ጥሬ ገንዘብ አሠራር ፤ አቶ ጌታቸው አስፋው (የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

ጥሬ ገንዘብ አሠራር
***

አቶ ጌታቸው አስፋው

(የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)


***

በሳለፍነው ሩብ ምዕተ ዓመት እንደ የዋጋ ንረት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያሰቃይ የኖረ ነገር የለም፡፡ የዋጋ ንረት ብዙ አቅመ ደካሞችን አስለቅሷል ብዙ ወጣቶችን አገር አስለቅቆ አስኮብልሏል፡፡ ብዙዎች የዋጋ ንረት የነጋዴ ስግብግብነት ይመስላቸዋል፡፡ የዋጋ ንረት የነጋዴ ስግብግብነት ብቻ ከሆነ ሁላችንም ስግብግብ ነን ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ያለንን ነገር ሽጠን የምንፈልገውን ሸቀጥ የምንገዛበትን ጥሬ ገንዘብ የምናገኝ ነጋዴዎች ነን፡፡ ራሳችንን ስግብግብ ከማድረጋችን በፊት የዋጋ ንረት ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ማወቅ ይጠቅማል፡፡

በእርግጥ ማንኛውም ነጋዴ በጥሬ ዕቃ ዋጋ ጭማሪ፣ በመንግሥት ግብር ጭማሪ፣ በደሞዝ ጭማሪና በሌሎች ምክንያቶች የጨመረበትን የማምረቻ ወጪ ወደ ሸማቹ ያስተላልፋል፡፡ የቀን ሙያተኞች ዋጋ ሲዋዋሉ ለድርድር የሚያቀርቡት በሆቴል ቤት የምግብ ዋጋ መጨመሩን ነው፡፡ የሌሎች ሸቀጦችን ዋጋ ጭማሪ መነሻ በማድረግ በመሸጫ ሸቀጥ ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ምክንያቶች ሁለተኛ ደረጃ ምክንያቶች ናቸው፣ ዋናውና አንደኛ ደረጃ የዋጋ ንረት ምክንያት በገበያው ውስጥ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን መብዛት ነው፡፡

የዋጋ ንረት ማለት በእያንዳንዱ ሰው ኪስ ውስጥ ብዙ ጥሬ ገንዘብ ማስቀመጥ ማለት ነው፣ የጥሬገንዘቡ የመግዛት አቅም መቀነስ ማለት ነው፡፡ ብዙ ብሮች ጥቂት ሸቀጦችን ያስድዳሉ ማለት ነው፡፡ ይኽ ነው ዋናውና የመጀመሪያው የዋጋ ንረት ምክንያት፡፡ ሌሎቹ ሁሉ ኹለተኛና ሶስተኛ ምክንያቶች ወይም ውጤቶች ናቸው፡፡ ጥሬ ገንዘብን የሚያሰራጩት እንማን ናቸው ለምንስ ነው ኑሮን በሚያንር ደረጃ ብዙ ጥሬገንዘብ የሚያሰራጩት፣ ብዙ ጥሬገንዘብ አሰራጭተው ኑሮን እንዳያስወድዱ የሚቆጣጠራቸው አካልስ የለምን፡፡

ጥሬ ገንዘብን ፈጥረው ወደ ገበያ ውስጥ የሚያሰራጩት ብሔራዊ ባንክ እና ንግድ ባንኮች ናቸው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ምንዛሪዎችን አትሞ ወደ ገበያ ያሰራጫል፡፡ ንግድ ባንኮችም ከቆጣቢ አስቀማጮች ያገኙትን ምንዛሪዎች መሠረት በማድረግ ምንዛሪዎች ሳይንቀሳቀሱ በግለሰቦች ሒሳብ ውስጥ ቁጥሮችን በመመዝገብ ብቻ አገበያይተው በገበያ ውስጥ የገባውን ጥሬ ገንዘብ ብዙ ጊዜ እጥፍ አድርገው በማርባት ለተበዳሪዎች ይሰጣሉ፡፡

ሸቀጥ የተገበያዩ ሰዎች ገዢ ለሻጭ የሸቀጡን ዋጋ ከንግድ ባንኩ እንዲወስድ ቼክ ጽፎ ሲሰጠው የሸቀጡ ሻጭ ቼኩን ለገዚው ንግድ ባንክ አቅርቦ የገዢው ንግድ ባንክም ለሻጩ ምንዛሪዎችን በመክፈል ፋንታ በባንክ ሒሳቡ ውስጥ ክፍያውን ሲያስተላልፍለት ምንም ዓይነት ምንዛሪዎች መቀባበል ሳይኖር ግብይይት ተፈፀመ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የንግድ ባንኮች ተቀማጮችም እንደ የክፍያ መሣሪያ ወይም ጥሬ ገንዘብ የሚቆጠሩት፡፡ ስለዚህም ጥሬ ገንዘብን በማብዛት ንግድ ባንኮችም ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡

ከብሔራዊ ባንኩ ይልቅ ከፍተኛውን የጥሬገንዘብ አቅርቦት ድርሻ የሚይዙት የቆጣቢዎችን የቁጠባና የጊዜ ተቀማጭ ብዙ ጊዜ የሚያረቡት ንግድ ባንኮች ናቸው፡፡ አዳዲስ ንግድ ባንኮች ሲከፈቱና ባሉት ንግድ ባንኮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲከፈቱ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠኑ ይጨምራል፡፡ ሆኖም ግን ለንግድ ባንኮች የማበደርን አቅም የሚፈጥሩት ብሔራዊ ባንክ ያለገደብ የሚያትማቸው የጥሬገንዘብ የጀርባ አጥንት የሆኑት ምንዛሪዎች (Currency) ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ባንክ አገልግሎት ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋር እንኳ ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የባንኮች መስፋፋት ቀጥሎ የገጠሩ ሕዝብ የባንክ ተጠቃሚ ሲሆን የጥሬገንዘብ አቅርቦትም ጨምሮ አሁን ሰማይ ሊነካ ጥቂት የቀረው የሸቀጦች ዋጋ የት ይደርስ ይሆን የሚለው ጥያቄ ለድሃ ኢትዮጵያዊ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ የሚያሰራጫቸው የምንዛሪ ጥሬ ገንዘቦች እና ንግድ ባንኮች የሚፈጥሩት የብድር ጥሬ ገንዘቦች እንዲሁም ጠቅላላው ጥሬገንዘብ ከ2000 እስከ 2008 በነበሩት ጊዜያት በምን ያህል ፍጥነት እንዳደጉ ብሔራዊ ባንክ በሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ሪፖርቶች ውስጥ ልናይ እንችላለን፡፡

በ2000 ከጠቅላላው ጥሬ ገንዘብ ውስጥ ሃያ ስድስት በመቶ ድርሻ የነበረው አስራ ስምንት ቢልዮን ብር ምንዛሪ በብሔራዊ ባንክ ተሰራጭቶ በገበያ ውስጥ የተዘዋወረው የብርና ሣንቲሞች ጥሬገንዘብ በ2008 መጠኑ አድጎ ስልሳ ሰባት ቢልዮን ቢሆንም ድርሻው ግን ወደ ዐሥራ አምስት በመቶ ዝቅ ሲል በአንጻሩ በ2000 ድርሻው ሰባ አራት በመቶ የነበረው ሐምሳ ቢልዮን ብር የንግድ ባንኮች ተቀማጭ በ2008 ወደ ሦስት መቶ ሰባ ስምንት ቢልዮን አድጎ ድርሻውም ሰማንያ አምስት በመቶ ሆኗል፡፡

የሁለቱ የምንዛሪና የተቀማጭ ድምር ሆኖ ጠቅላላው በገበያ ውስጥ የተሰራጨው የጥሬገንዘብ ብዛትም በ2000 ከነበረበት ስልሳ ስምንት ቢልዮን ብር በስድስት ተኩል እጥፍ ጨምሮ በ2008 አራት መቶ አርባ አምስት ቢልዮን ብር ደርሷል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሚያሰራጫቸው ምንዛሪዎች በሶስት ነጥብ ሰባት እጥፍ ሲያድጉ የንግድ ባንኮች ተቀማጮች በስምነት ነጥብ ስድስት እጥፍ አድገዋል፡፡

ጥሬ ገንዘብ ሰዎች ዋጋን ይተምንልናል፣ ሸቀጦችን ያገበያልናል፣ ንብረታችንን በጥሬነት ለመያዝ ያገለግለናል ብለው አምነው የተቀበሉት በራሱ ምንም ዋጋ የሌለው መንፈሳዊ አሠራር ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ አሠራር የተረዱ ከበሩ ስለመንፈሳዊ አሠራር ያልተረዱ ከሰሩ፡፡ መንግሥትም የተረዱትን ደገፋቸው ያልተረዱትን አሞኛቸው፡፡ መንፈሳዊ አሰራሩን የተረዱት ንግድ ባንኮችና ጥቂት የሸቀጦች ነጋዴዎች በጥቂት ዓመታት ውስጥ ናጠጡ፡፡

በርግጥ ምንዛሪዎች ብሮችና ሣንቶሞች ስለሆኑ የሚታዩና የሚዳሰሱ ነገሮች ናቸው:: የባንክ ተቀማጮችም በደንበኛው ሒሳብ ውስጥ የሚመዘገቡ ቁጥሮች ስለሆኑ ይታያሉ፡፡ ዋጋቸውና ሸቀጥን የመግዛት አቅማቸው ለምን ያን ያህል ሆነ ብሎ መናገር ስለማይቻል ነው በእምነት ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ አሠራር ነው የሚባለው፡፡

በቀድሞ ጊዜ ብሔራዊ ባንኮች ምንዛሪዎችን አትመው ሲያሰራጩ ለዋስትና ያሰራጩትን ምንዛሪ የሚያክል ወርቅና ብር ማስቀመጥ ይገደዱ ነበር:: ስለዚህም ከዋስትናው በላይ ምንዛሪ ማተም ስለማይችሉ ገበያ ውስጥ የሚዘዋወረው ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ በሕግ የተገደበ ነበር፡፡ በዛሬ ጊዜ ግን ብሔራዊ ባንኮች ካለ የወርቅና የብር ዋስትና በሕዝብ አመኔታ ብቻ የፈለጋቸውን ያህል ምንዛሪ አትመው ያሰራጫሉ፡፡ ዋጋ ተወደደብን ብሎ የሚያማርርና የሚጠይቃቸው ሕዝብ ከሌለም ከገደብ ያለፈ ምንዛሪ ያትማሉ፡፡

ይኽንን መንግሥት የፈጠረው መንፈሳዊ አሠራር ሰዎች ተረድተው ጥሬገንዘብ እንዴት ከነርሱ ኪስ ውስጥ ወጥቶ ሌሎች ሰዎች ኪስ ውስጥ እንደገባ አውቀው ስለኑሯቸው ከመንግሥት ጋር ካልተደራደሩ ሸቀጦች እንዳይወደዱብን የጥሬ ገንዘብ ሥርጭቱ በገደብ ይኹን ካላሉ እንዲስተካከል ካልጠየቁ ዘላለም ዓለማቸውን ተጎጂ እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶች ነበሩ በተቋቋምኩ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከሺሕ ተነስቼ ሚልዮኖች ውስጥ ገባሁ ይሉ የነበሩት አሁን ግን ንግድ ባንኮች ሆነዋል በተቋቋምኩ በጥቂት ዓመታት ሚልዮኖችን እና ቢልዮኖችን አተረፍኩ የሚሉት፡፡ ለቆጣቢው ከዋጋ ንረት በታች በሆነ የኪሳራ ወለድ መጣኝ እየከፈሉ እነርሱ የቆጣቢውን ሦስት እጥፍ ወለድ የሞኖፖል ትርፍ ዝቀው ከቢልዮን አልፈው ትሪልየን ውስጥስ ቢገቡ ማን ተቆጣጣሪ አላቸውጿ

ሲጀምሩ በተከራዩት ደሳሳ ጎጆ ሲያገለግሉ የነበሩትና በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ያደጉት የግል ንግድ ባንኮች፣ በአዲስ አበባ የሚያማምሩ ሕንጻዎችን ገንብተዋል ይኸን ያህል ገንዘብ ከየት አገኙ? የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ሰው ቢኖር መልሱ እነርሱ ከብድር ወለድ ከፍተኛ ትርፍ እያገኙ ለቆጣቢው አስቀማጭ ግን የሚከፍሉት ወለድ መጣኝ ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡
ሰዎች በመሠረተልማትና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች መስፋፋት መንግሥታትን ያደንቃሉ፡፡ በግለሰቦች የተሠሩትን ረጃጅምና ውብ ፎቆች አይተው በከተሞች መዋብ ይደነቃሉ፡፡ ባይገነዘቡ ነው እንጂ ማድነቅ ያለባቸው ራሳቸውን ነበር፡፡ የዋጋ ንረቱን በፀጋ ባይቀበሉት ተቃውሞ ቢያነሱ ነጋዴው ከፍተኛ ትርፍ ባያገኝ ኖሮ መንግሥት ያን ያህል ግብር ሰብስቦ ለመሠረተልማት ማስፋፊያ በቂ ጥሬ ገንዘብ ማግኘት አይችልም ነበር፡፡

ብሔራዊ ባንኩ አትሞ የሚያሰራጨውና ንግድ ባንኮች የሚፈጥሩት የብድር ጥሬ ገንዘብ እንዲበዛ የመንግስትም ፍላጎት ነው፡፡ ምክንያቱም ከሠራተኛው የሥራ ገቢም ሆነ ከድርጅት ትርፍ የሚያገኘው የትርፍ ገቢ ሠላሳ በመቶ ተመልሶ የመንግስት ካዝና ውስጥ ስለሚገባም ነው፡፡ ለመንግስት ጥቅሙ በኹለት አቅጣጫ ነው፣ በመጀመሪያ ደረጃ ያለምንም የዋስትና መያዣ ወይም ብር ከማሳተሚያ ወጪ በቀር ምንም ሳያወጣ ብሔራዊ ባንክ በሚያሰራጨው ምንዛሪ በኹለተኛ ደረጃ ግብር ከፋዮች በሚከፍሉት ግብር በሚያገኘው ገቢ ለሕዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያቀርባል፡፡

ከኢሕአዴግ በፊት የነበሩት የኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታት ኢኮኖሚውን ለማስፋፋትና መሠረተልማትን ለመገንባት ሲሉ በዋጋ ንረት ኑሮ እንዲወደድ አልፈለጉም ይኽ የራሳቸው ምርጫ ነበር ወይም ደግሞ ብዙ ጥሬ ገንዘብ አሰራጭተው ዋጋ ቢንር ሕዝቡ ይቃወመናል ብለው ስለፈሩም ይሆናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ የመሠረተልማት ጅማሮ የታየውና እንደ ስልክ፣ ፖስታ፣ የከተማ ውኃ አቅርቦት፣ የመኪና የአየርና የባቡር መንገድ፣ ትምህርት፣ ጤና ጥበቃ ወዘተ የተስፋፉት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትና የመንግሥት በጀት ዛሬ በአንድ ሰው እጅ ያለን ከሚልዮን ብሮች ያልዘለለ ጥሬ ገንዘብ መጠን በሚያክልበት ዘመን ነው፡፡

የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በዋናነት በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛት እንደሆነ ካወቅን ዘንዳ ይህ የጥሬገንዘብ መብዛት ዋጋን እንዴት እንደሚያንር እንመልከት፡፡ የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በሁለት መንገድ ነው አንዱ የሸማቹ የመግዛት አቅሙ አድጎ ለመሸመት ውድድር ውስጥ ሲገባና ውድ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሲሆን ነው፡፡ ሁለተኛው የዋጋ ንረት ምክንያት በአምራቹ ላይ ግብር ወይም የሠራተኛ ደሞዝ ወይም የጥሬዕቃ ዋጋ ጨምሮበት ምርቱን ሲያስወድድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የዋጋ ንረት የተፈጠረው በሁለቱም መንገድ ነው፡፡

ዋናው የትኛው መንገድ እንደሆነ ለማወቅ ጥናት ማድረግ ቢያስፈልግም በዓይን በሚታይ ደረጃ የሸማቹ አቅም ማደግ ዋናው ምክንያት ይመስላል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ከመጠን በላይ ስለጨመረ የሸማቹ ገቢ ከምርታማነቱና ከሚያመርተው ምርት ዕድገት በላይ አድጎ ነው፡፡ ሸማቹ በሚያገኘው የገቢ ዕድገት ልክ ምርቱና ምርታማነቱም ጨምሮ ቢሆን ኖሮ የምርት አቅርቦትም አብሮ ስለሚጨምር ዋጋ ይኽን ያህል አይወደድም ነበር፡፡

ገበያ ውስጥ በተሠራጨው ጥሬ ገንዘብ መብዛት ምክንያት የሸማቹ ገቢ ጨምሮና የመግዛት አቅሙ አድጎ የበለጠ ለመሸመት በመሻቱ፣ የሸቀጥ ፍላጎት ከሸቀጥ ከአቅርቦት በመብለጡ የሚከሰተው የዋጋ ንረት ፍላጎት ያመጣው ስለሆነ የፍላጎት ስበት የዋጋ ንረት ይባላል፡፡ አምራቾች የጥሬ ዕቃ፣ የሠራተኛ ደሞዝና የግብር ወጪ ሲጨምርባቸው የኸንን ለማካካስ በሸቀጦቻቸው ላይ ዋጋ ስለሚጨምሩ የሚመጣ የዋጋ ንረት የማምረቻ ወጪ ግፊት የዋጋ ንረት ይባላል፡፡ ስለዚህም የዋጋ ንረት በሸማቾች አማካኝነትም ይመጣል በአምራቾች አማካኝነትም ይመጣል፡፡

በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጨመር የፍላጎት ስበት የዋጋ ንረት ምክንያት እና በውጭ ምንዛሪ ተመን የብር ዋጋ መርከስ፣ በንግድ ትርፍ ግብር መጨመር፣ በጥሬ ዕቃ መወደድ በሚፈጠሩ የማምረቻ ወጪ ግፊት የዋጋ ንረት ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እንደሚጨምር ይገመታል፡፡

የዋጋ ንረት የመንግሥት ዓላማ ማሰፈጸሚያ መሣሪያም ነው፡፡ የዋጋ ንረት ሀብታሙ ከድሃው ጥሬ ገንዘብ የሚነጥቅበት ከነጠቀውም ውስጥ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር የሚሰጥበት ስለሆነ መንግሥት ከሀብታሙ የሚሰበስበውን ግብር መጠን ከፍ ለማድረግ ሲፈልግም ሆን ብሎ ጥሬ ገንዘብ በገበያው ውስጥ በመርጨት የዋጋ ንረት ይፈጥራል፡፡

የዚህ ዘመን ሰው ከዋጋ ንረት ጋር አብሮ ስለኖረ የዋጋ ንረትን እንደ ሁሌ የሚከሰት መደበኛና የተለመደ ነገር አድርጎ ቆጥሮታል፡፡ በቀድሞዎቹ መንግስታት ዘመን የኖሩ ሰዎች የሸቀጦች ዋጋ ሳይጨምር ለብዙ ዓመታት ይቆይ እንደነበር ስለሚያውቁ ይኽ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚያዩት የዋጋ ንረት ትልቅ ዱብዕዳ ነው የሆነባቸው፡፡ በተለይም የጡረታ ገቢያቸው ሳይጨምር የሸቀጦች ዋጋ ግን በየቀኑ የሚጨምርባቸው አረጋውያን ዘመኑን እየረገሙ ቀሪው ዕድሜያቸውን በሰቆቃ ይኖራሉ፡፡

ኢኮኖሚስቶች ዋጋን ለማረጋጋትና የሥራዓጥነትን ችግር ለመቅረፍ የገንዘብ አቅርቦቱ በዘፈቀደ በባለሥልጣን ማንአለብኝ ውሳኔ ሳይሆን ከአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ጋር በተገናዘበ ቋሚ መርህ ማደግ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ይኽ መርህ ባለመጠበቁ ባለሥልጣናት ሆን ብለውም ሆነ ሳያውቁ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱን ለገበያው በሚያስፈልገው ልክ ባለመመጠን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዋጋ ንረት ተሰቃይቷል፡፡

የትኛውን የኅብረተሰብ ክፍል በጣም እንደጎዳ ለማወቅ የዋጋ ንረቶች ዓይነት የሸቀጥ ምድቦች ተከፍሎ ይለካል፡፡ የመጀመሪያው ምግብ ነክ ሸቀጦች ሲሆን ኹለተኛው ምግብ ነክ ያልሆኑትን የተመለከተ ነው፡፡ የሁለቱ አማካይ ተወስዶም አጠቃላይ የሸማቾች ዋጋ አመልካች ይተመናል፡፡ የመጀመሪያው ዓይነት የዋጋ ንረት ከገቢያቸው ውስጥ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለምግብና የመሳሰሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚያወጡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች የሚጎዳ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተከታታ ዓመታት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለአጠቃላይ የሸማቾች ዋጋ ንረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርገው የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ነው፡፡

የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን መጠጋትና መምሰል
***

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስለ ምርት ብዙ ተወርቷል ስለግብርናው ምርትና ምርታማነት ስለ ኢንዱስትሪው ምርትና ምርታማነት ስለ አገልግሎት ምርትና ምርታማነት ስለመንገዱ ስለ ሕንፃው ስለተቋማት ስለመሠረተ ልማቶች ስለ አገራዊ ምርት ብዙ ተብሏል፡፡

ስለ ሸመታ ግን ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ የሚመረተው ለማን ነው የተመረተውን የሚሸምተውስ ማን ነው ለመሸመት የሚያስችለውን አቅም ወይም ገቢ ከየት አገኘ፡፡ ስለአምራቹ አውቆ ስለሸማቹ አለማወቅ ከአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታ ውስጥ አንዱን ብቻ አይቶ ሌላውን አለማየት ነው፡፡

አምራቹ የምርት ትዕዛዝ የሚቀበለው ከሸማቹ ነው፣ ሸማቹ ያላዘዘውን ምርት ቢያመርት ገዢ አያገኝም፡፡ አምራቹን በሥራ የሚያሰማራው የሸማቾች ባሕርይ የሸቀጥ ምርጫ እና በገቢያቸው መጠን ያላቸው የመሸመት አቅም ነው፡፡

ሸማቹ ሸቀጦቹን በምን መመዘኛ ነው የሚመርጠው፣ የሸማቾች ምርጫ ነው የሸቀጦችን ዋጋ የሚለዋውጠው ወይስ የሸቀጦች ዋጋ ነው የሸማቾችን ምርጫ የሚለዋውጠው፣ የገቢ መጠን በሸመታ ምርጫ ላይ ምን አስተዋጽዖ አለው፡፡ በሸመታ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ምክንያቶች አሉን ምንና ምኖች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሸቀጦች ሸመታ ምርጫ ድንብ ላይ ችግሮች አሉበትን ካሉበትስ በየትኛው የሀብትና የገቢ መደብ በየትኛው የትምህርት ደረጃ በየትኛው ጾታና በየትኛው የዕድሜ ክልል ይበረታል፡፡ ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤ በሸቀጥ ሸመታ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለን፣ ዘመናዊነትስ፣ የመረጃ ፍሰትስ፡፡ ዓመታት ባስቆጠረ ጊዜ ሠርቶ ለፍቶ ጥሮ ግሮ ሀብት ያገኘና በሻሞ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የከበረ በሸመታ ወቅት እኩል ጥንቃቄ ያደርገሉን፣ እነኚህ ጉዳዮች በኢኮኖሚያችን ውስጥ ፍጹም ያልተዳሰሱ የገበያ ኢኮኖሚ ጣጣ ፈንጣጣ ናቸው፡፡

የገበያ ኢኮኖሚን እየገነባን ለመሆናችን ወይም ነፃ ገበያን መምሰል አለመምሰላችን የሚታወቀው ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች በሚገባ ከተጠኑና ከተመረመሩ በኋላ ነው፡፡ ይኽ ግን በኢትዮጵያ እስከዛሬ ያልተደረገ ከመሆኑም በላይ ለጥናት የሚያመቹ መረጃዎች እንኳ አልተሰበሰቡም፡፡

ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ
***

የሸማቾችን ባሕርይና ለዋጋ ንረት ያላቸውን አስተዋጽኦ በመረጃ መልክ ተጠናቅሮ አናግኘው እንጂ በአዋቂዎች በልጆች በሴቶች በወንዶች፣ በሀብታሞች በድሆች፣ በተማሩ ባልተማሩ፣ በከተሜዎች በገጠሬዎች፣ በላጤዎች በባለትዳሮች ወዘተ. ከፋፍለን የየአንዳንዱን መደብ እንቅስቃሴ በዓን ዓይተን የምናውቀው ነገር አለ፡፡

በ2008 በዐሥራ አንደኛ ዙር የመንግሥት መሬት ሊዝ ሽያጭ በርበሬ ተራ መርካቶ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ጨረታ ሦስት መቶ ሰላሳ ሺሕ ብር ተሰጠ ተባለ፤ በ2009 እዚያው መርካቶ አሜሪካን ግቢ በሃያ አራተኛው የመንግሥት መሬት ሊዝ ሽያጭ ለአንድ ካሬ ሜትር አሸናፊው ድርጅት ሦስት መቶ ሐምሳ አምስት ሺሕ ብር ሲሰጥ ሁለተኛ የወጣውም ለካሬ ሜትር ሦስት መቶ ሐምሳ ሁለት ሺሕ ብር ሰጥቷል፡፡ አቃቂ ቃሊቲም አንድ ካሬ ሜትር ቦታ በሰባ አምስት ሺሕ ብር ሒሳብ ተሽጧል፡፡

የፓርላማ አባላት ደላሎች በቀን ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ዘው ይንቀሳቀሳሉ በማለት በዚህች አገር ውስጥ የአየር በአየር ንግድ ሰውን ከምንም በላይ እያከበረው እንደሆነ ተወያዩበት፣ ምንም ላያደርጉ ተንጫጩበት፡፡ ለሕጻን ልጆቻቸው በሺሕ የሚቆጠሩ ብሮች ሰጥተው ከመምሁሮቻቸው ጋር የሚጋጩ ወላጆች አሉ፡፡

በንግድ ተከብሮ ሚልየነር ቢልየነር ተኮነ በሙስና ተከብሮም ሚልየነር ቢልየነር ተኮነ፣ መሬት ሽጦ ሚልየነር ቢልየነር ተኮነ የጥቂቶች መክበር ሚልዮኖችን ድሃ አደረገ፡፡ አንድ ፍሬ ልጆች ሐምሳ ሺሕ መቶ ሺሕ ለደላላ ከፍለው በበረሃ አሸዋና በባሕር ለመበላት ይሰደዳሉ፡፡ ይኸ ሁሉ የገቢ ምንጭ ምን እንደሆነ የማይታወቅ ንግዱ ቅጥ ያጣ መሆኑን አመልካች ነው፡፡

በምግብ ሸቀጦች ገበያ ውስጥ በቅርብ ዓመታት ሸማቹን ኅብረተሰብ ግራ የሚያጋቡ በርካታ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡ ሽንኩርት ጎመን ሰላጣ ቲማቲም ቃሪያና ሎሚ የመሳሰሉ አትክልቶች በቀናት ውስጥ በኪሎ ከኹለት ብር እስከ ሐምሳ ብር ከሐምሳ ብር እስከ ኹለት ብር ከፍና ዝቅ ሲሉ ወይም ዋጋቸው ሲዋዥቅ በዓይናችን አየን፣ ሚጥሚጣ እንኳ ለማቃጠል በኪሎ ኹለት መቶ ብር ተሽጣለች፣ የኹለት መኝታ ክፍል ኮንዶሚንየም ቤት መሸጫ ዋጋ ከሚልዮን ብር በላይ ዘሏል ምክንያቱን የነገረን ግን አንድም ሰው አልተገኘም፡፡

ጤፍ፣ ጥራ ጥሬዎች፣ ሥጋ፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በኩንታልና በኪሎ ከአስር እጥፍ በላይ ጨምረዋል፡፡ በሌሎችም ዕቃዎች ላይ ተመሳሳይ ጭማሪ እና የተዘበራረቀ ሁኔታ ታይቶአል፡፡ ማንም ምክንያቱ ይኽ ነው ያለን ሰው ግን የለም፡፡ በደርግ ዘመን ስልሳ ብር የነበረ ኩንታል ጤፍ ሁለት ሺሕ አምስት መቶ ብር ገብቶም እንደልብ ይሸጣል፡፡ በደርግ ዘመን ዐሥር ብር የነበረ አንድ ኪሎ ሥጋ ሁለት መቶ ብር ገብቶም እንደልብ ይሸጣል፡፡ አምስት ብር የነበረ ዶሮ በአራት መቶ ብር ይሸጣል፡፡

ሎሚ፣ ቃሪያ፣ ሥጋ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ምስር፣ ፍራ ፍሬ፣ ቅመሞች፣ የሆቴል ምግብ፣ የጀበና ቡና፣ የመሳሰሉት የምግብ ሸቀጦች አልባሳትና መጫሚያዎች፣ የቤት ኪራይ፣ የከተማ ቦታ፣ የመሳሰሉ የመጠለያ መሠረታዊ የኑሮ ሸቀጦች እንዲሁም መዋቢያን መዝናኛን የመሳሰሉ የአገልግሎት ሸቀጦች ዋጋም ከአስር እጥፍ በላይ ጨምረዋል፡፡ ጥፍራቸውን ለመሠራት ብቻ ሦስት ሺሕ አምስት ሺሕ ብር የሚከፍሉ አሉ፡፡

እንደው ለመሆኑ ይኸ ሁሉ ጥሬ ገንዘብ ከየት ነው የሚመጣው፣ ብዙዎቻችን የማናውቀው የጥሬ ገንዘብ ማዕድን ይኖረን ይሆን እንዴ፡፡ እግዚአብሔር ደግ ነው ለፈረንጆች ዕውቀትን ሰጠ ለዐረቦች የነዳጅ ማዕድን ሰጠ ለእኛም የገንዘብ ማዕድን ሰጥቶን ይሆናል ብለን እናስብ? ወይስ ከላይ እንደተገለጸው መንግሥት ለድሃው ኑሮን አስወድዶ ለሀብታሞች መቀማጠያ ለማድረግ ጥሬገ ንዘብ በገፍ ስላሰራጨ ነው እንበል?

የአትክልቶቹ ዋጋ መዋዠቅ ምክንያት አቅራቢው ወደ ገበያ ያወጣቸው ሸቀጦች ሳይበላሹበት ቶሎ መሸጥ ስላለበት ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በከፊል የሸቀጦቹ መበላሸት ባሕርይ ሲሆን በከፊልም በአቅራቢዎች በየጊዜው የሚለዋወጠውን የሸማቾችን ፍላጎት ለማወቅና ለመተንበይ አለመቻል ነው፡፡

የአዝርዕት እና የጥራጥሬ ዋጋ መናር ምክንያትን በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል አንዱ ገበያው ውስጥ የተሰራጨው ጥሬገንዘብ መጠን ብዛት ሲሆን ሁለተኛው ለአገር ውስጥ ብቻ ተብለው ይመረቱ የነበሩ፡፡ በአቅማችን ልክ ዋጋቸው ይወሰን የነበረ ጥራ ጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ሥጋን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶቻችን በዓለም ዐቀፍ ገበያ ተነጋጅ (tradable) ሆነው ዋጋቸው በዓለም ዐቀፍ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ሲወሰን ነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ገቢያቸው ሠላሳና አርባ ሺሕ ዶላር ከሆነ ሰዎች ጋር በሦስትና አራት መቶ ዶላር ዓመታዊ ነፍስወከፍ ገቢያችን መወዳደር ስላቃተን ነው፡፡

አንድ ኢትዮጵያዊ ምስር፣ አተር፣ ሽምብራ፣ ባቄላ፣ ሥጋ ወይም የቅባት እህል ለመመገብ ከቻይና እና ከተባበሩት ዐረብ ኢመሬት ሸማች ሰው ጋር በመግዛት አቅም ወይም በገቢው መጠን መወዳደር ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

ከጠባብ አገር ዐቀፍ ግብይይት ሥርዓት ውስጥ ወጥተን ወደ ዓለም ዐቀፍ ግብይይት ሥርዓት ውስጥ ስንገባ ሊገጥሙን ከሚችሉት ችግሮች ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በዓለም ውስጥ እስከኖርን ድረስ ወደድንም ጠላንም ወደ ዓለም ዐቀፍ የግብይይት ሥራዓት ውስጥ መግባታችን እና በሸመታ እና በማምረት ባሕርያት ቀሪውን ዓለም መቀላቀላችን አይቀርም፡፡

ለዚህም መቼ ዝግጁ እንደምንሆንና ኑሯችን ከነርሱ ጋር እየተቀራረበ ነው ወይስ እየተራራቀ ነው የሚለውን ለማየት የእስከአሁኑ አካሄዳችን መረጃዎች ድንግዝግዞች ናቸው፡፡ በነፍስወከፍ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መመዘኛ እኛ ከመቶዎቹ ቤት ለመዝለል ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እንኳ አልበቃንም፡፡ በአንጻሩ እነርሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዐሥር ሺሕ ሃያ ሺሕ ሰላሳ ሺሕ እያሉ ሺሕዎችን በእምርታ እየዘለሉ ነው፡፡ በምን ዓይነት የጋራ ገበያ ውስጥ ነው እኩል ተገበያይ ልንሆን የምንችለው፡፡

ነፍስ ወከፍ ገቢያችንን ሺዎች ውስጥ ለማስገባት አስበን ዋጋዎች ለሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት በተመሳሳይ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ተመሳሳይ ጭማሪ ቢያደርጉ የዛሬ ዋጋቸውን በዐሥር አብዝተን የወደፊቱን ዋጋቸውን ልንገምት እንችላለን፡፡ እንደ የሸቀጦቹ አቅርቦትና ፍላጎት በዋጋ ለውጥ ተለጣጭነት ደረጃ (Price Elasticity of Supply and Demand) እና እንደ የሸቀጦቹ ፍላጎት በገቢ ለውጥ ተለጣጭነት ደረጃ (Income Elasticity of Demand) የአንዳንዶቹ ሸቀጦች ዋጋ ከዐሥር እጥፍ በላይ ወይም በታች ሊሆንም ይችላል፡፡ በጥቅሉ ስንወስደው ግን ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን በጨመረ ቁጥር ዋጋዎች እየተወደዱብን እንደሚሄዱ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በዚሁ ከቀጠለ የዋጋ ንረትም በእስከአሁኑ መልክ ይቀጥላል፡፡ ከሃያ ዓመታት በኋላ ሎሚ በቁጥር ዐሥር ብር፣ ቃሪያ በኪሎ ግራም አምስት መቶ ብር፣ ሥጋ በኪሎ ግራም ኹለት ሺሕ ብር፣ እንቁላል በቁጥር አርባ ብር፣ ወተት በሊትር ኹለት መቶ ብር፣ ምስር በኪሎ ግራም ስድስት መቶ ብር፣ ቅመሞች በኪሎ ግራም አምስት መቶ ብር፣ ፍራፍሬ በኪሎ ግራም ኹለት መቶ ብር፣ የሆቴል ምግብ ምሳ አንድ ሺሕ ብር፣ የጀበና ቡና በሲኒ ሐምሳ ብር የልብስና ጫማ ዋጋ ዐሥርና ሃያ ሺሕ ብር የአንድ ክፍል መኖሪያ ቤት ኪራይ ዐሥር ሺሕ ብር፣ ቢሆኑ ምን ይሰማናል፡፡

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በዚሁ መልክ ቀጥሎ በሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት የዋጋ ንረቶች ተመሳሳ ካልሆኑ ያለፉት ሃያ ዓመታት የእብደት ገበያ ውስጥ ነበርን ማለት ነው፡፡

የሸቀጦች ዋጋ በሸቀጦች አቅርቦትና በሸቀጦች ፍላጎት መስተጋብር እንደሚወሰን፣ ዋጋ የሚወደደው አቅርቦት ሲያንስ ወይም ፍላጎት ሲበዛ እንደሆነ፣ ኢኮኖሚው አደገ ምርታማነትም ጨመረ እየተባለ ለምን አቅርቦት እንደሚያንስና ለምን ፍላጎት እንደሚበዛ የሚናገር ጠፋ ሰውም ዝም መጽሐፉም ዝም ሆነ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት ተለበለበ አንዳንድ ሰዎች የዋጋን መወደድ በነጋዴ ያሳብባሉ፡፡

ሸቀጥ አምራችና ነጋዴ ያልሆነ ሰው ማን ነው፡፡ ጉልበቱን ሽጦ የሚያድረውም የጉልበት ነጋዴ አይደለምን፣ የሸቀጡን ዋጋ ያልጨመረስ ማን ነው፡፡ ለምን ሊጨምር አልቻለም? የጨመረውስ እንዴት ሊጨምር ቻለ? ሸማቹስ ዋጋ እንደዚህ እየናረ የመሸመት አቅም ከየት አገኘ? አምራችና ሸማች የተለያዩ ሰዎች ናቸውን? የትኛው ነጋዴ በየትኛው ነጋዴ ነው የሚማረረው?

ወዛደርም የቀን ውሎ ክፍያውን ከዐሥር ዓመት በፊት ከነበረበት ዐሥር ብር ወደ መቶ ብር አሳድል ስግብግብ ነጋዴ ሊባል ነው፡፡ የቤት ሠራተኞችም የወር ደመወዛቸውን ከሐምሳ ብር ወደ አንድ ሺሕ ብር አሳድገዋል ስግብግብ ነጋዴዎች ሊባሉ ነው፡፡ የሰው በረንዳ ላይ ተቀምጠው የአንድ ሲኒ የጀበና ቡና ዋጋን ከሐምሳ ሳንቲም ወደ አምስት ብር ያሳደጉ ለፍቶ ጥሮ ግሮ አዳሪዎች ስግብግብ ነጋዴ ሊባሉ ነው፡፡

ቃሪያ ከሦስት ብር የኪሎ ግራም ዋጋ ዐሥራ ሰባት እጥፍ ጨምሮ ሐምሳ ብር መድረሱ፣ ምስር ከአራት ብር የኪሎ ግራም ዋጋ ዐሥራ አምስት እጥፍ ጨምሮ ስልሳ ብር መድረሱ፣ ብርቱካን ከሁለት ብር የኪሎ ግራም ዋጋ ዐሥራ አምስት እጥፍ ጨምሮ ሠላሳ ብር መድረሱ፣ ወተት ከሁለት ብር የአንድ ሊትር ዋጋ አስር እጥፍ ጨምሮ ሃያ ብር መድረሱ፣ ከየትኛው ነጋዴ ስግብግብነት ጋር ነው የሚዛመደው፡፡

በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ እያንዳንዱ ኢትጵያዊ አልፏል እያለፈም ነው፡፡ ሕዝብ የሆነውን ሁሉ ያውቃል የማያውቀው ነገር ቢኖር የሆነው ለምን እንደሚሆን እና መፍትሔው ምን እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱንና መፍትሔውን አለማወቁም አንዱ በሌላው ላይ እንዲያሳብብ ጣቱን እንዲቀስር ምክንያት ሆነ፡፡

በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት ለሚሰቃይ ኑሮ ለከበደው ኢትዮጵያዊ የሸቀጦች ዋጋ እንዴት እንደሚወሰን ለምን እንደሚለዋወጥ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓቱን የሚያንፀባርቁት ነፃ ገበያ፣ አቅርቦት፣ ፍላጎት ምን እንደሆኑ፤ ስለ ንግድ ሥራ ውጣ ውረድ ፈረቃዊ ዙር (Business Cycle) እና የጥሬገንዘብ ፖሊሲ የንግድ ሥራ ውጣ ውረድ ዙር ልም ስለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት አስተዳደር ምን እንደሆነ ከመስማትና ከማወቅ በላይ አስፈላጊ ነገር የለም፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳይ የራስና የልጆች ሕይወት ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ የቀለደ ነገ ይቀለድበታል፡፡ ከባለሙያ የሚነገረውን የሚሰማ ይሰማል የማይሰማ ቢወድም ባይወድም ውጣ ውረዱን በዓይኑ ያያል በኑሮ ይቀምሳል፤ በልጆቹ ሕይወት ይመለከታል፡፡ የባለሙያ ምክር እርግማን እንዳይሆንብን ዛሬ ነው መስማት ዛሬ ነው መነጋገር፡፡ ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቁሞ ለማውረድ አዳገተ እንዳይሆንብን፡፡ ነገ የልጆቻችን ሕይወት በከንቱ ሁከትና አመጽ ከሚቀጠፍ ዛሬ ነው ማሰብ፡፡

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2008 የአሜሪካ ኢኮኖሚ ወደ ላይ ሽቅብ አድጎ የምርት መትረፍረፍ ጫፍ ላይ ደርሶ ተመልሶ ወደ ማቆልቆል ተጉዞ ነበር፡፡ ፕሬዜዳንት ኦባማ በወሰዱት ፈጣን የጥሬገንዘብ ፖሊሲ እርምጃ ኢኮኖሚው ከማሽቆልቆል እንዲወጣና እንደገና ወደ ላይ እንዲያሻቅብ አድርገዋል፡፡

እንደ ምሳሌ የግሪክን ኢኮኖሚ ሁኔታ ብናይ ግሪክ በሕንፃም ሆነ በአውራጎዳና ወይም በሌሎች መሠረተልማቶችና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማት ከብዙ አገራት ትበልጣለች፡፡ በነጻ ገበያ ሥርዓትም ለረጅም ጊዜ ኖራለች፣ ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢዋ እስከ ሃያ ሰባት ሺሕ የአሜሪካን ዶላር የደረሰበት ጊዜም ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢኮኖሚዋ ለረጅም ጊዜ በማሽቆልቆል ማንሰራራት አቅቶት፣ በአውሮፓ አገራት ምሕረት ሥር ጥሏታል፣ የዕዳ ክምር በአውሮፓ አገራት ዓይን አሳፍሯታል፤ መክፈልም አቅቷታል፡፡ የግሪክ ኢኮኖሚ የቁልቁለት ዝቅጠት ጫፍ ላይ ደርሷል አልደረሰም አላውቅም፡፡ ኢኮኖሚዋ አንሰራርቶ አንድ ቀን ከችግር መውጣቱ ግን የማይቀር ነው፡፡

ግሪክን ያየ በእሳት አይጫወትም ዓይናችንን ከሕንጻ መለካት፣ አውራጎዳና ምተራ፣ ከተቋማትና ምርት ቆጠራ ከእህል ሰፈራ ነቅለን ስለህዝቡ ኑሮና ስለገበያዎች ሁኔታ ከነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍናና ሥርዓት አንጻር መመልከት የሚገባን ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ትንታኔ የምንሰጥበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ የዓለም ባንክ እና ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት የመንግሥትን በጀት ቀንሱ ጨምሩ ጥሬ ገንዘብ ቀንሱ ጨምሩ የብር ምንዛሪን ዋጋ አውጡ አውርዱ እስከሚሉን መጠበቅ የለብንም፡፡