ኮማንድ ፖስቱ ለጠቅላይ ሚኒስተሩና ለፖለቲካው አመራር ሪፖርት አላቀርብም ማለቱ ተሰማ።

 

ኮማንድ ፖስቱ ለጠቅላይ ሚኒስተሩና ለፖለቲካው አመራር ሪፖርት አላቀርብም ማለቱ ተሰማ።

 

በፓርላማ ውድቅ የተደረገው ነገር ግን ህወሃት በጉልበት ያጸደቀው የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገበት የካቲት 9/2010 ዓ.ም ጀምሮ አገራችን ሙሉ በሙሉ በወታደራዊ አገዛዝ ስር ወድቃ እየማቀቀች እንደሚገኝ ይታወቃል። በመሆኑም ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በበላይነት የሚያስፈጽሙትና የሚቆጣጠሩት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፣የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቱ፣ የመከላከያ ሚኒስተሩ፣ የመከላከያ ኢታማዦር ሹም እንዲሁም የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ናቸው።

በዚህም መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተገኙ ውጤቶች፣ የጠፉ ጥፋቶች፣በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም እንዲገመገሙ በየቀጠናው የተሰበሰቡ መረጃዎች ተጠቃለው ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ዝርዝር ሪፖርት እንዲደረግ ያዛል።

ይሁን እንጂ ኮማንድ ፖስቱን በበላይነት የሚቆጣጠሩት የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዦች የሆኑት የህወሃት ወታደራዊ አዛዦች ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዝርዝር መረጃ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በመላ አገሪቱ ስለታሰሩት ዜጎች ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ለዶ/ር አቢይ አህመድ እንዲሁም ለፖለቲካው አመራር ሪፖርት አናደርግም ማለታቸውን የመረጃ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

የመረጃ ምንጮቻችን አክለው የህወሃት ሰዎች ለዶክተር አቢይ ሪፖርት ብናቀርብ ነገሮችን ያበላሽብናል ብለው መስጋታቸውን አብራርተዋል። በተለይ ጄነራል ሳሞራ የኑስ <<ትላንት ለእኔ በተጠንቀቅ ሰላምታ ይሰጠኝ ለነበረ ለአንድ ተራ ወታደር ዛሬ ገና ለገና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ብየ ሪፖርት አላቀርብም >> ሲል መናገሩ ተከትሎ ሁኔታው ዶ/ር አቢይ አህመድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ያበላሽብናል ከሚል የመነጨ ብቻ ሳይሆን ከነሳሞራ አንሸነፍም ባይነት እንዲሁም የመታብይና የበታችነት ስሜት የተቀዳ መሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል። በዚህም ምክንያት በእነሳሞራ በአጠቃላይ በህወሃት ሰዎች ጥርስ ውስጥ የገቡት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው ከተሰየሙ ከመጋቢት 24 ጀምሮ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስተሩ አልቀረበም ተብሏል።

በህገመንግስቱ መሰረት አንቀጽ 74 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የጦር ሃሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው ይላል። ስለሆነም የመከላከያ ሰራዊቱ ኤታ ማዦር ሹም ዝርዝር ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስተሩ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ያስገድዳል። ነገር ግን ህወሃት ህግ የሚያወጣው እራሱ እንዲገዛበት ሳይሆን ሰዎችን እያስፈራራ ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት እንዲያመቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ለዚህም ነው ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዝርዝር አፈጻጸምና ስለታሰሩ ሰዎች ሪፖርት አላቀርብም ያለው ሲሉ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት እየገለጹ የሚገኙት።

በተጨማሪም ዶክተር አቢይ በበአለ-ሲመታቸው እለት <<በተለያየ ጊዜ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቦርቁ ህይወታቸውን ለተቀጠፉ ለውጥ ፈላጊዎች፣ ለስነልቦናና ለአካል ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ>> በማለታቸው የመከላከያ ያሉ የህወሃት የጦር አዛዦችን በጣም ማስቆጣቱን ከመከላከያ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በዚህም ምክንያት እነሳሞራ የኑስ እንዲህ አይነት አቋም ላለውና እኛን ሆንብሎ በህዝብ ለማስጠላት ለቆመ ጠቅላይ ሚኒስተር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተመለከተ አፈጻጸምም ሆነ፣ ስለታሰሩ ሰዎች እንዲሁም እርምጃ ስለተወሰደባቸው አካላት ምንም አይነት ሪፖርት ላለመስጠት እያንገራገሩ እንደሚገኙ ታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመከላከያ ውስጥ ጄነራል ሳሞራ ከስልጣኑ ይነሳል በማለት በሰፊው እየተወራ እንደሆነ ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።

ESAT የጸጥታ ኃይሎች እና ማህበረሰብ

የጸጥታ ኃይሎች ዜና (ሚያዚያ 13, 2010 ዓ.ም)