽሐፍ በአባታቸው የበቾ ኦሮሞ እና በእናታቸው የተጉለት አማራ መሆናቸውን ሳያነብ በፊት ዐሥራ ሰባት ዓመት ሙሉ የመሩት ኮሎኔል መንግሥቱ እንኳ ብሔረሰባቸው ምን እንደሆነ አያውቅም ነበር፡፡ መጠርጠር የፈለጉ አንዳንድ ሰዎች ጂማ ሚያዝያ ሃያ ሰባት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለተማሩ፤ በቀድሞ አጠራሩ በከፋ ጠቅላይ ግዛት ሥር በነበረ ዛሬ በደቡብ ክልል በሚገኝ ጊሚራ የሚባል ስፍራ ተወላጅ እንደሆኑ ነበር የሚገምቱት፡፡ የማሸነፋቸውንም ምክንያት ኢሕአዴጎች አዛብተው ነው የሚያቀርቡት፡፡

ኮሎኔል መንግሥቱ ሶሻሊዝምን በመከተላቸው አሜሪካኖችን ከማስቀየማቸውም በላይ ፕሬዚዳንታቸው ሮናልድ ሬጋን የሊቢያን ቤተመንግሥት በቦምብ በመደብደባቸው ራምቦ ስታይል ጀብደኝነት ብለው ተወዳጅ መሪያቸውን አንቋሸው አናደዋቸው ስለነበር ለበቀል እነ ኸርማን ኮኸን እነ ጂሚ ካርተር ከወያኔ ጋር በምሥጢር ዶልተውባቸው ነው የጣሏቸው፡፡ ሌላው የመሸነፋቸው ምሥጢርም ሶቭየት ኅብረትና የምሥራቁ አጋሮቻቸው ከመፈራረሳቸውም በላይ ኮሎኔል መንግሥቱ ጓደኞቻቸውን ጄነራሎች በመግደላቸውም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ግፍና በደል በመፈጸማቸውም ጊዜና ሕዝብ ከድቷቸው ነው ኢሕአዴግ እጅ ላይ የወደቁት፡፡

ኢሕአዴጎች በዚያን ዘመን ያልተወለዱትን የዚህ ዘመን ወጣቶች ልብ ለመግዛት የሚሞክሩት እኛ በ1983 በቶሎ ባንደርስ ኖሮ አገሪቱ የመፈራረስ ጫፍ ላይ ደርሳ ነበር ብለው ነው፡፡ በአሜሪካ አጋፋሪነት በሻዕብያ የጦር ኃይል ድጋፍ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በውጭ አገር ስደት ላይ የነበሩ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን አሰባስበው በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን አቋቋሙ፡፡

የዛሬ የኢሕአዴግ ነባር ታጋዮችን ጨምሮ የ1960ዎቹ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዋነኞቹ የሕዝብ ጠላቶች ናቸው ያልናቸው የአካባቢ ተወላጆች የሆኑ ባላባቶችና ፊደል በመቁጠራቸው የመንግሥት ሥልጣንን አንቀው የያዙት የሸዋ መኳንንትን ነበር፡፡ ኢሕአዴግም ራሱ አንዳንዴ እየተሳሳተ የጥቂት ባላባቶች ጭቆና እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ ጭቆና አልነበረም ይላል፡፡ ኢሕአዴግ እንደሚለው አገር ሊያፈራርስ የደረሰ የብሔረሰብ ትግልና ግጭት ከነበረ መላው የአገሪቱ ወጣት በሁለት ጎራ ተከፍሎ በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ስም ደም አፋሳሽ ትግል ያካሄደባቸው በወለጋው ታጋይ በኃይሌ ፊዳ በሚመራው መኢሶን እና በትግሬው ብርሃነመስቀል ረዳ በሚመራው ኢሕአፓ ጥላ ሥር እንዴት ሆነ? ደም አፋሳሽ የብሔረሰብ ግጭት ያኔ ከነበረ ለምን እንደ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ለታሪክ አልተመዘገበም? ዛሬ የተገባው ቀውስ ውስጥ የተገባው የኢሕአዴጎች የሐሰት ወሬ ወደኋላ ተኩሶ ነው፡፡

ለ.) የኢኮኖሚ አጣብቂኝ
***

ኢሕአዴግ በረሃ ሲወጣ በየአካባቢው በነበሩ ተወላጅ ባላባቶች ላይ እና ፊደል በመቁጠራቸው የመንግሥት ሥራን አንቀው በያዙ የሸዋ መኳንንት ላይ ቂም ይዞ ነበር የወጣው፡፡ ሲመለስ ግን ደርግ በመሬት ለአራሹ አዋጁ የጪሰኛና ባላባት ግንኙነቱን በጣጥሶ መሠረተ ትምህርትን በማስፋፋት በመንግሥት መሥሪያ ቤት የሸዋ መኳንንት ተጽዕኖንም አዳክሞ ቆየው፡፡

ኢሕአዴግ ቂሙን ወደ ሌሎች አዞረ፡፡ ቂም ከያዘባቸው ወገኖች ደግሞ እኛ በረሃ ለበረሃ ስንንከራተት አርፈው ትምህርታቸውን ተማሩ ባላቸው ምሁራንና ለጦሩ ስንቅ አቀብለዋል ባላቸው የከተማ ኗሪዎች ላይ ነበር፡፡ ሥልጣን ከጨበጠ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርባ መምህራንን አባረረ፡፡ የመጀመሪያው የኢሕአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ላይ ስታዲዮም የአዲስ አበባ ሕዝብ ስላጉረመረመ በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባ ሕዝብ አቶ ታምራት ላይኔን ስለጠላቸው አይገርመኝም ቢወዳቸው ነበር የሚገርመኝ አሉ፡- የአዲስ አበባ ሕዝብ የምሁሩ ክፍል ስለሆነ የኢሕአዴግ ታሪካዊ ጠላት መሆኑን ሲገልጹ፡፡ ቀጥለውም ሊስትሮም ቢሆን በፖለቲካችን ከተጠመቀ ሚኒስትርነት እንሾመዋለን አሉ፡፡ በዚህም አቶ መለስ “በየአንዳንዱ የመማሪያ መጽሐፍ ላይ ብትማሩ ብትመራመሩ የጠሏችሁ ይወዷችኋል የናቋችሁ ያከብሯችኋል” የሚል መልዕክት ያስተላልፉ ከነበሩት ከአፄ ኃይለሥላሴ በጣም ተለይተዋል፡፡ ኢሕአዴጎች በምሁር ላይ ቂም በያዘ ልባቸው አሁን አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸውን እርምጃም ወስደዋል፡፡ ይኸውም የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅን ከፍተው እየተማሩና እየሠሩ ነባሩን ምሁር ማስወገድ ነበር፡፡

ከብዙ ጸሐፍት መካከል ሀዲስ ዓለማየሁ በፍቅር እስከመቃብር ገጸባሕርይ የፊታውራሪ መሸሻ ንግግር ሥርዓተ ማኅበሩን የገለጹባቸውን ወጎች እጅግ አድርጌ አደንቃለሁ፡፡ “ብዙ ከብት አርብቶ አቱን እየጠጣ ቦርጩን ቀፍትቶ በደምና በአጥንት የመኳንንት ዘርነት ያልወረሰውን እንደኛው ግራዝማች፣ ቀኛዝማች፣ ፊታውራሪ ተባለና ልጅህን ለልጄ አለኝ” አሉ ፊታውራሪ መሸሻ በአንዱ ጊዜ ያነሳው የቀኛዝማች ባለማዕረግ አሹፈው የጭሰኛ-ባላባታዊ ሥርዓቱን መደባዊ ክፍፍል ሀዲስ ዓለማየሁ በቀልድ ወግ ሲያጋልጡ፡፡ ሀዲስ ዓለማየሁ ከዘውዳዊው መንግሥታዊ ሥርዓት ሹመትና ማዕረግ ያገኙ ምሁር የጎጃም አማራ ተወላጅ ነበሩ፡፡ ግን ገዢው የእኔ ብሔረሰብ ነው ብለው አላቀነቀኑም፡፡ እነ አቤ ጉበኛም አላቀነቀኑም፡፡ ለብሔረሰቡ ያቀነቀነ የዚያን ዘመን ምሁርም አላውቅም፡፡

ኢሕአዴጎች የሚኒስትርነትና የከፍተኛ ሥራ ኃላፊነት ሥራቸውን ወዝፈው እየተማሩ እንደ አዲስ ዓለማየሁ ዘመን ግራዝማች ቀኛዝማቾች በደምና በአጥንታቸው የዕውቀት ዘር ሳይኖር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ቢጭኑም ሣር ቅጠሉ ዶክተር ፕሮፌሰር ቢባልም የዚህች አገር ኢኮኖሚ አካሄድ አልገባቸውም፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛዬ ስለ መምራትና ስለ ማስተዳደር ምሥጢር ሲነግረኝ አንድ ጨቅጫቃ አባ ወራ ባለቤቱን ለአስቤዛ የሰጠሁሽን ብዙ ገንዘብ እንዴት ጨረስሽው እያለ ይጨቀጭቃት ነበር፤ እማወራዋ በማግባባት አንተ አስቤዛውን ግዛና አቅርብልኝ እኔ ልሥራው አለችው፤ አባ ወራውም እሺ ብሎ የወሩን አስቤዛ በዐሥራ አምስት ቀን ጨርሶ ብድር እና ልመና ውስጥ ገባ፤ ባለቤቱን ይቅርታ ጠይቆም ወደ ቀድሞው ወደ ቤቱን መምራት ሥራው ተመለሰ፡፡

የገበያ ኢኮኖሚ አመራርና የልማት ኢኮኖሚ አስተዳደር የተለያዩ ናቸው፡፡ የገበያ ኢኮኖሚ አመራር ከውጭ ሆኖ በፖሊሲ መልክ ማስያዝ ሲሆን የልማት ኢኮኖሚ አስተዳደር ግን በውስጥ ሆኖ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን መቆጣጠር ነው፡፡ መሪ (Leader) አመልካች ጠቋሚ ሲሆን አስተዳዳሪ (Manager) አደራጅ ናቸው፡፡ ስለሆነም በገበያ ኢኮኖሚ መንግሥት ኢኮኖሚውን ይመራዋል፤ አያስተዳድረውም፡፡ በልማት ኢኮኖሚ መንግሥት ኢኮኖሚውን ያስተዳድረዋል፤ አይመራውም፡፡ በቅይጥ ኢኮኖሚ መንግሥት ገበያውን እየመራ ልማቱን ያስተዳድራል፡፡ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት መንግሥታትም ኢኮኖሚያቸውን ቅይጥ ኢኮኖሚ በማድረግ መርተዋልም አስተዳድረዋልም፡፡

የገበያ ኢኮኖሚን መምራት ማለት የሥራ አጥነት እንዳይከሰት፣ የሸቀጦች ዋጋ እንዳይንር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳይገጥም እና ኢኮኖሚው እንዲያድግ በፖሊሲ አረጋግቶ መምራት ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴጎች ያቃታቸውም ይኽ የገበያ ኢኮኖሚውን መምራት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የገበያ ኢኮኖሚውን አሠራር አጥንቶና ተስማሚ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ነድፎ መምራት ትቶ በልማት ስትራቴጂና ፕሮጀክቶች አተገባበር ላይ ብቻ በማትኮሩና ከአቅሙ በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ለመሥራት በመሞከሩ የኢኮኖሚ ልማት አስተዳደርን ከገበያ ኢኮኖሚ አመራር ጋር አጋጨው፡፡

የገበያ ኢኮኖሚ አመራር በባለሙያ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ የልማት ኢኮኖሚ አስተዳደር በሕዝብ ተሳትፎ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ለታዳጊ አገር ዕድገት ሁለቱ መመጣጠን አለባቸው፡፡ ወደ አንዱ ብቻ ማዘንበል ኢትዮጵያ ዛሬ የገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያ ስሌታዊ ቴክኒኩን እስኪረሳ ድረስ በተሳትፏዊ የልማት ዲስኩር ላይ ብቻ ከተመረኮዘ ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ሙያዊ ሥራ አይሠራም፡፡ በሙያ የሚሠራ የገበያ ኢኮኖሚ አመራር የሥራ መሣሪያ የጭንቅላት ስሌት ነው፤ በተሳትፎ የሚሠራ የልማት ኢኮኖሚ የሥራ መሣሪያ የአፍ ልፍለፋ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ሃያ ሰባት ዓመታት ያለ በቂ ፖሊሲ ተጉዞ በሞተ ሰዓት አሁን በንግድ ባንኮች ላይ ለዚህ ዘርፍ ይኽን ያህል ትሰጣላችሁ እያለ ራሽን መደልደል ትዕዛዝና ቁጥጥር ማብዛቱ ውድቀትን የሚያመለክት ነው፡፡ የገበያ ኢኮኖሚ በሽታ በትዕዛዛዊ የልማት ኢኮኖሚ ሊታከም እንደማይችል አሁንም አላወቀም፡፡

ይኽ በልማት አስተዳደሩ ላይ ከልክ በላይ ማትኮርና የገበያ ኢኮኖሚውን በፖሊሲ አለመምራት ግጭት ፈጥሮ ከ2008 እስከ 2010 የተራዘመ ሁከትና ብጥብጥ ተከስቷል፡፡ የገበያ አመራርና የልማት አስተዳደር ግጭቱ በጊዜ ካልተስተካከለ፣ ኢሕአዴግ ከወረደበት የልማት አስተዳደር ከፍ ብሎ የገበያ ኢኮኖሚውንም በፖሊሲ ካልመራው ኢኮኖሚው ከገባበት ቀውስ አይወጣም፡፡ ረብሻውና ብጥብጡም ሊቆም አይችልም፡፡